የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለግብርና ምርት አቀነባባሪ ኢንዱስትሪዎች የከፈተውን ልዩ የግብይት መስኮትን በይፋ ከፈተ፡፡ አዲስ በተከፈተው መስኮትም 16 አቀነባባሪዎች ወደ ግብይት ሥርዓቱ እንዲገቡ ተደረገ፡፡ በምርት ገበያው የሚገበያዩ ምርቶች ወደ 12 ከፍ አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ኅዳር 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ እንዳደረገው ለግብርና ምርት አቀነባባሪዎች የተዘጋጀው ልዩ መስኮት ኢንዱስትሪዎቹ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አባል ባይሆኑም በግብይት ሥርዓቱ አሠራርና ቴክኖሎጂ በግብዓትነት የሚጠቀሙበትን የጥራት ደረጃው በላቦራቶሪ የተረጋገጠ የአኩሪ አተር ምርት በኤሌክትሮኒክስ የግብይት ሥርዓት አማካይነት የሚገዙበት ነው፡፡ በዚህ የልዩ የግብይት መስኮት በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተመዝግበው ዕውቅና የተሰጣቸው 16 አቀነባባሪዎች ወደ ግብይት ሥርዓቱ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ የልዩ መስኮት አገልግሎቱ በአኩሪ አተር ምርት የተጀመረ ሲሆን፣ ኢንዱስትሪዎቹ በግብይት ሥርዓቱ ሕጋዊ አሠራርና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ሥልጠና ተሰጥቷቸው በኤሌክትሮኒክ የግብይት መድረክ አማካይነት መግዛት የሚችሉበት አሠራር የተፈጠረ መሆኑንም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አስታውቋል፡፡ በቅርቡም ተጨማሪ ኢንዱስትሪዎች ወደ ልዩ የግብይት መስኮት የሚቀላቀሉ ምርቶች እንደሚኖሩ ልዩ መስኮቱን ሥራ በይፋ ያስጀመሩት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ገልጸዋል፡፡
በልዩ የግብይት መስኮት ማገበያየት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ (ከጥቅምት 25 እስከ ኅዳር 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ) ለግብርና ምርት አቀነባባሪዎች ከቀረበው 141,857 ኩንታል አኩሪ አተር ውስጥ 26,455 ኩንታል መገበያየት መቻሉንም ምርት ገበያው አስታውቋል፡፡
በዕለቱ የግብይት ሥርዓቱን የተቀላቀሉ የዥንጉርጉ ቦሎቄና የነጭ የርግብ አተር ግብይት በይፋ መጀመሩም ተበስሯል፡፡ የምርቶቹ ግብይት በምርት ገበያ በኩል መካሄዱ ምርቱ የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝ፣ አርሶ አደሩ በቂ የገበያ መረጃ በማግኘት የመደራደር አቅሙን እንዲያሳድግና ጥራቱን የጠበቀ ምርት ወደ ገበያ እንዲገባ የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል፡፡
የአገሪቱ የተለያዩ ሥነ ምኅዳሮች ለነዚህ ምርቶች ተስማሚ ሲሆኑ በየዓመቱም ዥንጉርጉር ቦሎቄ ወይም ፒንቶቢን ከ435 ሺሕ ኩንታል በላይ፣ ነጭ የርግብ አተር ከ120 ሺሕ ኩንታል በላይ የሚመረቱ ስለመሆኑ የሚገልጸው የምርት ገበያው መረጃ ከዚህ ውስጥ ዥንጉርጉር ቦሎቄ 70 በመቶ ነጭ የርግብ አተር 90 በመቶ ከቤተሰብ ፍጆታ አልፈው ለገበያው የሚቀርቡ ይሆናል፡፡ እነዚህ ምርቶች በዓለም ገበያ የሚፈለጉ ስለመሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በተለይ ህንድ፣ ፓኪስታን፣ ኬንያና ታንዛኒያ ዋነኛ ገዥዎች ናቸው ተብሏል፡፡
ዥንጉርጉር ቦሎቄና ነጭ የርግብ አተር በምርት ገበያው መገበያየት መጀመራቸው በምርት ገበያው የሚገበያዩትን ምርቶች ቁጥር ወደ 12 የሚያሳድግ ይሆናል፡፡
እንደ ምርት ገበያው መረጃ ዥንጉርጉር ቦሎቄ ጥቅል ስያሜ ሆኖ በሥሩ ቀይ በነጭ፣ ነጭ በግራጫ፣ ክሬም በቀይና ነጭ በቀይ፣ እንዲሁም ክሬማማ፣ ቢጫና ጥቁር ቦሎቄዎችን የሚያጠቃልል ነው፡፡ ይህ ምርት በምርት ገበያው ግብይቱ በመጀመሩ በምርት ዘመኑ ዥንጉርጉር ቦሎቄ ምርት እየደረሰ በመሆኑ ወደ ምርት ገበያው እየቀረበ የሚገኝ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ ግብይቱ በይፋ ኅዳር 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ቢጀምርም ከጥቅምት 14 እስከ ኅዳር 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ 7,370 ኩንታል ዥንጉርጉር ቦሎቄ ከአቅራቢዎች ተረክቦ እስከ ኅዳር 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ 4,967 ኩንታል ምርት ማገበያየት መቻሉም ተጠቅሷል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሚጠበቅበትን አገራዊ ኃላፊነት ለመወጣትና ደንበኞቹን ለማገልገል አዳዲስ አሠራሮችን በመቀየስና ያሉትንም በማሻሻል በየጊዜው በለውጥ ሒደት ላይ ይገኛል፤›› የሚለው የምርት ገበያው መረጃ በዚህ ዓመት በቡሌ ሆራና በመቱ አዲስ ያሠራቸውን ሁለት መጋዘኖች እንዲሁም በጎንደር፣ በአዳማና በጂማ የገነባናቸውን የኤሌክትሮኒክ የግብይት ማዕከላት ሥራ እንደሚያስጀምር ገልጿል፡፡ በተጨማሪም በሚዛንና በቴፒ ሁለት ተጨማሪ ቅርንጫፎች እንከፍታለን፡፡ አዲስ በሚከፈቱትና አሁንም በሥራ ላይ ባሉት የኤሌክትሮኒክ የግብይት ማዕከላት አርሶ አደሮችና አቅራቢዎች የምርት ገበያው አባል ሳይሆኑ ምርታቸውን በቀጥታ መሸጥ የሚችሉበትን አሠራር በስፋት ሥራ ላይ እንደሚያውልም አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በ2013 በጀት ዓመት 784 ሺሕ ቶን ምርት ለማገበያየት ያቀደ ሲሆን፣ ከሐምሌ 2012 እስከ ጥቅምት 2013 ባሉት አራት ወራት ውስጥ 142 ሺሕ ቶን ምርት በ9.5 ቢሊዮን ብር ማገበያየት መቻሉንም ጠቅሷል፡፡