Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትሁሉንም ዓይነት የጦርነት መነሻና ምክንያት መገላገል

ሁሉንም ዓይነት የጦርነት መነሻና ምክንያት መገላገል

ቀን:

በገነት ዓለሙ

አገራችን ጦርነት ውስጥ ነች፡፡ በደንብና በሥርዓት የጦር አደጋ ምልክት የተሰጠበት፣ የጦርነት ክተት የታወጀበት፡፡ ወይም ኢትዮጵያ ጦርነት ሁኔታ ውስጥ ገብታለች ተብሎ የተነገረበት ስለመሆኑ እርግጠኛ ባልሆንም፣ ባለፈው ሳምንት የተነጋገርንበት ‹‹ለአገር መከላከያ ክብር እቆማለሁ›› ማለት የመጣው ከዚህ ነው፡፡

በአጠቃላይ ሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ ያጋጠመን ብርቱ ጉዳይ የዓለም የመገናኛ ብዙኃን፣ የሰብዓዊ መብት ተቋማት፣ የስደተኞችና የተፈናቃይ ጉዳይ ድርጅቶች ትኩስና አጣዳፊ ርዕስና አጀንዳ ሆኗል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ አድርጎ ተነጋገረበት መባሉን ሰምተናል፡፡

- Advertisement -

በአገር ውስጥም በውጭ አገርም የሚኖሩ ጉዳዩ የሚያሳስባቸው ሁሉ የሚሉት ጦርነቱ ይቁም ነው፡፡ ጥሩ ነው፣ ይህ ጦርነት መቆም አለበት፣ መጀመርያም መኖር አልነበረበትም፡፡ በተለይም ባለጉዳይዋ ኢትዮጵያ ይህንና ይህን ብቻ ጦርነት ከማቆም በላይ፣ የሁሉንም ጦርነት ዓይነቶች መነሻና መጀመርያዎች ማቆምና መገላገል ትፈልጋለች፡፡ ኢትዮጵያ ይህን ጦርነት ብቻ ሳይሆን የትኛውንም ወደ መጠፋፋትና ወደ ዕልቂት የሚመራውን ጎዳና መዝጋት የምትችለው ጦርነቱ በተለኮሰበት፣ በተቀጣጠለበትና የአሁኑ ችግራችን በተጀመረበት ሁኔታ የሁሉንም የጦርነት መነሻና መጀመርያ ምክንያቶች ወደ ማጥፋት ስናመራ ብቻ ነው፡፡

ታዲያ የሁሉም ጦርነቶች መነሻ ምንድነው? ይህንን አሁን የሚያስደነግጥ የሰብዓዊ መብቶች ሪፖርት የቀረበበትን የሚያስፈራራ አደጋና ሥጋት የሚያንዣብብበትን ጦርነት ብቻ ሳይሆን የዚህም፣ የሌሎችምና የሁሉም ጦርነት ሁሉ መነሻ ምንድነው? የጦርነት ዕድልን ዘግተንና አምክነን ዴሞክራሲን የመቀዳጀት ዕድልን የምንይዘው በምን መንገድ ነው? አገር ሊቆጭበትና ሊነጋገርበት የሚገባ፣ ከሞላ ጎደል ለሦስት ዓመት ያህል የወዘፍነው፣ በከፊልም ያሾፍንበት በአንዳንዶች ዘንድ ደግሞ የታገሉት የወጉት ነገር ነው፡፡ ይህ ችግር ውስጣችን የኖረ፣ በአፈናና በጥርነፋ ‹‹ምልክት›› አጥፍቶ ከፕሮፓጋንዳው ምንጣፍ ሥር ሲንተከተክ የቆየ የአገር ሕመም ነው፡፡

የመጠፋፋት አደጋ አብሮን የኖረ በሽታችን ነው፡፡ የዚህ በሽታ ልክፍት የጀመረንም አስተዳደራዊ አከላለልን የየብቻ አገርና መሬት ቅርጫ፣ ወሰንን የውስጣዊ አገር ድርሻ፣ አካባቢያዊ ሥልጣንን የተወሰነ ማኅበረሰብ ርስት ያደረገ፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መድኃኒት ‹‹ያዘዝን›› ወቅት ነው፡፡ በሽታውና ችግሩ እውነት ነው፡፡ የቡድንና የማኅበረሰብ መብት ታሞ ኖሯል፡፡ ብሔረሰባዊ መብት ጨምሮ ሌሎች መብቶችን የመጎናፀፍ ጤና ዕይታና ትግል ግን ክፍልፋይነትንና መጠፋፋትን የወለደ መድኃኒት ተክሎ አመሰን፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ እስከ 1983 ዓ.ም. ሆነ እስከ ዛሬ ድረስ የተካሄዱና የሚካሄዱ የመብት ትግሎች የለፉትም፣ የተለፈባቸውም በእኩል መብቶች ውስጥ መኖርን ለመቀዳጀት እንጂ በተበላለጠ መብትና ዜግነት ውስጥ መኖርን በሌላና በአዲስ መልክ ለማስፈን በጭራሽ አልነበረም፡፡

ዛሬ ሰሜናዊው የአገራችን ክፍል ላይ የታየው ችግርና ችግሩም ፈንድቶ የተቀጣጠለው እሳት፣ እንዴት አድርጎ ምን ያህል ጉዳት እንዳስከተለና እንዴት ያለ የአገር አደጋ ደግሶ እንደነበር የቅርብ ጊዜ የ2010 የክረምት ወር የሶማሌ ክልል ትዝታችንና ልምዳችን ትምህርት በሆነ ነበር፡፡ ምሳሌነቱ ከሁሉም በላይ የተሰጠው መፍትሔ የአስተማሪነትና የማስረጃነት/ማሳያነት ዋጋው ከፍተኛ ነውና መለስ ብለን እንመልከተው፡፡

27 ዓመታት የኢትዮጵያ ልምድ እንደታየው በብጥስጣሽ ብሔርተኛ ሚዛን ሕዝብን ከሕዝብ እያንጓለሉ የሚገዙና የሚዘርፉ አልጠግብ ባዮች፣ ‹‹የእኛ›› የሚሉትና የሚላቸው ሕዝብ ዘረፋና ግፋቸውን እንዳያይባቸው ለመከለል ወይም በደላቸው የአደባባይ ሚስጥር ሆኖ ሕዝብ ሊተፋን ነው የሚል ሥጋት ሲገባቸው፣ በክልላቸው ውስጥ ባሉትና ባይተዋር ተደርጎ ለመታየት በተፈረደባቸው ‹‹መጤ›› ማኅበረሰቦች ላይ፣ ሀብትና ጥቅም ተቀራመቱ፣ ወይም ምሥጋና ቢስ ዕብሪትና መዳፈር አሳዩ የሚል ዓይነት ነገር እየሠሩ፣ ወይም ተጎራባች ሕዝብ ወሰን እየገፋ ስለመሆኑ ወሬ አቡክተውና ፀብ አስነስተው፣ በዜጎች እንባና ደም ለብሔራቸው ‹‹ተቆርቋሪነታቸውን›› ይጋግራሉ፡፡ አንዱን ግፍ በሌላ ግፍ ያረሳሳሉ/ይሰውራሉ፡፡ በዚህ አልጨበርበር ወይም አልደለል ያለ ከራሳቸው ብሔር የበቀለ ተንከሲስ ሲገጥማቸው ደግሞ፣ በአሸበሪነትም ሆነ በሌላ ወንጀል ጠልፈው ወህኒ ይከቱታል፡፡ ደብዛውን ያጠፉታል፡፡

በሶማሌ ክልልም አቢዲ ኢሌ ነገሠና የክልሉ ፓርቲም መንግሥታዊ አውታርም የንግድ መረብም እሱና ቡድኑ ሆኖ ውሎ አደረ፡፡ የተበዳዮች የሰሚ ያለህ ጩኸትም የንጉሡ አንቀጥቃጭነትም ባህር ማዶ ድረስ ተሻገረና ልዩ ፖሊስን ለዓለም አስተዋወቀ፡፡ ይህ ፖሊስ መጀመርያ የተቀቀመው ለሆነ ‹‹በጎ›› ዓላማ ነበረ (የተወሰነች የፖለቲካ ችግር ለመመከት ሲባል ክልላዊ መንግሥትን በብሔርተኝነት ለመውዋጥ የተመቸ የልዩ ታጣቂ ኃይል ባለቤት ማድረግ ምን ያህል ወደ ዕብሪት ሊወስድ እንደሚችል ታየ፣ አሁንም ነገሮች በጥንቃቄ ካልተያዙ ወደ ሌላ ሌላ ዓይነት መባረቅ ሊቀየሩ የመቻላቸው ዕድል ክፍት ሆኖ መኖሩን የሰሜን ዕዝ ‹‹ውሳኔ›› ሲሰጥ፣ ‹‹የከልል መከላከያ ኃይል››፣ ‹‹የክልል አየር ኃይል›› ሲባል በዓይናችን በብረቱ አየን)፡፡

 የግርግር ንፋስን ተንተርሶ የታጠቁ ጥቃቶችን እያራቡ በሚሊዮን የሚቆጠር ኦሮሞን ከሶማሌ ክልል ከማፈናቀል አንስቶ፣ እስከ ዛሬ በተደጋጋሚ የተፈጸሙ የወሰን አካባቢ ግጭቶች፣ ብሔርና እምነት ለይቶ የመኖሪያ ቤትና የንግድ ንብረቶችን፣ ባንክን እስከ መዝረፍ፣ ሰውን በገጀራና በድንጋይ ከመቀጥቀጥ አንስቶ እሳት ውስጥ እስከ መማገድ ድረስ የተፈጸሙ ሰቅጣጭ ድርጊቶች ሁሉ፣ የገዥነት ግፍን ለብሔሬ የቆምኩ በሚል ቀጣፊ ካባ ለመሸፈን የተሞከረባቸው መሰሪና ጨካኝ ‹‹ጥበቦች›› ሶማሌ ውስጥ ታዩ፡፡

ያ ሁሉ ሕዝብ በገፍ እንዲፈናቀል የተደረገው፣ ከዚያም በኋላ ቁጣ ውስጥ የሚያስገቡ ወሰን ዘለል የግድያ ጥቃቶች በተደጋጋሚ የተፈጸሙት፣ ጨፍጭፎ ተጨፈጨፍን  እስከ ማለት ዓይነ ደረቅ ውሸት ሲለቀቅ የነበረው ሁሉ ከቁጥጥር የወጣ ዘመቻ፣ ኦሮሞ ከፍቶ ወይም መከላከያ የግድያና የገፍ እስራት ከፍቶ ይኸው የሶማሌ ሕዝብ ተዘመተብህ፣ ምን ትጠብቃለህ የሚል ኡኡታ አቅላጭ ለመሆንና ከዚህ ሸረኛ ኡኡታ ጀርባ የሶማሌን ሕዝብ ሁሉ ለማሠለፍና ከተመቸ በኢትዮጵያ መንግሥት አይነኬ ገዥነትን ለማደስ፣ ካልተመቸ ደግሞ ወደ ሶሚሊያና ወደ ሶማሌላንድ ዘንበል ብሎና በሰላማዊ ጉርብትና ላይ ሽብልቅ ሆኖ ‹‹የሃርነት መሪነት›› ዘውድ ለመድፋት ነበር፡፡  ለዚህ ማመከኛ የሚሆን ማዕበል ከኦሮሚያ ገንፍሎ ወደ ሶማሌ ክልል አልፈስ አለ አንጂ፡፡ የፌዴራል መንግሥትም የፌዴራል የፀጥታ ኃይሉን አንቀሳቅሶ ጣልቃ ሊገባ የሚችልባቸውን ሕገ መንግሥታዊ ቀዳዳዎች ሁሉ ለመጠቀም አልፈጥን ብሎ ቆየ፣ በብዙ ምክንያቶች፡፡ ንጉሥ አብዲ ኢሌና ማፊያ ቡድኑ ላይ ሲነሳ የቆየው የሶማሌ ሕዝብ እሮሮ ደግሞ መቆሚያ አጣ፡፡ የፌዴራል መንግሥት አንድ ነገር እንዲያደርግ የአቤቱታ ደጅ ጥናቱ አዲስ አበባ ከገባ ውሎ አደረ፡፡ በዚያው ልክ የተቅበጠበጠውና ሥጋት የገባው የክልሉ ንጉሥ ከበፊቱ የበለጠ የኢትዮጵያን ፌዴራል መንግሥትንና መከላከያን ጥይት በአስቸኳይ የሚያመጣ ሌላ ብርቱ ትንኮሳ ውስጥ ገባ፡፡ ቀሳውስት እስከ መግደልና ቤተ ክርስቲያናት እስከ ማቃጠል. . . ከዚያም አልፎ የሶማሊያን ባንዲራ እስከ መስቀልና የመነጠል ምክር ቤታዊ ሴራ እስከ ማዘጋጀት ይለይለት አለ፡፡ ያ ሁሉ በተገንጣይ አሸባሪነት እየጠለፉ የመቅጠፍ፣ ወህኒ የማበስበስ፣ የማሰቃየት፣ የማውደም፣ የመዝረፍ፣ የማፈናቀልና የገጀራ ግፍ ሁሉ አንድ ዱርዬ ፈላጭ ቆራጭ ከኢትዮጵያ አካባቢያዊ ገዥነት እስከ ‹‹ነፃ አውጪነት›› እየተፈናጠረ በሕዝብ ጫንቃ ላይ እንዲቆምር የተከፈለ ግብር ነበር፡፡ የዚህ ግብር ከፋዮች እነማን ናቸው? ሶማሌዎችና ሌሎች ድብልቅ ዜጎቻችን!

ይህ በሶማሌ አካባቢ የታየ እጅግ መራራ ልምድ በብጥስጣሽ ብሔርተኝነት ህሊናና አገዛዝ ውስጥ መውደቅ ወገን ሳይለይ፣ ሁላችንንም የመልቲዎች መጫወቻ ለመሆን ምን ያህል እንደሚያጋልጥ የማይረሳ ትምህርት የሚሆን ነው፡፡ ትምህርቱ ደግሞ ቋንቋን የተከተለ አጥር ከማጠር መውጣትን፣ አንዱን ሕዝብ ከሌላው ከሚያገል ብሔርተኛ የፓርቲ አደረጃጀትና ገዥነት ወጥቶ ሁሉን አሳታፊ ወደ ሆነ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲና የአካባቢን ጥንቅር ያንፀባረቀ የመንግሥታዊ አውታራት ግንባታ ውስጥ መግባትን፣ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ዴሞክራሲን፣ ፍትሕንና እኩልነትን መተማመኛ አድርጎ በተግባር መያዝን ይጠይቃል፡፡

 ትምህርቱ ግን በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይደለም፡፡ የመጠፋፋት አደጋን አምክነን ዴሞክራሲን የማደላደልና የመቀዳጀት ዕድልን የምንጨብጠው፣ የአገሪቱ የመከላከያ ኃይል ከመናጋትና ከመፍረስ አደጋ ጋር ሳይገናኝ፣ የመረጃና የደኅንነት አውታሩም የአገሪቱን የልማት ሀብቶች የሕዝቦችን ደኅንነትና ሰላም ነቅቶ ከመጠበቅ ለአንድ ጊዜም ሳያቋርጥ፤ በተለይም ከገዥ የፖለቲካ ቡድን ታማኝነትና ደባል አገልጋይነት እንዲላቀቅ በአጠቃላይም የተክለ መንግሥቱ (የስቴቱ) አውታራት ገለልተኛ ተፈጥሮና ባህሪን እንዲጎናፀፉ በማድረግ ነው፡፡ ይህንን ኢትዮጵያን የጎደላትንና ለዚህም አደጋ ያበቃንን ይህንን ተግባር መፈጸም የሚቻለው ደግሞ፣ ከዚህ በፊት (ለውጡ እንደ ተጀመረ) ኢሕአዴጎች እርስ በርሳቸውና ተቃዋሚዎች አሁንም ብልፅግናና የተቃወም ወገኖች በጠረጴዛ ዙሪያ ገጥመው አብሮ ለመሥራትና የተክለ መንግሥቱን መጣመም ለማቃናት ማለትም ዴሞክራሲን ለማደላደል መስማማታቸው ነው፡፡

