Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የጉድ አገር

‹‹አገራችን ምን ውስጥ ነበረች?›› የምንልባቸው ብዙ ድርጊቶችና ሸፍጦችን የምንሰማበት ጆሮ አላጣንም፡፡ ዓይናችንን በደንብ ከከፈትን ብዙ ልናያቸው የምንችላቸው ነገሮች እንዳሉም እናምናለን፡፡ የችግሮቹን ልክ ማወቅና ለዚያ የሚሆን መፍትሔ ማፈላለጉ ላይም የዛኑ ያህል እጅግ ወደኋላ የቀረን መሆኑንም እንገነዘባን፡፡ ‹‹ሙስና ተስፋፍቷል፣ ሕገወጥ ተግባራት ተበራክተዋል›› እያልን ከመናገር በዘለለ የችግሩን መጠን፣ እያደረሰና ሊያደርስ የሚችለውን ችግር በቅጡ አደራጅቶ ማሳወቅ ባለመቻሉ አገርን አደጋ ላይ የጣሉ ብዙ ድርጊቶችን እያየን ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተሰወነ ደረጃ እየተደረጉ ያሉ ፍተሻዎች አስገኙ የተባለው ውጤትም፣ ሕገወጥነት እንዴት ሥር እየሰደደ እንደነበር ማሳያ ነው፡፡ ይህም በአገር ላይ የተሠራውን ሸፍጥና ሌብነት ገና የተደረሰበት ስላለመሆኑም የሚመሰክሩ ናቸው ወደሚል መደምደሚያ ይመወስደናል፡፡

ሌላውን ነገር ሁሉ ትተን ከሰሞኑ በአንድ መድረክ ላይ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ፣ ‹‹አዲስ አበባ ውስጥ ባለቤት አልባ የሆኑ 100 ሕንፃዎች ተገኙ፤›› የሚለው አንደበታቸውን ብቻ እንውሰድ፡፡ ይህንን ንግግር ደግመን ደጋግመን ካሰብነው አንዳንዴ ለማመን የሚከብድ ነው፡፡ ልብ በሉ በከተማዋ ውስጥ ባለቤት የሌላቸው ሆነው የተገኙ 100 ሕንፃዎች ናቸው፡፡ ይህ ግኝት ደግሞ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት የተደረሰበት ከመሆኑ አንፃር፣ አሁንም ተመሳሳይ ሥራ ቢሠራ ከዚህ በላይ አጀብ የምንልበት ሕገወጥ ተግባራት ይገኛሉ፡፡

ከዳሰሳ ጥናት ወጣ ብሎ አድምቶ ከተፈተሸ ዛሬ ጉድ ያልንበት የ100 ሕንፃዎች ቁጥር ከዚህም ልቆ የሚገኝ መሆኑ ምንም አያጠራጥርም፡፡

አሁን ተደረሰ በተባለበት ደረጃ ግን ‹‹እነዚህን 100 ሕንፃዎች የገነቡ ሰዎች እነማን ናቸው?›› ከሚለው ጥያቄ ጀምረን ብዙ ጥያቄዎች እንድናነሳ ያደርገናል፡፡

አንድ ሕንፃ ለመገንባት ያለው ቢሮክራሲ የምናውቀው ነው፡፡ ከሕንፃ ግንባታው በፊት ‹‹የሕንፃ መገንቢያ ቦታው እንዴት ተገኘ? በሊዝ የተወሰደ ነው አይደለም? የግንባታ ፈቃዱ እንዴት ተሰጠ? ግንባታዎቹ ሲካሄዱ ገንዘቡን ማን አመጣ? ሕንፃዎቹ ዝም ብለው የሚበቅሉ አይደሉምና የኮንስትራክሽን የግንባታ ሥራው ማን ነበር የሠራው?›› የሚሉትን ጥቂት ጥያቄዎች አክለን ብንነሳ እንኳን፣ ለእነዚህ ባለቤት አልባ ሕንፃዎች ግንባታ ዙሪያ ብዙዎች እጃቸው እንዳለበት ያመለክተናል፡፡ ካልሆነ ‹‹ከግንባታና መሬት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ኃላፊነት ያለባቸው ተቋማትና ኃላፊዎች ምን እየሠሩ ነበር?›› ሊነግሩን ይገባል፡፡

በእርግጥም ሕንፃን የሚያህል ትልቅ ግንባታ ሲሠራ የማነው? ምንድነው? ብሎ የሚጠይቅ ደፋርስ የጠፋበት ምክንያት በራሱ የሌብነቱ ተዋንያን ሕንፃውን አስገንብተው ጠፉ የተባሉት ላይ ብቻ የሚወድቅ አለመሆኑ ነው፡፡

እነዚህ ሕንፃዎች ተገኙባቸው የተባሉ ክፍለ ከተሞች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ውስጥ ያሉ አመራሮች አፍንጫቸው ሥር ስለሚገነቡ ሕንፃዎች ካላወቁ ‹‹ምን ሲሠሩ ነበር?›› እነዚህ አካላት ባለቤት አልባ ናቸው የተባሉት ሕንፃዎች ሲገነቡ ትንፍሽ እንዳትሉ ተብለው ከሆነም ይህንኑ ጥያቄ በማቅረብ ባለቤቶቹን ነቅሶ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡

ለማንኛውም አገራችን ያለችበትን አስከፊ ሁኔታ የሚያሳየን በመሆኑና ከዚህም በላይ የምናገኘው ብዙ ነገር ስለመኖሩ የከተማ አስተዳደሩ ከዚህም በላይ ብዙ መሥራት ያለበት መሆኑን የሚጠቁም ነው፡፡

ስለዚህ ባለቤት አልባ ሕንፃ አገኘን ብቻ ሳይሆን ባለቤቶቹን የማወቅ ሥራው ትልቁ ተግባር መሆን አለበት፡፡ በምንም መንገድ ቢሆን አስተዳደሩ ባለቤት አልባ ሕንፃውን አገኘን በሚለው መረጃው ብቻ መቆም የለበትም፡፡ ግንባታውን ማን ሲያካሄድ እንደነበር ማጣራትና ሥውሩን ባለቤት ማደን፣ አድኖም ማንነቱን ማወቅ በቀጣይ ተመሳሳይ ሥራዎች እንዳይሠሩ በማገዝ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ እንደህ ያሉ መረጃዎችን ለማግኘት ደግሞ የአካባቢውን ነዋሪ በዚያ ሕንፃ ግንባታ ላይ ይሠሩ የነበሩ ሠራተኞች ሕንፃውን ሲያስጠብቁ የነበሩ ግለሰቦች ሁሉ ለመረጃ ማሰባሰቡ ጠቃሚ ይሆናሉ፡፡

ምክንያቱም ባለቤት አልባ የሆኑ ሕንፃዎች ማግኘት ብቻ በራሱ ግብ ያለመሆኑን መግለጽ የሚያስፈልገው የአገር ሀብት እንዴት ሲመዘበር እንደነበር በማስረጃነት የሚረዳና እንዲህ ያለውን ሕገወጥ ተግባር ሲፈጽሙ የነበሩትን ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ለሕግ በማቅረብ ስለሚረዳ፣ ተመሳሳይ ሥራ እንዳይሠራ ከዚህ በኋላ ምን ይደረግ የሚለውን መፍትሔ ስለሚያስቀምጥልን ጭምር ነው፡፡ በዚህች አገር ላይ እንዲህ ያለውን ሸፍጥ የሠራውና የተባበረውን አፈላልጎ ማንነቱ ካልተገለጸ፣ ተገልጾም ለሕግ ካልቀረበ ደግሞ ለአገር አደጋ መሆኑንም ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ዜጎች መጠለያ አጥተው የኮንዶሚኒየም ቤት ለማግኘት አሥርና አሥራ አምስት ዓመታት እየጠበቀ ባለበት ከተማ፣ ‹‹መቶ ሕንፃዎች ባለቤት  አልባ ሆነው ተገኙ›› ማለት በትውልድ ላይ ምን ያህል እንደተቀለደ የሚያሳይ ነውና የእነዚህን ሕንፃዎች ጉዳይ ከከተማው ቤት ፈላጊዎች አንፃርም በማየት ዕርምጃው እንዲፈጥን ይፈለጋል፡፡ ሕንፃዎቹ በአንጡራ ሀብት የተገነቡ ቢሆኑ ባለቤት አያጡም፡፡ አሁን ካለው አንፃር ግን ለእነዚህ ሕንፃዎች ባለቤት መጥፋት አንዱ ምክንያት ግንባታው የተካሄደው በራስ ገንዘብ ያለመሆኑንና በሌብነት በተገኘ ገንዘብ የተገነባ ብቻ መሆኑን በመጥቀስ ብቻ መቅረት የሌለበት አገራዊ ጉዳቱ ተተንትኖ መቅረብ ይኖርበታል፡፡

ስለዚህ አስተዳደሩ በጥናቱ የደረሰበትና እስካሁን ያገኘው ውጤት ሊያስመሠግነውና ሌብነትን ለማስቀረት የሚኖረው አስተዋጽኦ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በዚህች ምስኪን አገር በዚህ ደረጃ ሲሸፍጡባትና ሕገወጥነትን ሲያስፋፉ የነበሩ ጠላቶቿን ማወቅ አለባት፡፡ እንዲህ ያሉ በግልጽ የሚታይ ግንባታ ሲካሄድ ብዙ ተባባሪዎች አሉና እነሱንም ከሕግ ፊት ማቅረብ የሕግ የበላይነቱን ለማስፈን የሚረዳ ነው፡፡ ሕግና መንግሥት እንደሌለ፣ በድፍረት ይህን ሕገወጥ ተግባር የፈጸሙ አካላትን ማግኘት፣ ብሎም መቅጣት፣ መሰል ድርጊት እንዳይፈጸም ስለሚረዳ፣ አስተዳደሩ በነካ እጁ ይግፋበት፡፡ ይሆናል ተብሎ የማይታመነው ነገር ግን በአዲስ አበባ የሆነውን ነገር እስከመጨረሻው ሊሠራበት ይገባል፡፡ ደግሞም ሕንፃዎቹ የትኞቹ እንደሆኑ ሕዝብ እንዲያውቃቸውና ከዚህ በኋላ ዕጣ ፈንታቸው ምን ሊሆን እንደሚችልም ማወቁ ተገቢ ነው፡፡ እንደገና ሌላ ወንጀል መፈጸሚያ እንዳይሆኑም ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት