Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሁሉም የድርሻውን

የመንግሥት ኃላፊነት ትኩረት ማድረግ ያለበት ሕግ የማስከበር ተግባር ላይ ነው፡፡ ሕግ የማስከበር ሥራው ግን ሀብት የሚያስፈልገውና መስዋዕትነትን የሚጠይቅ ጭምር  መሆኑም ግልጽ ነው፡፡

የህልውና ጉዳይ ነውና ዛሬ መንግሥት ከሕዝብ ጋር ሆኖ በትግራይ ክልል እያካሄደ ያለው ሕግ የማስከበር ተግባር በብዙ መንገድ የሚያስከፍለው ዋጋ ይኖራል፡፡ እንደ አገር ዋጋ ያለው ውጤት የሚኖረው ስለመሆኑ ታምኖበት የተገባበት ነው፡፡ ይህ እንዳይሆን ግን ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ አድማጭ ጠፍቶ እልህ ውስጥ ተገብቶ ወደ እማይፈለገው ጦርነት ተገብቷል፡፡ ያማል፡፡ ለዚህ መብቃቱም ያሳዝናል፡፡

ይህ አልበቃ ብሎ ዜጎች ማንነታቸው እየተለየ ተጨፈጨፉ ሲባል ደግሞ ጉዳዩን ያብሰዋል፡፡ የጭካኔያችን መጠን ልክ ያጣ መሆኑን የምንገነዘብበት ብቻ ሳይሆን እንዲህ ያለውን አረመኔያዊ ተግባር መቋጫ ልናበጅለትም ግድ ይለናል፡፡ ስለዚህ አሁን ያለንበት ሁኔታ በብዙ መልኩ የሚጎዳን ስለመሆኑም ማወቅ ይገባናል፡፡

አገር እንዲህ ባለው ወሳኝ በሚባል ሁኔታ ውስጥ በመሆኗ የመንግሥት ሙሉ ትኩረት በዚህ ጉዳይ ላይ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ዜጎችም መንግሥት ሕግ በማስከበሩ ረገድ እየወሰደ ላለው ዕርምጃ ድጋፋቸውን አሳይተዋል፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱን በሚያበረታቱ ተግባራት ላይ መሆናቸውንም በግልጽ እያየ ነው፡፡

ይህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ይህንኑ ብርቱ ጉዳይ በቅርብ እየተከታተሉ የዜግነት ድርሻቸውንም እየተወጡ ብቻ ሳይሆን ውጤቱንም እየጠበቁ ነው፡፡ ስለዚህ ወቅታዊ አጀንዳችን ይኸው በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለው የሕግ ማስከበር ተግባር ጋር የተያያዘ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

መስዋዕትነትን በመቀነስ ንፁኃን በዚህ እሳት እንዳይለበለቡ በማድረግ ሕግ የማስከበር ሥራውን ለማጠናቀቅ እየተደረገ ያለውም ጥረት ቢሆን ከአንድ ኃላፊነት ከሚሰማው መንግሥት የሚጠበቅ ነው፡፡ ነገም አብረው የሚኖሩ ዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል እየተደረገ ያለው ጥንቃቄ ውጤቱ መልካም እንዲሆን መመኘት አግባብ ነው፡፡ እንዲህ ባለው ጊዜ ሁሉንም ሥራ ለመንግሥትና ለፀጥታ ኃይሉ ብቻ መተው የሌለበት መሆኑ የሚታመን ነው፡፡

እዚህ ላይ መታሰብ ያለበት የመንግሥት ትኩረት በትግራይ ክልል በሚካሄደው ሕግ የማስከበር ሥራ ላይ የተጠመደ መሆኑን በመገንዘብና አጋጣሚውን በመጠቀም፣ በሕገወጥ ተግባራት ላይ የሚሰማሩ አካላት ግን በአገር በጠላትነት የሚፈረጁ፣ ኢኮኖሚያዊ ጦርነት በመክፈት የምንወነጅላቸውም ይሆናሉ፡፡

ገበያው እንዳይረጋጋ በማድረግ አጋጣሚውን ለመጠቀም የሚሹ ስግብግቦችን እጃቸውን እንዲሰበስቡ ማድረግ ካልተቻለ ሌላ ችግር እንዳይፈጠር መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡

ስለዚህ በዚህ ወቅት ራስን በማስቀደም አጋጣሚውን በመጠቀም አደብ እንዲገዙ ተገቢ የሆነ ሥራ መሠራት አለበት፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ገበያው ውስጥ ችግር እንዳይኖርና የግብይት ሥርዓቱ እንዳይበረዝ ማድረግና ግንዛቤ መፍጠርም ያስፈልጋል፡፡ በተለይ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች እጥረት እንዳይፈጠር መረባረብ አንዱ ነው፡፡ በተለይ በከተሞች አካባቢ ያሉ የሸማቾች ማኅበራት ድርሻ ከፍ ያለ በመሆኑ፣ በዚህ ረገድ መንግሥት የሸማቾች ማኅበራት ለኅብረተሰቡ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች በበለጠ ለማቅረብ እያደረገ ያለው ጥረትም የሚበረታታ ነው፡፡

ከሰሞኑ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ለነዚህ የሸማቾች ማኅበራት ፋይናንስ በማቅረብ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶችን ለማቅረብ የሚችል ከሆነ ኃላፊነት ከማይሰማቸው ስግብግብ ነጋዴዎች ይጠበቃል፡፡

የንግዱ ኅብረተሰብ በዚህ ወቅት ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ መሥራታቸው አገርን እንደ መታደግ የሚቆጠር መሆኑ ነው፡፡

ቢቻል ቢቻል የትርፍ ህዳግን አጥብቦ ኅብረተሰቡን ማገልገል ይገባል፡፡ እንዲህ ያለውን ወቅት ጎንበስ ብሎ እርስ በርስ ተደጋግፎ ማሳለፍም ብልህነት ነው፡፡

ቢሆንም ግን አገር ለማተራመስ የሚሠሩ ሸፍጦች በተለያየ መንገድ የሚገለጹ በመሆናቸው በመንግሥት ደረጃ ከሚደረጉ ጥረቶች ባሻገር፣ ኅብረተሰቡም የራሱ የሆነ ሚና ስላለው ያልተገቡ ተግባራትን በመከላከል የበኩሉን ማድረግ አለበት፡፡

አገር የህልውና ዘመቻ ላይ ነኝ እያለች ባለችበት ሰዓት መስገብገብ አያዋጣም፡፡ መተባበርና መተጋገዝ የዚህ ወቅት መለያችን መሆን አለበት፡፡ ህሊናቸውን ሸጠው ለሥራ ያደሩ እዚህም እዚያም አይጠፉምና እነሱን ማጋለጥ ተገቢ ይሆናል፡፡

አንዳንዶች ከአገር ራሳቸውን አስቀድመው አጋጣሚውን በመጠቀም የሚፈጽሙት ሸፍጥ መገለጫዎቹ ብዙ የመሆኑን ያህል፣ በዚያው ልክ መንቃት ተገቢ ይሆናል፡፡  ሕገወጥ የብር ኖቶችን በማተም ኢኮኖሚው ላይ ጫና ለመፍጠር የሚደረጉ መፍጨርጨሮችም የዚሁ ሸፍጥ አካል ናቸው፡፡ አዲሱን የብር ኖት አስመስለው በማተም ገበያ ውስጥ ለማሠራጨት የሞከሩ ግለሰቦች ከሰሞኑ ስለመያዛቸው ስንሰማ፣ የአንዳንዶች ስግብግብነትና ለአገር ደንታቢስነትን የሚያሳይ ነውና በዚህ ወቅት አገርንና ሕዝብን የሚጎዳ ተግባር ላይ የሚሰማራ ሁሉ ብርቱ የሆነ ዕርምጃ እንዲወሰድበት  ማድረግ ተገቢ ይሆናል፡፡

መንግሥት እያደረገ ያለውን ሕግ የማስከበር ሥራ እንደግፋለን ከተባለ አንዱ ማሳያ ሁሉም በያለበት በአግባቡ ኃላፊነቱን ሲወጣ ነው፡፡ ዛሬ እያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ ሥራውን በአግባቡ ካልሠራ፣ እንደ አገር ጉዳት እያደረሱ ነውና ሕገወጦችን ማጥራት የሚያስፈልግበት ወቅት ነው፡፡ ለሌሎች ማሰብም ግድ የሚልበት በመሆኑ እንዲህ ያሉ ወቅቶችን በመተሳሰብና በመረዳዳት ማሳለፍ ራስንም አገርንም መጥቀም ነው፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት