Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትጦርነቱ ዋናውን የአገር አደራና ግዳጅ እንዳያስረሳን!

ጦርነቱ ዋናውን የአገር አደራና ግዳጅ እንዳያስረሳን!

ቀን:

በገነት ዓለሙ

‹‹ለአገር መከላከያ ክብር እቆማለሁ›› ማክሰኞ ኅዳር 8 ቀን 2013 ዓ.ም. አብዛኛውን ኢትዮጵያውያንን ያስተባበረና ያነቃነቀ መርሐ ግብር ነበር፡፡ እንኳንስ እንዲህ ባለ በከፋና በወሳኝ ጊዜ በመደበኛውና በዘወትር ኑሮ ውስጥም ከየትኛውም ሥራ በጭራሽ እኩል የማይታየው ሕይወትን ለመስጠት በመፍቀድ ላይ የተመሠረተው የመከላከያ ሥራ ከሌላው የሥራ ዘርፍና መስክ የበለጠ እንክብካቤና አክብሮት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑ በመላው ዓለም ቢያንስ ቢያንስ በመርህና በወግ ደረጃ የታወቀ ነው፡፡

አገራችን ውስጥ ለዴሞክራሲ የሚደረገው ትግል መልሶ መላልሶ መሰናክልና መክሸፍ ከለማመደበት ከ1966 ዓ.ም. አብዮት ጊዜ ጀምሮ (በተለይም ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ)፣ የአገራችን ሰው በዚህ ላይ እንኳን የጋራ መገናኛና መግባቢያ አጥቶ የደርግ ሠራዊት የኢሕአዴግ ሠራዊት ማለት መጥቶና ፀድቆ፣ ስያሜውም ለተቃውሞና ለዴሞክራሲ የሚደረገው ትግል ምልክትና አካል ሆኖ ኖሯል፡፡

እውነት ነው ዴሞክራሲን ለማደላደል በዋናው የአገር የበላይ ሕግ ውስጥ የተደነገጉ መብቶችና ነፃነቶች የሚታይና የሚጨበጥ የሰዎች ሁሉ መኗኗሪያ መሆናቸውን ለማረጋገጥ፣ ከቡድን ቁጥጥር የተላቀቁ ወገናዊ ያልሆኑ ተቋማትን ማደራጀት ያስፈልጋል፡፡ መንግሥታዊ አውታራት ከቡድን ታማኝነትና ወገናዊነት መላቀቅ ካልቻሉ፣ ገዥው በሕዝብ ድምፅ ወደ ሥልጣን የሚወጣበትና የሚወርድበት ሥርዓት ሊዘረጋ አይችልም፡፡ አምባገነናዊነትንና የፓርቲ ወገናዊነትን እንዲያገለግሉ ሆነው የተቀናበሩ አውታራት ለሕዝብና ለሕዝብ ብቻ ታምነው ሊያገለግሉ ስለማይችሉ፣ የዴሞክራሲ ትግሉ እንደ መከላከያ ሠራዊቱ ባሉ ዓምደ መንግሥቶች ላይ የማሻሻያ ሥራ መሠራት ያለበት በዚህ ምክንያት ጭምር ነው፡፡

የማክሰኞው ‹‹ለአገር መከላከያ ክብር እቆማለሁ›› ሥነ ሥርዓትና ድጋፍ አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ያስተባበረና ያነቃነቀ ነው ስል፣ ድጋፉን የነፈገው ከዚያም በላይ የተቃወመው መኖሩን ጭምር ለማስረገጥም ነው፡፡ የትግራይ ክልል (ኦፊሴል ኢትዮጵያ የቀድሞ መሪ የምትላቸው) መሪ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ከማክሰኞ በፈት በነበረው ሳምንት ደጋግመው በሰጡት መግለጫ፣ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊትን ‹‹ወራሪ ሠራዊት›› ማለት ድረስ ክደውታል፡፡ ክደት የፈጸመ ሠራዊት ብለውታል፡፡ ‹‹ያ ሁሉ ታሪክ የፈጸመ ሠራዊት ያ ሁሉ መሪ ያወጣ ሠራዊት››፣ ‹‹የትግራይ መኮንኖች ተለቅመው የወጡበት ሠራዊት›› ‹‹የትግራይ ተወላጅ የሚባል እንዳይኖር›› የተደረገበት ሠራዊት እያሉ አጣጥለውታል፡፡

ትናንት ከ2010 ዓ.ም. መጋቢት በፊት ብቻ ሳይሆን ይህን የመሰለው የጥቅምት 24ቱ የመረረ ነገር ከመምጣቱ በፊት፣ የሕዝብ ወገን ይባል የነበረ በአንፃሩም ይበልጡኑ በተቃራኒውም የኢሕአዴግ/የሕወሓት ሠራዊት ሲባል በፕሮፓጋንዳም ‹‹በሕጋዊና›› በፖለቲካዊ ዕርምጃም ይከላከሉት የነበረው መከላከያ ነው፣ ዛሬ በአንድ ጊዜ እንዲህ ያለ የተለያየ ድጋፍና ውግዘት የደረሰበት፡፡ የሚገርመውና ይኸው የመከላከያ ሠራዊት አካል የሆነው አንዱ ክፍል ወይም አሀድ ለምሳሌ የሰሜን ዕዝ፣ ከፌዴራሊዝም የራስን ዕድል በራስ ከመወሰን ጋር ‹‹ወገነ›› ‹‹ወሰነ›› ማለት ፀንቶ በቆየበት ወቅት ጀግናና ሕዝባዊ የተባለው ሠራዊት ነው ‹‹ካደ፣ ወረረ›› የሚባለው፡፡ እኩል የሚገርመውም ትናንት የዚህን ሠራዊት የብሔረሰብ ቅንብር በየደረጃው ስንቆጥር ከነበርን ውስጥም፣ ‹‹ለአገር መከላከያ ክብር እቆማለሁ›› ብለን ማክሰኞን እኩል ማድመቃችን ነው፡፡

ይህ ሁሉ ዥንጉርጉርና የተዘበራረቀ ስሜት ከሁሉም በላይ ደግሞ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ሌሊት የተፈጸመው ጥቃት የሚያሳየንና ያረጋገጠው፣ ዴሞክራሲያችንና ፌዴራሊዝማችን ፈጽሞ የውሸት መሆኑን ነው፡፡ መጀመርያ ዴሞክራሲ ወይም የሕዝብ አስተዳደር ቡድናዊ ወገንተኛነት በተጎናፀፈ የታጠቀ ኃይልና ያንኑ በሚመስል የቢሮክራሲ አውታር ላይ መቋቋም አይችልም ብሎ፣ የጥቅምት 24 ቀን 2013  ዓ.ም. ጥቃት አረዳን፡፡ ‹‹የ[ክልል] መከላከያ ሠራዊት›› ‹‹የ[ክልል] አየር ኃይል›› ማለት ያህል ነውር አያልቅበት መሆናችን ፌዴራሊዝማችንን ዕርቃኑን አወጣው፡፡ የለውጥ ኃይሎች ገና ብዙ የተወዘፈ ሥራ ያለባቸው መሆኑን አጋልጦ አረዳ፡፡

ሁሉም፣ ሁለቱም ችግሮችን የመከላከያ አደረጃጀታችን ውስጥ የተሸፈኑ በመሆናቸው፣ ይህንን ጉዳይ ከዚህ ማዕዘን ዘርዘር አድርገን እናያለን፡፡

የኢሕአዴግ/ሕወሓት የሥልጣን ጉልበት የራሱ ሠራዊት ነበር፡፡ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ከወታደራዊ ትግልነት ወደ ሥልጣን የመጣው ጊዜያዊ መንግሥት ሆኖ፣ የደርግን ሠራዊት በትኖና የራሱን ሠራዊትና የፀጥታ መረብ የሥልጣኑ ጉልበት አድርጎ ነው፡፡ ይህ የሕወሓት ኢሕአዴግን የጊዜያዊ መንግሥትነት ወራት የሚመለከተው ነው፡፡ ቡድኑ የሽግግር መንግሥት ሆኖ በቀጠለበት ጊዜም በመከላከያ ኃይልነት ‹‹ዕውቅና›› አግኝቶ ይሠራ የነበረው የራሱ ሠራዊት ነው፡፡ በ1984 ዓ.ም. የብሔራዊ አካባቢያዊ ምርጫ ተብሎ ክልሎች በተዋቀሩ ጊዜም፣ የሌሎች ቡድኖችን የታጠቁ ኃይሎች ካምፕ አስገቢ፣ ተቆጣጣሪና እምቢ ባይን ቀጪ፣ የምርጫውን ፀጥታ አስከባሪም የነበረው የራሱ ጦር ነው፡፡ የሕወሓት/ኢሕአዴግ ጦር፡፡

ከሕወሓት/ኢሕአዴግ ፍላጎት እንዳያፈተልክ ሆኖ በረቀቀና በፀደቀ ሕገ መንግሥት አማካይነት በተካሄደ የ1987 ዓ.ም. ምርጫ፣ ሕወሓትና ርቢዎቹ የ‹‹ኢትዮጵያ ሕዝቦች መንግሥት›› ሆነው እንደተሰየሙ ሁሉ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል መሆን የቻለውም በመሠረቱ የሕወሓት/ኢሕአዴግ ሠራዊት ነው፡፡ ሠራዊቱ ከፓርቲው ወጥቶ የሕገ መንግሥቱ ተገዥ እንዲሆን ቢደነግግም፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ መኮንኖች አብዮታዊ ንቅናቄ (ኢዲመአን) የተባለው የኢሕአዴግ አካል የነበረው ፓርቲ ለዚህ ሲባል ተሰናበተ ቢባልም፣ የውስጥ አዋቂው አቶ ገብሩ አሥራት በ2007 ዓ.ም. መጽሐፋቸው እንደሚነግሩን ፓርቲው የሚወያይባቸው አጀንዳዎች ትንሽ ለውጥ ተደርገው የሠራዊቱም መወያያ ይሆኑ ነበር፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲም የሠራዊቱ ጭምር አመለካከት እንዲሆን ተደርጎ ኖሯል፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱን ኅብረ ብሔረሰባዊ ሥጋ የማሟላቱ ሒደትም የሕወሓት/ኢሕአዴግን አፅምነት አላናጋም፡፡ የደኅንነትና የፖሊስ ኃይል ግንባታው የተዋቀረውም (በሰው ኃይልም በአመለካከትም) በሕወሓት/ኢሕአዴጋዊ አከርካሪ ላይ ነበር፡፡

በ1993 ዓ.ም. የሕወሓት/ኢሕአዴግ ክፍፍል ጊዜ መከካከያ ሠራዊቱ የአንጃ ጎራ ለይቶ እንዳይታኮስ እንደተፈራው ሳይሆን የቀረው፣ በአንጃ ተቆራርጦ ከመታኮስ በቀደመ መንገድ ነገሮች ስለተቀላጠፉ እንጂ የአንጃ ልዩነት በሠራዊቱ ውስጥ ስላልነበረ አልነበረም፡፡ የክፍፍሉ ዕምብር የነበሩት የሕወሓት የአመራር ሰዎች ያካሄዱትም ትንቅንቅ የድምፅ ብልጫ አግኝቶ ፍላጎትን ውሳኔ በማድረግ ወይም ውሳኔ በማስገልበጥ ላይ የታጠረ አልነበረም፡፡ የእነ ተወልደ ቡድን ከሠራዊቱ አመራር በኩል መፀናወት እንደማይገጥመው ከመተማመን ጋር በተቀናቃኙ ላይ በነበረው የድምፅ ብልጫ ተመክቶ ሳለ፣ የመለስ ቡድን አካሂዶት የነበረው የድምፅ ድጋፍ ከማበርከት አልፎ መከላከያ ሠራዊት ውስጥ የገባ መራወጥ (የወታደራዊ አዛዦችን ድጋፍ ለማግኘት ያካሄደው የውስጥ ለውስጥ ሥራ፣ በቦናፓርቲዝምና በመበስበስ አደጋ ላይ ጄኔራሎች እንዲወያዩ መደረጉ) ጠመንጃ ይዞ መንገድ ላይ ያልወጣ የፍንቀላ ክንዋኔ ነበር፡፡ የእነ ተወልደ ቡድን መታገድና የታገዱት በሌሉበት የኢሕአዴግን አስቸኳይ ስብሰባ ማካሄድ አይገባምና እናስታርቅ ባዮች ላይ፣ በፀጥታና በመከላከያ ሰዎች የተካሄደው ማዋከብና ማስፈራራት፣ የሕወሓት የቁጥጥር ኮሚሽን ውሳኔ ወግድ መባልና ከዚያ በኋላ የተከተሉ ዕርምጃዎች ሁሉ የድል አድራጊው ግልበጣ የአጥቂነት የማወራረድ ክንዋኔዎች ነበሩ፡፡ በዚህ መሠረት ክንፈ ገብረ መድኅን በኢሕአዴግ ውስጥ መበስበስ ስለመድረሱ የሚያወራውን የመለስ ሰነድ ይዞ ወታደራዊ ሰዎችን ሲያወያይ በተከሰተ አለመግባባት ከተገደለ በኋላ፣ የመለስ ቡድን አጥቂነትና ድጋፍ አሰባሳቢነት ዕመርታ አሳየ፡፡ የማጥራት ሹምሽሩ፣ ብጠራውና ፕሮፓጋንዳዊ ተሃድሶ በአባል ድርጅቶችና በሠራዊቱ ውስጥ ተካሂዶም ፍንቀላው የመለስ ዜናዊ አይደፈሬ አዛዥነት የሰፈነበት ሆነና በዚያው ቀጠለ፡፡ በተለይ ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ ልምድ በኋላ ደግሞ መከላከያና ፖሊስን በመለስ ኢሕአዴግ አስተሳሰብ የማጥመቅ፣ የአመለካከት ታማኝ አድርጎ የመቅረፁ ሥራ ለአንዴም የማይቦዝንበት ሆነና አረፈው፡፡

በአፄ ኃይለ ሥላሴም ሆነ በደርግ ዘመነ መንግሥት የአገሪቱ የታጠቀ ሠራዊት ለገዥው ታማኝ እንዲሆን ተደርጎ የተቀረፀ ነበር፡፡ የዚያን ዘመን ከኢሕአዴጉ ጋር ለማወዳደር መሞከር አይቻልም፡፡ የእነዚያኞቹ ኢሕአዴግ አጠገብ የሚደርስ አይደለም፡፡ በመንግሥት መገናኛ፣ በየስብሰባውና በየኮንፈረንሱ አጋጣሚ ከሚካሄደው ጥምቀት ባሻገር የኢሕአዴግ መንግሥት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በወታደራዊ ሥልጠና ካሪኩለም ውስጥ ተዋቅሮ እስከ መስጠት  የጠለቁ ነበሩ፡፡ በደመወዝ፣ በሙያ ማሻሻያና በመሳሰሉት ያለው አያያዝ ከቀድሞ እጅግ የተሻለ መሆኑም ለጠመቃው ሥር መያዝ በጣም አግዟል፡፡ እዚህ ላይ የምንቃወመው እንክብካቤውን አይደለም፡፡ እንዲያውም ከየትኛውም የሥራ መደብ እኩል መታየት የሌለበት፣ ሕይወትን ለመስጠትና ለመሰዋት በመፍቀድ ላይ የተመሠረተው የመከላከያ ሥራ ከሌላው የሥራ መስክ የበለጠ አያያዝ፣ እንክብካቤና አክብሮት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡ እንክብካቤው ግን ይህንን የመንግሥት አውታር የአንድ ወይም የሌላ ቡድን ታማኝና ደባል አገልጋይ አድርጎ የመያዣ ‹‹ክፍያ›› እና ዋስትና መሆን የለበትም፡፡

በዚህ ላይ ደግሞ ከመደበኛው የታጠቀ ኃይል በታች (. . .በሕግ ከመደበኛው ኃይል በታች ነው) በተጠባባቂ ጦር ዓላማ እየሠለጠነ ወደ ኅብረተሰቡ የሚመለሰው፣ በተለያየ የመተዳደሪያ ሥራ ላይ እየተሰማራ የታጠቀ ሚሊሺያ ሚናን የሚጫወት በብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠር ኃይል አለ፡፡ ይህ ኃይል የተቋቋመው የማቋቋሚያው ሕግ (327/95) እንደሚደነግገውና እንደሚያብራራው፣ ‹‹የሕዝቡ ሉዓላዊነትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ የመከላከያ ሠራዊቱ አካል በመሆን የሚመክትና የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ፈጥኖ ለሕዝቡ ሊደርስ የሚችል፣ በሰላም ጊዜ መደበኛና የግል ሥራውን የሚያከናውን ሕዝባዊ መሠረት ያለው ብሔራዊ ተጠባባቂ ኃይል ማቋቋም በማስፈለጉ›› ነው፡፡ በዓላማው ‹‹በጦርነት ወይም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመከላከያ ሠራዊቱን ተቀላቅሎ ለመሰማራት›› በአደረጃጀቱ በሁሉም የፌዴራል መንግሥታት ክልሎች የሚደራጅ በአገር መከላከያ ሚኒስቴር የሚመራ የተጠባባቂ ኃይል ነው፡፡ በየክልሉ ‹‹በወረዳ ደረጃ በአሀድ ተዋቅሮ እንዲደራጅ›› የሚደረገው ይህ ኃይል ራሱ፣ የመንግሥት ሥልጣንን በማዕከላዊውና በክልል መንግሥታት መካከል ባከፋፈለው ሕገ መንግሥት መሠረት የፌዴራል መንግሥት ነው፡፡ የተጠቀሰው አዋጅ ቁጥር 327/1995 ራሱ የብሔራዊ ተጠባባቂ ኃይል ማደራጃና ማስተባበሪያ ቢሮ የሚባል ቢሮ አቋቁሟል፡፡ በአገር መከላከያ ሚኒስቴር ሥር ተቋቁሞ የሚገኝ የብሔራዊ ተጠባባቂ ኃይልን በበላይነት የሚያደራጅ የሚያስተዳድርና የሚመራ ቢሮ ነው፡፡

ፌዴራሊዝማችንና ዴሞክራሲያችንን አስገራሚና አስደማሚ የሚያደርገው፣ ከሌሎች በተጨማሪ ከዚህ ‹‹በሰላም ጊዜ መደበኛ የግል ሥራውን የሚያከናውን ሕዝባዊ መሠረት ያለው ብሔራዊ ተጠባባቂ ኃይል›› ጭምር ክልሎች የታጣቂ ሚሊሺያን ሚና የሚጫወት፣ ቋሚና ሥልጣኑም የእነሱ የሆነ/ያደረገ ኃይል እንዲያቋቁሙ መመረቁም ነው፡፡ የዚህ ኃይል ሰዎች ደግሞ እንደ መከላከያ ሠራዊቱ አባላት በውስጥ ለውስጥ፣ በዙሪያ ጥምጥምና በአሠራር ብቻ ሳይሆን በይፋ የኢሕአዴግ አባል ከመሆን የሚያግዳቸው የለም፡፡ ይህንን አቶ ገብሩ አሥራት የምስክርነት ቃላቸውን በመጽሐፋቸው ሰጥተውበታል፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ እንዴት ታጣቂ ሚሊሺያዎችን በአባልነት ያቅፋል የሚል ጥያቄ ሲነሳ፣ እነዚህማ ብረት ከማንገባቸው በስተቀር ሲቪል ናቸው የሚል መልስ ይሰጥ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

በክልልና በማዕከላዊ መንግሥታት መካከል ያለውን ከሁሉምና ከሁለቱም በላይ የሆነ ሥልጣን፣ ማለትም ሕገ መንግሥቱ ያደላደለውን ሥልጣንና ተግባር የሚያናጋና የሚረግጥ ሌላም መከላከያን የሚመለከት ችግርና አደጋ አለ፡፡ የክልል ፖሊስና የልዩ ኃይል ያልተወሰነ፣ መለኪያም ደረጃም ያልወጣለት መረን የለቀቀ ዕብጠትና ‹‹ዕብደት›› ያደረሰ አደጋ፡፡ እነዚህን ሲጀመር ‹‹በእንቁላሉ ጊዜ›› ገና ሳይገነትሩ ዕልባት ያልተሰጠባቸው፣ መቃኛ ያልተበጀላቸው ሕገወጥነቶች የመከላከያ ሠራዊቱን የአንዱን ወይም የሌላውን ድምፅና ጥያቄ እየሰማ ‹‹ውሳኔ›› የሚሰጥ አካል ማድረግን፣ ‹‹ሕዝባዊ›› ‹‹ሕገ መንግሥታዊ›› እምነታቸው እስከማድረግ ድረስ እንዲሄዱ አድርጓል፡፡ የምርጫው ጊዜ ይራዘም ሲባል፣ የ2012 የመስከረም ወር የመጨረሻ ሰኞ እየተቃረበ ሲመጣና ካለፈ በኋላ የመከላከያ ሠራዊ አቋም ይወስዳል፣ ውሳኔ ይሰጣል ብለው ፀሎትም አቤቱታም ጥያቄም ቅስቀሳም ያደረጉና ያቀረቡ ነበሩ፡፡

በአጠቃላይ እስከ ለውጡ ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያ የነበረችበት ሁኔታ ገዥው ቡድን ኢሕአዴግ በየአምስት ዓመቱ በምርጫ እያሸነፈ ወንበሩን ያለ አንድ ተቀናቃኝ የሚያፀና ብቻ ሳይሆን፣ የሚቀመጥበት ወንበር [ዙፋን] ይሁን ከእነ ካስማና ማገሩ ጭምር የራሱን ንረት ያደረገ፣ ከመንግሥትነት አልፎ ተርፎ ራሱ አውታረ መንግሥት  (State) የሆነ፣ አውታረ መንግሥት ከመሆኑም አልፎ መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላትም ውስጥ መረቡን የዘረጋ፣ የሙያና የሕዝብ የሚባሉ ማኅበራትም ውስጥ ዓይን፣ ጆሮና አንደበቱ ገብቶ መዋቅራቸውን የተበተበ አውሬ ሆኖ ኖሯል፡፡ ለውጡ የመጣው ይህን ለመለወጥ ነው፡፡ ሽግግሩም ሥራዬ ብሎ የያዘው ይህንን ሁሉ ነው፡፡

የዓብይ መንግሥት ብሔረሰባዊ ማንነቶችን ከኢትዮጵያዊ ማንነት ጋር አስማምቶ፣ ከዴሞክራሲ አልባነት ወደ ዴሞክራሲ የመሸጋገር ትልምን መርጦ፣ የአገሪቱን የሥልጣን ዓምዶች ከፓርቲ ታማኝነትና መዳፍ የማላቀቅ ማሻሻያን የማካሄድ ሒደት ውስጥ መግባቱ፣ ከዚህ በፊት በአገሪቱ ታሪክ ያልነበረ አዲስ ውጤት ማለትም ሕዝቦች በድምፃቸው ሿሚና ሻሪ የሚሆኑበትን ሥርዓተ መንግሥት የሚያመጣ ነው፡፡ በዚህ ሥርዓት መቋቋም፣ ፓርቲዎች መንግሥታዊ ዙፋንንና ቢሮክራሲን በፍላጎታቸው ቀርፀው ከመንፈላሰስና በልሽቀትና በንቅዘት ከመበከል ነፃ ይወጣሉ፡፡ ሥልጣን ማግኘት አለማግኘታቸውም ሆነ የሥልጣን ቆይታቸው በሕግና በሕዝብ ይሁንታ ሥርዓት ውስጥ መውደቁ፣ ሕዝብ የሚማርክ ነገር ይዞ ለመምጣትና ለመሥራት ያተጋቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦችም የነፃነት ዋስትና ተሰምቷቸው የሚኖሩበት ምዕራፍ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ምክንያቱም የመብቶቻቸው ህልውና በዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ ሪፐብሊካዊ ሥርዓተ መንግሥት ውስጥ የተካተተ ስለሚሆን፣ እንዲሁም በምርጫ መጥቶ ከአናት የሚቀመጠው ፓርቲያዊ አስተዳዳሪነት መብቶቹንም ሆነ ፌዴራላዊውንና ሪፐብሊካዊውን ሥርዓት እንዳሻው መገነዝና መቆልመም ስለማይቀለው፣ ሊገንዝና ሊቆለምም ቢቃጣው ሕግና ሥርዓቱ ከግለሰብና ከፓርቲ በላይ ነውና ይታገለዋል፣ ይቆነጥጠዋል፡፡ ሕግና ሥርዓቱ ጊዜያዊ መንፈዝ ቢደርስበት፣ ሕዝቦች ነፃነታቸው ከሥርዓተ መንግሥቱ ነፃነት ጋር ሲሰለብ ዝም አይሉም፡፡ መሪ እስከ ማውረድና በአዲስ ምርጫ እንደራሴዎች እስከ መቀየር ሊሄዱ ይችላሉ፡፡

ይህ ሥርዓት ሕዝቦችን በብሔረሰብ ማንነትን ወይም በጎጥ ለማንጓለል ወይም መጤና ባይተዋር አድርጎ ለመጨቆን ስለማይመች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕዝብ ተቀባይነት ለማግኘት ለዚህ ሥርዓት የሚስማማ ሁሉን በእኩል የሚያይ፣ ሁሉን ወገኔ የሚልና የትኛውንም ዓይነት ጭቆና የሚታገል አስተሳሰብ ውስጥ መግባት ግዳቸው ነው፡፡ በየብሔርተኛ ጎጆ ውስጥ ተወሽቆ፣ ጎጆ ድርጅቶችን በግንባር ቢያያይዙ የአገር ልጆችን ሁሉ እኔነቱ ያደረገ አመለካከት አይገኝም፡፡ ምክንያቱም በግንባሩ ውስጥ ክፍልፋይና አንጓላይ ፍላጎቶችና አስተሳሰቦች ድርጅታዊ ቅንብሮች ፈጥረው ተኮልኩለዋልና፡፡ እስከ ተኮለኮሉ ድረስም አገራዊ ፍላጎትና ጎጇዊ ሩጫዎች እየተሻሙ መቋሰል መጠራጠር መተማማት መርኮምኮም መፍጠራቸው አይቀርም፡፡ መፍትሔ ካላገኙም በሒደት የእኩልነት እምነትን፣ ፍትሕንና ዴሞክራሲን መሸርሸራቸው አይቀርም፡፡ ፓርቲያዊ ዕይታና አስተሳሰብ መስፋት የሚጀምረው ከአንጓላይ አደረጃጀት ወደ ተዋህደ ኅብረ ብሔራዊ አደረጃጀት ውስጥ ከመግባት ነው፡፡

ሕገ መንግሥትና ፌዴራላዊ ሥርዓት በተግባር እንዲሠራ ዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት በአግባቡ መቋቋሙ ግድ ነው፡፡ በዚህ አባባል ውስጥ የሥርዓተ መንግሥት ወታደራዊና ሲቪል ቢሮክራሲ ከፓርቲ ማጠንትና ሰንሰለት መለያየት፣ የፓርቲዎች ከባለ ጠመንጃነት መሰነባበት፣ የፓርቲዎች ከአግላይነት መውጣትና ከዴሞክራሲ አሠራርና እሴቶች ጋር መግባባት ታዝለዋል፡፡ ፓርቲዎች ወደ ሥልጣን የሚደርሱበት ብቸኛ ሕጋዊ መንገድ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎቻቸውን በነፃነት አወዳድረው በተዓማኒ የምርጫ ሒደት በሚገኝ የድምፅ ውጤት መሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ወደዚህ ሥርዓት ለመግባት ጉዞው ተጀምሯል፡፡ በግርግሮች ደንበር ገተር ማለት ቢኖርም፣ የለውጡ አሠረጫጨት ጥሬ የበዛበት ቢሆንም፣ ‹‹ለውጡ በትምክህተኞች ተጠልፏል የለም በፅንፈኛ ብሔርተኞች ተጠልፏል›› በሚሉ የንጭንጭ ወስፌዎች ከሁለት በኩል የሚጨቀጨቅ ቢሆንም፣ እንደ ምንም ወደ ፊት እየተጓዝን ነው፡፡

