Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየኢትዮጵያ ጠላቶች ያሰቡት ስለማይሳካ አርፈው ይቀመጡ

የኢትዮጵያ ጠላቶች ያሰቡት ስለማይሳካ አርፈው ይቀመጡ

ቀን:

በአሰፋ አደፍርስ

ሰዎች የአገራቸውን ጉዳይ የመፈጸም፣ የወገናቸውንና የሕዝባቸውን ሰላምና ሥነ ሥርዓትና ወሰናቸውን የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ አለባቸው። ማንም በሰው አገር የውስጥ ጉዳይ ሊገባ አይይችልም፡፡ ይህም በድግግሞሽ የታየ የዓለም ጉዳይ ነው። አዎን አንድ መንግሥት በይፋ በወገኑ ላይ በጭካኔና ሕገወጥ በሆነ መንገድ ኢሰብዓዊ የሆነ ድርጊት ያላግባብ ከፈጸመ፣ ወገኑን በግፍ ካሰቃየ፣ ለግል ጥቅሙ ብሎ ዜጋውን ከጎዳ ያን ጊዜ የሰው ልጅ መብት ተሟጋቾች የሉም እንጂ፣ ቢኖሩ አቤቱታ ሊሰሙና የግላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይችሉ ይሆናል። ይህም ለሁሉ ከሆነ እንጂ ሦስተኛ ዓለም በሚሉት አገሮች ብቻም መሆን የለበትም። በየጊዜው ጥቁሮች እባብ አንገት አንገታቸውን ተረግጠው ሲደበድቡና ሲገደሉ በምዕራባዊያን አገር እየታየ፣ አንድም ቀን ደብዳቢው ወይም ገዳዩ ለፍርድ ቀርቦ ፍትሕ ሲሰጥ አይታይም፡፡ በሌላው አገር የሆነና ያልሆነውን በማሳበብ እንደ እርጎ ዝንብ ጥልቅ ሲሉ ግን ያታያሉ፡፡

ይህ በኢትዮጵያ የሚሞከር እንዳይምስላቸው ይጠንቀቁ። በሰው የውስጥ ጉዳይ አይግቡ፣ ከገቡም የራሳቸውን ያስታውሱ። ለመሆኑ የብራይተን ክፍለ ከተማ ለሎንዶኑ ዋና ቢሮው አልታዘዝም ቢልና የእንግሊዝ መንግሥት ጦርነት ቢሰብቅበት፣ የዓለም መንግሥታት በጉዳዩ ሊገቡ ነው? ስቴት ኦፍ ካሊፎርኒያ ለፌዴራል መንግሥት አልታዘዝም ብሎ ጦር ቢሰብቅ፣ የፌዴራል መንግሥቱ በዝምታ ሊያይ ይሆን? የቱር ክፍለ ከተማ ለፈረንሣይ ዋና መንግሥት አልታዘዝም ብሎ ጦር ቢሰብቅ፣ ዋናው መንግሥት በዝምታ ሊያየው ይሆን? ወይስ የዓለም መንግሥታት በጉዳዩ ገብተው ሊገላግሉ? እንዲያው ታሪክን ታሪክ ያስታውሳልና ሰሜንና ደቡብ ዩናትድ ስቴትስ በባሪያና በሌሎች ጉዳዮች እንለያይ፣ አንለያይ በሚል ሁኔታ ሲዋጉ እስከ 700 ሺሕ ሰዎች አልቀዋል፡፡ ታዲያ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ምን አግብቷቸው ነው የዓለም መነግሥታት የሚዘባነኑብን?

በእርግጥ የአሜሪካን የደቡብንና የሰሜኑን ማንሳቱ ትንሽ የዘገየ በመሆኑ እንለፈው፡፡ የአሁኑን ዘመን እንኳ ብናነሳ ከላይ የጠቀስኳቸው እነ እንግሊዝ፣ ፈረንሣይና አሜሪካ በቂ ይሆናሉ። ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ያልተደረገ አልነበረም፡፡ ከጄኔራል ናፒዬር ጀምሮ በተሠራ ሴራ እስከ 1953 ዓ.ም. የክብር ዘበኛን አመፅ አስከትሎ በየበረሃው በውኃ ጥም፣ በረሃብና በጠላት ጦር ሳይሸነፉ ሌትና ቀን ዳገቱንና ቁልቁለቱን ወርደውና ወጥተው ለአገራቸው የተንከራተቱትን ወገኖቻችን እንደ እነ ራስ አበበ አረጋይ፣ አቶ መኮንን ሀብተ ወልድ፣ ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ፣ ጄኔራል አሰፋ አየነንና የመሳሰሉትን አሰውተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ያሰቡት የኢትዮጵያ መከፋፈልና መበታተን እንደ ፈለጉት ሳይሳካላቸው ቢቀርም፣ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ተቀምጠው ሁኔታውን ያማከረና ሳይሳካ ሲቀር በአጥር ዘለው የወጡትን እነ አምባሳደር ሪቻርድን ስናስታውስ፣ ምንም ወዳጅ እንደ ሌለን በመገንዘብ ራሳችንን መጠበቅ ይኖርብናል፣ ዝግጁ ሆነን መጠባበቅ ያሻናል።

ቀጥለው ያሰቡት እንቅስቃሴ ወዳልፈለጉት መንገድ ዞሮ አሁንም መስመር ሳይዝ ለሁላችንም የቀውጢ ዘመን ሆኖ አለፈ። የ1966 ዓ.ም. አብዮትን ማለቴ ነው።  አሁንም ሊተኙልን ያልቻሉ አሉ፡፡ የተሻለና በእነሱ መንገድ ሊሄድ የሚችል ጮሌ ኢትዮጵያን ለመሸጥ የተዘጋጀ አግኝተው ተሳካልን ብለው የመከፋፈል ዘመቻቸውን እንደ ቀጠሉ ደግሞ፣ ቀኝ እጅ ሊሆናቸው የተዘጋጀውን የኢትዮጵያ አምላክ ባልታሰበና ባልተጠበቀ ሁኔታ በቃህ ብሎ ለኢትዮጵያ ታላቅ ምልክት አሳየ፡፡ ይሁን እንጂ ከጥፋታቸው መማር ያልቻሉ መኃይምናን ወገንን ያላግባብ ሲያብጠለጥሉና ሲያዋርዱ፣ አሁንም በፈጣሪ ኃይል ወረዱ፡፡ ወርደው ደግሞ ጊዜያቸውን ጠተብቀው ሁሉንም ማየት ሲችሉ፣ ከእኛ በላይ ላሳር ሲሉ በወገናቸው ላይ የለመዱትን ወንጀል ከመፈጸም ሊቆጠቡ አልቻሉም፡፡ ወንጀሉን እንደ ቁምነገር ተያያዙት፡፡

መንግሥትም በትዕግሥት ይቅርባችሁ አላቸው፡፡ ሕዝቡም የደረሰበትን ጉዳት፣ ቅሚያና ዘረፋ በትዕግሥት ይዞ ግድ የለም አድሮ ውሎ ይሻሻሉ ይሆናል ብሎ በተሰፋ ሲጠባበቅ፣ ይባስ ብለው ከእኛ በላይ ማንም የለም፣ ልዩ ኃይል አለን፣ ለመንግሥት አንታዘዝም፣ እንገድላለን እንጂ ሞት እኛን አይነካንም ሲሉ በትዕቢት ተጀንነው መንግሥትንም አናውቅም አሉ፡፡ አልፈው ተርፈው የአገር ድንበር ለመጠበቅ የተሠለፉትን ወጥቶ አደሮች (ወታደሮች) በችግራቸው ደራሽና አገልጋያቸውን በተኙበት በመድፍ፣ በመትረየስና በታንክ ፈጁ፡፡ ልብሳቸውንም ገፈውና እንደ አውሬ እያረዱ ዕርቃነ ሥጋቸውንም ሜዳ ላይ ጣሏቸው። ታዲያ ይህንን ነው አስታርራቂ ነን ባዮች ተቀምጣችሁ ተደራደሩ የሚሉት? የሚሳካላቸው መስሏቸው በቤተ መንግሥቱ ቁጭ ብለው በማማከር የጀግኖች አባቶቻችን ደም ሲፈስስ በመመልከት፣ በአጥር ዘለው የጠፉትን አምባሳደር አርተር ሪቻርድንና የመሳሰሉ አወዳደቃችን ተስፈኞች፣ አገራችንን መቅኖ ለማሳጣት የሚጥሩ ወገኖች ናቸው እኮ አስታራቂ ነን ብለው የሚደልሉን።

