Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

 ‹‹በትግራይ ክልል የተፈጠረው ችግር ሲቋጭ የበጀት ድጎማው በቀጥታ እንዲደርስ ይደረጋል›› የገቢዎች ሚኒስትር፣ አቶ ላቀ አያሌው

የገቢዎች ሚኒስቴር የዘንደሮ በጀት ዓመት የአራት ወራት የገቢ አሰባሰቡን በተመለከተ ባለፈው ረቡዕ ኅዳር 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቶ ነበር፡፡ በዚህም በተጠቀሱት ወራት ለመሰብሰብ አቅዶ ከነበረው ገቢ 103 በመቶ ብልጫ ያለው ገቢ መሰብሰቡን አስታውቋል። መግለጫውን የተከታተለው ዮሐንስ አንበርብር በገቢ አሰባሰቡ ዙሪያ ከገቢዎች ሚኒስትሩ አቶ ላቀ አያሌው ጋር አጠር ያለ ቆይታ ያደረገ ሲሆን እንደሚከተለው ቀርቧል። 

ሪፖርተር– ባለፉት አራት ወራት ከፍተኛ ገቢ መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡ የተሰበሰበው ገቢ ምን ያህል እንደሆነና ካለፈው ዓመት አፈጻጸም ጋር እያነፃፀሩ ቢገልጹልን?

አቶ ላቀ– በዘንድሮው የበጀት ዓመት ለመሰብሰብ ያቀድነው አጠቃላይ ገቢ 290 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ይህ በ12 ወራት ተሸንሽኖ ታቅዷል፡፡ በዚህም መሠረት የአራት ወራት ዕቅዳችን 104.5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ነበር፡፡ በአራት ወራት የሰበሰብነው ግን 107.6 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ የዕቅዳችን 103 በመቶ መሰብሰብ ችለናል፡፡ ይህንን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ስናነፃፅረው የ17.3 ቢሊዮን ብር ዕድገት፣ ወይም 19.17 በመቶ ዕድገት አለው፡፡

ሪፖርተር– በአራት ወራት ውስጥ ከፍተኛ ገቢ ሊሰበሰብ ያስቻሉትን ምክንያቶች ቢገልጹልን? ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በኢኮኖሚው ላይ መቀዛቀዝ እየታየ ስለሆነ እንቅስቃሴዎች ተዳክመዋልና እንዴት ከፍተኛ ገቢ ልትሰበስቡ ቻላችሁ?

አቶ ላቀ፡– እውነት ነው ይህ ገቢ የተገኘው በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ኮሮና መጠነኛ ተግዳሮት ባደረሰበት፣ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች የፀጥታ ችግሮች በነበሩበት ሁኔታ ውስጥ ነው፡፡ ኮሮና ወረርሽኝን መከሰቱ እንደ ልብ እንዳንንቀሳቀስ፣ የተለያዩ የታክስ አሰባሰብ ተግባራትን የሚያሳልጡ ስብሰባዎችን እንዳናደርግ፣ እንዲሁም አገልግሎት አሰጣጣቻችንም በጤና ሚኒስቴር መመረያ መሠረት የተገደበ በሆነበት የተሰበሰበ ገቢ ነው፡፡ ግብር ከፋዮቻችንም በኮሮና ወቅትና ኮሮና ሳይኖር የሚኖራቸው የንግድ እንቅስቃሴ የተለያየ በመሆኑ አንዱ ተግዳሮት ነው፡፡ ቢሆንም በዚህ ውስጥና አንዳንድ የምናውቃቸው አካላት በሚፈጥሩት የፀጥታ ችግር ውስጥ ሆነን፣ ካለፈው ዓመትም ሆነ ከዚያ አስቀድሞ ከነበረው የተሻለ ግብር ባለፉት አራት ወራት መሰብሰብ ችለናል፡፡ ለዚህ ስኬት ዋነኛውን ድርሻ የሚይዙት ግብር ከፋዮቻችን ናቸው፡፡ ምክንያቱም ግብር ላለመክፈል የተለያዩ ሰበቦችን ለማቅረብ ያስችል ነበር ይህ ወቅት፡፡ ነገር ግን ምንም ሳያስቡ ያለባቸውን ግብር በወቅቱ በመክፈላቸው ትክክለኛ አገር ወዳድ፣ ታማኞች፣ ሕዝባቸውን የሚወዱ በመሆናቸው የተገኘ ስኬት ነው፡፡

በመሆኑም ከሁሉ አስቀድሜ ትልቁን ምሥጋና ለግብር ከፋዮቻችን እሰጣለሁ፡፡ የመሥሪያ ቤቶቻችን አመራሮችና ሠራተኞች፣ እንዲሁም እንደ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ባንኮችና የፀጥታ አካላት ያሉ አጋር አካላትም የበኩላቸውን ድርሻ ስላበረከቱ ሊመሠገኑ ይገባል፡፡ ሌሎቹ እንዳሉ ሆነው የግብሩ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ሊያድግ የቻለበት ምክንያት ግን፣ በዕዳ አሰባሳብ ላይ ስኬታማ ሥራ በመሠራቱ ነው፡፡ ዕዳ ያለባቸው ግብር ከፋዮችን ተከታትሎ ዕዳቸውን እንዲከፍሉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በዚህም ረገድ በአራት ወራት ውስጥ ለመብሰብ ያቀድነው ውዝፍ ዕዳ 8.3 ቢሊዮን ብር ዕዳ ለመሰብሰብ ነበር፡፡ የፈጸምነው ግን 11.4 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ይህም የዕቅዳችን 137.8 በመቶ ነው፡፡

ካለፈው ዓመት አራት ወራት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ ልዩነቱ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት አራት ወራት ውስጥ የተሰበሰበው የግብር ዕዳ መጠን 6.4 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም በዘንድሮ ዓመት ከተሰበሰበው 11.4 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የዘንድሮው 77 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ የሚለውንም ጠቅሶ ማለፉ ተገቢ ነው፡፡ ቀደም ሲል እንዳልኩት ግብር ከፋዩና የተቋማችን ሠራተኞች ያደረጉት ጥረት እንዳለ ሆኖ፣ ዋነኛው ግን መንግሥት በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ባለፈው ዓመት የዕዳ ምሕረት ማድረጉ ነው፡፡ መንግሥት በተለይም እስከ 2007 ዓ.ም. ድረስ ወለድ፣ ቅጣትና ፍሬ ግብር ላይ ምሕረት ያደረገ ሲሆን፣ ከ2008 ጀምሮ እስከ 2011 ዓ.ም. ድረስ ደግሞ ቅጣትንና ወለድን ምሕረት አድርጓል፡፡ ይህ ምሕረት የግብር ከፋዮቻችንን ሸክም የቀነሰ በመሆኑ፣ ግብር ከፋዮቻችን ፍሬ ግብሩን ብቻ መክፈል ቀላል ሆኖላቸዋል፡፡ በመሆኑም ግብር ከፋዮቻችን እየመጡ ያለባቸውን ዕዳ እየከፈሉና እየዘጉ ነው ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም ተቋሙ የታክስ ሕግ ተገዥነት እንዲጎለብት ለማድረግ የሚያስችሉ አገልግሎቶችን መጀመሩ፣ ለታማኝ ግብር ከፋዮች ዕውቅና መስጠቱና የመሳሰሉት የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ ባለፉት አራት ወራት የሰበሰብነው ጥቅል ግብር ከምንጊዜም የተሻለ ነው፡፡ የአራት ወራት የተጣራ የግብር አፈጻጸማችን ወይም ለመንግሥት ግምጃ ቤት ፈሰስ የተደረገውን ስንወስድ ደግሞ 98.8 ቢሊዮን ብር ነበረ ዕቅዳችን፡፡ 96 ቢሊዮን ብር ወይም 97.6 በመቶ አሳክተናል፡፡ የተጣራ ግብር ማለት ወደ ክልል የሚላከውን የጋራ ገቢ የሚባለው ቀንሰን፣ እንዲሁም ቫት ተመላሽ የሚለውን ቀንሰን ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር ፈሰስ ያደረግነው ማለታችን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቀደም ሲል የተጣራ ገቢ ማለት ለክልሎች ተመላሽ የሚደረግ የጋራ ገቢ ከተቀነሰ በኋላ የሚገኘው መጠን እንደሆነ ገልጸዋል። ባለፉት አራት ወራት ውስጥ ለክልሎች የተከፈለው የጋራ ገቢ ድርሻ ምን ያህል ነው? ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር መሻሻል ታይቶበታል?

