Thursday, June 13, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የወሬ ትርፍ የለውም

በሽንኩርት

በዚህ ጋዜጣ ላይ በ“እኔ የምለው” ዐምድ ሥር ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም. የወጣውን የ’ሞቱማ ወልተጂ’ የብልፅግና ትሩፋቶች. . .! በሚል ርዕስ የተጻፈውን ጽሑፍ አንብቤዋለሁ፡፡ እናም የሞቱማን ግራ መጋባትና የቁልቁለት ጉዞ አንባቢዎች እንዲገነዘቡት ትንሽ ምላሽ መስጠት አሰብኩ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የመንግሥት የልማት ድርጅት እንደመሆኑ መጠን ለኅብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጥ የንግድ ድርጅት ሆኖ ሳለ ሞቱማ ሆዬ የፖለቲካ ትችት ማጣፈጫ ለማድረግ ለምን እንዳሰበ አልገባኝም፡፡ ጸሐፊው ሞቱማ የአገሪቱን የፖለቲካ ለውጥና በለውጡ ሒደት የነበሩትን ስንክሳሮች ያትታል፣ የብልፅግና ፓርቲን ርዕዮተ ዓለም ባለአዋቂ ሐሳቡ ይተቻል፣ ይህ አልበቃ ብሎት መላው የአገራችን ሕዝቦችና ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ያደነቀውን በአጭር ጊዜ ታላላቅ የልማት ኘሮጀክቶችን ዕውን መሆን በጥላቻ ይኮንናል፡፡

የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ወደ ሥልጣን ሲመጣ የተወሳሰቡና የተከማቹ ችግሮችን እንደ ተረከበ ይገልጽና በዚህ ችግር ውስጥ ሆነው የሠሯቸውን ድንቅና ተዓምራዊ ኘሮጀክቶች (የቤተ መንግሥት ዕድሳትና ለሕዝብ ክፍት መሆን፣ የእንጦጦ ፓርክና የወዳጅነት አደባባይ መዝናኛዎችን፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ደረጃቸውን ጠብቀው ባማረ መልኩ መሥራታቸውን) የተብለጨለጨ ሥራ በማለት የገለጸበት መንገድ አሳፋሪ ከመሆኑም ሌላ፣ ይኼ ሰው ኢትዮጵያዊ ነው ወይስ ግብፃዊ? የሚል ጥያቄ አጭሮብኛል፡፡ የእነ ሞቱማ አንዱ በሽታ እጅግ ሲበዛ ቀናተኛ መሆናቸው ነው፡፡ በመንግሥት ይቀናሉ፣ በሥራ ባልደረቦቻቸው ይቀናሉ፣ በሥራ ኃላፊዎቻቸው ይቀናሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በእሳቸው አጋፋሪነት የተሠሩ ኘሮጀክቶችን ለኅብረተቡ ሲያስተዋውቁ የሰጧቸውን ምሳሌዎች ሳይቀር ጥላሸት ቀብተው ለማለፍ ይሞክራሉ፡፡

እነ ሞቱማ ካለባቸው የወሬ ጥማት የተነሳ የፖለቲካ ትችታቸውን ሳይጨርሱ ወደ ሃይማኖት ተቋማት ጉዳይ በመግባት መርዛቸውን ለመርጨት ሲሞክሩም ይታያሉ፡፡ በደቡብ ክልል የጥምቀትና ደመራ በዓል ተከለከለ ብለው ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ መርዝ ከጣሉ በኋላ ስለመደመር ፍልስፍና ሊነግሩን ይሞክራሉ፡፡ ይህንኑ ሐሳብ በብስለት መተቸት ሲያቅታቸው እንደ ገና ስለ ፖለቲካ ኘሮፓጋንዳና ብሽሽቅ፣ ስለሚዲያ አጠቃቀም በጭፍን ሊያወሩ ይፈልጋሉ፡፡

እኔን በጣም የገረመኝ ግን ምንስ የወሬ ጥማት ቢኖርባቸውም ስለብልፅግና እያወሩ የኢትዮጵያ ጦር ወደ ሶማሊያ መግባትና የአልሸባብ ጦርነት ሲያወሩ አለማፈራቸው ነው፡፡ በእርግጥ ከዚህ በፊት ለሞቱማ በጻፍኩት ምላሽ የሰውየውን የአዕምሮ ጤንነት እንደ ምጠራጠር ነግሬያችሁ ነበር፡፡ አሁን እውነታውን አረጋግጫለሁ፡፡ ስለዚህ መታከምና መድኃኒት ማግኘት ይገባቸዋል ብዬ ስላሰብኩ መድኃኒት ላዝላቸው ወድጃለሁ፡፡ እኔስ ሽንኩርት አይደለሁ እስኪ ይጠቀሙብኝ፡፡

የእነ ሞቱማ ችግር ከላይ እንደ ገለጽኩት ቀናተኛ ናቸው፡፡ በእኔ አተያይ የኮርፖሬሽናችን ‹‹ሞቱማዎች›› ሁለት ናቸው፡፡ አንዱ ትልቁ ሁለተኛው ትንሹ ሞቱማ፡፡ ትልቁ ሞቱማ በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽንን እየጠቀሰ የአደረጃጀትና የሠራተኛ የምደባ ላይ ችግሮች እንደ ነበሩ ሲጽፍ ቆይቷል፡፡

በተጨማሪም በቅርቡ ለኮርፖሬሽኑ የተመደቡ ኃላፊዎችን የኋላ ታሪክ እያነፈነፈ ባልተጣራ መረጃ ሲካሰስ ነበር፡፡ ትልቁ ሞቱማ ከነበረበት የሥልጣን ጥም በመነሳት እሱ ተወዳድሮ የወደቀበትን የሥራ ዘርፍ ኃላፊነት ባለማግኘቱ የመጣው አመራር ሁሉ አይዋጥለትምና ዝናብ ባካፋ ቁጥር እሱ እያለቀሰ የዝናቡን ውኃ ያበዛው ይመስለዋል፡፡ ትልቁ ሞቱማ ያልተረዳው በአንድ አጀንዳ ላይ ከአንድ ጊዜ በላይ በጋዜጣ መተቸት የአንባቢን ጊዜና ለኅትመትም የሚወጣውን ወጭ ማባከን ነው፡፡ ይህ ደግም የአገራችንን ብልፅግና ወደ ኋላ ይጎትታልና እነ ሞቱማ ከብልፅግና ትሩፋቶች እንዳይቋደሱ ስለሚያደርጋቸው ማልቀሳቸውን አያቋርጡም፡፡

መቼም ስለትልቁ ሞቱማ ከዚህ በፊት በነበረው “ላለፈ ክረምት ቤት ይሠራ ይሆን” በሚል ርዕስ ሐምሌ 19 ቀን 2012 ዓ.ም. በወጣው የሪፖርተር ዕትም ላይ ምላሽ ስለሰጠሁ በዚሁ ይብቃኝ፡፡ ወደ ትንሹ ሞቱማ ልመለስ፡፡ ትንሹ ሞቱማ በኮርፖሬሽኑ በአንድ የንግድ ሥራ ዘርፍ የሒሳብ ክፍል ኃላፊ ሆኖ ሲሠራ የቆየ የትልቁ ሞቱማ አምሳያ ልጅ ነው፡፡

ትልቁና ትንሹ ሞቱማ የጋራ ግንባር እንዲፈጥሩ ያደረጋቸው ደግሞ የውስጣቸው የአቅም ማነስ ነው፡፡ እነኚህ ሁለቱ የኮርፖሬሽኑ ባልደረቦች ራሳቸውን ከማንም በላይ ከፍ አድርገው ያስቀምጣሉ፡፡ በሥራ ሲመዘኑ ግን ታናናሾች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል ትንሹ ሞቱማ ቀደም ሲል እንደ ገለጽኩት የአንድ ዘርፍ የሒሳብ ኃላፊ ሆኖ ሳለ የበጀት ዓመቱን የሒሳብ ሪፖርት በጊዜው ሠርቶ ባለማቅረቡ ሒሳቡ ከዓመት ዓመት ሲንከባለል በመቆየቱና ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ከኃላፊነት ተነስቶ ወደ ከፍተኛ የሒሳብ ባለሙያ ዝቅ እንዲል መደረጉን ልቦናው ያውቀዋል፡፡ በወቅቱ ያዙኝ ልቀቁኝ በማለት አስቸግሮም ነበር፡፡ እንግዲህ እንዲህ ዓይነቱ ስብስብ ራሱን ከድክመቱ ከማላቀቅ ይልቅ ሌሎች ጠንካሮችን እንደ እነሱ ደካማ ለማድረግ ከላይ ታች ሲሉ ይታያሉ፡፡ ኮርፖሬሽኑ ከተመሠረተ ወዲህ ላለፉት አራት ዓመታት ዓመታዊ ሒሳቡን በአግባቡና በወቅቱ ለመዝጋት ባለመቻሉ ሠራተኛው ተገቢውን ጥቅም እንዳያገኝ አድርጎት ቆይቷል፡፡

