Saturday, June 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አቢሲኒያ ባንክ ከፍተኛውን የተቀማጭ ገንዘብ ዕድገት አስመዘገበ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሀብት መጠኑ 57 ቢሊዮን ብር ደርሷል

ከግል ባንኮች 25ኛ ዓመት ላይ ከደረሱት ጥቂት ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የአቢሲኒያ ባንክ በ2012 የሒሳብ ዓመት፣ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን 47 ቢሊዮን ብር በማድረስ ከፍተኛ የሚባለውን ዕድገት ማስመዝገቡንና ከታክስ በፊት 1.08 ቢሊዮን ብር ማትረፍ መቻሉን አስታወቀ፡፡

ባንኩ የ2012 የሒሳብ ዓመት ለባለአክሲዮኖች ይፋ ባደረገበት ሪፖርቱ፣ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ማሰባሰብ የቻለው ተቀማጭ ገንዘብ በኢንዱስትሪው ከፍተኛ የሚባል የዕድገት ምጣኔ ያሳየበት ነው፡፡

የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ መሠረት ታ እንደገለጹትም፣ ለአንድ የንግድ ባንክ ዕድገት ዋነኛ መሠረቱ ተቀማጭ ገንዘብን ማሳደግ በመሆኑ፣ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ አቢሲኒያ ባንክ በ2012 የሒሳብ ዓመት ግልጽ አቅጣጫ አስቀምጦ በመንቀሳቀሱ ከፍተኛ የሚባለውን የተቀማጭ ገንዘብ ዕድገት ሊያስመዘግብ ችሏል፡፡ በዚህ መሠረት ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ 15.48 ቢሊዮን ብር ወይም 48.1 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ፣ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ከ32.15 ቢሊዮን ብር ወደ 47.63 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ችሏል፡፡ ይህ አፈጻጸም ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ማሰባሰብ አለብኝ ብሎ ካቀደውም በላይ ውጤት የተገኘበት ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ አቅዶ የነበረው 14.5 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር አፈጻጸሙ በ1.18 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ያሳየ መሆኑን የቦርዱ ሊቀመንበር ገልጸዋል፡፡ የተቀማጭ ገንዘቡ ዕድገት የተገኘው በዋናነት የገንዘብ አስቀማጭ ደንበኞቹን ቁጥር በማሳደጉ መሆኑም ተመልክቷል፡፡ የቦርድ ሊቀመንበሩ እንዳመለከቱትም ባንኩ በ2012 የሒሳብ ዓመት ብቻ 1.3 ሚሊዮን አዳዲስ ደንበኞችን ማፍራት በመቻሉና የባንኩን ጠቅላላ የገንዘብ አስቀማጭ ደንበኞችን ቁጥር ከቀደመው የሒሳብ ዓመት በእጥፍ በማሳደግ 2.6 ሚሊዮን ብር እንዲደርስ አስችሏል፡፡

ለባንኩ ደንበኞች ቁጥር መጨመር ሌላው ዓይነተኛ ምክንያት ተደርጎ የተጠቀሰው ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ብቻ የሚሰጡ ቅርንጫፎችን ቁጥር ማሳደግ በመቻሉም እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ በ2012 የሒሳብ ዓመት ከተሰበሰበው አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ የ5.9 በመቶ ድርሻ የያዘው ይኼው ከላይ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበ እንደሆነም የባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት ያመላክታል፡፡

ባንኩ በተጠናቀቀው 2012 የሒሳብ ዓመት እመርታ አሳይቼበታለሁ ብሎ በሪፖርቱ ያቀረበው፣ ለደንበኞቹ የሰጠው የብድር መጠንና ዕድገት ነው፡፡ በባንኩ መረጃ መሠረት የሰጠው ብድር መጠን ከቀዳሚ ዓመት የ56.9 በመቶ ወይም 13.5 ቢሊዮን ጭማሪ ያለው ነው፡፡ ይህም በሒሳብ ዓመቱ ዕቅድ አንፃር ሲታይም 106.6 በመቶ ወይም ከዕቅዱ በላይ ብድር ማቅረቡን ያሳያል ተብሏል፡፡

በአገር ውስጥ የተፈጠረውን የንግድ መቀዛቀዝ ተከትሎ የግንባታና ትራንስፖርት ዘርፎች ካስመዘገቡት ከእጥፍ በታች የሆነ አፈጻጸም የታየባቸው ቢሆንም፣ በሌሎች የቢዝነስ ዘርፎች የብድር አሰጣጥ ካለፈው የሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከእጥፍ በላይ ዕድገት የታየበት ነው፡፡ በሒሳብ ዓመቱ የተሰጡት ብድሮች ዕድገት የወጪ ንግድ 172.2 በመቶ፣ ኢንዱትሪ 146.3 በመቶ፣ ግንባታ 86.3 በመቶ፣ የገቢ ንግድ 184.5 በመቶ እና ግብርና 143.9 በመቶ ዕድገት እንደነበራቸወም አቶ መሠረት ተናግረዋል፡፡

የብድር ሥርጭቱን ከተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች አንፃር ሲታይም በሒሳብ ዓመቱ ለብድር ከዋለው ገንዘብ ውስጥ በመቶኛ ተከፋፍሎ ሲታይም የወጪ ንግድ 32 በመቶ፣ የአገር ውስጥ ንግድ 29 በመቶ እንዲሁም ኢንዱስትሪ 13 በመቶ በመያዝ ቀዳሚውን ድርሻ ይዘዋል፡፡

ባንኩ ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ጋር በተያያዘ በ2012 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ 400.3 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ አግኝቷል፡፡ ይህ አፈጻጸም ከቀዳሚው የሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ57.67 ሚሊዮን ዶላር ወይም የ16.8 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ የቦርድ ሊቀመንበሩ እንደገለጹት ደግሞ ይህ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ግን ባንኩ አገኘዋለሁ ብሎ ካቀደው የ503.9 ሚሊዮን ዶላር ጋር ሲነፃፀር በ103.6 ሚሊዮን ዶላር ያነሰ መሆኑን ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ለዚህም በአቻ ባንኮች ጋር ያለው የገበያ ፉክክርና ከውጭ ምንዛሪ ዝውውር ገበያው ጋር ተያይዞ ያሉ ሕገወጥ አሠራሮች እንዲሁም ኮቪድ-19ን ተከትሎ የተከሰተው አጠቃላይ የዓለም አገሮች ኢኮኖሚ መቀዛቀዝ፣ ከውጭ ሐዋላ መቀዛቀዝ ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ከውጭ ምንዛሪ ግዥና በውጭ ባንኮች ከሚገኙ የባንኩ ሒሳቦች የተገኘው ወለድ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር፣ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆኑ፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን በዕቅዱ ልክ ማሳካት እንዳልተቻለ አመልክተዋል፡፡

አቢሲኒያ ባንክ በሒሳብ ዓመቱ አፈጻጸም የባንኩ ጠቅላላ ገቢ 5.67 ቢሊዮን እንዲደርስ ያስቻለው ሲሆን፣ ይህ የባንኩ ጠቅላላ ገቢ ከ2011 የሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ32.3 በመቶ ወይም 1.38 ቢሊዮን ዕድገት እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዓመቱ ከተገኘው ጠቅላላ ገቢ ውስጥ ከብድር ወለድ የተገኘው ገቢ የ85.5 በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን፣ ቀሪው 14.6 በመቶ የሚሆነው ገቢው ደግሞ ከአገልግሎት ክፍያና ከሌሎች የገቢ ምንጮች የተገኘ መሆኑን የባንኩ ሪፖርት ያመለክታል፡፡

በአንፃሩ የባንኩ የ2012 የሒሳብ ዓመት ጠቅላላ ወጪ በ40.6 በመቶ አድጓል፡፡ በ2012 የሒሳብ ዓመት ጠቅላላ ወጪ 4.59 ቢሊዮን ብር ሲሆን ይህም ከቀዳሚው ዓመት ወጪ ጋር ሲነፃፀር 1.33 ቢሊዮን በመቶ ዕድገት የታየበት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የባንኩ ወጪ በዚህን ያህል ደረጃ ያደገበትን ምክንያት በተመለከተ አቶ መሠረት ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለጹት ለአጠቃላይ ወጪው መጨመር በዋናነት የሚጠቀሱት የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ማደግን ተከትሎ ለአስቀማጮች የተከፈለው ወለድ እየጨመረ በመምጣቱ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ጠቅላላ ወጪ ውስጥ ለአስቀማጮች የተከፈለው ወለድ የ39.4 በመቶ ድርሻ ሊይዝ ችሏል፡፡ ከዚህም ሌላ ለሠራተኞች የተከፈለው ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ለውጭም ጭማሪ አስተዋጽኦ ነበረው ተብሏል፡፡

ባንኩ ከሀብት አንፃር ያስመዘገበው ውጤት ከፍተኛ የሚባል ስለመሆኑ የተወሳ ሲሆን፣ በ2012 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ አቢሲኒያ ባንክ አጠቃላይ የሀብት መጠን 57 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህም ከ2011 የሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር የሀብት መጠኑን በአንድ ዓመት ውስጥ በ17.60 ቢሊዮን ወይም የ44.8 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ባንኩ በ2011 የሒሳብ ዓመት የነበረው ጠቅላላ የሀብት መጠን 39.3 ቢሊዮን ብር እንደነበር ሪፖርቱ አስታውሷል፡፡

ባንኩ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በተመለከተ ሰፊ ሥራ እየሠራ መሆኑንና የኤቲኤም ማሽኖቹን ቁጥር ከ173 ወደ 233 ማድረሱ ተገልጿል፡፡ በአሁኑ 400 ኤትኤምና 300 ፖስ ተገዝተው በመተከል ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የካርድና የሞባይል ባንክ ተጠቃሚ ደንበኞችን ቁጥር በማሻሻል፣ የካርድ ባንኪንግ ደንበኞች ቁጥር 910,567፣ የሞባይል ባንኪንግ ደንበኞች ቁጥር ደግሞ 708,945 ደርሷል፡፡ ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የባንክ ካርድ ደንበኞች ቁጥር የ40 በመቶና የሞባል ደንበኞች ቁጥር የ47 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡

ከባንክ ቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ ባንኩ ፈር ቀዳጅ የሆነበት አገልግሎ ተጠቅሷል፡፡ በአገሪቱ በዓይነቱ የመጀመርያ የሆነውን በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካይነት በርቀት ባሉ የደንበኛ አማካሪዎች በመታገዝ፣ የባንክ አገልግሎት የሚሰጠውን የቨርቹዋል ባንክ አገልግሎት መሠረት የተጣለበት የበጀት ዓመት የነበረ ሲሆን፣ ሥራው ተጠናቆ በዚህ በጀት ዓመት የመጀመርያ ሩብ ዓመት ላይ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አቶ መሠረት አስታውሰዋል፡፡

ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ያስመዘገበው የተሻለ አፈጻጸም ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔው ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ እንዲሆን አስችሎታል፡፡ በባንኩ ሪፖርት መሠረት በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በፊት ያስመዘገበው ትርፍ 1.08 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህ የትርፍ ምጣኔው ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ ስድስት በመቶ ወይም 57.3 ሚሊዮን ብር ብቻ ጭማሪ የታየበት ሆኗል፡፡ የትርፍ መጠን ዕድገቱ መጠነኛ በመሆኑም፣ የባንኩ የትርፍ ድርሻ ክፍፍል ዲቪደንድ መጠነኛ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ በ2011 የሒሳብ ዓመት የባንኩ አንዱ አክሲዮን ያስገኘው 7.23 በመቶ ሲሆን በ2012 ግን 7.20 በመቶ ሆኗል፡፡

የዘንድሮው የባንኩ ጠቅላላ ጉባዔ ከዓመታዊው የሥራ ክንውን ባሻገር ባለፉት ስድስት ዓመታት  በቦርድ አባልነት ሲሠሩና ሲያገለግሉ የቆዩ አመራሮች የሥራ ዘመን የሚጠናቀቅበት በመሆኑ፣ ተሰናባቹ ቦርድ የስድስት ዓመት ቆይታውን በአኃዝ ያመለከተበት ነበር፡፡  ተሰናባቹ ቦርድ ኃላፊነቱን በተረከበበት ሰኔ 2015 ላይ 11.12 ቢሊዮን ብር የነበረው የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ፣ በ2012 መጨረሻ ላይ 47.5 ቢሊዮን ብር መድረሱን እንዲሁም የአስቀማጭ ደንበኞች ቁጥር ከ478.000 ወደ 2.6 ሚሊዮን ደርሷል፡፡

የባንኩ የሀብት መጠን ከድስት ዓመታት በፊ ከነበረበት 13.7 ቢሊዮን ብር አሁን 56.42 ቢሊዮን መድረሱ ከተጠቀሱት ውስጥ ይገኙበታል፡፡

የተከፈለ ካፒታል መጠኑ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተመዘገበው 2.81 ቢሊዮን ወደ 3.15 ቢሊዮን በማደጉ የ12 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል፡፡ አቢሲኒያ ባንክ በአሁኑ ወቅት በ503 ቅርንጫፎቹ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን ከ6,700 በላይ ሠራተኞችን በመያዝ የሚንቀሳቀስ ባንክ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች