Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየሕወሓትን ወንጀል ዓለም ማወቅ አለበት!

የሕወሓትን ወንጀል ዓለም ማወቅ አለበት!

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

በአገራችን ከብዙ ውጣ ውረድና መስዋዕትነት በኋላ ለውጥ መምጣት ጀምሮ ነበር፡፡ ለውጡም በአብዛኛው በዴሞክራሲ ምኅዳር መስፋት ላይ ያተኮረ ሲሆን ከሰላም፣ ከልማትና ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ ገና በርካታ ሥራዎችን የሰነቀ ተስፋም ነበር፡፡ በዚህ መነሻም ሕዝብና  መንግሥት  ከመቼውም ጊዜ በላቀ ደረጃ እጅና ጓንት ሆነው ለአገር ጥቅም መሠለፍ እንዳለባቸው የታመነ ቢሆንም፣ የለውጥ ተግዳሮቶች አገራችንን እየፈተኑ ነው፡፡ ከፈተናው ሁሉ የከበደው ደግሞ በሕወሓት ጁንታ አማካይነት፣ በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ትንኮሳና አሁን የተለኮሰው ጦርነት ነው፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት እንደታየው ሕወሓት የኢሕአዴግ መሥራችና አገርንም ከእነ ችግሩ ለ27 ዓመታት የመራ ቢሆንም፣ ከሕግና ሥርዓት ያፈነገጠ ሆኖ ነው የቆየው፡፡ ሕወሓት የትግራይ ክልልን በማስተዳደር ስም የተለየ ፖሊስና  ልዩ ኃይል ምልመላ (አሁን የመከላከያ ኃይላችን እስከ ማለት ይናገራል)፣ የፌዴራል መንግሥትን ትዕዛዝ አለመቀበልና ሕገወጥ የተባለ ምርጫ እስከ ማካሄድ መድፈር፣ የመከላከያን እንቅስቃሴ መግታት፣ ለፌዴራል መንግሥቱ ዕውቅና መንፈግ፣ ወዘተ. ዓይነት ተግባራት ፈጽሟል፣ አስፈጽሟል፡፡

እነዚህ የለውጥ ብቻ ሳይሆኑ የዴሞክራሲና የሕግ እንቅፋቶች በግልጽ ሕወሓት የፈጸማቸው ይሁኑ እንጂ፣ በስውር በአገሪቱ በተፈጸሙ የብሔር ግጭቶችና የንፁኃን ግድያዎች ላይ በአንድም በሌሌላም እጁ እንዳለበት መንግሥት ሲከሰው ቆይቷል፡፡ በእርግጥም ቡድኑ የሕዝቦች አንድነትና መተባበርን የሚያበረታታ ለውጥ ከሚቀበል ሞቱን እንደሚመርጥ አሁን የገባበት ጦርነትም አመላካች ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አገራዊ ኅብረቱ፣ በአናሳ ፍላጎት አገር ቀጥቅጦ ለመግዛት ያለውን ምኞት ስለሚከሽፍበት፣ ለውጡን ለማደናቀፍ እንደማይተኛ የታመነ ነው፡፡ ስለሆነም ከእነ ግብፅ፣ ኦነግ ሸኔና አክራሪ ብሔርተኞች ጋር ተቧድኖ እንደሚንቀሳቀስ ነው መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡

እንደ አገር አሁን ያሉትን ወቅታዊ ፈተናዎች ለማለፍ መንግሥትና ፀጥታ ኃይሉ ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝቡም ሚናው ከፍ ያለ ነው፡፡ ሕወሓት/ትህነግ ግን ሁሉንም አለመረጋጋቶች እያባባሰ ለራሱ ፍጆታ ማዋሉ ስለማይቀር ብቻ ሳይሆን፣ ጦርነቱንም በተራዘመ ትግል መልክ ለማስኬድ ስለሚዘጋጅ ነገሩን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በጥሞና እንዲገነዘብና አስፈላጊውን ጫና እንዲያደርግ በትኩረት መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡ ሕዝቡም ሴራውን ተረድቶ በርትቶ መታገል ነው ያለበት፡፡ በትንንሽ ቅሬታ ከዋናው አደናቃፊ ዓይን መንቀልም አይገባም፡፡

በየትኛውም ወገን የተጀመረን ለውጥ አጠናክሮና ጠብቆ ከመሄድ ይልቅ፣ ጠልፎ  ለመጣልና አገርን ወደ ትርምስ ለመውሰድ የሚደረገውን ሴራ ማጋለጥና ተደራጅቶ ከመንግሥት ጋር በመሆን የአገር ደኅንነትን መጠበቅ የሁላችንም ኃላፊነት መሆንም አለበት፡፡ አገራችን የሁላችንም በመሆኗ፣ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በኃላፊነት መንፈስ መንቀሳቀስ ግድ ይለናል ከተባለ የዲፕሎማሲ ሥራውንም ቸል ብሎ ማለፍ አይቻልም፡፡

በመላው የአገራችን ሕዝብ እንደሚታመነው ለዘመናት ሕዝብ ሲበዘብዝና ሲጨቁን የነበረው፣ የተጀመረውን ለውጥም ሲገዳደር የቆየው ሕወሓት፣ አሁን ደግሞ አገር ለማፍረስ እየሠራ በመሆኑ በኃይል ሊመታ ይገባል የሚሉ ወገኖች ብዙ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የለውጥ ኃይሉ የትህነግ/ሕወሓት ቱባ አዛዦችንና ጨቋኞችን በተመለከተ ከተገቢው በላይ ትዕግሥት አሳይቷል. . . ምን እስኪሆን ነው የሚጠብቀው?. . . ለምን ጠበቅ ያለ ዕርምጃ አይወስድም ?. . . ወዘተ የሚሉ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ባሉበት ጊዜ ነው ቀድሞ የሰሜን ዕዝን በውስጥ ጁንታና በልዩ ኃይሉ ሊያፈርሰው የዘመተበት፡፡ ቀላል የማይባል የሰው ኃይልና የንብረት ጉዳት ማድረሱም ተሰምቷል፡፡

የዘገየም ቢሆን ይህ ጥፋተኛ ኃይል ጉዳት ካደረሰ በኋላ ዕርምጃ መውሰድ የጀመረው መንግሥት፣ ሕዝቡን በአጀንዳው ዙሪያ በስፋት እንዲግባባ በማድረግ ሙሉ ድጋፉን እያገኘ ሲሆን፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ከፍተኛ የዲፕሎማቲክ ልዑካን ቡድን በምሥራቅ አፍሪካና ሌሎች ጎረቤት አገሮች ጉዳዩን የማስረዳት ዘመቻ ሲያካሄድ ሰንብቷል፡፡ በእርግጥ እንደ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ቱርክና ሩሲያን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ አገሮችም በአገራችን ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶችና መሪዎች ደረጃ ሕግ የማስከበሩ ዕርምጃ እንዲገለጽላቸው ተደርጓል፡፡ የብዙዎቹ ምላሽም ተስፋ ሰጭና አጋርነት የታየበት መሆኑን መንግሥት ገልጿል፡፡

እዚህ ላይ የዲፕሎማሲ የበላይነትን ፋይዳና ኃያልነት በማጤን የተጀመረው ጥረት የሚበረታታና ጠቃሚ ነው፡፡ ለአብንት ያህል በቀደመው የአሜሪካ መሪዎች ታሪክ የወታደራዊና የኢኮኖሚያዊ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ብቻ ሳይሆን፣ ዲፕሎማሲያዊ የበላይነትን ማረጋገጥም የተለመደ ተግባራቸው ነበር፡፡ እንኳንስ በሦስተኛው ዓለም ጉዳይ ይቅርና በተፈጥሮ ሀብትና ነዳጅ በበለፀጉት የመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካ ውስጥ የአሜሪካ እጅ የሚመዘነው በዚህ መንገድ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር አገር እያተራመሰና እያሸበረ ያለ ኃይልም ቢሆን፣ የሕወሓትን ሴራ በተጨባጭ መረጃ ማስረዳት ይበል የሚሰኝ ሥራ ነው፡፡

እውነትና ፍትሕ ላይ ተመሥርቶ ለሕዝብም ሆነ ለሌላው ዓለም በሕወሓት የሚተፈጸመውንና የሚፈጸመውን አደናቃፊነት ማስገንዘብ፣ ለተጀመረው ሕግ የማስከበር ሥራ ጠቃሚ ነው፡፡ የውጭው ዓለም ደግሞ በተገቢው መረጃ መዝኖ አጥፊው መንግሥት ነው ሸማቂ ብሎ ሳይሆን፣ ከእውነታውና ከሚኖረው ፋይዳ አንፃር የትኛውንም ሁኔታ የሚመዝን ሥርዓት እንዳለው የታወቀ ነው፡፡ በመሆኑም ትግሉ ሕግ የማስከበር መሆኑን ከአገሬው በላይ ለውጭ ኃይሎች ማስረዳቱ  በእጅጉ  ጠቃሚ ነው፡፡ ተጠናክሮ መቀጠልም  አለበት፡፡

ከዚህ አንፃር አረረም መረረም በአገራችን የሰው ብቻ ሳይሆን የሥርዓት ለውጥ እየታየ መምጣቱን፣ የዚህ ለውጥ መነሻ ደግሞ የሕዝቡ የዓመታት ቁጣና ግፊት እንዲሆንና የራሱ የኢሕአዴግ ድርሻ እንደነበረው መወሳት አለበት፡፡ በተሃድሶው ምክንያት የአመራር ለውጥ መደረጉን፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች ከእስር መለቀቃቸውን፣ 45 ሺሕ የሚደርሱ የህሊና (የፖለቲካ) እስረኞች ነፃ መውጣታቸው ጎረቤቶቻችን ብቻ ሳይሆኑ አሜሪካ፣ ቻይናና መላው አውሮፓ እንዲያውቁ መደረግ አለበት፡፡

የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎችና ጋዜጠኞች (ሚዲያዎች) በነፃነት በአገራቸው እንዲንቀሳቀሱ መሆናቸው፣ እንደ የምርጫ፣ የሚዲያ፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የፀረ ሽብርተኝነት፣ የንግድ፣ የፕራይቬታይዜሽንና መሰል ሕጎች መሻሻልና መቀየር መጀመራቸው ብቻ ሳይሆን፣ በየመዋቅሩ የሰው ኃይሉን ለማስተካከል መሞከሩም ተጠቃሽ የለውጥ ጅምሮች ናቸው፡፡ ሕወሓት ከመጀመርያውም በእነዚህ ሪፎርሞች ደስተኛ እንዳልነበርና በተለያዩ መንገዶች ወደ ማደናቀፍ መግባቱንም እንዲሁ፡፡

ለውጡ ከሁሉ በላይ ነበሩን የፀረ ዴሞክራሲያዊ/ነጣጣይ አካሄድ ለማስቀጠል የሚገፉ የአመራር፣ የአሠራርና የአደረጃጀት ዘውጎችን በመቀየር ረገድ አንድ ዕርምጃ ወደፊት ለመሻገር ቢሞክርም፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲያ የተባለውን የወዳጅና የጠላት ፍረጃ ግራ ዘመም ርዕዮት ለመቀየር የተጀመረውን ጥረት ማንም ወዳጅ አገር ቢሆን የሚያደንቀው ነው፡፡

በአንድ በኩል የነፃ ገበያን ዕሳቤ ያለ ገደብ ለማራመድ፣ በሌላ በኩል መደመር በሚል አተያይ ሁሉም የራሱን በጎ እሴቶች አሰባስቦ ጠንካራ አገራዊ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለመፍጠር የሚያስችለው ጉዞ መሬት እንዳይዝ የገጠመው ፈተና ግን ቀላል አልሆነም፡፡ ይህን እውነታ ተገንዝቦ ዓለም “ለምን?” እንዲል ካልተደረገ የግጭቱ መነሻ ተራ ፀብ እንዳልሆነ ይረዳዋል፡፡ ሕገወጡ ቡድንና በውጭ ያሉ ተባባሪዎቹ ለመንዛት የሚፈልጉትን የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ለማክሸፍም ይረዳል፡፡

