የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወቅታዊ ሁኔታ ላይ በከተማው ከሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ጋር በተደረገ ውይይት፣ በትግራይ፣ ክልል እየተወሰደ ያለው ሕግ የማስከበር ዕርምጃ ላይ ሥጋታቸውን ገለጹ፡፡
የትግራይ ክልል ተወላጆች ሥጋታቸውን የገለጹት፣ ኅዳር 18 ቀን 2013 ዓ.ም. በቂርቆስ ክፍለ ከተማ አዳራሽ በተደረገው ውይይት ፕሮግራም ላይ ነው፡፡
አቶ አክሊሉ ገብረሥላሴ የተባሉ ነዋሪ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት፣ መንግሥት በትግራይ ክልል በሚያደርገው ሕግ የማስከበር ዘመቻ፣ የአየር ላይ ድብደባ ሲያደርግ ንፁኃን ዜጎችን እንዳይጎዳ የሚል ሥጋት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል የባንክ አገልግሎት መቋረጡና የስልክ መስመር በመቋረጡ እዚያ የሚገኙ ቤተሰቦቻቸው በምን ሁኔታ እንደሚገኙ ባለማወቃቸው ሥጋት እንደገባቸው ተናግረዋል፡፡
ሁሉም ማኅበረሰብ የትግራይ ሕዝብንና ጥቂት የሆኑ የሕወሓት አጥፊ አመራሮች የተለያዩ መሆኑን መዘንጋት እንደሌለበት አቶ አክሊሉ ተናግረዋል፡፡ ወጣት ሀብታሙ ገብረ ኪዳን በበኩሉ፣ ከለውጡ በኋላ በሚደረጉ የሴፍቲ ኔት ድጋፍ የክልሉ ተወላጆች የሚገፉበት ሁኔታ መኖሩን ገልጾ፣ መስተካከል እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡በትግራይ የሚገኘው የሕወሓት ቡድን ከሕዝቡ ሥር ወጥቶ እጅ እንዲሰጥ ጥሪ ቀርቧል፡፡
በየአካባቢው የሚገኙ አንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍሎች በክልሉ ተወላጆች ላይ የሚደርሰው ተፅዕኖ የማይገባ መሆኑን የገለጸው ወጣት ሀብታሙ፣ ይህ አካሄድ ተገቢነት የለውም ብሏል፡፡
በሌላ በኩል በሚዲያዎች የሚተላለፉ መረጃዎች አወዛጋቢ መሆናቸውን የጠቆሙት ተወያዮቹ፣ መሬት ላይ ያለው ነገር ለሕዝብ ቢቀርብ የተሻለ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የብልፅግና ፓርቲ ቢሮ ኃላፊ አቶ መለሰ ዓለሙ በበኩላቸው፣ የሕወሓት አጥፊ ቡድን ሕዝቡን የማይመጥን መሆኑን በመጠቆም፣ የሕግ ማስከበር ሥርዓቱ እየተደረገ ያለው፣ መንግሥት የሕዝብን ደኅንነትና ሰላም ለማስከበር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል የፌዴራል መንግሥት ወደ ሕግ ማስበር ዕርምጃ የገባው ተገዶ መሆኑን በመግለጽ፣ ሕወሓት በትግራይ ሕዝብም ላይ ከፍተኛ በደል ማድረሱንም ተናግረዋል፡፡
በተደጋጋሚ የተደረገለትን ሰላማዊ ጥሪ በመርገጥ አምባገነንነቱን መቀጠሉን በመግለጽ፣ አሁን የሚደርገው ዘመቻ አገርንና ሕዝብን ለማደን መሆኑን አቶ መለሰ ተናግረዋል፡፡ ጥቅምት 24 ቀን 2013 በሰሜን ዕዝ ላይ የሕወሓት ቡድን ባደረገው ጥቃት የተጀመረው ሕግ ማስከበር ሒደት ሦስት ሳምንት ማለፉ ይታወቃል፡፡ የሕወሓት ቡድን እጁን እንዲሰጥ የተሰጠው 72 ሰዓት በመጠናቀቁ የመጨረሻ የሕግ ማስከበር ዕርምጃ መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