Sunday, June 16, 2024

ዘመኑን የማይመጥን አስተሳሰብ ከፖለቲካ ምኅዳሩ ውስጥ ይወገድ!

ኢትዮጵያን ለዓመታት ለአላስፈላጊ ውዝግቦችና ግጭቶች ከሚዳርጓት መሠረታዊ ችግሮች መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሰው፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ ባህል ዘመኑ ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ ጋር አለመመጣጠኑ ነው፡፡ ከግለሰባዊ አቋም እስከ ቡድናዊ ፍላጎት የሚስተዋሉ ወቅትን የማይዋጁ መስተጋብሮች የጋራ የሆነ አማካይ ከመፈለግ ይልቅ፣ ለተካረሩ ጭቅጭቆችና ትንቅንቆች በር እየከፈቱ በአገር ህልውና ላይ አደጋ ሲጋብዙ ኖረዋል፡፡ አብዛኞቹ ብሔርተኛ ድርጅቶችና ፖለቲከኞች ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያላቸው ዕሳቤ በመርህ ስለማይመራ፣ ብዙውን ጊዜያቸውን የሚያባክኑት ተፎካካሪያቸውን ለማጥፋት እንጂ ተሽለው ለመገኘት አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት ለሰብዓዊና ለዴሞክራሲያዊ መብቶች ደንታ የላቸውም፡፡ ለሐሳብ ልዕልና ቦታ አይሰጡም፡፡ ተፎካካሪነትን የለየለት ጠላትነት በማድረግ ለቂም፣ ለጥላቻና ለመጠፋፋት መንገዱን ያመቻቻሉ፡፡ ይህ ሥር የሰደደ በሽታ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ ኢትዮጵያዊያን ለሞት፣ ለእስራት፣ ለሥቃይ፣ ለእንግልትና ለስደት ተዳርገዋል፡፡ ይህ ሁሉ ፈተና አልበቃ ብሎ በየጊዜው ግጭት እየተቀሰቀሰ አገር የከሰረ ፖለቲካ ማወራረጃ ሆናለች፡፡ በውይይትና በድርድር ሊፈቱ የሚገባቸው ችግሮች፣ በጀብደኞች ምክንያት ኢትዮጵያን የደም ምድር እያደረጓት ነው፡፡

የቴክኖሎጂ ምጥቀት እጅግ አስደማሚ በሆነበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን በተቻለ ፍጥነት የበረከቱ ተቋዳሽ በመሆን ለዕድገት መረባረብ ሲገባ፣ በወጣት ሀብት የታደለች አገርን ልጆች በትምህርት ማነፅ እየተቻለ፣ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ የሚችሉ በርካታ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እያሉ፣ አገሩን ከሠለጠኑት አገሮች ተርታ ለማሠለፍ ትልቅ ራዕይና ፍላጎት ያለው ትውልድ ምን ላበርክት እያለና በአጠቃላይ ከድህነት ለመውጣት የሚያስችሉ በርካታ አማራጮች መኖራቸው እየታወቀ የአጥፍቶ መጥፋት ፖለቲካ ምን ይጠቅማል? ኢትዮጵያን የምታህል ትልቅ የጋራ አገር በስምምነት የነፃነትና የእኩልነት ምድር ማድረግ እየተቻለ፣ በየቦታው የክልል አጥር እየሠሩ ትንንሽ ጎጆዎች ለመቀለስ የሚደረገው የብሔርተኝነት ፉክክር ግቡ ምን ይሆን? በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የብሔራዊ መግባባት መድረኮችን እየፈጠሩ ለኢትዮጵያ ዕድገት መመካከር ሲቻል፣ የጉልበት አማራጭ ብቻ እየተፈለገ ግጭት መቀስቀስና አገር ማተራመስ ምን የሚሉት ዕብደት ነው? የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ሁሉን አሳታፊና መደላድሉ የተመቻቸ እንዲሆን የራስን አስተዋጽኦ ማድረግ ሲገባ፣ እኔ ብቻ እንደፈለግኩ የምፈነጭበት ካልሆነ በሚል አሮጌ አስተሳሰብ አገርን ማሸበር ወንጀል እንደሆነ አይታወቅም?

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ዘመኑ የሚጠይቀውን ዕውቀት፣ ጥበብ፣ ሞራል፣ መርህና አስተሳሰብ የሚመጥኑ ልሂቃን ሊኖሩት ይገባል፡፡ ልሂቃኑ የአገር ፍቅር ስሜት፣ ጨዋነት፣ አስተዋይነትና ትዕግሥት መላበስ ይኖርባቸዋል፡፡ ከጠባብ ቡድናዊ ፍላጎት በላይ ለአገር ህልውና፣ ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት፣ ለሕግ የበላይነት መከበር፣ ለሰብዓዊና ዴሞክራዊያዊ መብቶች መረጋገጥና ለመሳሰሉት በጎ ተግባራት የሚተጉ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ተፎካካሪን ማክበር፣ ሐሳቡ እንዲደመጥ ጠበቃ መሆን፣ በሕዝብ ድምፅ ለመዳኘት ዝግጁ መሆን፣ የሕዝቡን የጋራ ማኅበራዊ እሴቶች ማክበርና ሌሎች ገንቢ ተግባራትን ማክበር አለባቸው፡፡ ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎችም መሠረታዊና አስፈላጊ ጉዳዮች ራስንም ሆነ ድርጅትን ሳይገሩ፣ በሕዝብ ስም መማልም ሆነ መነገድ ለዚህ ዘመን አይመጥንም፡፡ በሕዝብ ስም የሚነግዱ ምን ዓይነት አስከፊ ድርጊቶችን እየፈጸሙ እንደሆነ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነጋሪ እንደማያስፈልገው እየተከናወኑ ያሉ አደገኛ ነገሮች ከበቂ በላይ ይናገራሉ፡፡ የገዛ ኃጢያታቸው የሚያሳድዳቸው በሕዝብ ስም የፈጠሩት አደገኛ ትርምስም በግልጽ እየታየ ነው፡፡ ለዘመናት በቂምና በጥላቻ የታጨቀ አሮጌ አስተሳሰብን መለወጥ ባልቻሉ ግለሰቦች ምክንያት፣ ኢትዮጵያዊያንና አገራቸው የገቡበት ፈተና ራሱ ምስክር ነው፡፡

ኢትዮጵያ የበርካታ ማንነቶች፣ እምነቶች፣ ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ ወጎች፣ ልምዶችና የመሳሰሉት ባለቤት ናት፡፡ እነዚህ ልዩነቶች ጌጥ ሆነው ኢትዮጵያዊያን በርካታ የሚጋሩዋቸው የጋራ ጉዳዮች አሉዋቸው፡፡ እነዚህ የጋራ ጉዳዮቻቸው ደግሞ ጠንካራ ማኅበራዊ ትስስሮችን በመፍጠር ተጋብተው እንዲዋለዱ ጭምር ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በትውልዶች ቅብብል እዚህ የደረሰችውም፣ በኢትዮጵያዊያን አስተዋይነት፣ መተሳሰብና ፍቅር መሆኑን ማንም ሊክድ አይችልም፡፡ በዚህ ወቅት እንኳ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸውና ለወገኖቻቸው እያሳዩ ያሉት ተቆርቋሪነት ህያው ምስክር ነው፡፡ በትግራይ ክልል እየተካሄደ ባለው ዘመቻ ለወገኖቻቸው የትግራይ ተወላጆች የዕርዳታ እጃቸውን ከመዘርጋት በተጨማሪ፣ እንደ እምነታቸው በፀሎታቸው ጭምር እያሰቧቸው ነው፡፡ ይህንን የመሰለ እርስ በርሱ የተጋመደን ሕዝብ ጽንፈኛ ብሔርተኞች ለመለያየት ያልሠሩት ደባ የለም፡፡ የንፁኃንን ደም እያፈሰሱ አንዱን ብሔር በሌላው ላይ ለማነሳሳት አሲረዋል፡፡ የታሪካዊ ጠላቶች ተላላኪ በመሆን ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚችሉትን ሁሉ ሞክረዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ ከጀመረችው የልማት ጉዞ የሚያስተጓጉል አደገኛ ምዕራፍ ውስጥ እንድትገባ አድርገዋል፡፡ ዘመኑን በማይመጥኑ ድርጊቶች ሳቢያ ነው ኢትዮጵያ እየተበደለች ያለችው፡፡

ችግሮቹ ቢዘረዘሩ በርካታ መሆናቸው የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን የዘመኑ የፖለቲካ ልሂቃንም ሆኑ ሌሎች የአገር ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ ወገኖች፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ለዓመታት የተንሰራፋው ደዌ ከሥሩ እንዲነቀል የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት አለባቸው፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የሚያስችሉ መፍትሔዎች ላይ ማተኮር ሲኖርባቸው፣ ከዚያ በፊት ግን መሠረታዊ የሚባሉት ችግሮች መታወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ራሳቸውን ከሴራና ከሸፍጥ አስተሳሰብ ማፅዳት እንዳለባቸው፣ ለውይይትና ለድርድር ቅድሚያ የሚሰጥ ዓላማ ሊኖራቸው እንደሚገባ፣ ከሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ጀርባ ጉልበተኝነትን ማስወገድ እንደሚያስፈልግ፣ ለሕዝብ ሰላምና ለአገር ደኅንነት ቅድሚያ መስጠት ግዴታ መሆኑን የሚያስገነዝብ መርህ መከተልና የመሳሰሉት ሊታሰብባቸው የግድ ይላል፡፡ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምኅዳር የሚፈልገውን ጨዋነትና የጨዋታ ሕግ ማበላሸት በመለመዱ ነው፣ ኢትዮጵያ በብሔርተኛ ጉልበተኞችና በሥርዓተ አልበኞች ፍዳዋን ስታይ የኖረችው፡፡ ኢትዮጵያዊያን መብቶቻቸው ተገፈው በግፍ ሲገደሉ፣ ሥቃይ ሲደርስባቸውና በገዛ አገራቸው ባይተዋር ሲደረጉ የቆዩት በጠመንጃ በሚያመልኩ ነውጠኞች ምክንያት ነው፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ ኋላቀር አስተሳሰብ በፍጥነት መላቀቅ ይገባል፡፡

ዘመኑን የማይመጥን አሮጌ አስተሳሰብ ለአገር እንደማይበጅ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ ዘመኑን የሚዋጅ አስተሳሰብ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች አማካይነት አገር ለማሳደግ ሲተጋ፣ አሮጌው ግን አካሉም አስተሳሰቡም ያለው የጠመንጃ ቃታ ላይ ነው፡፡ ለሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ምኅዳር መፈጠር ደንታ የለውም፡፡ ከቡድናዊ ስብስብ በላይ የአገርና የሕዝብ ጉዳይ ስለመኖራቸው አይጨነቅም፡፡ ለግልጽነት፣ ለኃላፊነትና ለተጠያቂነት መርህ ስለማይገዛ ዝርፊያና ውድመት መታወቂያዎቹ ናቸው፡፡ ዓላማን ለማስፈጸም ጉልበት ዋነኛ ተመራጭ ሥልቱ ነው፡፡ ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች፣ ለሕግ የበላይነት መከበር፣ ለጋራ ብሔራዊ እሴቶች ክብር፣ ለሞራል፣ ለሥነ ምግባርና ለህሊና ዳኝነት ዋጋ አይሰጥም፡፡ በአጠቃላይ ለሰብዓዊ ፍጡራን ርህራሔና አዘኔታ ስለሌለው፣ ከቡድኑ ፍላጎት ተቃራኒ የመሰለውን ከማጥፋትና ከማውደም አይመለስም፡፡ ይህም ኢትዮጵያ ውስጥ ከበቂ በላይ ታይቷል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከአሁን በኋላ ቦታ ሊሰጠው የማይገባው ይህ ዓይነቱ ዘመኑን የማይዋጅ አስተሳሰብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በሴረኝነት፣ በጥላቻ፣ በቂመኝነትና በጭካኔ ጥርሳቸውን ከነቀሉ የአሮጌ አስተሳሰብ ባለቤቶች መላቀቅ አለባት፡፡ ዘመኑን የማይመጥን  አስተሳሰብ ከፖለቲካ ምኅዳሩ ውስጥ እንዲወገድ ኢትዮጵያዊያን መጠንከር ይኖርባቸዋል!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...

የዘመኑ ትውልድ ለአገሩ ያለውን ፋይዳ ይመርምር!

በዚህ በሠለጠነ ዘመን ኢትዮጵያን የሚያስፈልጓት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከብዙዎቹ በጣም ጥቂቱን አንስተን ብንነጋገርባቸው ይጠቅሙ ይሆናል እንጂ አይጎዱም፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ብዙኃኑ ሕዝቧ ያስፈልጓቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ...