በተያዘው ወር መጨረሻ አካባቢ ይሰጣል ተብሎ የነበረው የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ላልተወሰነ ጊዜ ሲራዘም፣ የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ብሔራዊ ፈተና ደግሞ እንደ ክልሎች ዝግጁነት ከታኅሳስ 1 እስከ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚሰጥ ትምህርት ሚኒስትር አሰታወቀ፡፡
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ፈተናውን አሁን ባለው አገራዊ ሁኔታ ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን አስመልክቶ፣ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የ12 ክፍል አገር አቀፍ ፈተና መንግሥት የትግራይ ክልልን ጨምሮ፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሕግ ማስከበርና የፀጥታ ችግሮችን መልክ ሲያሲዝ የሚሰጥ መሆኑን አቶ ሚሊዮን ገልጸዋል፡፡
ተማሪዎች ይህንን ተገንዝበው ለፈተና እየተዘጋጁ እንዲጠባበቁ ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል።
በሁለቱም የትምህርት ደረጃዎች የሚሰጠው ፈተና በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ ለነበረው የ2012 ዓ.ም. የትምህርት ክፍለ ጊዜ ሲሆን፣ የ2012 ዓ.ም. ሁለተኛ ሴሚስተር እንደሚያካትት ተገልጿል፡፡