በየጊዜው በኢትዮጵያ በሚታየው የፀጥታ ችግርና ከዓምና መጋቢት ጀምሮ በተከሰተው ኮቪድ-19 ምክንያት ለሆዳቸው ያደሩ ነጋዴዎች አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ በተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ ሲያደርጉ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በመንግሥትና በትግራይ ክልል መካከል በተፈጠረው አለመግባባትና ጦርነት ምክንያት አንዳንድ ነጋዴዎች በሸቀጣ ሸቀጦች እና እህል ላይ አላስፈላጊ ጭማሪ አድርገዋል፡፡
የዋጋ ንረትን በተመለከተ ሪፖርተር በመሳለሚያ እህል በረንዳ፣ ሾላ እና የተለያዩ የግብይት ቦታዎችን ቃኝቷል፡፡ በመሳለሚያ ገበያ የሚሸምቱት አብዛኞቹ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ነጋዴዎች ሲሆኑ፣ እታች እየወረደ ሲመጣ ዋጋው ሊጨምር እንደሚችል ይገመታል፡፡ ሁኖም ጭማሪው ከመጠን በላይ መሆኑን ያነጋገርናቸው ሸማቾች ነግረውናል፡፡
በእህል በረንዳ የአድአ ጤፍ ዝቅተኛው በኪሎ 39 ብር ከሃምሳ ሳንቲም እየተሸጠ ሲሆን፣ አንደኛው ነጭ ጤፍ 40 ብር እና ከዚያ በላይ ሆኗል፡፡
የማረቆ በርበሬ በኪሎ 150 ብር ገበያ ላይ የዋለ ሲሆን፣ የፀዳሌ ከቦታው ከ180 እስከ 190 ብር ላይ እየተገዛ መሆኑን በስፍራው ያገኘናቸው ነጋዴው አቶ ጌታቸው ነግረውናል፡፡ የጎጃም በርበሬ ከ145 ብርና ከዚያ በላይ እየተሸጠም ነው፡፡
በኪሎ 150 ብር የነበረው ኮረሪማ 190 ብር ፣ ጥቁር አዝሙድ በኪሎ እስከ 160 ብር የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ እስከ 280 ብር በኪሎ እየተሸጠ ነው፡፡ ያነጋገርናቸው ነዳዴዎችም የጥቁር አዝሙድ እጥረት መኖሩን ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ሾላ አካባቢ ላይ ከሳምንት በፊት ለጤፍ ሸመታ የወጡ እናት አንድ ኪሎ በ46 ብር መሸመታቸውን ገልጸው፣ አሁን በየደረጃው ከ48 እስከ 50 ብርና ከዚያ በላይ ጭማሪ ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡
በዚያው አካባቢ የበርበሬ ዋጋ አንድ ኪሎ እስከ 175 ብር እና ከዚያ በላይ እየተሸጠ ነው፡፡ ተክለ ሃይማኖት በኪሎ ከ120 ብር ጀምሮ የሚሸጠው በርበሬ በዘነብ ወርቅ 150 ብር ይሸጣል፡፡ ዓምና በተመሳሳይ ወቅት የበርበሬ ዋጋ በኪሎ እስከ 80 ብር ወርዶ እንደነበር ይታወሳል፡፡
አንድ ኪሎ ሽንብራ 26 ብር፣ ባቄላ ከ25- 27 ብር እየተሸጠ ሲሆን፣ አተር ክክ፣ ድፍን አተር ከ40 እስከ 42 ብር እየተሸጠ መሆኑን የእህል በረንዳ ነጋዴ አቶ ሙራድ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በሾላ ገበያ የጤፍ ዋጋ 46፣ 48 እና 50 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ይኼም ካለፉት ወራት ጋር ሲነፃፀር መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ገበያተኞች ገልጸዋል፡፡
ጥራጥሬ ቀድሞም በነበረው ዋጋ እየተሸጠ እንደሚገኝ የገለጹልን ሸማቾች ምናልባት በተለያዩ ክልሎች የበረሃ አንበጣ በመከሰቱ ምክንያት ዋጋ ጭማሪ ሊኖር ይችላል ብለው መሥጋታቸውን ሆኖም ከታኅሣሥ በኋላ አዲስ እህል ሲገባ ይበልጥ ቅናሽ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ነጋዴዎችም ይህንኑ ሐሳብ ተጋርተዋል፡፡
ሰሞነኛ ኮሽታ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተነሳ ቁጥር የንግድ ሰንሰለቱ ላይ የዋጋ ንረት መታዘብ ከጀመርን ሰንበት ያለ ቢሆንም መንግሥት በትግራይ ክልል ላይ በጀመረው ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴ ምክንያት የተወሰነ የዋጋ ጭማሪዎች መኖሩ በተዘዋወርንባቸው የገበያ ማዕከላት ታዝበናል፡፡
አንዳንድ ነጋዴዎች እንደተናገሩት ደግሞ የዋጋ ንረት ሊኖር የቻለው ከገበሬው ማሳ ጀምሮ ነጋዴ እጅ እስኪገባ ባለው ሰንሰለት ነው፡፡ ችግሩ መፍትሔ ተበጅቶለት ዕልባት ካገኘ ነጋዴዎችም ሆኑ ተጠቃሚው ማኅበረሰብ አገልግሎቱን በተመጣጣኝ መልኩ ማግኘት እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 አካባቢ ላይ የጥራጥሬ እህሎችን በመሸጥ ላይ የሚገኙ ነጋዴዎች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በተለያዩ የጥራጥሬ እህሎች ላይ የዋጋ መናር እንደታየና አብዛኛው ሸማችም ቅሬታ እያቀረቡባቸው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በተለይም ጤፍ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
የእህል ዋጋም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣበት ዋነኛ ምክንያት በአገሪቷ በሚከሰቱ ሁከቶች አማካይነት እንደሆነና አቅራቢውም ይህንን ተገን በማድረግ የዋጋ ጭማሪ በማሳየቱ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊትም ይሸጡ የነበሩ የእህል ዘሮች ዋጋቸው ተመጣጣኝ የሚባል እንደነበርና በአሁኑ ወቅት ግን ተገላቢጦሽ መሆኑ ትልቅ ችግር እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡
የዋጋው ንረትም ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ እንደሚገኝ፣ በዚሁ ከቀጠለም የእህል ቤታቸውን ዘግተው እንደሚቀመጡ በአሁኑ ወቅትም ትርፋቸው የቤት ኪራይ መክፈል ብቻ መሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
ያለውን ችግር መንግሥት ዕልባት ካላገኘለት አቅራቢዎችም ለነጋዴው በተመጣጣኝ ዋጋ ማስረከብ ካልቻሉና የዋጋ ንረቱ እየቀጠለ ከሄደ ትልቅ ፈተና እንደሚገጥማቸው ነጋዴዎቹ ገልጸዋል፡፡
በተለይም ደግሞ ለነጋዴው የሚያቀርቡ ግለሰቦች እህል አከማችተው እንደሚያስቀምጡና ጥራታቸውን የጠበቁ የእህል ዓይነቶችን ለነጋዴው እንደማያስረክቡ ጠቁመዋል፡፡
በአካባቢው ላይም በሸመታ ላይ የነበሩ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሰዎች እንደተናገሩት ፣ በየዕለቱ እየጨመረ የመጣው የጤፍና የጥራጥሬዎች ዋጋ አሳሳቢ እንደሆነና መንግሥትም ዕርምጃ መውሰድ እንዳለበት ይህ ካልሆነ ግን ከፍተኛ የሆነ ችግር እንደሚፈጠር አስገንዝበዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም አንድ ኪሎ ነጭ ጤፍ ከ47 እስከ 50 ብር ድረስ እየገዙ እንደሆነ ይኼም የሚፈለገውን ያህል ጥራቱን ያልጠበቀ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በተመሳሳይ አንድ ኪሎ ቀይ ጤፍ ከ43 እስከ 45 ብር እየገዙ መሆኑን ያከሉት፣ በሌሎች የጥራጥሬ የእህል ዓይነቶች ላይም የዋጋ ጭማሪው ከፍተኛ እንደሆነና ያሉበት ሁኔታም አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በመግለጽ ነው፡፡
ሌላው ደግሞ በታሸገ ውኃ ላይ የታየው ጭማሪ ነው፡፡ በ50 ብር ሲሸጥ የነበረው 20 ሊትር ውኃ (ጃር)
አሁን ላይ እስከ 65 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዳንኤል ሚኤሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ በመዘዋወር የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ነጋዴዎች ላይ ዕርምጃ ተወስዷል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ከ48 ሺሕ በላይ የንግድ ተቋማት ጋ በመሄድ ክትትል ማድረጋቸውንና ከዚህ ውስጥም 1973 የሚሆኑ የንግድ ተቋማት ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ መወሰዱንና የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን አቶ ዳንኤል ገልጸዋል፡፡
113 የሚሆኑ መጋዘኖች ላይም ዕርምጃ አንደተወሰደባቸው፣ እነዚህም መጋዘኖች አብዛኞቹ የምርት ክምችት በመደበቃቸውና ያለፈቃድ እየሠሩ በመገኘታቸው መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
የምርት አቅርቦቱ አናሳ እንዳይሆን ከክልልና ከአዲስ አበባ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር በቅንጅነት በመሥራት አገልግሎቱን እያቀረቡ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ተቋሙ የተለያዩ ኮሚቴዎችን በማዋቀር በየክፍለ ከተማው በመሄድ ሕገወጥ በሆነ መልኩ የሚሸጡ ነጋዴዎች ላይ ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በሕገወጥ መልኩ ሲሸጡም ሆነ ሲደብቁ የነበሩ ነጋዴዎችም ተገቢው ዕርምጃ እንደተወሰደባቸውና ከዚህ በኋላ እንደዚህ ዓይነት ተግባር የሚፈጽሙ ነጋዴዎች ተገቢውን ቅጣት እንደሚያገኙ ሳያሳውቁ አላለፉም፡፡
ከማኅበረሰቡ ጋር በመሆን ሕገወጥ ነጋዴዎችን በመከታተልና በመለየት ያለውን ችግር መፍታት እንደሚቻልም አስታውሰዋል፡፡
በተመስገን ተጋፋውና በሔለን ተስፋዬ