Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሰሜን የአገሪቱ ክፍል የተፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶችን የሚያጣራ ቡድን መሰማራቱ ተገለጸ

በሰሜን የአገሪቱ ክፍል የተፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶችን የሚያጣራ ቡድን መሰማራቱ ተገለጸ

ቀን:

ሦስት ሳምንታትን ካስቆጠረው የትግራይ ጦርነት ጋር በተገናኘ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ተፈጽመዋል ተብለው ሪፖርት የተደረጉ የተለያዩ ወንጀሎችን ለመመርመር፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መርማሪ ቡድን መሰማራቱን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጌድዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡

ዋና ዓቃቤ ሕጉ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት ቃል አቀባይ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) ጋር በመሆን ማክሰኞ ኅዳር 15 ቀን 2013 ዓ.ም. በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሰብሰቢያ አዳራሽ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፣ በማይካድራ ጭፍጨፋ ላይ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣውን ሪፖርትና ሌሎች ሪፖርቶች ላይ መሠረት በማድረግ የምርመራ ሥራ ለማከናወን አጣሪ ቡድን ተሰማርቷል፡፡

የማይካድራን ጭፍጨፋ ‹‹ለሕወሓት ታማኝ በሆኑ የሚሊሻና የልዩ ኃይል አባላት›› ተፈጽሟል በማለት አምነስቲ ኢንተርናሽናልን የጠቀሱት ዋና ዓቃቤ ሕጉ፣ አሁን ምርመራው ገና ስለሆነ ዝርዝር ማብራሪያ መስጠት እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡

ዋና ዓቃቤ ሕጉ ከዚህ ጋር አያይዘው በትግራይ ክልል በተሰማራው የአገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃትና ከዚያ በኋላ በነበሩ ክስተቶች ወንጀል ፈጽመዋል በመባል የተጠረጠሩ የተለያዩ 167 ግለሰቦች ላይ የእስር ማዘዣ መውጣቱን በመጠቆም፣ ይኼ ቁጥር የመጨረሻ እንዳልሆነና ምርመራው ስለሚቀጥል የተጠርጣሪዎች ቁጥር ሊጨምር ይችላል ብለዋል፡፡ የእስር ማዘዣ ከወጣባቸው ግለሰቦች መካከል በርከት ያሉት፣ በተለይም በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ከሕወሓት ትዕዛዝ ተቀብለው ሲሠሩ ነበሩ የተባሉ በቁጥጥር ሥር ውለዋል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚደረገው የወንጀል ምርመራ እስካሁን በሕወሓት የተላለፉ ውሳኔዎች፣ መግለጫዎችና ንግግሮች የአገር ክህደት ወንጀል፣ በመከላከያ ላይ ጥቃት መፈጸም፣ የትጥቅ አመፅ ማስነሳት፣ በአገሪቱ አንድነት ላይ ጥቃት መፈጸም፣ በሕገ መንግሥቱ ላይ ማመፅ፣ በባህር ዳርና በጎንደር ሮኬት በመተኮስ የሽብር ወንጀል መፈጸም፣ እንዲሁም ወደ አስመራ ሮኬት በማስወንጨፍ በወዳጅ አገር ላይ ጥቃት ማድረስ የሚሉ ወንጀሎች ተፈጽመዋል በሚል መነሻ እንደሆነ ዋና ዓቃቤ ሕጉ አስረድተዋል፡፡

ለዚህም ይረዳ ዘንድ የ38 ድርጅቶች የባንክ ሒሳቦችና ንብረቶች እንዲታገዱ መደረጉን በመግለጽ፣ ለ48 ሰዓታት በዓቃቤ ሕግ ውሳኔ ታግደው ከቆዩ በኋላ ውሳኔው በፍድር ቤት እንዲፀና መደረጉ ጠቁመዋል፡፡ ይሁንና የእነዚህ ድርጅቶች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች እንዳይስተጓጎሉ ለማድረግ፣ በመንግሥት በተሰየሙ ተቆጣጣሪዎች አማካይነት እየተንቀሳቀሱ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ይኖራቸዋል ተብለው የተጠረጠሩ 343 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው እንደነበር፣ ከእነዚህ ውስጥ 116 ያህሉ ከእስር ተለቀዋል ብለዋል፡፡

ሬድዋን (አምባሳደር) በበኩላቸው፣ በትግራይ ክልል በተካሄደው ዘመቻ የመከላከያ ሠራዊቱ ከተሞች ላይ ከበባ በመፈጸም ልዩ ኃይልና ሚሊሻው ከአዣዦች ጋር ግንኙነት እንዳይኖረው በመቁረጥ አክሱም፣ አዲግራት፣ አድዋንና ሌሎች ከተሞችን መቆጣጠሩን በማስታወስ፣ መቀሌም በቀለበት ውስጥ ገብታለች ብለዋል፡፡

የአክሱም ኤርፖርትና ስድስት ድልድዮች መውደማቸውን በማስታወቅ፣ በመቀሌም ተመሳሳይ ጥቃት በሕወሓት ኃይሎች ሊፈጸም ይችላል ብለዋል፡፡

በጦርነቱ ሳቢያም ከትግራይ መውጣት ያልቻሉ የውጭ ዜጎች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች እንዲሁም የኤምባሲ ሠራተኞች እየወጡ እንደሚገኙ ጠቁመው፣ አንዴ መቀሌን ከለቀቁ በኋላ በመከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ሥር ወዳሉ ቀጣናዎች ስለሚመጡ ይኼንን ተግባር ቀላል አድርጎታልም ብለዋል፡፡

መቀሌን በታንክ ለመድረስ በሚያስችል ደረጃ ከ50 እስከ 60 ኪሎ ሜትር ከበባ ውስጥ ማስገባት መቻሉንና ዘመቻው ያለበትን ደረጃ በመግለጽ፣ ቡድኑ መሣሪያዎችንና ተዋጊዎችን በቤተ ክርስቲያኖች፣ በመስጊዶችና በርካታ ዜጎች በሚኖርባቸው ሥፍራዎች በማስቀመጥ ለጦርነት መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...