አይ ኢትዮጵያ! ብልህ ትውልድ፣ ሳይማር የተማረ፣ ነገ ምን ይመጣ ይሆን ብሎ አርቆ የሚያስብ ትውልድ አልፎ አገርን የሚከፋፍል፣ ከታላቅነት ይልቅ ታናሽነት የሚሻ፣ ከአገር አንድነት ይልቅ የመለያየት አባዜ የያዘን ጥቂት ትውልድ አተረፈች። አይገርምም?  በርካታ ኢትዮጵያዊያን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ለረቡዕ አጥቢያ የደረሰውን ግፍና በደሉን በትክክል ከመናገር ይልቅ፣ በቀጥታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመከላከያ ሠራዊት ዕርምጃ እንዲወስድ ትዕዛዝ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ ሳቢያ በርካታ ኢትዮጵያዊያን በድንጋጤና በጭንቀት ውስጥ ይገኛሉ ተብሎ፣ ጦርነቱ መጀመሩን ተከትሎ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ጉዳዩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ብለዋል፡፡ የሚገርመው ነገር በእውነት እነዚህ ሰዎች ከልባቸው ይሆን ይህንን የሚሉት? ምነው እስከ ዛሬ በእነዚህ ጦርን በሚሰብቁ ሰዎች ሲገደሉ፣ ሲታረዱና ንብረታቸው ተዘርፎ መድረሻ ሲያጡ ሳይተነፍሱ ዛሬ ከየት ብቅ አሉ? የጋራ ጥቅም አላቸው ይሆን? እኔ ሰላም አይስፈን ማለቴ ሳይሆን፣ ሁሉም በአግባቡ ይሁን ለማለት ነው።

የተሰዉት ወጥቶ አደሮች (ወታደሮች) በምን ዕዳቸው፣ አገር ባገለገሉ፣ ድንበር በጠበቁና ሰላን ባስከበሩ ነው የሚገደሉት? ወይስ መሣሪያቸውን ለመንጠቅ? ከሆነስ እጅ ስጥ ተብሎ አሻፈረኝ ካለ ለማስፈራሪያ ያህል አንድ ሁለት ሰው መግደል ሳይሆን፣ በማስፈራራትና በማግባባት ይወሰዳል እንጅ እንዴት የገዛ ወገን ይገደላል? ይህ የፋሽስት ሥራ ነው እንኳ ሊባል አይችልም? ከዚያ በላይ ነው። ምናልባት የአውሮፓ ኅብረት ምክትል ፕሬዚዳንት የአያታቸውና የአባታቸው ምኞት የተሳካላቸው መስሏቸው ይሆናል፡፡ የአፍሪካ ኅብረቱም ለዝናና አዎንታ ለማግኘት ይሆናል፡፡ ነገር ግን አንዱ ኢትዮጵያዊ ይመስለኛል ታዲያ በየትኛው ካምፕ ውስጥ ያለ ነው? ይህንን ያልኩበት ምክንያት ዕርቅ አይኑር ለማለት ሳይሆን፣ ቁጭ ብለው ይነጋገሩ መሳይ አስተያየታቸው በጣም  አስቆጥቶኝ ነው። ይቅርታ ጠይቀውና ለጥፋታቸው ተገቢው ፍርድ (ፍትሕ) ተሰጥቷቸው ለአገርና ለወገን ሰላም ይምጣ በማለት ፈንታ፣ ወንጀለኛውንም እንደ ሌላ አገር በማድረግ ይደራደሩ የሚለው አነጋገር በጣም የሚያስቆጣና የበለጠ የሚያለያይ ነው።

ምናልባት ዴሞክራት ነን ባዮች ይሆናሉ፣ ዴሞክራሲ አገር ሲኖር ብቻ ነው። አዎን ኢትዮጵያዊያን ይቅር ባዮች ነን፣ ግን መሠረቱን ሳይለቅ። የሰው ልጅ እንደ አውሬ እየታረደና በየሜዳው እየተጣለ፣ ያውም ዕርቃነ ሥጋውን፡፡ ወገኑን ከወራሪ የታደገውን እንዴት? ደግሞ መንግሥት ያልሆነን አናሳ ጁንታ እንደ ልዩ ራሱን የቻለ መንግሥት በማስመሰል የተደረገውና የተሰጠው አስተያየት፣ ከአንድ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ ሳይሆን ለአሉባልታ የተዘጋጀ የወገንተኝነት አስተያየት ይመስላልና ጥንቃቄ ያሻል።

በአምነስቲ ኢንተርናሽናል ውስጥ ተቆርቋሪ መስሎ የሚያወናብድ የአንድ በኩል ወገንተኛ የሚመስል ሰው ያለ ስለሚመስል፣ የብዙኃኑ ቃል አቀባይም ይህንን ልብ ቢልና በሚገባ ቢተነትነው የተሻለ ይሆናል። ይህ ኢትዮጵያን ሊያጠፉ የቀመሩትንና ከብዙ ዓመታት በኋላ ሊሳካላቸው መስሏቸው ያዘጋጁልንን ተንኮል ገብቷቸው ይሁን ሳይገባቸው ተቀብለው ዘርን በዘር፣ ሃይማኖትን በሃይማኖት ላይ አነሳስተው አገራችንን መቀመቅ የሚሰዱትን ቀላጤዎች በእነሱ በኩል ሳያጤኑ፣ እንዲያው እንደ መንግሥት ቁጭ ብለው ይደራደሩ ማለት እጅግ የሚያሳፍር ነው። የዓለም መንግሥታት ውኪል ነን ባዮች ምነው እስከ ዛሬ በሺዎች ለሚቆጠሩ የተጨፈጨፉ ንፁኃን ኢትዮጵያዊያን ደም አንድ ድምፅ እንኳ ሳያሰሙ የቀሩት የእነሱን መልዕክት ይዘውላቸው ይሆን ዛሬ ዳር ከዳር የሚወራጭት?

ኢትዮጵያ እንኳንስ ዛሬ የተማሩ፣ የተመራመሩና የሠለጠኑ ልጆቿ ደርሰውላት ቀርቶ፣ ባልተማሩና አገር ወዳድ በነበሩ ወገኖቿ ታፍራና ተከብራ ከሌላው ዓለም ተለይታ በቅኝ ሳትገዛ አሻፈረኝ ብላ የኖረች አገር መሆኗን መገንዘብ ያሻል። ከዚህ በመቀጠል ታላቁ ዩሑዲ ዶክተር ሔኔሪ ኪሲንጀር የወጠኑላትና ያዘጋጁላት በሕይወት ኑረው ባያዩም መንገድ የያዘላቸው በሚመስል ሁኔታ፣ በአንዳንድ ከሃዲያን ልጆቿ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ እየተከናወነ ነው። ይሁን እንጂ ጀግኖቹ የኢትዮጵያ ልጆች እንዲህ በዋዛ የሚበገሩ አይደሉምና ይጠንቀቁ። የኪሲንጀርን ሐሳብ በአማርኛ ብተረጉመው መልካም ነበር፡፡ ነገር ግን ሐሳባቸውን እንደ ወረደ ከኢንተርኔት እንድታነቡት ብዬ ነው። የበለጠም ነበር፣ ነገር ግን ወሬ ቢበዛ በአህያ አይጫን ይሉ የለ?

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ግለ ሕይወታቸውንና የጉዞ ታሪካቸውን የከተቡበት ‹‹ከባቹማ እስከ ቨርጂኒያ›› በሚል ርዕስ ለአንባብያን ያቀረቡት መጽሐፍ ደራሲ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...