ዴሞክራሲ ላይ አብሮ ለመሥራት የሚጣላ ይኖራል አይባልም፡፡ በዚህ በምንነጋገርበት የዴሞክራሲ ማዕቀፍ ወይም ቅጥር ግቢ ውስጥ እስካሰብን ድረስ ብልፅግና ፓርቲ እንዲቆይ፣ እንዲገዛ መፈለግ ወይም የለም ብልፅግና ይቀየር፣ ይለወጥ ወይም መግዛት ያለበት ሌላ ፓርቲ ነው ማለት በጭራሽ አያጣላም፡፡ የዚህ ምክንያት ለየትኛውም የዴሞክራሲ ናፋቂ፣ ለሁሉም ዓይነት የዴሞክራሲ ናፋቂዎች ዋናው ጥያቄና ጭብጥ የትኞቹም ፍላጎቶች (የሥልጣን ፍላጎቶች ጭምር) በሕዝቦች እውነተኛ ድምፅ መወሰናቸውና ይህንን ደግሞ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ገለልተኛ ሥርዓት መዘርጋቱ ስለሆነ ነው፡፡ የጋራ ጥያቄ መሆን ያለበት ይህ ነው፡፡ በሌላ ቋንቋ ዴሞክራሲን የማደላደልና መሠረት በማስያዝ ተግባር ውስጥ መንግሥታዊ አውታራትን  (መከላከያን፣ ደኅንነትን፣ ፖሊስንና የፍትሕ ተቋማትን፣ እንዲሁም ምርጫ አስፈጻሚ አካላትን) ከማንኛውም ፓርቲ ወገናዊነት የፀዱ አድርጎ ማነፅ ቅብጥርጥሮሽ የማይሻና ወለም ዘለም የማይባልበት፣ ዴሞክራሲን የሚናፍቁና የሚሹ የየትኞቹም ቡድኖች ደጋፊዎች ሁሉ አንድ ላይ ሊቆሙለት የሚገባ ተልዕኮ ነው ማለት ነው፡፡

እዚህ አስከፊ ጦርነት ውስጥ ከተውናል ከሚባሉ ‹‹የህልውና›› ጥያቄዎች መካከል ሕገ መንግሥታዊነትና ፌዴራሊዝም ‹‹አንዳንዶቹ›› ናቸው፡፡ ሁሉም ምክንያቶች እዚህ ውስጥ ይከተታሉ ማለት ይቻላል፡፡ በተለይም ይህ ከሁሉም በላይ በ‹‹አሀዳዊነት›› የሚከሰሰውና ዋናው የአገራችን የፖለቲካ ጥያቄ አገሪቱን ከፈላጭ ቆራጭነት/ከአምባገነንነት፣ ሕገ መንግሥቱ ከተሰነካከለበት ሁኔታ ወደ ዴሞክራሲ ወደ ሕገ መንግሥታዊነት የማለፍ ጥያቄ ነው የሚለው መንግሥት ‹‹የወንጀል ዝርዝር››፣ ‹‹ፌዴራሊዝምን›› በማፍረስ፣ በመካድ ወዘተ. ይባላል፡፡ ስለዴሞክራሲው ከዚህ በላይ በመጠኑ ገልጸናል፡፡ መብቶችና ነፃነቶች መኗኗሪያ የሚሆኑት፣ የመንግሥት አውታራት የማንም ፓርቲ ወይም ቡድን ታማኝ ወይም አገልጋይ ከመሆን በሽታ ሲፀዱ ነው፡፡ የለውጡ መንግሥትን የሚመራው ዓብይ አህመድ በፓርላማ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ የተሰየመው በ‹‹አክላሜሽን›› ነው፣ ያለ ተቃውሞ ነው፡፡ አራት መቶ ሰባ ስምንት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የተገኙበት የምክር ቤት ስብሰባ የተጠራውም፣ በዚያው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ያገኘው የፖለቲካ ድርጅት ዕጩ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንዲጠቁምና ምክር ቤቱም እንዲመርጠው ነው፡፡ የሽግግሩ ሥራ ከሞላ ጎደል የተጀመረው ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት በፓርላማ ንግግሩ እንዳሳየውና በተከታታይ አቋሞቹና ዕርምጃዎቹ እንዳስረዳው፣ ከሌሎች መካከል ከዴሞክራሲ አልባነት ወደ ዴሞክራሲ የመሸጋገር ትልምና ጉዞ መረጠ፡፡ የአገሪቱ የሥልጣን ዓምዶች ሕመማችን፣ በሽታችንና ነቀርሳችን ከሆነው ከፓርቲ ታማኝነትና መዳፍ የማላቀቅ ማሻሻያዎችን የማካሄድ ሒደት ውስጥ መግባቱን አስታወቀ፡፡ በዚህ ድምርና አዲስ አያያዝም ከዚህ በፊት በአገሪቱ ታሪክ ያልነበረ አዲስ ነገርና ውጤት፣ ማለትም ሕዝቦች በድምፃቸው ሿሚና ሻሪ የሚሆኑበትን ሥርዓተ መንግሥት ለማምጣት ተረባረበ፡፡ የዚህ ዓይነት ጅምርና የዚህ ዓይነት ሥርዓት መቋቋም ነው ፓርቲዎች መንግሥታዊ ዙፋንንና ቢሮክራሲውን በፍላጎታቸው ቀርፀው ከመንፈላሰስ፣ እንዲሁም በልሽቀትና በንቅዘት ከመበከል ነፃ የሚያወጣቸው፡፡ ስለ ‹‹ግለሰባዊ አምባገነንነት››ም ሆነ ስለሌላ ዓይነት ፈላጭ ቆራጭነት እሰጥ አገባ ውስጥ ከመግባታችንና ለዴሞክራሲው የማይጠቅም ስድብ ከመወራወራችን በፊት፣ ምን እንደተባለ፣ ምን እየተባለ እንደሆነ በቅጡ መረዳት አለብን፡፡ አድራጊ ፈጣሪነት ሕዝብን መፍራት የሚጀምረው፣ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተዘረዘሩት መብቶች የሰዎች ሁሉ መኗኗሪያና የግንኙነቶችን መግሪያ የሚሆኑት ከፖለቲካ ፓርቲ ፍላጎት፣ መሃላና በጎ ፈቃድ ውጪ የሆኑ በተጠያቂነትና በሥነ ምግባር የሚገዙ ተቋማትና የመንግሥት አውታራት ላይ ዴሞክራሲን ማደላደል ስንችል ነው፡፡ ከእነዚህ ተቋማት መካከል አንዱ መከላከያ ነው፡፡ ይህ የአገር የመከላከያ ኃይል ጉዳይ ደግሞ ወደ ፌዴራሊዝም ጥያቄ ይመልሰናል፡፡

ተደጋግሞ እንደተገለጸው ዴሞክራሲ ይናፍቀናል፣ ዴሞክራሲን እንናፍቃለን፣ ለዚህም ስንታገል ኖረናል፣ እንታገላለንም የሚሉ ሁሉ ሊስማሙበት የሚገባና የጋራ አደራ የወል አቋም ማድረግ ያለባቸው ጉዳይ የትኞቹም ፍላጎቶች በሕዝብ እውነተኛ ድምፅ የሚወሰኑበትና ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ ገለልተኛ ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡ መከላከያን ጨምሮ ሌሎች መንግሥታዊ አውታራት ሁሉ ከፓርቲ ወገንተኝነት ፀድተው መታነፅ አለባቸው፡፡

በመከላከያ ተቋሙ ፍጥርጥርና አስተናነፅ ውስጥ አንዱ ጎዶላችን ይህ ነበር፡፡ በንጉሡም፣ በደርግም፣ በኢሕአዴግም ዘመን ችግራችን ይህ ሆኖ ኖሯል፡፡ ይህ ችግር ግን ዴሞክራሲያችንን ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንዱ አስኳል የሆነውን ፌዴራሊዝማችንንም በእጀጉ ይነካል፡፡ እውነቱን ለመናገር ፌዴራሊዝማችን የውሸት ‹‹የወረቀት ላይ ነብር›› ብቻ መሆኑን ያረዳ መርዶ ነው፡፡ የሌለንን ሁሉ አለን ስንል የቆየነው ዴሞክራሲን፣ ሪፐብሊክን ብቻ አይደለም፡፡ ሁሉንም የሕገ መንግሥቱን አስኳሎች ነው፡፡

በዓለም ላይ ያሉት ፌዴራል አገሮች ወደ ሃያ አምስት አካባቢ ናቸው፡፡ ሃያ አምስት ብቻ ቢሆኑም ህንድን፣ አሜሪካን፣ ብራዚልን፣ ጀርመንና ሜክሲኮን የመሰሉ ግዙፍና በጣም ውስብስብ ዴሞክራሲዎችን ጭምር ያካትታሉ፡፡ እነዚህ ዴሞክራሲዎች ናቸው፡፡ አማራጭ ሐሳቦችና አማራጭ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ነፃ ምርጫ አለ፡፡ በምርጫ የሕዝብ ድምፅ ያገኘ ሥልጣን ላይ ያልነበረ አማራጭ ሥልጣን ሊይዝ መቻሉ ብርቅ ወይም ወግ አይደለም፡፡ በምርጫ ሥልጫን የያዘ መሪ ቢሮው ሲገባ መከላከያውንና ደኅንነቱን ለማዘዝ ይቸግረኛል የሚል ጣጣ የለበትም፡፡ ይህ ሁሉ አሁንም የሚመለከተው ዴሞክራሲውን ነው፡፡

ከእነዚህ አገሮች መካከል ሁለቱ አሜሪካና ህንድ ናቸው፡፡ አሜሪካ በዓለም የጥንት ዴሞክራሲ የምትባል ፌዴራላዊ አገር ናት፡፡ ህንድ በዓለም ግዙፍ ዴሞክራሲ እየተባለች የምትሞካሽ ፌዴራላዊ አገር ናት፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ በሁለቱም አገሮች ውስጥ የመንግሥት ሥልጣንን በማዕከላዊውና በስቴቶች መካከል ያደላድላል፡፡ በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ነው፡፡ በዚህ መሠረት የአገር መከላከያ ጉዳይ የፌዴራል ሥልጣን ነው፡፡ የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች፣ የህንድ የጦር ኃይሎች፣ የዩኤስ አሜሪካ የጦር ኃይሎች የየአገሩ የወታደራዊና የመከላከያ ኃይሎች ናቸው፡፡ የሁሉም የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥም የማዕከላዊው ወይም የፌዴራሉ ወይም የዩኒየን መንግሥቱ የበላይ ነው፡፡ ሥራቸውን የሚመራውም የመከላከያ ሚኒስቴር የሚባለው ተቋም ነው፡፡ የክልል የመከላከያ ሚኒስቴር የሚባል የካቢኔ ቦታ እነዚህ ፌዴራል አገሮች ውስጥ የለም፡፡ የየአገሩ የመከላከያ ሠራዊት (የምድር፣ የአየርም፣ የባህርም ኃይሉ) በየሥምሪት ክልላቸው እንደ ፍጥርጥራቸው በአገሩ የተለያዩ አካባቢዎች የተደለደሉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ፎርት ብራግ (Fort Bragg) ማለት የአሜሪካ ትልቁ የጦር ሠፈር ነው፡፡ አዲስ አበባን ያክላል፡፡ 570 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡ ከስፋቱ አንፃር ሳይሆን ካሰባሰበው የሕዝብ ብዛት አኳያ ሲበዛ ግዙፍ ነው ይባላል፡፡ የሚገኘውም ሰሜን ካሮላይና የምትባለው የፌዴራሉ ግዛት ክፍል ውስጥ ነው፡፡ ይህን የጦር ሠፈር የማዘዝ፣ የማንቀሳቀስ፣ የሥልጣንና የባለመብትነት የባለቤትነት ጉዳይ ግን የፌዴራሉ መንግሥት ነው፡፡

ህንድም እንደዚሁ መላው ግዛቷ በሚዘረጋበት ዳር ድንበር ውስጥ በርካታ ግዙፍ የጦር ሠፈሮች አሏት፡፡ ሥልጣኑም ባለቤትነቱም ጭምር ከሚስጥርነታቸው ጋር የጉጅራት ወይም የታሚልናዱ ወይም የአንድራ ፕራዴሽ በጭራሽ አይደለም፡፡

በኢትዮጵያም ይህ ሁሉ እውነት ነው፡፡ ይህን ያደረገው ከገዥው ፓርቲ ቁጥጥር ባልወጣ ምርጫና ሕገ መንግሥት የማዘጋጀትና የ‹‹መስጠት›› ሒደት፣ እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦና ሕዝቦች ‹‹እንዲወክሉን መርጠን በላክናቸው ተወካዮቻችን አማካይነት በሕገ መንግሥቱ ጉባዔ›› ያፀደቅነው ሕገ መንግሥት ነው፡፡

ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 52/1 ‹‹በሕገ መንግሥቱ ለፌዴራል መንግሥት በተለይ ወይም ለፌዴራል መንግሥትና ለክልሎች በጋራ በግልጽ ያልተሰጠ ሥልጣን የክልል ሥልጣን›› ነው ሲል፣ የአገር መከላከያና የመከላከያ ሥልጣን የፌዴራል መንግሥቱ ለብቻና በተለይ የተሰጠው ሥልጣን መሆኑን ሳይዘነጋ ጭምር ነው፡፡ የመከላከያ ሥልጣን የፌዴራሉ መንግሥት የብቻው ሥልጣን ነው፡፡ ለፌዴራል ብቻ የተከለለ፣ ለክልል የተከለከለ ሥልጣን ነው፡፡ እንደ ዳኝነት የሚጋሩት ሥልጣን እንኳን አይደለም፡፡

ይህን ሕገ መንግሥት ያወጣው ደግሞ ከክልሎችም ከፌዴራሉ መንግሥትም በላይ ያለ የሥልጣን አካል ነው (ይህን ብለን መነሳት ያለብን ከአወጣጡም ከአተገባበሩም የተሰነካከለውን ሕገ መንግሥት ለዴሞክራሲ ማደላደሉ ሥራ መነሻ ይሆናል ብለን ስላመንን ነው)፡፡ ይህን የአገር መከላከያ ጉዳይ የማዕከላዊው ወይም የፌዴራሉ መንግሥት ብቻ የሚያደርገውን የሥልጣን ክፍፍል ግን አንዱ ብቻውን ሊለውጥው አይችልም፡፡

የመጀመርያውና የሥር መሠረቱ ‹‹ኃጢያት›› የተሠራው ግን ሕግን እንዳሻ የሚነሳና የሚጣል ማድረግ በመቻላችን ብቻ አይደለም፡፡ የተቋማት ግንባታችን በተለይም የመከላከያ ሠራዊቱ ግንባታ ሲጀመር በአንድ ወይም በሌላ ቡድን መዳፍ ውስጥ የወደቀ፣ የትኛውም ዓይነት ዝንባሌና እዚያ ግቢ ውስጥ የሚወድቅና የሚታመን በማድረጋችን ነው፡፡ ለውጡ የመጣው ሽግግሩ የተጀመረው ይህንን ለብዙ ዘመን አገር የለከፈ፣ በተለይም ባለፉት 27 ዓመታት ውስጥ ነውሩን የዘረገፈ ሕመም ለመሻርና ለማዳን ነው፡፡ መንግሥታዊ አውታራትን በተለይም መከላከያን፣ ደኅንነትን፣ ፖሊስን፣ የፍትሕ ተቋማትንና የምርጫ ማስፈጸሚያ አካላትን ከየትኛውም ፓርቲ ወገናዊነትና ደባልነት የፀዱ አድርጎ ለማነፅ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...