Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልበ46ኛ ዓመቷ ‹‹ሉሲ ምን ትላለች?››

በ46ኛ ዓመቷ ‹‹ሉሲ ምን ትላለች?››

ቀን:

‹‹መልሴ ‹ሉሲ የሰው ልጅ ሁሉ የዘር ግንዱ አንድ ነው› ትላለች የሚል ነው፡፡ ሉሲ የእኛ ብቻ ሳትሆን የዓለም ሕዝቦች ቅድመ አያት ተደርጋ የምትቆጠር እንደመሆኑ፣ ይህንኑ እውነታ እንደ መልካም አብነት በመውሰድ እኛም የአንድ እናት ኢትዮጵያ ልጆች በጋራ፣ በሰላምና በፍቅር፣ በመረዳዳትና በመተጋገዝ አገራችንን ወደ ከፍታ ማማ ለማድረስ በርትተን መሥራት ይኖርብናል፡፡››

ይህን ዓረፍተ ነገር የ3.2 ሚሊዮን ዓመታት ባለ ዕድሜዋ ሉሲ በአፋር፣ ሀዳር በተባለ ሥፍራ የተገኘችበት 46ኛ ዓመት በ‹‹ብሔራዊ ሙዚየም›› ሲከበር፣ ‹‹ሉሲ ምን ትላለች?›› ለሚለው ጥያቄ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) የሰጡት ምላሽ ነው፡፡

‹‹ሉሲ ምን ትላለች›› በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀውን ሥነ በዓል ቤተ ጥበብ መልቲ ሚዲያ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ነው፡፡

‹‹ድንቅነሽ›› የሚል አገርኛ ስያሜን ከቆይታ በኋላ ያገኘችው ሉሲ፣ በአሜሪካዊው ፕሮፌሰር ዶናልድ ጆንሰን መሪነት የተገኘችበት ኅዳር 15 ቀን 1967 ዓ.ም. በዓመቱ ለማክበር ርዕይ መሰነቁን የቤተ ጥበብ መልቲ ሚዲያ ተጠሪ ከያኒ ፈለቀ አበበ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ገልጿል፡፡

‹‹የኅብር ኢትዮጵያ መገናኛዎች መርሐ ግብር አንድና ዋነኛ ዓላማ፣ የመላው ኢትዮጵያ ቁሳዊና መንፈሳዊ ቅርሶቻችንን ሀብትና ውበት ለሰላምና አንድነት በጎ ዓላማ በማዋል የውይይትና የአብሮነት መገናኛ መድረክን ማመቻቸት ነው፤›› ያለው ከያኒው፣ ሥነ በዓሉ በተለያዩ ሦስት ቀናት በሚኖሩ ጥበባዊ ዝግጅት ሲከበር የፓናል ውይይትና የመዝጊያ ዝግጅት ይኖረዋል ብሏል፡፡

በቀጣይ በኅብር ኢትዮጵያ መገናኛዎች መርሐ ግብር (Bridge Ethiopia Events) አማካይነት የሚዘጋጁ የኢትዮጵያ ቅርሶችና ጭብጦች የየራሳቸው መጠሪያ እየተሰየመላቸው መርሐ ግብር እንደሚቀርፅላቸውም አመልክቷል፡፡  

በኢትዮጵያዊ ስያሜዋ ‹‹ድንቅነሽ›› የምትባለው ሉሲ የሚለውን መጠርያዋን ያገኘችው ፕሮፌሰር ዶናልድ ጆንሰን ከተባባሪዎቻቸው ጋር ቅሪተ አካሏን ካገኙ ከሰዓታት በኋላ አረፍ ብለው ካደመጡት 1960ዎቹ የቢትልሶች፣ ‹‹Lucy in the SKY with Diamond›› (ሉሲ ኢን ስካይ ዊዝ ዳይመንድ) ዘፈን ነበር፡፡

ሉሲ ማን ናት?

