በአሮጌው የብር ኖት መገበያየት የሚቻልበት የጊዜ ገደብ በሁለት ሳምንት እንዲያጥርና ከኅዳር 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ መገበያየት እንደማይቻል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከብር ኖት ለውጡ ጋር በተያያዘ ይፋ ባደረገው መረጃ፣ የብር ኖት ለውጡን ለማካሄድ የተሰጠው የሦስት ወራት ጊዜ ቢሆንም፣ አሮጌውን ብር የመለወጫ ጊዜ እንደተጠበቀ ሲሆን፣ በአሮጌው ብር መገበያየት የሚቻለው እስከ ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ብቻ ነው፡፡ ከኅዳር 22 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ አሮጌ ብር መቀየር እንጂ መገበያየት አይቻልም፡፡ ከመስከረም 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ አሮጌውን ብር በአዲስ የብር ኖቶች እየተቀየረ መሆኑን የሚያስታውሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ አሮውን ብር የመቀየር ሥራ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተወስኖ እስካሁን ባለው የመቀየሩ ሒደት በተሳካ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ ሆኖም ግን አሮጌው ብር በአዲስ ብር የመቀየሪያው የመጨረሻ ቀን ታኅሳስ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ነው፡፡ ከዚህ ቀን በኋላ አሮጌ ብር በባንኮች የማይቀየር እንደሆነም አስታውቋል፡፡
የብር ኖቶቹ መቀየሪያ ጊዜ የቀሩት ከሦስት ሳምንት ያነሰ ጊዜ በመሆኑ፣ በቀሪዎቹ ቀናት ያልተቀየረ ብር እንዲቀየርና ሒደቱን ለማፋጠን ሲባል ከኅዳር 22 ቀን 2013 ዓ.ም. እስከ ታኅሳስ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ባሉት 15 ቀናት በአሮጌ ብር ግብይት መፈጸም የተከለከለ እንደሆነም አስታውቋል፡፡ ከኅዳር 22 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ ግብይት በማከናወን የሚቻለው በአዲሱ ብር ብቻ እንደሚሆንና በእነዚሁ የመጨረሻዎቹ 15 ቀናት ማንኛውም ሰው አሮጌውን ብር ወደ ባንክ ሄዶ መቀየር እንጂ ሊገበያይበት የማይቻል መሆኑንም ማወቅ እንዳለበት ከባንኩ መረጃ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡
ታኅሳስ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. የመጨረሻው የብር መቀየሪያ ቀን መሆኑ ታውቆ ኅብረተሰቡ በእጁ ያለውን አሮጌ ብር እንዲቀይር ያሳሰበው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የፌዴራል፣ የክልል፣ የከተማ አስተዳደርና የፀጥታ አካላትም ተገቢውን ትኩረት በመስጠት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያደርጉ ዘንድም ጠይቋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የብር ኖቶቹን ለመቀየር ሥራ ሲጀምር በሦስት ወራት ውስጥ አሮጌውንና አዲሱን የብር ኖት ጎን ለጎን እኩል ለግብይት እንደሚውሉ አስታውቆ የጀመረ ሲሆን፣ አሁን የአሮጌውን ብር የመገበያያ ጊዜ በ15 ቀን ያሳጠረው፣ የብር ኖት ለውጡ በአብዛኛው እየተጠናቀቀ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ያነጋገርናቸው የባንክ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡
ቀደም ብሎ የሦስት ወራት ጊዜ መሰጠቱን ተገቢ እንዳልነበርና የብር ኖት ለውጡ በሁለት ወራት ውስጥ መጠናቀቅ ይችል እንደነበርም የጠቀሱ አሉ፡፡ አሁን ባንኩ አሮጌውና አዲሱ የብር ኖቶች እኩል ሦስት ወራት ማገልገላቸው ቀርቶ፣ አሮጌው ብር በአዲሱ የብር ኖት የመቀየርያ ጊዜ ከመጠናቀቁ 15 ቀን በፊት በገበያው ውስጥ እንዳይኖር መደረጉ የብር ኖቱ ለውጡን ለማፋጠን ይረዳልም ይላሉ፡፡
እንደ ኃላፊዎች ገለጻ፣ በአሁኑ ወቅት የብር ኖት ለውጡ ወደ መጠናቀቅ ደረጃ ላይ በመሆኑ፣ ወደ ባንክ የሚመጡ አሮጌ የብር ኖቶች ቁጥር እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ ስለዚህ አሮጌን ብር በገበያ ውስጥ መገበያያ እንዳይሆንና የብር ኖት መጠናቀቂያ ጊዜው ከመድረሱ ከ15 ቀናት በፊት በገበያ ውስጥ እንዳይዘዋወር መደረጉ፣ ቀሪውን የብር ኖት በቶሎ ለመለወጥ ያስችላል፡፡ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ አሮጌውን ኖት የያዙ ወደ ባንክ መምጣትና መቀየር እንጂ ሊጠቀምበት ስለማይችል ኅብረተሰቡ አሮጌውን ብር በቶሎ ወደ ባንክ ያመጣል ተብሎ ይታመናል፡፡