Saturday, June 15, 2024

ሕዝብን ለአደጋ ማጋለጥ ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል ነው!

መንግሥት በትግራይ ክልል የጀመረው ዘመቻ ሦስተኛውና የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ በማስታወቅ፣ የሕወሓት አመራሮችና ታጣቂዎች እጃቸውን እንዲሰጡ የ72 ሰዓታት ጊዜ ሰጥቷል፡፡ የአገር መከላከያ ሠራዊትም መቀሌ ከተማን በመክበብ ለሦስተኛው ምዕራፍ በተጠንቀቅ ቆሞ ትዕዛዝ በመጠባበቅ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በዚህ የመጨረሻ የጭንቅ ወቅት ሕይወታቸው ለአደጋ የተጋለጠ ዜጎች ጉዳይ በጣም ያሳስባል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የዘመቻው ዓላማ ሕዝብን መታደግ እንደሆነ ገልጸው፣ በተለይ በከተሞች አካባቢ ሠራዊቱ ሰላማዊ ዜጎች የጥቃት ዒላማ እንዳይሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡ የትግራይ ሕዝብም በሕወሓት ከተነዛበት ፕሮፓጋንዳ በተቃራኒ የሠራዊቱን ሕዝባዊነት በዓይኑ አይቶ መመስከሩን ተናግረዋል፡፡ በዚህ በሦስተኛው የመጨረሻ ምዕራፍ በመቀሌ ከተማና ዙሪያ የሚገኙ ነዋሪዎች፣ የአልሞት ባይ ተጋዳይነት ሰለባ እንዳይሆኑ ይኸው ተግባር በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊከናወን ይገባል፡፡ በተለይ ንፁኃን ሰብዓዊ ጋሻ ሆነው እንዳይታገቱና ቀውስ እንዳይፈጠር ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚደረግ ተስፋ አለ፡፡ የመንግሥት ተቀዳሚ ዓላማም የሕዝብን ደኅንነት ማስከበር ስለሆነ፣ በዕገታ ሥር ያለው ሕዝብ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ እንደሚሰጠው ይታሰባል፡፡ የሕወሓት አመራሮችም ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል  እንዳይሠሩ ይጠንቀቁ፡፡

የሕወሓት አመራሮች በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ሆነው ያልተገባ ድርጊት ከሚፈጽሙ፣ እጃቸውን ሰጥተው ሕዝቡን ከአደጋ እንዲታደጉት በተለያዩ አቅጣጫዎች ጥሪ እየቀረበላቸው ነው፡፡ ይህንን ታሪካዊ አጋጣሚ ለራሳቸው ፍላጎት ብቻ ለማዋል ሲሉ ይህንን ጥሪ ችላ ቢሉ፣ ከሕግ ተጠያቂነት በተጨማሪ የታሪክና የትውልድ ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡ ለሕዝብ አለማሰብና ለራስ ብቻ መጨነቅ ወንጀል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም፣ ነፃነት፣ ዕድገትና ፍትሕ ያለበት ሥርዓት ነው የሚያስፈልገው እንጂ፣ ለጥቂቶች ፍላጎት ሲባል ብቻ ተገዶ የጦርነት ማገዶ መሆን የለበትም፡፡ ይህ ወሳኝ ወቅት ለሕዝብ የሚያስቡና በሕዝብ ላይ የሚቆምሩ የሚለዩበት ስለሆነ፣ ለሕዝብ ጠቃሚ ተግባር በማከናወን ቢያንስ በታሪክ መዝገብ ላይ ጥቂት ሥፍራ ማግኘት ቀላል አይደለም፡፡ ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት የማይጨነቅ ዓላማ ይዞ ሕዝባዊ ነኝ ማለት በፍፁም አይቻልም፡፡ ከዚህ ቀደም ሕዝባዊ ነን እየተባለ በሕዝብ ላይ የተፈጸሙ አሰቃቂ ድርጊቶች ብዙዎችን ሕይወታቸውን አስገብረዋል፣ ለእስር፣ ለሥቃይና ለስደት ዳርገዋል፡፡ በተጨማሪም ለከፍተኛ ሥነ ልቦናዊ ጉዳቶች አጋልጠዋል፡፡ በኢትዮጵያዊያን ስም መቆመርና መነገድ ጊዜው ያለፈበት በመሆኑ፣ ከአሁን በኋላ ማንንም ማታለል አይቻልም፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለያዩ ዘመናት የመከራ ቀንበሮችን እንዲሸከም ቢገደድም፣ በአገሩ ጉዳይ ግን መቼም ቢሆን ተደራድሮ አያውቅም፡፡ ይህ አኩሪና አስመኪ እሴቱ ኢትዮጵያን ለመከፋፈልና ለመበታተን ሲያሴሩ በነበሩ ጽንፈኞች ተጎሳቁሎ የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ግን በአራቱም ማዕዘናት አንድ ላይ ሆኖ ሉዓላዊነቱን ለማስከበር ተሠልፏል፡፡ በተጨማሪም በጦርነት ቀጣና ውስጥ ላለው የትግራይ ወገኑ የዕርዳታ እጁን መዘርጋት ጀምሯል፡፡ ይህ የሚያሳየው ደግሞ የትግራይ ወገኑ ከአስጨናቂ ችግር ተላቆ በሰላምና በነፃነት እንዲኖር ያለውን ልባዊ ፍላጎቱን ነው፡፡ በተለያዩ ክልሎች በተካሄዱ ሠልፎች በግልጽ የተነገረውም፣ ኢትዮጵያዊያን ለትግራይ ወገኖቻቸው አጋር መሆናቸው ነው፡፡ ሠራዊቱም በየደረሰበት ሥፍራ ለትግራይ ወገኖቹ አለኝታ መሆኑ በተግባር ተረጋግጧል ሲባል፣ በሰብዓዊ ጋሻነት አግተው የያዙት ኃይሎች በሕግና በታሪክ የሚያስጠይቅ ወንጀል ከመፈጸም መቆጠብ አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያዊነትን አኩሪ የጋራ ማኅበራዊ እሴቶች የሚንዱ ድርጊቶች ለታሪካዊ ጠላቶች ይጠቅሙ ይሆናል እንጂ፣ ለኢትዮጵያዊያን ግን ጥፋትና ውድመት ነው የሚጋብዙት፡፡ የሕወሓት አመራሮች ንፁኃንን ሰብዓዊ ጋሻ ለማድረግ ከወሰኑ፣ ከዚህ በፊት በፈጸሙዋቸው ወንጀሎች ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል እንደሚፈጽሙ ሊረዱት ይገባል፡፡

በዚህ ወሳኝ ወቅት የእምነት ተቋማት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ምሁራንና ወጣቶች በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ በሚገኙ ሚዲያዎች በይፋ ንፁኃንን ያገቱ ኃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ግፊት ማድረግ አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ ሳትወድ ተገዳ ከገባችበት ጦርነት በፍጥነት ተላቃ ወደ ልማትና ዕድገት መገስገስ አለባት፡፡ ለአደጋ የተጋለጡ ወገኖችን ሕይወት መታደግ ይገባል፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ አካባቢዎች በማንነታቸው ምክንያት የሚጨፈጨፉ ወገኖች ጉዳይ ዕልባት ማግኘት አለበት፡፡ በግፍ ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለው በየመጠለያው የሚገኙ ወገኖቻችን በፍጥነት እንዲቋቋሙ፣ ከማናቸውም ዓይነት ጥቃት የሚከለሉበት አስተማማኝ ጥበቃ እንዲያገኙና ጥቃት የሚፈጽሙ ኃይሎችም ታድነው ለሕግ እንዲቀርቡ መረባረብ ግዴታ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ማግኘት የምትችለው ሕግና ሥርዓት ሲከበር ነው፡፡ ሕግና ሥርዓት የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት ደግሞ የመንግሥት ተግባር ነው፡፡ መንግሥት ይህንን ተግባሩን መወጣት ሲያቅተው አገር አላስፈላጊ መስዋዕትነት ለመክፈል ትገደዳለች፡፡ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍልም ሆነ በተለያዩ አካባቢዎች የገጠሙ ፈተናዎች፣ ሕግን ለማስከበር አለመቻል ውጤት መሆናቸውን ማመን የግድ ነው፡፡

መንግሥት በትግራይ ክልል የጀመረው ሕግ የማስከበር ዘመቻ ብልኃትና ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንዲጠናቀቅ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያሳየውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ጥርጣሬ የሚያጭሩና በሕዝቡ መሀል አለመግባባት የሚፈጥሩ ሐሰተኛ መረጃዎች እየተበራከቱ ስለሆነ፣ መንግሥት የመረጃ ፍሰት ማዕከሉን ንቁና ብቁ በማድረግ መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ማሳወቅ ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ አስጨናቂ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ግብግቡ የሚካሄደው ሕዝብ በሚኖርባቸው ሥፍራዎች ስለሚሆን፣ ሐሰተኛ መረጃዎች ቀልባቸውን ወደ አካባቢው ያደረጉ ኢትዮጵያዊያንንና ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ጭምር ሊረብሹ ይችላሉ፡፡ ያልተጣሩ መረጃዎች በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ማንነታቸው በማይታወቁ ምንጮች እየተጠቀሱ ሲሠራጩ፣ መንግሥት ተጨባጩን ሁኔታ ከሥር ከሥር ማሳወቅ ይጠበቅበታል፡፡ የመጨረሻውን ምዕራፍ ለመጀመር ሰዓታት በሚቀሩበት በዚህ ከባድ ጊዜ የንፁኃን ሕይወት ትልቅ ትኩረት ስለሚሰጠው፣ ኢትዮጵያዊያን እንደ ወትሮው በአንድነት በመቆም ሁኔታውን በአንክሮ መከታተል አለባቸው፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ሕዝብን ሰብዓዊ ጋሻ አድርጎ ለመጠቀም ያሰበው ኃይል ማን እንደሆነ በትክክል እንዲገነዘብ፣ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ በተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ኃላፊነት የማይሰማቸውን ግለሰቦችና ቡድኖች በማጋለጥም፣ ወደፊት በሕግ እንዲጠየቁ መተባበር የግድ ይሆናል፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ ዘመቻ መልስ በፍጥነት አገግማ በሙሉ ኃይሏ ፊቷን ወደ ልማት ማዞር አለባት፡፡ በተቻለ መጠን ሰብዓዊ ቀውስ እንዳይፈጠር ብልኃትና ጥንቃቄ በሁሉም መስኮች መደረግ ይኖርበታል፡፡ በንፁኃን ሕይወት በመቆመር ዓላማን ማሳካት እንደማይቻል በተግባር እየታየ ስለሆነ፣ ኢትዮጵያውያን በሰላምና በነፃነት የሚኖሩበት ሥርዓት ለመመሥረት የሚያግዝ ዝግጅት ላይ ማተኮር ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የልማት፣ የነፃነት፣ የፍትሕና የእኩልነት ምድር እንድትሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ የሆነ መተሳሰብ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ልዩነትን በጠመንጃ ሳይሆን በሐሳብ ልዕልና መፍታት ወይም ማቀራረብ እንደሚቻል የሚያስችሉ ብሔራዊ ውይይቶችን የሚፈጥሩ መድረኮች እንዲፈጠሩ መዘጋጀት መሠልጠን ነው፡፡ ሕዝብ የሚፈልገው ከአስመራሪው ድህነት በፍጥነት ወጥቶ በክብርና በነፃነት መኖር ነው፡፡ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህ ክብር ይገባዋል፡፡ ሕዝብን አፍኖና ጨቁኖ መግዛት ጊዜ ያለፈበት ያረጀ አስተሳሰብ ነው፡፡ ዓላማን በጉልበት ለማስፈጸም በሕዝብ ሕይወት ላይ መቆመር ለዚህ ዘመን አስተሳሰብ አይመጥንም፡፡ በትዕቢትና በዕብሪት ተወጥሮ ጦርነት መቀስቀስ ያዋርዳል እንጂ አያስከብርም፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚመጥነው በአርቆ አስተዋይነትና በብስለት የሚመራው እንጂ፣ በጥጋብ ተነሳስቶ አገርን ዶግ አመድ የሚያደርግ ጦርነት በመቀስቀስ ማጣፊያው ሲያጥረው ሕዝብ የሚያግት አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ሕዝብን ለአደጋ ማጋለጥ ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል የሚሆነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...

የ‹‹ክብር ዶክትሬት›› ዲግሪ ጉዳይ

በንጉሥ ወዳጅነው ‹‹የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ግልጽ የሆነ መመርያ እስኪወጣ ድረስ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...

የዘመኑ ትውልድ ለአገሩ ያለውን ፋይዳ ይመርምር!

በዚህ በሠለጠነ ዘመን ኢትዮጵያን የሚያስፈልጓት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከብዙዎቹ በጣም ጥቂቱን አንስተን ብንነጋገርባቸው ይጠቅሙ ይሆናል እንጂ አይጎዱም፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ብዙኃኑ ሕዝቧ ያስፈልጓቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ...

ከግጭት አዙሪት ውስጥ የሚወጣው በሰጥቶ መቀበል መርህ ነው!

የኢትዮጵያን ሰላም፣ ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅሞች ማዕከል በማድረግ መነጋገር ሲቻል ለጠብ የሚጋብዙ ምክንያቶች አይኖሩም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሚደረጉ ክንውኖች በሙሉ ከጥፋት የዘለለ ፋይዳ አይኖራቸውም፡፡ በኢትዮጵያ ዘርፈ...