ማንይንገረው ሸንቁጥ ‹‹ባለ አከርካሪዎች›› በተሰኘው መጽሐፋቸው፣ በአገርኛ አጠራር ድንቅነሽ የተባለችው ሉሲን እንዲህ ገልጸዋታል፡፡ ሉሲ በቀላል አማርኛ በሁለት እግሯ የምትሄድ ኤፕ (ቺምፓንዚ) መሰል አካል ነች፡፡ የጭንቅላቷ መጠን ከኤፕ ያልተሻለ ሆኖ ሲገኝ በሁለት እግሯ መንቀሳቀሷ ደግሞ ለሰው የተሻለ ቅርብ ያደርጋታል፡፡

የሉሲን ቅሪተ አካል የተለየ ያደረገው በጊዜው ከተገኙትም ሆነ አሁን ከሚገኙት አንፃር ሲታይ 40 በመቶ የሚሆነው የአካል ክፍሏም መገኘት ነው፡፡ ሉሲ ጾታዋ ታውቆ በሴት ስም የምትጠራው የዳሌዋ አጥንት በመገኘቱ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በቴክሳስ የሚገኘው የአውስቲን ቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በጋራ ባደረጉት ጥናት የቅድመ ሰው ዝርያዋ ሉሲ ለኅልፈት የተዳረገችው ከዛፍ ወድቃ መሆኑን የሚያመላክተው ግኝታቸውን በኔቸር (Nature) መጽሔት ላይ ከአራት ዓመት በፊት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

በሳይንሳዊ ስሟ ‹‹አውስትራሎፒተከስ አፋራንሲስ›› በመባል የምትታወቀው ሉሲ፣ በአፋር አዋሽ ወንዝ አቅራቢያ ሀዳር በተሰኘ ቦታ የተገኘው ቅሪተ አካሏ አንድ ሜትር ከአሥር ሳንቲ ሜትር ቁመት የነበረውና 40 በመቶውን አካል የሚሸፍኑ ቁርጥራጭ ቅሬተ አካላቷም ነበሩበት፡፡

በ1999 ዓ.ም. የሉሲ ወደ አሜሪካ መሄድና የአምስት ዓመት ቆይታ ማድረግ ምቹ ሁኔታ የፈጠረላቸው ተመራማሪዎች፣ በሉሲ አጥንቶች የውስጥ ስብራቶች ላይ የሲቲ ስካን ቴክኖሎጂን ተጠቅመው በማጥናት የደረሱበትን ግኝት ይፋ አድርገዋል፡፡

ሉሲ በአሜሪካ ቆይታ ካደረገችባቸው ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ በሆነው ቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ በ2000 ዓ.ም. በሚስጥር ለአሥር ቀናት በሲቲ ስካን ጥልቅ ምርመራ ተደርጎባታል፡፡

በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣንና በአውስቲን ቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ ስምምነት መሠረት በሉሲ አጥንቶች የውስጥ ስብራቶች ላይ በተደረገው ጥናት ከተገኙት መረጃዎች አንዱ፣ የሉሲ የቀኝ እጇን ከትከሻዋ የሚያገናኘው አጥንት ስብራት ለየት ያለ መሆኑን ያሳያል፡፡ የጥናት ቡድኑን ከመሩት የቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ጆን ካፔልማን ጋር አብረው የሠሩት ኢትዮጵያዊው የፓልዮ አንትሮፖሎጂ ተመራማሪ ዶ/ር ሙሉጌታ ፍሥሐ (አሁን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር)፣ ግኝቱን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ነሐሴ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ይፋ ሲያደርጉ ስብራቱ በአሁን ዘመን ሰዎች ከትላልቅ ሕንፃዎች ወይም ከረዥም ገደል ሲወድቁና ለመነሳት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከሚነሳ የአጥንት ስብራት ጋር በጣም ይመሳሰላል ብለው እንደነበር ይታወሳል፡፡

ሌሎቹም የሉሲ የራስ ቅል፣ መንጋጋ፣ የማህፀንና የጎን አጥንቶች፣ የግራ እግር ጉልበትና የቀኝ እግር ቁርጭምጭሚት ሉሲ ከትልቅ ዛፍ በመውደቅ ያጋጠማት የአጥንት ስብራቶች መሆናቸውን ያሳያሉ፡፡

ሃቻምና ‹‹ጉዞ ሉሲ ለሰላምና ለፍቅር›› በተሰኘ ፕሮጀክት፣ የሉሲ ቅሪተ አካል ከሌሎች ባህላዊ ቅርሶች ጋር በመሆን በተወሰኑ ክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ መዘዋወሯ አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...