Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊኅብረተሰቡን ከኮቪድ-19 ለመታደግ ያለመው የአፍሪካ የማስክ ሳምንት

ኅብረተሰቡን ከኮቪድ-19 ለመታደግ ያለመው የአፍሪካ የማስክ ሳምንት

ቀን:

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም ከተከሰተ ወደ አንድ ዓመት የተጠጋ ሲሆን፣ እስከ ኅዳር 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በአፍሪካ በበሽታው የተያዙት 2,069,923፣ ያገገሙት 1,747,263 ሲሆኑ፣ 49,702  ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በኢትዮጵያም በበሽታው የተያዙት 106,203,፣  ያገገሙት 65,839 ሲሆኑ፣ ሕይወታቸው ያለፈው 1,651 መሆኑን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በድረ ገጹ አስታውቋል፡፡

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ በየጊዜው የሚያዙት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ የሚመጣባት፣ ሕይወታቸውን የሚያጡት ቁጥርም ቀላል የማይሆንባት አፍሪካን ከበሽታው ለመታደግ ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው፡፡ ከነዚህም አንዱ ቫይረሱን ለመቆጣጠር ማስክን በአግባቡ የማድረግ ንቅናቄ ይገኝበታል፡፡

ከዚህ አኳያ የአፍሪካ በሽታዎች መከላከልና ቁጥጥር ማዕከል (ሲዲሲ) ከኅዳር 14 እስከ ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. የሚዘልቅ የአፍሪካ የማስክ ሳምንትን ይፋ አድርጓል፡፡

ኅብረተሰቡን ከኮቪድ-19 ለመታደግ መሠረታዊ የሆነውን የአፍና የፊት መሸፈኛ ማስክን በአግባቡ ማጥለቅን ማበረታታት አስፈላጊ መሆኑን ያመለከተው የአፍሪካ ሲዲሲ ንቅናቄውን ያዘጋጀው ከፓንዴሚክ አከሽን ኔትወርክ፣ ከአፍሪካ ኅብረት የወጣቶች መልዕክተኛ ጽሕፈት ቤትና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር ነው፡፡

በሌላ በኩልም በኢትዮጵያ በየቀኑ በቫይረሱ የሚያዘው ሰው ቁጥር እየጨመረ መሄዱን ተከትሎ መንግሥት ሕዝብ በሚበዛበትና ከቤት ውጭ በሆኑ ሥፍራዎች ሁሉ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግን ግዴታ የሚያደርግ መመርያ አውጥቶ እየተገበረ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

የቫይረሱን መስፋፋት ለመቆጣጠር እንዲያስችል በሚል ካለፈው ግንቦት ጀምሮ ማንኛውም ሰው ከመኖሪያው ቤት በሚወጣበት ጊዜ ማስክ ማድረግ እንደሚገባው፣ ካላደረገ ግን በሕግ ሊቀጣ እንደሚችል ፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመታደግ ሳይንሳዊ መረጃን በዜና መጽሔቱ አማካይነት ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ፣ በቅርቡ ባወጣው ዕትሙ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጠቀሜታን፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ የት የት መደረግ እንዳለበት፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛን ማድረግ ያለባቸውና የሌለባቸው እነማን እንደሆኑ እንደሚከተለው በዝርዝር አስቀምጦታል፡፡

ለመሆኑ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ለምን ይጠቅማል?

ሰዎች በሚያስሉበት፣ በሚያስነጥሱበትና በሚያወሩበት ጊዜ ከአፍ የሚወጡ ፍንጣቂዎች በአየር ላይ ተለቀው በቅርበት ባለው ሰው አፍና አፍንጫ ያርፉና በመተንፈስ ሒደት ወደ ሳምባ ይገባሉ፡፡ ስለሆነም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ፡-

  • በዋነኝነት ከአፍ የሚወጡ ብናኞችን ወደ ሌላ ሰው እንዳያልፉ ስለሚገድባቸው፣ የኮሮና ቫይረስ ከትንፋሽ ጋር በሚወጡ ብናኞች ምክንያት የሚተላለፍበትን መንገድ ለመቀነስ ይጠቅማል፤
  •  በኮቪድ-19 የተያዘ ሰው ቫይረሱን ወደ ሌላ ሰው እንዳያስተላልፍ ይከላከላል፤
  • ቫይረሱ፣ ከአፍ በሚወጡ ብናኞች አማካይነት በቫይረሱ መያዛቸውን ካላወቁና ምልክቶችን ካላሳዩ ሰዎች ወደ ሌላው ሰው እንዳይዛመት ይከላከላል፤
  • በተለይ ደግሞ ሰዎች በሚበዙበትና ማኅበራዊ/አካላዊ ርቀትን መጠበቅ በማይቻልበት ሁኔታ (በመገበያያ ሥፍራዎች፣ በሕዝብ ማመላለሻ መኪናዎች፣ ርቀትን ጠብቆ ለመሥራት የማያስችሉ የሥራ ቦታዎች) እጅግ ወሳኝ የሆነ የመከላከያ መንገድ ነው፡፡
  •  ስለሆነም ጭምብል ማድረግ ቫይረሱ ከሌላ ሰው እንዳይተላለፍብን ራሳችንን ለመከላከል ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ለመጠበቅ ጭምር የምናከናውነው፣ ለሌሎች አሳቢ መሆናችን የሚገለጽበት የትብብር ድርጊት ነው፡፡

ነገር ግን የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ መጠቀም ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው እንዳይተላለፍ የሚረዱ ሌሎች ጥንቃቄዎችን በሙሉ ሊተካ አይችልም፡፡ የቫይረሱን መስፋፋት የሚቀንሰው ማኅበራዊ ርቀትን ከመጠበቅና ከሌሎች የተለያዩ የመከላከያ ተግባራት ጎን ለጎን ዘወትር ሲተገበር መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡

የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ የት የት መደረግ አለበት?

የኮሮና ቫይረስ ካለበት ሰው ከአፍ የሚወጡት ጠብታዎች በቅርበት (ከሁለት ሜትር ባነሰ ርቀት) ወዳለ ሰው ይገባሉ፡፡ ስለሆነም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ የሚገባን ሥፍራዎች የሚከተሉት ናቸው (የበሽታ ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል ሐምሌ 30 ቀን 2012)

  • ሕዝብ በሚበዛባቸው ሥፍራዎች ላይ ሲገኙ (የመገበያያ ሥፍራዎች፣ የሕዝብ ማመላለሻ መኪናዎች፣ ወዘተ…)፤
  • አብረዋቸው ከሚኖሩ የቤተሰብ አባላት ውጪ ከሆኑ ሰዎች ጋር ሲገናኙ፤
  • ማኅበራዊ ርቀትን ለመጠበቅ አስቸጋሪ በሚሆንበት ሁኔታ ላይ ሲሆኑ፤

የቅርብ ጊዜ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት አብዛኛዎቹ ኮቪድ-19 ያለባቸው ሰዎች የሕመሙ ምልክቶች የማይታዩባቸው በመሆናቸው ቫይረሱን በቀላሉ ወደ ሌላ ሰው ሊያስተላልፉ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ከቤት ውጭና ሕዝብ በሚበዛቸው ሥፍራዎች በምንሆንበት ጊዜ ሁሉ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የሥራቸው ሁኔታ (መመገቢያ ሥፍራዎች፣ ሱቆች፣ ወዘተ…) አብዛኛውን ጊዜ ከሰዎች ጋር የሚያገናኛቸው ሰዎችና በቫይረሱ ከተያዙ ለከፍተኛ ሕመም ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች መሸፈኛውን ማድረግ አለባቸው፡፡

የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛን ማድረግ ያለባቸው እነማን ናቸው?

  • ዕድሜያቸው ከ12 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ሁሉ ዕድሜያቸው ከ6-12 የሆኑ ልጆች የጭምብል አጠቃቀም በአካባቢያቸው ባለው የኮቪድ-19 የመተላለፊያ መጠን፣ በልጆቹ ጭምብልን በትክክል የማድረግ ብቃትና ጭምብል ማድረግ በመማር፣ በሥነ ልቦናና በማኅበራዊ ዕድገት ላይ በሚኖረው ተፅዕኖ ይወሰናል (የዓለም ጤና ድርጅት ነሐሴ 15 ቀን 2012)፤
  •  በኮቪድ-19 የተያዘ ወይም ሊኖርብኝ ይችላል ብሎ የሚያስብ ሰው በቤት ውስጥም ሆነ ከቤት ውጪ ካሉ ሰዎች አጠገብ በሚሆንበት ጊዜ፤
  • በቤት ወይም በጤና ተቋም ውስጥ የኮቪድ-19 ሕመምተኞችን የሚከታተሉ ሰዎች፡፡ የበሽታ ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል እንደገለጸው በቤት ውስጥ ወይም ከጤና ተቋም ውጭ በሆነ ሥፍራ የኮቪድ ሕመምተኞችን የሚንከባከቡ ሰዎች ከጨርቅ የተሠራ ጭምብል ማድረግ ቢችሉም ጭምብሉ ቫይረሱ ከተያዘው ሰው ወደ ጤነኛው ሰው መተንፈሻ ክፍል እንዳይገባ የመከላከል ብቃቱ በደንብ የተረጋገጠ ስላልሆነ ሌሎችን የመከላከያ መንገዶችም የግድ መጠቀም ይኖርባቸዋል::

የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛን ማድረግ የሌለባቸውስ እነማን ናቸው?

  • ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት የመተንፈስ ችግር ያለባቸው፤
  • መስማት የተሳናቸው፤ · በጤና ችግር ምክንያት ራሳቸውን የማያውቁ፤
  • መንቀሳቀስ የማይችሉና መሸፈኛን ያለዕርዳታ ማውለቅ የማይችሉ፤  የአዕምሮ ዕድገት ውስንነትና የአዕምሮ ጤና ችግር ያለባቸው፤
  • ከባድ እንቅስቃሴየሚጠይቅ ሥራ የሚሠሩ (ለምሳሌ፡- የሚሮጡ)፤
  • መሸፈኛውን ማድረግ አደጋ ሊፈጥር በሚችልባቸው የሥራ ሁኔታዎች ውስጥ የሚሠሩ ሰዎች (ከሚፈጥረው ሙቀት ጋር የተያያዘ ሕመም የሚያስከትል ወይም የደኅንነት ችግር የሚፈጥር ከሆነ)፡፡
spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...