አቶ ላቀ፡- ባለፉት አራት ወራት ካከናወናቸው የሪፎርም ሥራዎች አንዱና ትልቅ ድል የተመዘገበበት ጉዳይ ቢኖር፣ ለክልሎች የሚገባውን የጋራ ገቢ ድርሻ ማስተካከል ነው። የፌዴራል መንግሥትና የክልሎች የጋራ ገቢ ክፍፍል የሚደረገው 23 ዓመታት በፊት በተሠራ ቀመር ነበር። ይህ ቀመር ላለፉት 23 ዓመታት ሳይከለስ ቆይቷል፡፡ የፖለቲካ ለውጡ ካመጣቸው መልካም ጉዳዮች አንዱ ይህንን ቀመር ማሻሻል ነበር። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይህንን የጋራ ገቢዎች ማከፋፈያ ቀመር ከልሶ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ አፅድቆታል። በአሁኑ ወቅትም ወደ ትግበራ የገባ ሲሆንየገቢዎች ሚኒስቴርም በአዲሱ ቀመር መሠረት የጋራ ገቢዎች ተብለው በተለዩት የግብር ዓይነቶች ላይ፣ አዲሱን ቀመር በመጠቀም የክልሎችን ድርሻ መላክ ጀምሯል።

በቀመሩ መሠረት የክልሎችን ድርሻ ከማስላታችን በፊት መረጃ የማሰባሰብ ሥራ አከናውነን፣ በቀመሩ መሠረት ድርሻቸውን ልከናል። ለውጡ ካስገኛቸው ግዙፍ ስኬቶች መካከል አንዱ ይህ በመሆኑ፣ በተገቢው መንገድ ሕዝብ ሊያውቀው ይገባል። በአዲሱ ቀመር መሠረት የጋራ ገቢዎች ክፍፍል ባለፉት ሦስት ወራት የተከናወነ ሲሆን፣ ለምሳሌ በአዲሱ የጋራ ገቢዎች ማከፋፈያ ቀመር መሠረት ባለፉት ሦስት ወራት ለሐረሪ ክልል የተላከውን በመውሰድ፣ ይኸው ክልል ባለፈው ዓመትም ሆነ ላለፉት 23 ዓመታት ሲያገኝ የነበረውን ድርሻ ማነፃፀር የነበረውን ኢፍትሐዊነት ያሳያል። ባለፈው ዓመት የሐረሪ ክልል በቀድሞው የጋራ ገቢዎች ማከፋፈያ ቀመር መሠረት ተሰልቶ ለሐምሌ፣ነሐሴናመስከረም ወራት ወይም የበጀት ዓመቱ ሦስት ወራት ከጋራ ገቢዎች የተከፈለው ድርሻ 5,854 ብር ብቻ ነበር። 

ዘንድሮ ተግባራዊ መሆን በጀመረው አዲስ ቀመር ለተመሳሳይ ሦስት ወራት የተከፈለው የሐረሪ ክልል የጋራ ገቢዎች ድርሻ ግን 37.6 ሚሊዮን ብር ነው። ስለሆነም የሐረሪ ክልል ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ካገኘው 37.6 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው ገቢ አግኝቷል ማለት ነው። ያውም በሦስት የግብር ዓይነቶች ማለትም ኤክሳይስ ታክስ፣ ቫትና ተርን ኦቨር ታክስ ብቻ። ሌሎች የታክስ ዓይነቶች ሲጨመሩ ደግሞ ገቢው ከፍተኛ ይሆንለታል። ይህ የበጀት ድጎማን አይጨምርም፡፡ የጋራ ገቢ ክፍፍልን ብቻ ነው። ስለዚህ ለውጡ ለክልሎች ያስገኘው ይህንን ያህል ሀብት ነው። ከሐረሪ ውጪ ያሉት ክልሎችም በተመሳሳይ ከፍተኛ ገቢ ነው ያገኙት።

ለምሳሌ ባለፉት ሦስት ወራት ለሶማሌ ክልል የተከፈለውንከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ያለውን ልዩነት እንመልከት። የሶማሌ ክልል ባለፈው ዓመት የመጀመርያ ሦስት ወራት የተከፈለው የጋራ ገቢ ድርሻ 448,426 ብር ነበር። ዘንድሮ ግን በመጀመርያ ሦስት ወራት የተላከለት የጋራ ገቢ ድርሻ በአዲሱ ቀመር መሠረት  467 ሚሊየን 232 ሺሕ ብር ነው። ልዩነቱም 466 ሚሊየን 784 ሺሕ ብር ነው። ልዩነቱ በጣም የተጋነነ ስለሆነ በፐርሰንት መናገር አስፈላጊ አይደለም። ይህ በሦስት ወራት ብቻ የተከፈላቸው ነው፡፡ 12 ወራት ሲሆን ደግሞ ምን ያህል ጠቃሚ ገቢ ክልሎች ሊያገኙ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል።