ይኼ ብቻ ሳይሆን በውጭ ግንኙነት ረገድ ኤርትራን ከመሰሉ ጎረቤት አገሮች ጋር ለመቀራረብ የሚያስችልና በሰጥቶ መቀበል ላይ የተመሠረተ ግንኙነት መጀመሩ የለውጡ ቱሩፋት ነበር፡፡ እንዲሁም ዜጋ ተኮር በሆነው የውጭ ግንኙነት አቅጣጫ መሠረት፣ በትንሹ 20 ሺሕ የሚደርሱና በተለያዩ አገሮች ለዓመታት ታስረው የነበሩ ዜጎች ተፈትተው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጋቸው አይዘነጋም፡፡

ምንም እንኳን ከግብፅ ጋር ያለው ግንኙነት የተጨበጠ ለውጥ ባያሳይም፣ አንዳንድ የዓረብ አገሮች ከወትሮው የተለየ ድጋፍና አጋርነት ማሳየት የጀመሩትም  አሁን ነው፡፡ ይህ አካሄድ ለሕወሓታዊያን ሊዋጥላቻው ያልቻለና መርህ አልባ ተደርጎ የሚወሰድ እንደነበር ግን አይዘነጋም፡፡ በተለይ ከኤርትራ ጋር የተጀመረው የሰላም ጮራ ብረሃን፣ የደበዘዘው በሕወሓት ሽማግሌዎች መሆኑ መብራራት አለበት፡፡

እነዚህና መሰል ተግባራት ግን በተሃድሶው አማካይነት ከተነደፉ የመግባቢያ ነጥቦች እየተመዘዙ  በግልና በቡድን ወደ ተግባር የገባባቸው ነበሩ፡፡ እርግጥ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ከግንባርነት ወደ ውህድ አገራዊ ፓርቲነት መለወጥ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የልዩነት ሐሳቡን ሲያራምድ ነበር የቆየው፡፡ በመጨረሻም ከእርሱ በስተቀር ኢሕአዴግን የመሠረቱ እህት ፓርቲዎችና ለዓመታት አጋር ሲባሉ የኖሩትን የታዳጊ ክልሎች ገዥ ፓርቲዎችን  ያዋሀደ “ብልፅግና” የተሰኘ ፓርቲ ሲመሠረት ቆሞ ከመመልከት ውጭ ሌላ ዕድል አልነበረውም፡፡ አሁንም የልዩነት ሐረጎቹ እየተመዘዙ ሕወሓት በመሠረተው ሥርዓት ውስጥ ብቻ ሳይሆን፣ በጀመረው ተሃድሶ ረገድም ወደ ተቃዋሚ ደረጃ ወርዶ እየተሞገተ ቆይቶ ነው ወደ ለየለት የሕግ ጥሰትና የአገር መከላከያን ወደ መውጋት ኪሳራ ውስጥ የወረደው፡፡

ይህን መላው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በቅርብ የተመለከተ የውጭ ታዛቢም ሊገነዘበው ይችላል፡፡ ለዋናውና ተፅዕኖ ፈጣሪው የዓለም ማኅበረሰብ ግን ሒደቱን እያወከ የቆየውም ሆነ አገርን ወደ ጦርነት ያስገባው ሕወሓት መራሹ የአክራሪ ብሔርተኝነት ዘዋሪ ኃይል እንደሆነ በሚገባ መነገር አለበት፡፡ ይነስም ይብዛም የሕዝብን የልብ ምት ለማዳመጥ እየሞከረ ያለው የለውጥ ኃይል የነበረውን ትዕግሥትና ሆደ ሰፊነትም በተጨባጭ ማስረጃ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ ይኼ ደግሞ ታሪክና አምላክ ይፍረደው ተብሎ የሚተው ሳይሆን፣ የበለፀጉት አገሮችን ብቻ ሳይሆን የዓለምን ድጋፍና ይሁንታ ለመጨበጥ በሰፊው የሕወሓትን ወንጀል ማጋለጥ ግድ ይላል፡፡

