Sunday, April 14, 2024

በትግራይ የተቀሰቀሰው ጦርነት ያስከተለው አሳሳቢ ሰብዓዊ ቀውስ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በቅርቡ ሕይወታቸው ያለፈው ታዋቂው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች፣ የአደባባይ ምሁርና ፖለቲከኛ መስፍን ወልደ ማርያም (ፕሮፌሰር) እ.ኤ.አ. በ1999 ባሳተሙት፣ ‹‹The Horn of Africa Conflict and Poverty›› በሚለው መጽሐፋቸው ላይ፣ ‹‹አፍሪካ ትራጀዲ ነች፡፡ ካሉት አኅጉራት ሁሉ ኋላቀር የሆነች አኅጉርም ነች፡፡ በአኅጉሩ በትክክለኛ አቅጣጫ የሚሄድ ነገር ያለ አይመስልም፤›› በማለት አስፍረው ነበር፡፡

ከዓመታት በፊት በተጻፈው በዚህ መጽሐፍ ላይ ፕሮፌሰሩ አጠቃላይ አፍሪካ እንደ አኅጉር የሚደርስባትን የተደራረቡ ችግሮችና መከራዎችን የዘረዘሩ ሲሆን፣ በዋነኛነት ግን የአፍሪካ ቀንድ ተብሎ በሚጠራው ክፍለ አኅጉር አካባቢ የሚገኙ አገሮች ያሉባቸውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ እንዲሁም የፀጥታ ችግሮችን አጽንኦት ሰጥተው ጽፈዋል፡፡

በተለይ በዚህ ክፍለ አኅጉር ከዴሞክራሲያዊና ከሰብዓዊ መብቶች፣ ከኢዴሞክራሲያዊ አስተዳደር መስፈን፣ ከፀጥታ ሥጋት፣ እንዲሁም ከኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚመነጩ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ውጥንቅጦችን በተመለከተ ዘርዘር አድርገው በመጻፍ፣ አካባቢው ዴሞክራሲያዊና በሕዝብ የሚመረጥ መሪ ማስተናገድን በአስቸኳይ ካልተለማመደ በርካታ ንፁኃን ዜጎች ለሞት፣ ለአካል መጉደል፣ እንዲሁም ለስደት ከሚዳርገው የቀውስ አዙሪት መውጣት አዳጋች እንደሚሆንም አስገንዝበው ነበር፡፡

ከዓመታት በፊት በጻፉት መጽሐፍ ላይ የሠፈሩት የዜጎች መጎሳቆልና መፈናቀል እስካሁንም አልቆሙም፡፡ በክፍለ አኅጉሩ የሶማሊያ የእርስ በርስ ጦርነት፣ የሱዳን መገነጣጠል፣ እንዲሁም በደቡብ ሱዳን መሪዎች መካከል በተከሰተ የሥልጣን ሽኩቻ ሳቢያ የተፈጠሩ አለመግባቶች ጦር አማዘው በርካታ ዜጎች ለሞትና ለስደት መዳረጋቸው ለዚህ ማሳያ ነው፡፡

በክፍለ አኅጉሩ ከዚህ የቀውስ አዙሪት ገሸሽ ብላ የሰነበተችው ኢትዮጵያም፣ ከሁለት ሳምንት በፊት በተቀሰቀሰ ጦርነት ሳቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿ ጦርነቱን በመሸሽ ወደ ሱዳን እየተሰደዱ ነው፡፡፡

የጦርነቱ ቀናትና መጠን እየጨመረና እየሰፋ በሄደ ቁጥር ጦርነቱን በመፍራትና በመሸሽ ድንበር አቋርጠው ወደ ሱዳን የሚሰደዱ ዜጎች ቁጥር እንዲሁ እየጨመረ የሚገኝ ሲሆን፣ በርካታ የዓለም አገሮችና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ ተቋማት የስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን በመሥጋትና ሊደርስ የሚችለውን ሰብዓዊ ቀውስ ለማስቀረት፣ ጦርነቱ እንዲቆምና ለችግሩ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲበጅለት በመወትወት ላይ ናቸው፡፡  

እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን (UNHCR) ማብራሪያ ከሆነ፣ አሁን ወደ ሱዳን እየጎረፈ ያለው የስደተኞች ቁጥር ቢያንስ ባለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት ያልታየ መሆኑን በመጥቀስ ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጥና የንፁኃን ዜጎች ደኅንነት እንዲረጋገጥ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ጦርነቱን ተከትሎ ከተፈጠረው የስደተኞች ቁጥር በተጨማሪ ደግሞ፣ የንፁኃን ዜጎች ግድያን የተመለከቱ ዘገባዎችና ሪፖርቶች በመውጣት ላይ ናቸው፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያ በማይካድራ የደረሰውን ግድያ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡

ጦርነቱ ባስከተለው ስደትና የንፁኃን ዜጎች ሞት ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚያቀርቡት ‹‹የተነጋገሩ›› ውትወታ ምንም ዓይነት ፍሬ አላፈራም፡፡

በዚህ መሀል ዓርብ ኅዳር 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለትግራይ ክልል የሚሊሻና የልዩ ኃይል አባላት፣ በሦስት ቀናት ውስጥ እጃቸውን ለመከላከያ ሠራዊት እንዲሰጡ መልዕክት በማስተላለፍ አላስፈላጊ ከሆነ ዕልቂት ራሳቸውን እንዲያድኑ ጥሪ አቅርበው ነበር፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሳምንት መጀመርያ ላይ የተሰጠው የጊዜ ገደብ መጠናቀቁን በመግለጽ፣ የመንግሥት ሕግና ሥነ ሥርዓት የማስከበር ዘመቻ ወደ ወሳኙና የመጨረሻው ምዕራፍ መሸጋገሩን አስታውቀዋል፡፡

ከመጀመርያው አነስቶ የጦርነት ይቁም ጥሪ ሲቀርቡ የነበሩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና አገሮችም፣ በዚህ የመጨረሻውና ወሳኙ የተሰኘው ምዕራፍ የዜጎች ደኅንነት ሁኔታ እንዳሳሰባቸው በመግለጽ አሁንም ውትወታቸውን ቀጥለውበታል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ መሥሪያ ቤት (UNHCR) በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሪፖርት መሠረት የጦርነቱ መቀጠልን ተከትሎ ወደ ጎረቤት ሱዳን የሚሰደዱ ስደተኞች ቁጥር በሺዎች መጨመሩን በመግለጽ፣ ይህም አገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል አሳስቧል፡፡

ሴቶች፣ ወንዶችና ሕፃናት ወደ ሱዳን የሚያደርጉት ስደት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን የገለጸው ይህ ተቋም፣ በተለይ ከኅዳር 1 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ ባሉት ቀናት ውስጥ ቢያንስ በቀን 4,000 ስደተኞች ወደ ሱዳን እንደሚገቡ በመግለጽ፣ ይህም በሥፍራው ያለውን ለሰብዓዊ ዕርዳታ ምላሽ የመስጠት አቅምን እየተፈታተነ እንደሆነ ሁኔታውን አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት (UNOCHA) ማክሰኞ ኅዳር 8 ቀን 2013 ዓ.ም. በትግራይ ክልል ያለውን የሰብዓዊ ጉዳዮች ሁኔታን አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት መሠረት፣ ኢትዮጵያውያኑ በሦስት የድንበር መግቢያ በሮች አማካይነት ወደ ሱዳን እየገቡ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ እነዚህ ሦስት መግቢያዎች ደግሞ ሀምዳየት፣ ሉግዲና አብድራፊ እንደሆኑም ይፋ አድርጓል፡፡

በዚህም መሠረት ከማክሰኞ ኅዳር 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በየቀኑ ወደ ሱዳን የሚሰደዱት ኢትዮጵያውያን ቁጥር 4,000 እንደሆነ በመግለጽ፣ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ዓርብ ኅዳር 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ምሽት ድረስ ወደ ሱዳን የተሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ30,000 ሺሕ መብለጡን ገልጿል፡፡ ይህም የሰብዓዊ ዕርዳታን ከማከፋፈል አንፃር ያለው አቅም ውስን እንዲሆን ማስገደዱን አመልክቷል፡፡

ምንም እንኳን የተለያዩ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶችና የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች ሁለቱም ወገኖች ወደ ሰላም በመምጣት የተጋረጠውን ሰብዓዊ ቀውስ የመቀልበስ ሥራ እንዲከናወን ቢያሳስቡም ጦርነቱ በመቀጠሉ የስደተኞች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት በማሻቀብ ላይ ነው፡፡

በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚሰጥበት አንድ ራሱን የቻለ ዴስክ እንዲቋቋም ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን በበኩሉ ደግሞ፣ ‹‹ከኢትዮጵያ ባህል ፍፁም ያፈነገጠ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም የተወገዘና የአገራችንን ስም የሚያጎፍ ግድያ፣ ጥቃትና መፈናቀል እንዲቆምና ተጣርቶ አጥፊዎች በሕግ ይጠየቁ፤›› በማለት በአጽንኦት አሳስቧል፡፡

የሰብዓዊ ቀውስ መከሰትና መባባስ ያሳሰባቸው በርካታ ተቋማት በተለይ ዘንድሮ ካጋጠሙ የአንበጣ ወረርሽኝ፣ የጎርፍና የኮቪድ-19 ተፅዕኖዎች አንፃር በርካታ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር ሊያሻቅብ ይችላል የሚል ትንበያ ሲሰነዝሩ በነበረበት፣ የዚህ ጦርነት መከሰት ጉዳዩን ‹‹በእንቅርት ላይ … ›› እንደሚባለው አድርጎታል፡፡

የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ቃል አቀባይ የሆኑት ባባር ባላክ፣ ‹‹እዚህ የደረሱት ሰዎች ትንሽ ነገር ብቻ አንጠልጥለው ነው የመጡት፡፡ ይህም ስደተኞቹ ምን ያህል በጥድፊያ ብድግ ብለው መምጣታቸውን ያሳያል፡፡ ሕፃናቱ ድካምና ፍርኃት ይታይባቸዋል፡፡ የመንግሥታቱ የረድኤት ድርጅቶችና አጋሮቻችን ዕርዳታዎችን በፍጥነት ለማድረስ ቢሞክሩም፣ በላይ በላይ የሚመጡት አዳዲስ ስደተኞች በእጃችን ላይ ካለው ዕርዳታ በላይ እየሆኑ ነው፤›› በማለት የሁኔታውን አስከፊነት ገልጸውታል፡፡

እየደረሰ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ ከግምት በማስገባት ‹‹የተደረደሩ›› ጥያቄዎች እየጎረፉ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ ሕግና ሥርዓት የማስከበር ስለሆነ፣ ሕግና ሥርዓት ሳይሰፍን የሚደረግ ድርድርም ሆነ ንግግር እንደማይኖር በተደጋጋሚ በመግለጽ ላይ ነው፡፡

ሆኖም የሰብዓዊ ዕርዳታ በሚደርስበት ሁኔታ ላይ አጽንኦት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ሐሙስ ኅዳር 10 ቀን 2013 ዓ.ም. በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫና ማብራሪያ የሰጡት የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት የመረጃ ፍሰት ቃል አቀባይ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በተጀመረው ‹‹ሕግን የማስከበር ዕርምጃ›› ሥጋት፣ የተሰደዱ ኢትዮጵያውያንን ከሱዳን ለመመለስ መንግሥት እየሠራ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሰብዓዊ ዕርዳታዎችን ለማድረስም ከአገራዊና ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ ተቋማት ጋር በትብብር እየሠሩ እንደሆነም በማብራራት፣ ከሱዳን የሚመጡ ፈቃደኛ ስደተኞችን ለማስጠለል የሚችሉ ግንባታዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ፈቃደኛ ሆነው የሚመለሱ ስደተኞችን በመመለስ ዳንሻ አካባቢ እንደሚቀመጡም ተናግረዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ተቋማትም ሆኑ አገሮች ሰብዓዊ ቀውስ እየተከሰተ እንደሆነ ከመግለጽ ባይቦዝኑም፣ መንግሥትም ቀውሱን ለመቀልበስ እየሠራ እንደሆነ ቢገልጽም፣ ቀውሱን ከመስፋፋና በርካቶችን ሰለባ ከማድረግ የሚታደገው ሰላም ብቻ መሆኑን የሚገልጹ ድምፆች አሁንም በርካቶች ናቸው፡፡          

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -