ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት ላይ ከተገደለው ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ ክስ ተመሥርቶባቸው በእስር ላይ የሚገኙት እነ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ በንብረታቸው ላይ የተጣለው ዕግድ እንዲነሳ ያቀረቡትን አቤቱታ ፍርድ ቤት ውድቅ አደረገው፡፡
አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባና አቶ ሐምዛ አዳነን ጨምሮ ሌሎቹም አብረዋቸው የተከሰሱ ግለሰቦች ‹‹ዕግድ የተጣለባቸው የባንክ ሒሳብና ሌሎች ንብረቶች ዕግድ ይነሳልን›› አቤቱታ ውድቅ የተደረገው፣ ማክሰኞ ኅዳር 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ነው፡፡
አቤቱታውን የሚመራውና ክሱን እያየው ያለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት፣ ‹‹ዕግዱ ሊነሳ አይገባም›› በማለት ብይን ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን ቤተሰቦች ቀለብ በሚመለከት ማስረጃ ሲያቀርቡ ትዕዛዝ እንደሚሰጥም አስታውቋል፡፡
ተከሳሾቹ ያቀረቡትን ‹‹ዕግድ ይነሳልን›› ጥያቄ የተቃወመው ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ንብረቱ የወንጀል ፍሬ እንደሆነ በመግለጽ አቤቱታቸው ውድቅ እንዲደረግ መከራከሩና መዘገቡ ይታወሳል፡፡
አቶ ጃዋር፣ አቶ በቀለና አቶ ሐምዛ አዳነ ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ሲሆን፣ ምክንያታቸው ደግሞ ለደኅንነታቸው ሲባል እንደሆነ የተከሳሾቹ ጠበቆች ለፍርድ ቤት ተናግረዋል፡፡