በመሠረቱ ሕወሓት የሚከተለው መንገድ ዘመኑን ያልዋጀ፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ የማያምን፣ የሕዝቦችን አንድነት የሚበትንና የአገር ህልውናን የሚፈትን መሆኑን ሕዝቡ በግልጽ ተረድቷል፡፡ በአሸናፊነት ስሜትና በዕብሪት ተነሳስቶ በአንድ አገር ውስጥ ትርምስ ለመቀስቀስ የሄደበት ርቀትም እጅግ አደገኛ መሆኑ፣ በተለይ በቅርቡ በሚገባ ከተመታ በኋላ ይበልጥ ተጋልጧል፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ለተለያዩ አገሮች ዲፕሎማቶችና አታሼዎች እንደተደረገው ማብራሪያ፣ በቀጣይም እስከ ጦርነት ጀማሪነቱ ሴራውን ማጋለጥና ነገ ከአገር አልፎ የቀጣናው አደጋ እንዳይሆን፣ ለሁሉም ወገኖች ደጋግሞ ማስገንዘብ ወሳኙ ተግባር መሆን አለበት፡፡

ለዚህ ደግሞ የተጀመረው ሕግን የማስከበር ዘመቻ በአንድ በኩል ሕዝባዊ ድጋፍ እንዳለው ማሳየት (አሁን በየአካባቢው እየተደረገ ያለው ሠልፍና ድጋፍ ጥሩ አብነት ነው)፣ በሌላ በኩል ንፁኃንን ከጥቃት የጠበቀና መሠረተ ልማቶችን ከውድመት የታደገ በማድረግ ሊፈጸም ይችላል፡፡ እንዲሁም ሸማቂው ኃይል በንፁኃን ወገኖች ላይ የሚያደርሰውን ጥፋት በማጋለጥ፣ ኤርትራን ጨምሮ ግጭቱን ወደ ጎረቤት አገሮች ለመውሰድ የሚያደርገውን ርብርብ ማስቆምና ለገለልተኛ ወገኖች ማሳየት ለነገ የማይባል የውጭ ግንኙነቱ ተግባር መሆን አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ነው ሕወሓት ይበልጥ ሊጋለጥ የሚችለው፡፡

ምንም እንኳን በአገራችን ጦርነት የተቀሰቀሰው ሕግ ማስከበር ባለበት መንግሥትና አፈንጋጭ ቡድን መካከል  ቢሆንም፣ ግጭቱ ከተራዘመ የሚያደርሰው ሰብዓዊ ጥፋት ከበዛ ለመነጋገር በሩ ዝግ መደረግ የለበትም፡፡ በተለይ አማፂው ላደረሰው ጥፋት በጦርነት ተገቢውን የመልስ ምት ካገኘ በኋላና በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን አሳልፎ ከሰጠ እንደ አንድ ቅድመ ሁኔታ ይታያል፡፡ በሕጋዊው መንገድ ለትግራይ ክልል በጊዜያዊ አስተዳደርነት የተመደበውን ኃይል የመቀበል አዝማሚያ ካለ፣ አሁንም መንግሥት ሆደ ሰፊ ሆኖ ነገሮችን መመልከት ይጠቅመዋል እንጂ አይጎዳውም፡፡

በእርግጥ አንዳንድ ወገኖች ይኼን ምክረ ሐሳብ ሕወሓትን ሕጋዊ ከማድረግና ዕርምጃውን ከማዳከም ጋር ሊያያይዙብኝ ይችላሉ፡፡ ጦርነትን መርጦ እንደ ገባበት ኃይልም በሚገባው ቋንቋ ብቻ ነው ማናገር የሚቻለው ብለው ሊቃወሙኝ እንደሚችሉ ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን በየትኛውም ደረጃ ቢሆን ጦርነት የሚያስከትለውን ጥፋትና ሰብዓዊ ውድመት ለመቀነስ፣ ከጦርነትም በላይ አማራጭ ሆኖ የሚወሰደው ውይይት መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ዋናው ነገር ሕወሓት ትናንት ባበጠ ዕብሪት ላይ ሆኖ ለመደራደር የሚመኘው ዓይነት ቁመና ላይ አለመሆኑን ማረጋገጡ ነው፡፡ ቢያንስ ከዚያ በኋላ ከባባድ ወንጀሎች ተፈጽመዋልና፡፡

በእርግጠኝነት የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ በውጊያው ዓውድማ የሚጠበቅባቸውን ውጤት ፈጠን ብለው ካካሄዱና በክልሉ ተገቢው መንግሥታዊ መዋቅር መዘርጋት ከተጀመረ፣ ወደ ተጨማሪ የአጥፍቶ መጥፋትና የጎሬላ ትግል እንዳይገባ መዝጋት ይገባል፡፡ የተራዘመ የግጭት አዙሪት ለአገራችን ካለው ኪሳራ በላይ ወዳጅ የምንላቸው የዓለም አገሮች፣ እንዲሁም የአፍሪካ ወንድሞቻችን ተስፋ እንዲቆርጡብን ስለሚያደርግ ቆም ብሎ ማሰብ ይገባል፡፡ ይህም ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡

በየትኛውም ደረጃ አገራችን ጦርነትና ግጭት ውስጥ ሆና ኢኮኖሚውም ሆነ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ መዳከሙ አይቀርም፡፡ በተለይ እንደ ውጭ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ያሉት መስኮች እየተዳከሙ፣ ገጽታችንም መልሶ እየጨለመ ከሄደ በአጠቃላይ ኪሳራው ቀላል ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚህ አንፃር በአገር ጉዳይ ኃላፊነት ወስዶ ነገሮችን መመዘን ያለበት መንግሥት ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ሕዝቡ በተለይም በመንቻካና አሮጌ አቋማቸው የሚታወቁት የሕወሓት መሪዎችን ተሸክሞ የኖረው የትግራይ ሕዝብ፣ በሚገባ ነገሩን መዝኖ ከችግር ለመውጣት መታገል አለበት፡፡

አገራችን  ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት በአንፃራዊነት ከከፍተኝ የእርስ በርስ ጦርነቶች ወጥታ፣ የልማትና ዕድገት ጉዞ ማስመዝገቧ አይታበልም፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በተሠሩ ሥራዎች፣ በዓመት ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ገር ጎብኚዎች  ከውጭ በመምጣት ታሪካዊገር ይጎበኙ ነበር በርካታ የውጭ ባለሀብቶችና ተመራማሪዎችም የሚመላለሱባት ምድርም ነች፡፡

እንደ ታላቁ የህዳሴ ግድብን የመሰሉ ግዙፍና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸው የልማት ፕሮጀክቶችም መገለጫዎቻችን ሆነዋል፡፡ ለውጥ ሲመጣም ሁሉም በአገሩ ጉዳይ ያገባኛል ወደሚል ዕሳቤ ከመምጣት ባሻገር፣ በመሪ ደረጃ ለመጀመርያ ጊዜ የሰላም ኖቤል ሽልማት ያገኘነውም በቅርቡ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር ግጭትና ጦርነት እነዚህን ሁሉ የሚያሳጣን እንደ መሆኑ ተገደን እንጂ መርጠን የምንገባበት አይደለም፡፡ በእርግጥም መንግሥት ከረጅም ትዕግሥትና ሆደ ሰፊነት በኋላ ተገዶ ወደ ጦርነት እንደገባ ቢታመንም፣ ፈጥኖ መቋጨት የሚኖርበት ለዚሁ ነው፡፡

በመሠረቱ ጦርነትና ግጭት ሞልቶ በተረፈው ምድር ላይ እኛም ተጨማሪ የጦር ቀጣና፣ የስደተኛና ተፈናቃይ ተቀባይ ሳንሆን አፈናቃይ፣ በዚህም ሒደት ለቀጣናዊ መቃወስ ምክንያት እንድንሆን ዓለምም አይፈቅድልንም፡፡ ስለሆነም በአንድ በኩል የሕግ የበላይነትን የማስከበርና የአገር ህልውናን የማረጋገጡን ተግባር አጥብቆ፣ ሕዝብን ባሳተፈና ወንጀለኞችን ነጥሎ ለሕግ በሚያቀርብ መንገድ መካሄድ አለበት፡፡ የሕዝቡ ድጋፍና ትኩረት በዚሁ ግብ ላይ መሆን ነው ያለበት፡፡

በሸማቂዎቹ በኩልም ቢሆን ከአራት አሥርት ዓመታት በፊት በነበረ ድርቅናና ዓለም አቀፍ ሁኔታ ተሰንክለው አገርን ወደ ማፍረስ መሄዳቸው፣ እጅግ ነውርና የወንጀል ወንጀል መሆኑን መገንዘብ አለባቸው፡፡ ስለዚህ የባሰ ጥፋት ሳይደርስ እጃቸውን ለፀጥታ አካላት መስጠትና ሕግ ፊት መቆሙ ነው የሚበጃቸው፡፡ ዓለምና የአፍሪካ ወንድሞቻችንም እንዲኮንኑት በተለይ የዳያስፖራው ማኅበረሰብና ምሁራን የጎላ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በእርስ በርስ የፖለቲካ ውዝግብም ይባል፣ የሥልጣን ፍላጎት፣ ወይም በዘርና ሃይማኖት መካረር በተነሳ ትርምስ እነ የመን፣ ሶሪያ፣ ኢራቅ፣ ሶማሊያ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኮንጎና መሰሎቹ የደረሰባቸውን ሰብዓዊ ቀውስ እንዳላዩና እንዳልሰሙ መሆንም ግን ለማንም አያዋጣም፡፡

በመሠረቱ አሜሪካና ኢራንን በኑክሌር ሰበብ ወደ ጦርነት የሚያስገባ ውዝግብና በዚያው ተያይዞም ሦስተኛ የዓለም ጦርነትን የሚጋብዝ የተባለለት መካረር አሁን የለም፡፡ በዓለም በአምባገነንነታቸው የተፈሩና እንደ መርግ የከበዱ (እነ ሳዳም፣ ጋዳፊ፣ ሙባረክ፣ አል በሽር. . .) መሪዎች በዋናነት በራሳቸው ሕዝብ ማዕበል ተገፍትረዋል፡፡ የሕወሓት ጁንታም ቢሆን ይኼ ዕጣ ፈንታ ሊገጥመው ይችላል፡፡ በሕዝቡ ትዕግሥትና ዕድል የመስጠት ፍላጎት፣ ራሱ ወደ ሌላ ወንጀል ገብቶ አደጋ በመፍጠሩ አይቀርላትም፡፡

በአጠቃላይ  እንደ መንግሥት በአንድ በኩል የሕወሓትን ወንጀልና ጥፋት ማጋለጥ፣ በሌላ በኩል ሕግ የማስከበሩን ሥራ የማጠናከር ኃላፊነቱን መወጣት ግድ ይለዋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ለሕዝብና ለአገር ጥቅም ሲባል የሚደረግ ውይይትም ሆነ ድርድር፣ ሕግ ከማስከበር በታች በሆነ መንገድ ከየትኛውም አካል ጋር እንዲካሄድ ሐሳብ ቢመጣ በር መዘጋትም የለበትም፡፡ ይህን ማድረግ ደግሞ ፍርኃት ሳይሆን ሥልጣኔና ብስለት ነው፡፡ እውነታውን ሁሉ ዓለም እንዲያውቀው ማድረግ ደግሞ ትልቁ ተግባርና ብልህነት ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...