ስለዚህ ለውጡ ክልሎች ለይስሙላ ይከፈላቸው የነበረውን ትርጉም ባለው ደረጃ በመቀየር፣ ለልማት ሥራዎቻቸው ጠቃሚ የሆነ ገቢ ማግኘት እንዲችሉያደረገ ነው። ከዚህ የተሻለ ማግኘት እንዲችሉ ደግሞ አጠቃላይ ገቢው እንዲጨምር በከፍተኛ ደረጃና በቁርጠኝነት ገቢ ማሰባሰብ ሥራ ላይ ጠንክረው መሥራት አለባቸው። 

ሪፖርተርለክልሎች የጋራ ገቢ ድርሻ መጨመር አስተዋጽኦ ያደረገው በፌዴሬሽን ምክር ቤት የፀደቀውን የማከፋፈያ ቀመር ለውጦችን ቢያስረዱን? 

አቶ ላቀ፡- ቀመሩ ካሻሻላቸው የጋራ ገቢዎች የማከፋፈያ ስሌት መካከል አንዱ፣ በፌዴራልና በክልል መንግሥት የተቋቋመ የልማት ድርጅት የትርፍ ድርሻ ክፍፍልን የሚመለከት ነው። ቀደም ብሎ በነበረው ቀመር መሠረት በጋራ ካቋቋሙት የልማት ድርጅት የሚገኝ ትርፍን የሚከፋፈሉት ባዋጡት ካፒታል መሠረት ነበር። አሁን በተደረገው ማሻሻያ ግን በጋራ ካቋቋሙት የልማት ድርጅት የሚገኝን ትርፍ እኩል ሃምሳ በመቶ እንዲከፋፈሉ ነው በቀመሩ የተወሰነው። 

ሌላው በጋራ በተቋቋመ ድርጅት ውስጥ የሚገኝ የሥራ ግብር ገቢን የሚከፋፈሉበትን መንገድ የተመለከተ ነው። ቀደም ብሎ በነበረው ቀመር መሠረት ይህንን የሥራ ግብር በእኩል ሃምሳ በመቶ ነበር የሚከፋፈሉት፡፡ አሁን በተሻሻለው ቀመር መሠረት ግን ድርጅቱ የሚገኝበት ክልል ከደመወዝ የሚገኝ ግብርን መቶ በመቶ እንዲጠቀምበት ነው የተወሰነው። 

በሌላ በኩል ከኤክሳይስ ታክስና ከቫት የሚገኝ ገቢ የሚከፋፈሉበትን ቀመር የተመለከተ ነው። በፊት በነበረው አሠራር ከቫት የሚገኝ ገቢ 70 በመቶ ለፌዴራል መንግሥት፣ ቀሪው 30 በመቶ የክልል ድርሻ ነበር። በተሻሻለው ቀመር መሠረት ግን ከቫት የሚገኝ ገቢ 50 በመቶ ለፌዴራል፣ ቀሪው 50 በመቶ ደግሞ ድርጅቱ የሚገኝበት ክልል ድርሻ እንዲሆን ነው የተወሰነው። ድርጅቶ ከአንድ በላይ በሆኑ ክልሎች ውስጥ ቅርንጫፎች ያሉት ከሆነ ደግሞ፣ ለሠራተኛ በሚያወጣው ወጪ መሠረት እንዲከፋፈል ነው የተወሰነው። 

ሌላው በቀመሩ ማሻሻያ የተደረገው ከማዕድን የሚገኝ ገቢ የሚከፋፈልበት አሠራር ሲሆን፣ ቀደም ባለው አሠራር ከማዕድን የሚገኝ ገቢ 60 በመቶ ለፌዴራል መንግሥት፣ ቀሪው 40 በመቶ ደግሞ ማዕድኑ የሚወጣበት ክልል ድርሻ ነበር። አሁን በተሻሻለው ቀመር ደግሞ ሃምሳ በመቶ ማዕድኑ ለወጣበት ክልል ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ አሥር በመቶው ማዕድኑ የተገኘበት ማኅበረሰብ በቀጥታ ተጠቃሚ እንዲሆን ለወረዳው ወይምዞን የሚከፈል ነው። ከተቀረው ሃምሳ በመቶ ውስጥ የፌዴራል መንግሥት 25 በመቶ ድርሻ እንዲያገኝ የተወሰነ ሲሆን፣ ቀሪው 25 በመቶ ለሁሉም ክልሎች የሚከፋፈል ነው። ምክንያቱም ማዕድን የአንድ ክልል ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የአገር ሀብት ስለሆነ።

ሪፖርተርበትግራይ ክልል ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ከክልሉ የሚገኘውን የታክስ ገቢ አልቀነሰውም? በአጠቃላይ የገቢ ዕቅዳችሁ ላይ ያለው አንድምታ ምን እንደሆነ ቢያብራሩልን?

