ሰላም! ሰላም! ድሮ የእኛ ሰው በአገሩ ጉዳይ ቀልድ አያውቅም ይባል ነበር። ጉድ እኮ ነው ዘንድሮ፡፡ የአሁኑ ትውልድ ደግሞ በአገር ጉዳይ ቀልድ የለም ብሎ እንደ አንበሳ እያደረገው ነው፡፡ የማየውና የምሰማው የአገር ፍቅር ስሜት ግለት አስገርሞኝ፣ ‹‹ባሻዬ የዓድዋ ጀግኖችን ታሪክ ሊደግም የተዘጋጀ ትውልድ እንዳለ መኖሩ አላስገረመዎትም?›› ስላቸው አዛውንቱ ባሻዬን፣ ‹‹እኛ ላይ ላዩን ስናይ ይመስለናል እንጂ፣ እውነት ነው የምልህ የጀግኖች የልጅ ልጆች አሁንም እንዳሉ ናቸው፡፡ ለካ አገር አፍራሾች ነበሩ ይህንን ጀግና ትውልድ አንገት አስደፍተው የኖሩት…›› አሉኝ። እውነታቸውን ነው፡፡ ትውልድ የሚያባክን የአገር ጠላት ዘራፊ ቡድን ያን ያህል ዓመት ላያችን ላይ የናጠጠው አናደደኝ። ‹‹እኛ ኢትዮጵያዊያን ወደ ቀልባችን ስንመለስ እኮ በአገራችን ጉዳይ አንደራደርም…›› ብለውኝ፣ ‹‹አሁን ዋናው ጉዳያችን መሆን ያለበት አገራችንን ትልቅ ለማድረግ ተባብረን መነሳት ነው…›› ካሉ በኋላ ተሰነባበትን፡፡ ከእሳቸው ተለይቼ ስሄድ አዕምሮዬን ሰቅዞ የያዘው ትዝታ ነበር፡፡ ትዝ የሚል ነገር ደግሞ ችላ አይባልም፡፡ እውነት ነው!
‹‹አምባሰል ተንዶ ግሸን ገድቦታል፣ የቆመውን ጀግና የተኛው ገድሎታል፣ የቆመውን ጀግና የተኛው መግደሉ፣ ሥፍራ በመያዙ በመደላደሉ…›› ያለችው ድምፃዊ ናት ትዝ ያለችኝ። ይህች ዕንቁ ድምፃዊ ምን ታይቷት ነበር? ይህንን አሳፋሪ ድርጊት ቀድማ ተገንዝባው ይሆን? ፈጣሪ ልባቸውን ብሩህ ያደረገላቸው ሰዎችን መስማት ምንኛ ደግ ነው እባካችሁ? ይህንን ዘመን ተሻጋሪ ዘፈን በትካዜ እያንጎራጎርኩ ሳለሁ፣ ‹‹ጀግና ፊት ለፊት ይገጥማል እንጂ ከጀርባ አድብቶ ወዳጁን አይጎዳም፡፡ በጦርነት የገጠመውን ጠላት ሲማርክም በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ትጥቁን አስፈትቶ፣ እንደ ሰላማዊ ሰው ይይዘዋል እንጂ እንደፈለገ አይጫወትበትም፡፡ የቆሰለ ጠላቱን አሳክሞ ሕይወቱን ይታደጋል እንጂ የራስህ ጉዳይ ብሎ አይተወውም፡፡ የማይረቡ የታሪክ ተወቃሽ ወንጀለኞች የሠሩት ግን በሰማይም በምድርም ያስጠይቃቸዋል፡፡ እውነቴን ነው የምልህ ከጀርባ የሚያደባ የአገር ጠላት እንጂ ምንም ሊሆን አይችልም…›› ያለኝ ደሙ ሲንተከተክ ያገኙት ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ ስንቶች ይሆኑ የተንተከተኩት!
እናላችሁ እንዲህ ዓይነቱን ሰይጣናዊ ነገር ሳስብ ክፉኛ እያዘንኩ ነው። ያሳዘነኝ ምኑ መሰላችሁ? ‹‹ክፋት በሰው ልጅ ታሪክ የአንበሳውን ድርሻ እየተጫወተ መቆየቱ ቢታወቅም፣ የሰው ልጅ የሰይጣንን ገጸ ባህሪ ወክሎ መጫወቱ የተለመደ ቢሆንም፣ እንዴት ሆኖ ነው ራሱ ሰይጣንን የሚያስደንቅ ሥራ ሠርቶ የሚኩራራው?›› ብዬ ምሁሩን የባሻዬን ልጅ ስጠይቀው፣ ‹‹ድሮ ቢያንስ ይሉኝታ የሚሉት ነገር ነበር፡፡ ዛሬ ሰይጣን የሚሳቀቅባቸው ፍጡሮች ግን ሌላው ቀርቶ ለልጆቻቸው ጭምር መጥፎ ታሪክ እያኖሩ እንደሆነ አልገባቸው ማለቱ ይደንቀኛል…›› አለ። እሱ ሲያወራ ብዙ ነገር አሰብኩ። አንድ ጊዜ አንድ ደንበኛዬ የነገረኝ አይረሳኝም፡፡ እንዴት ይረሳል!
ጎረቤቱ የሆነ ሰው ሁልጊዜ እየጠጣ እኩለ ሌሊት ቤቱ እየገባ ሚስቱንና ልጆቹን ይደበድባል፡፡ ጎረቤት ደርሶ እንዳይገላግል ማንም ሊደፍረው የማይችል በግንብ የታጠረ ግዙፍ ቪላ ውስጥ ነው ይህ ጉድ የሚፈጸመው፡፡ ሚስት ዓይኗ በልዞና ፊቷ ተጋግጦ ስትታይ በጣም ታሳዝናለች፡፡ ልጆችም እንዲሁ የዱላ ምልክት ፊታቸው ላይ ይታያል፡፡ ይህ አሳዛኝ ድርጊት ያበሳጫቸው ጎረቤቶች ይሰባሰቡና ለምን እንዲህ ዓይነት ክፉ ነገር እንደሚፈጽም አባ ወራውን ይጠይቁታል፡፡ ሰውየው በቤተሰቤ ማንም አያገባውም ብሎ ደንፍቶ ይሄዳል፡፡ ጎረቤቶች ለፖሊስ አቤት ይሉና ክስ ይመሠረትበታል፡፡ ፍርድ ቤት ቀርቦ ክሱ ሲነገረው ዳኞችን በመናቅ እንደለመደው መሳደብ ይጀምራል፡፡ ችሎት በመድፈር ተብሎ ስድስት ወራት ከርቸሌ ይላካል፡፡ ሁለት ወር ሳይሞላው በድንገት ሕይወቱ እስር ቤት ያልፋል፡፡ ቤተሰቡ መሞቱ ተነግሮአቸው ለቀብር ተዘጋጁ ሲባል፣ ‹ዕልልል…ዕልልል…ዕልልል…› አሉ አለኝ፡፡ የሕዝባችንን የሰሞኑ ሁኔታ ለሚያስተውል የጨካኞቹ ዕጣ ፈንታ እንዲህ አይመስላችሁም? ማን ያውቃል!
በመውጣትና በመግባት ዓይን የማያየው ጆሮ የማይሰማው ነገር የለም። በዚህ በእኛው አገር ደግሞ ደህና አምነውት ሐሳብን ትውት አድርገው ከተጋደሙበት አልጋ ብንን እንዳሉ፣ ከንፈር አስመጣጭ ዜና ይዞ ብቅ ይልባችኋል ከጎረቤት። ሰሞኑን በአገራችን ላይ የተከሰተው ዕልቂትና ውድመት ከተለመደው ውጣ ውረዴ ጋር ተደራርቦ ነው መሰለኝ፣ በነጋታው ድካሜ አልወጣልኝ ብሎ እስከ ረፋዱ ድረስ ተጋድሜያለሁ። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ማንጠግቦሽን አስፈቅዶ ገብቶ፣ ‹‹ድሮስ እንዳንተ ዓይነቱ ቀብራራ ደላላ ምን አለበት? በል ተነስ አሁን ቀብር ልንሄድ ነው…›› አይለኝ መሰላችሁ? ከተቀበርንበት የእንቅልፍ ጉድጓድ ሳንነቃ ቀብረን የጨረስነው ስንቱ ይሆን እናንተ? ክው አልኩና ተስፈንጥሬ ተነስቼ፣ ‹‹ማን ሞተ?›› ስለው፣ ‹‹ማን ያልሞተ አለ?›› አለኝ እየሳቀ። በሙታን አጉል ሲሳለቅ ሳየው ይኼው የእኔ ወዳጅ መቃብር ቆፋሪ መሰለኝ። ‹‹ቀልዱን ትተህ ምናለበት ብትነግረኝ? እኔ የሰማሁት ነገር የለም አልኩህ እኮ?›› ብለው ኮስተርና ቆምጠጥ ብዬ እሱ ግን አልተለወጠም። ለውጥ ላይ ሆነን አንለወጥም እንደሚሉት ይሆን እንዴ!
ጭራሽ ‘የአገር ልጅ በገንዘብ ይለወጣል ወይ፣ ሲሞቱ የሚቀብር ሲታመሙ የሚያይ’ ብሎ ይሞዝቅልኛል። ጉድ እኮ ነው! ‹‹ኧረ እባክህ አንተ ሰው?›› ብለው ብሠራው ሊሰማኝ አልቻለም። በስንት መከራ የሞተውን ሰው ማንነት ሲነግረኝ ለካስ በሠፈሩ የታወቀ የዋህ ሰው ኖሯል። ‹‹በነገራችን ላይ…›› አለኝ ጉድ የማያልቅበት ምሁሩ የባሻዬ ልጅ። ‹‹ስንትና ስንት መሰሪዎችና ሴረኞች በሰው ሕይወት የሚቆምሩ እያሉ፣ ደጋጉና የዋሁ ሲሞት ያበሳጨኛል…›› ሲለኝ ማንጠግቦሽ ወጣ ገባ ስትል ሰምታው ኖሮ፣ ‹‹ምን ዋጋ አለው? እነሱ ለሥልጣናቸውና ለጥቅማቸው ሲሉ የዋሁን እየነዱ እየላኩ ያስፈጃሉ፡፡ የማይጋፈጡት ጥቃት ሲቃጣባቸው ደግሞ እንደራደር እያሉ የማርያም መንገድ ለማመቻቸት የሚቀድማቸው የለም…›› አለችው። እነሱ በሰሞነኛው ጉዳይ የተግባቡ ይመስላሉ። በርካታ የሚያግባቡን የጋራ ጉዳዮች እያሉን በሴረኞች ምክንያት መግባባት አቅቶን፣ ለዕልቂትና ለውድመት የምንዳረገው ለምን ይሆን ብለን መጠየቅ መልመድ አለብን፡፡ ሴረኞች አገራችንን ሲያወድሙና ወገኖቻችንን ሲገድሉ እንዳላየ ሆነን የምናልፈው ለምንድነው? ያ ሁሉ ውርጅብኝ ከደረሰ በኋላ ለምን እናለቅሳለን? ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በቃ ማለት አለብን!
በሉ እስኪ እንሰነባባበት። ምንም እንኳ የሚሰማውና የሚታየው የመኖር ትጥቃችንን ሊያስፈታ ቢታገለንም፣ ይህን ያህል መተንፈሳችን አልጎዳንም። እሱም ተራው ደርሶ አትቁም እስኪባል ቋሚ ምን ይሆናል አትሉኝም? አዎ! ተስፋ ሳለ ምን ይሆናል። አዛውንቱ ባሻዬ ምን ሲሉኝ ነበር መሰላችሁ? ‹‹እሱ እስካለ ድረስ ብታጣ፣ ብትራቆት፣ ብትታረዝ ምን ማድረግ ትችላለህ? ‘እሱ የከፈተውን ጉሮሮ ሳይዘጋው አያድርም’ ትላለህ። ዳሩ እሱ የከፈተውን ጉሮሮ አረመኔ ሲዘጋው ዝም ያለ ቢመስልም፣ አሁን ግን እሱም ትዕግሥቱ ያበቃ ይመስላል። ሃይማኖትህም ሆነ ዘርህ ምንም ሆነ ምን መሠረቱ ትግሥትና ፍቅር መሆን አለበት። ይኼውልህ ምሳሌ፡፡ አንድ የቆሎ ተማሪ ‘በንተ ስለማርያም’ ይላል ጭራሮ አጥር ጥግ ቆሞ። ውስጥ ያሉ እናት ሰምተው ‘ተሜ አትቁም’ ይሉታል። ‘እመቤቴ እኔ መቼ ቆሜ? በእኔ ተመስሎ ፈጣሪ ነው የቆመው’ ቢላቸው፣ ‘ከምኔው አንተ ዘንድ ደረሰ? አሁን ሌማቴ ባዶ መሆኑን ከፍቼ አሳይቼ ሳልከድነው?’ አሉት። ተሜ ተራውን ‘ነው? እንግዲያስ ልቀመጥ’ ብሎ ተማሪነቱን ተወው ይባላል። የእኛ አገር ሰውም ለፈጣሪው ያደረሰው አቤቱታ እንዲህ ነው እየተሰማ ያለው ለማለት ነው!
አዛውንቱ ባሻዬ ቀጥለዋል፣ ‹‹ከከሃዲ ወዳጅ፣ ከአስመሳይ ፖለቲከኛ፣ ከሐሜተኛ ጎረበቴ ይሰውርህ የሚባለው ይኼኔ ነው። ስንፍና የጥበብና የተግሳፅ ጠላት ናት። አየህ ዓለም በማጣትና በማግኘት፣ በመውጣትና በመውረድ፣ በሞትና በሕይወት ጋጣ ስትከፋፈል ታግሶ ለሰነበተ፣ ቆሞ ለታዘበ፣ ታክቶ ላልተቀመጠ የማስተዋልንና የዕውቀትን ብርሃን ታበራለት ዘንድ ነው። ጅብ ቸኩሎ ምን ነከሰ? ቀንድ አትለኝም? ምንድነው እኔን ብቻ የምታስለፈልፈኝ? አዎ! ሁሉን ታግሰን እኛው በእኛው እዚሁ ተረባርበን ይህችን ምድር ብናርሳት ታጠግበናለች። እየተስገበገብን ግን ምንም አናገኝባትም። እህቴ ወንድሜ ተባብለን ካልተጋገዝን ፋይዳ ቢስ ነን፡፡ ክፉዎችንና ሴረኞችን የምናሸንፈው በአገር ፍቅር ስሜት በአንድነት ስንሠለፍ ነው፡፡ ‘ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱን፣ ነብር ዥንጉርጉርነቱን አይቀይርም’ ብሎ ወገብን ጠበቅ ማድረግ ይበጃል። እህ ሌላማ ያልሞከርነው ምን አለ?›› ሲሉኝ፣ ‹‹ምንም!›› ከማለት ውጪ ሌላ መልስ አልመለስኩም። ባሻዬ መልዕክታቸው ግልጽ ነው፡፡ እኛ እርስ በርሳችን ከተደጋገፍን አገራችንን ታላቅ ማድረግ አያቅተንም ነው የሚሉት፡፡ አገራችን ለሁላችንም ትበቃለች፡፡ አገራችንን ከክፉዎች እንጠብቃት፣ አገርን አንበድል፣ ሕዝብን አናሰቃይ ነው እያሉ ያሉት፡፡ መልዕክቱ በአገር ቀልድ የለም ነው፡፡ ጠንከር ሲል ደግሞ፣ ‹‹የመጣው ቢመጣ የማያሳፍረው፣ የአገር አለኝታ ጀግና ኢትዮጵያዊ ነው›› የሚል ነው፡፡ ሲጠቃለል ግን ሁላችንም አንድ ላይ ነን ይሆናል፡፡ መልካም ሰንበት!