ከዚህም ሌላ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት የሒሳብ ሪፖርት መቅረብ ባለመቻሉ በንግድ ሥራውና በንግድ ፈቃድ ዕድሳት ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል፡፡ እንግዲህ በዚህ ሁኔታ ላይ ነው ለኮርፖሬሽኑ በተጓደሉ የሥራ ኃላፊዎች ቦታ አዳዲስ አመራሮች የተመደቡት፡፡ ይህን ጉዳይ ትልቁ ሞቱማ ደጋግሞ በሪፖርተር ላይ ሲጽፈው ቆይቷል፡፡ አሁን ደግሞ በአምሳያ ልጁ በኩል እንደ ገና አጀንዳ አድርጎታል፡፡ የአሁኑ የሚለየው ወቀሳው ዘር ተኮር መሆኑ ነው፡፡

እገሌ አዴፓ ነው እገሌ አይደለም ወደሚል ባልተጣራ መረጃ አሉባልታ ይረጫሉ፡፡ ለነገሩ ሁሉም አመራሮች የብልፅግና ትሩፋቶች በመሆናቸው እነ ሞቱማ ደግሞ የብልፅግና ጠላት በመሆናቸው ማንም ቢሆኑ አይዋጥላቸውም፡፡ ለማንኛውም መረጃችሁ ፎርጅድ ነውና እንደ ገና አጣሩት፡፡ ምነው ወሬውን ትተው ያጨማለቁትን ሰነድ ባስተካከሉት፣ የከፈቱትን ሒሳብ በዘጉት ኖሮ? ያኔ ጆሯችንን ከፍተን እንሰማቸው ነበር፡፡

በቅርቡ ለኮርፖሬሽኑ የተመደቡት አመራሮች እነ ማንም ይሁኑ ከየትም ይምጡ በአጭር ጊዜ መሠረታዊ ለውጥ አምጥተዋል፡፡ እነ እንቶኔ ያዝረከረኩትን ሲሰበስቡ፣ የበተኑትን ሲለቅሙ፣ የወዘፉትን ሲያፀዱ. . . ቆይተው የአራት ዓመት የሒሳብ ውዝፍ በአራት ወር ማፅዳት ችለዋል፡፡ የሒሳብ አዋቂ ነኝ የሚሉትን እነ ሞቱማ ትንሹ ደግሞ ሥራቸውን ትተው ደራስያን ሆነዋል፡፡ “ያሉሽን በሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ” እንዲሉ የራሳቸውን ጉድ በጀርባቸው ተሸክመው በቅናት መንፈስ ኮርፖሬሽኑን ማፍረስ ይመኛሉ፡፡

የነ ሞቱማ ሌላው ችግር እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ነው፡፡ አይሠሩም ግን ሰው ሠርቶ ለውጥ ሲያመጣ አያመሠግኑም፡፡ እነሱ ባለመሥራታቸው የሠራተኛውን ጥቅም ሲያሳጡ አዲሱ አመራር ስህተታቸውን አርሞ ሠራተኛውን የቦነስና የእርከን ተጠቃሚ በማድረጉ ሊያመሠግኑትና ሊያወድሱት ይገባ ነበር፡፡ ግን ንፉግ ናቸውና ራሳቸውንም ሌላውንም ይዘው ይጠፋሉ፡፡

ለአመራሩ የቤት ኪራይ ክፍያ ለምን ተስተካከለ ብለው ይጮሀሉ፡፡ ዞር ብለው ደግሞ ኑሮ ተወዷል፣ የቤት ኪራይ ጨምሯል፣ የኮርፖሬሽኑ ደመወዝና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችም የወቅቱን የኑሮ ውድነት ያገናዘበ አይደለም ብለው በመድረክ ይጮሀሉ፡፡ ከመነሻው እንዳልኳችሁ ሞቱማዎቹ ግራ ገብቷቸው ሌላውንም ግራ እያጋቡ ነውና ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ማለፍ ነው፡፡ የብልፅግና እንጂ የወሬ ትሩፋት የለውምና!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles