Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸው የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ከወረራ የመታደግ ጥሪ

የይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸው የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ከወረራ የመታደግ ጥሪ

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ ከመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ በርካታ ችግሮች ሲነገሩ ይደመጣል፡፡ በዚህ ምክንያት በከተማዋ ለተለያዩ ዓላማዎች ይውላሉ በሚል ታሳቢነት ታጥረው የሰነበቱ ከፍተኛ ስፋት ያላቸው መሬቶች የሕገወጦች የመሬት ወረራ ሰለባ ሆነዋል፡፡

በሕገወጡ የመሬት ወረራ ሰለባ ከሆኑ ሥፍራዎች በዋነኛነት በተለያዩ ክፍላተ ከተማ የሚገኙና ለስፖርት ማዘውተሪያ ዓላማ የተከለሉ ሥፍራዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን በተለያዩ ጊዜያት ለስፖርት ማዘውተሪያነት የታጠሩ ሥፍራዎችን አስመልክቶ መፍትሔ እንዲበጅ ሲወተውት የነበረ ቢሆንም፣ ጉዳዩ ሁነኛ መፍትሔ ሳያገኝ እየተንከባለለ እዚህ ደርሷል፡፡

በዚህ መሠረት ኮሚሽኑ ከመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጋር ለችግሩ ሁነኛ መፍትሔና ዕልባት ለማበጀት ያለመ የምክክር መድረክ ሐሙስ ኅዳር 17 ቀን 2013 ዓ.ም. በኤሊያና ሆቴል አከናውኗል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽነር አቶ በላይ ደጀን የችግሩን መጠንና ጥልቀት ያብራሩ ሲሆን፣ ከዚሁ የመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ሁለት መሠረታዊ ችግሮችን ገልጸዋል፡፡ እንደ ኮሚሽነሩ ማብራሪያ ከሆነ፣ በየክፍለ ከተማው የሚገኙ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ወረራን ለማስቆም አዳጋች የሚያደርገው የመጀመርያውና ዋነኛው፣ ለስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራነት የተከለሉት መሬቶች የባለቤትነት ማረጋገጫ ዕጦት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በተለይም ከግንባታ መጓተት ጋር ተያይዞ በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ የተለያዩ ቢሮዎች በዋናነት ኮንስትራክን ቢሮዎች ጋር ተናቦ ያለመሥራት ችግር እነዚህን የማዘውተሪያ ሥፍራዎች ለመታደግ ከፍተኛ ችግር መሆኑን በመግለጽ የመገናኛ ብዙኃንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከዚህ አንፃር ተባብረው እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በእነዚህና መሰል ተግዳሮቶች የተነሳ የኢትዮጵያና የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ፣ በተለይ በስፖርቱ ነዋሪዎቿን የሚመጥን የ‹‹እኔ›› የምትለው የስፖርት መሠረተ ልማት እንደሌላት በመድረኩ ተነስቷል፡፡ ከአበበ ቢቂላ ስታዲዮም ጀምሮ ያሉት ከግንባታ ጥራት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ችግር እንዳለባቸው ያስረዱት ከሚሽነሩ፣ ‹‹አሁን ያለው አመራር የችግሩ መንስዔ እስካልታወቀ ድረስ የአበበ ቢቂላ ስታዲየምን ጨምሮ  ሌሎችንም ለመረከብ ዝግጁ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ኮሚሽኑ ባለፈው ሳምንት ነባሩን አመራር በአዲስ ከተካው የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በእግር ኳሱ ቀጣይ የአሠራር ሥርዓት ላይ ውይይት ማድረጉ ታውቋል፡፡ ኮሚሽነሩ አቶ በላይ ደጀን አዲስ የተመረጠው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በአዲስ ጉልበት፣ ዕውቀትና ልምድ እንዲሁም ኃላፊነትና ተጠያቂነትን ታሳቢ በማድረግ ሥራቸውን እንዲሠሩ መመርያ ሰጥተዋል፡፡

ኮሚሽነሩ ኅዳር 18 ቀን ከአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ በከተማዋ እግር ኳስ ተወዳጅና ተዘውታሪ የመሆኑን ያህል፣ ያንን የሚመጥን ተግባር ተከናውኗል ማለት እንደማይቻል መግለጻቸው ታውቋል፡፡

ውይይቱን አስመልክቶ የኮሚሽኑ መግለጫ እንደሚያስረዳው ከሆነ፣ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አገር አቀፉን የስፖርት ምክር ቤት ሕግ፣ ደንብ፣ መመርያና አሠራር መሠረት አድርጎ መንቀሳቀስ ተገቢነት ያለው በመሆኑ፣ በተለይም የሴቶች የላቀ ተሳትፎና የአመራር አቅምና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡

እግር ኳሱን ከመንግሥት ድጎማ በማላቀቅ የራሱን ገቢና የሀብት አሰባሰብ በማጠናከር የሚሠሩ ተግባሮች እንዲሁም ከዘላቂ የስፖርት ሜዳና ተያያዥ ጉዳዮች አንፃር የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ በከተማዋ የሚገኙ ባለሀብቶችና ተቋማትን ማሳተፍ እንደሚያስፈልግ ጭምር መናገራቸውን በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...