የሕገ መንግሥቱ አስኳል ፌዴራላዊ ሪፐብሊካዊ የሕዝብ ሥልጣን ነው፡፡ ይህ በነፃ ዴሞክራሲያዊ ሒደት አንዴም ዕውን ሆኖ አያውቅም፡፡ የኖርንበት የሩብ ምዕት ዓመት በላይ አገዛዝ በፌዴራላዊነትና በዴሞክራሲያዊነት ቅርፅ የሚነግድ የሕወሓት/ኢሕአዴግ አምባገነንነት ነበር፡፡ በፌዴራልም ሆነ በክልል ምክር ቤት ደረጃ ሕዝብን ይወክላሉ ተብለው ሲመረጡ የኖሩት ሰዎች የዚሁ አምባገነንነት አገልጋዮች ነበሩ፡፡ ሕገ መንግሥቱ ፓርቲና መንግሥት ይቀላቀሉ፣ ፓርቲ የመንግሥት ሥራዎችን ከላይ እስከ ታች ይዋጥ አይልም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ከፖለቲካዊ ወገናዊነት ገለልተኛ መሆን የሚገባቸውን ሁነኛ አውታራት፣ ገዥ ፓርቲ ያቦትልካቸው አይልም፡፡ ስንቱ ይቆጠራል! ኢሕገ መንግሥታዊ የሆነ ብዙ ነገር በኢትዮጵያ ምድር ኑሮ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

ዛሬ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ሆነን ለውጥ እናካሂድ ስንል፣ ምስቅልቅል ውስጥ እንዳንዘፈቅ በ‹ሆድ ሲያውቅ. . .› ሕገ መንግሥታዊ ወግ ውስጥ ስለመኖራችን ራሳችንን እየሸነገልን፣ ወደ ሕገ መንግሥታዊ/ዴሞክራሲያዊ ኑሮ እናምራ ማለታችን እንጂ፣ ኑሯችንን ረስተን ብልሽቶችን አራግፈን አይደለም፡፡ ያልቦተለኩ አውታራት (መከላከያ፣ ፖሊስ፣ ደኅንነት፣ ፍትሕ፣ ምርጫ አስፈጻሚ፣ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ፣ ወዘተ.) እንዲኖሩ ዛሬ የማሻሻያ ሥራዎች የሚካሄዱትም ያለፈውን ሕገ መንግሥት የደፈጠጡ ብልሽቶችን ለማረምና የሕዝብ ልዕልናን የተቀዳጀ ፌዴራላዊነትን ለመቆናጠጥ ተብሎ ነው፡፡ ያለንበትን ምዕራፍ የሽግግር ጊዜ የምንለውም ሕገ መንግሥትን ካሰነካከለ አፈና ወደ ሕገ መንግሥታዊነትና ወደ ዴሞክራሲ የማለፍ ጉዞ ውስጥ ስለሆንን ነው፡፡

ዛሬ የሽግግሩ ዋና ሥራ በመደናቀፍና በሌሎችም በተገለጹት ምክንያቶች ጦርነት ውስጥ ብንገባም፣ ይህ ግዳጅ ግን ዋናውን ጉዳይ ሊያስረሳን ከዚያም ትኩረታችንን ልናነሳ አይገባም፡፡ ዴሞክራሲ ገለልተኛ በሆኑ ተቋማት ላይ ካልተገነባ እንዲህ ያሉ ውስጣችን የሚፈነዱ የተቀበሩ ቦምቦች መላ ሰውነታችንንና መላ አገራችንን ሰቅዘው ይይዛሉ፡፡ የአገሪቱን የሥልጣን ዓምዶች ከየትኛውም ፓርቲና ቡድን ታማኝነትና መዳፍ ማላቀቅ ዛሬም ዋናው አደራችንና ግዳጃችን ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...