አቶ ላቀ፡- በትግራይ ክልል ውስጥ ያለው ውጊያ ከክልሉ በሚሰበሰበው ገቢ ላይ ተፅዕኖ አይኖረውም ወይ ላልከው ይኖረዋል። በተለይም ደግሞ ቶሎ የማይቋጭ ከሆነ የበለጠ ተፅዕኖ ይኖረዋል። ለምሳሌ መቀሌ ያለው ቅርንጫፋችን ባለፉት ሦስት ወራት ሲሰበስብ የነበረው የዕቅዱን መቶ በመቶ ነበር፡፡ ለተከታታይ ሦስት ወራት። በአራተኛው ወር ግን የተሰበሰበው 61 በመቶ ብቻ ነው። ውጊያው ከተጀመረ በኋላ ያለው ደግሞ አልተሰበሰበም ማለት ነው። መቀሌ ውስጥ ባለን ቅርንጫፍ በዚህ ዓመት ይሰበሰባል ብለን ያቀድነው 2.4 ቢሊዮን ብር ነው። ይህንን በአጠቃላይ በዓመት ውስጥ ለመሰብሰብ ካቀድነው 290 ቢሊዮን ብር አንፃር ከመዘንከው ኢምንት ነው። ግን ደግሞ 2.4 ቢሊዮን ብር ቀላል ገቢ አይደለም። ጦርነቱ ከመጀመሩ ቢፊት በነበሩት ወራት በክልሉ በየወሩ ይሰበሰባል ተብሎ የታቀደውን መቶ በመቶ ሲሰበሰብ የነበረ በመሆኑ፣ ጦርነቱ እስኪጀመር ድረስ 860 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል። ስለዚህ በቀሪዎቹ ወራት 1.5 ቢሊዮን ብር ይጠበቃል ማለት ነው ከትግራይ ክልል። የተጀመረው ሕግ የማስከበር ዘመቻ ቶሎ ከተጠናቀቀ ቀሪውንም ገቢ መሰብሰብ ይቻላል። ነገር ግን የቀረው ገቢ በአጠቃላይ ዘንድሮ ይሰበሰባል ተብሎ ከታቀደው ዓመታዊ የታክስ ገቢ ውስጥ የትግራይ ክልል ድርሻ ኢምንት ነው። ከሌሎች የገቢ ዓይነቶች ሊካካስ የሚችል ነው። ነገር ግን ዋናው ጉዳይ ይህ አይደለም፡፡ የትግራይ ሕዝብም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም ማግኘቱ፣ በዚህ አካባቢ በመሸጉ ቡድንኖች አማካይነት በመላ አገሪቱ እየፈነዳ ያለው ግጭት መቅረቱና በሙሉ አቅማችን ወደ ልማት የመግባታችን ጉዳይ ነው። 

ሪፖርተር፡- ለትግራይ ክልል የሚተላለፈው የጋራ ገቢና የበጀት ድጎማ በቀጥታ እንዳይተላለፍ መወሰኑ ይታወቃል። ለክልሉ ሕዝብ መድረስ ያለበትን ይህንን ድጎማ እንዴት ነው የምታስተላልፉት? 

አቶ ላቀ፡- የትግራይ ክልልን በተመለከተ ጉዳዩ በገቢዎች ሚኒስቴር ብቻ የሚወሰን አይደለም። ችግሮች ሲቋጩ የትግራይ ሕዝብ ሊጎዳ ስለማይችል ይስተካከላል። ካሁን በፊትም የተወሰነው ክልሉ በቀጥታ እንዳያገኝ እንጂ፣ ለወረዳዎችና ለከተማ አስተዳደሮች መላክ እንዲቆም አልተባለም። አሁን ደግሞ ችግር ፈጣሪውን ለማስወገድ እየተሠራ ነው፡፡ በትግራይ ክልል የተፈጠረው ችግር ሲቋጭ የበጀት ድጎማ በቀጥታ እንዲደርስ ይደረጋል ማለት ነው። ለዚህም ሲባል ክልሉን በጊዜያዊነት የሚያስተዳድር አካል እየተዋቀረ ነው። ዋናው ነገር የተጀመረውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ መቋጨት ነው። ይህ ዘመቻ ሲቋጭ ክልሉም ይገላገላል፣ ሁላችንም ኢትዮጵያዊያን እንገላገላለን፣ ተጠቃሚም እንሆናለን ብዬ አስባለሁ። 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች