Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየመከላከያ ሠራዊት የመቐለ ከተማን ተቆጣጠረ

የመከላከያ ሠራዊት የመቐለ ከተማን ተቆጣጠረ

ቀን:

ለአፍሪካ ኅብረት ልዩ ልዑካን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ተሰጠ

 

በትግራይ ክልል ከጥቅምት 24 ቀን 2013 .. ምሽት ጀምሮ 25 ቀናት በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ቡድንና በመከላከያ ሠራዊቱ መካከል ሲደረግ የሰነበተው ውጊያ፣ ቅዳሜ ኅዳር 19 ቀን  ከሰዓት በኋላ  የመከላከያ ሠራዊቱ  የክልሉ ዋና ከተማ  መቐለን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ(/) እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ አረጋግጠዋል።

- Advertisement -

መከላከያ ሠራዊቱ ባካሄደው ዘመቻ ንጹኃን ዜጎች ዒላማ ሳይሆኑና ቅርሶች ሳይጎዱ መቐለ ለመግባት መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ  አስታውቀዋል።

ሠራዊቱ   የመቐለ ከተማ ነዋሪ ላይ ጉዳት ሳይደርስ እንዴት ከተማዋን መቆጣጠር ይቻላል በሚለው ላይ ኅዳር 18 ቀን ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን በመግለጫቸው ያስታወሱት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ  ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ፣ በዕቅዱ መሠረት ከተማዋን መቆጣጠር መቻሉን ገልጸዋል።

የመከላከያ ሠራዊቱ  በደረሰባቸው አካባቢዎች ሁሉ የትግራይ ሕዝብ ለአገሩ ያለውን ፍቅርና ለመከላከያ ሠራዊቱ ያለውን ክብር ማሳየቱንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይገልጹ አላለፉም።

የሕወሓት ቡድን ካስታጠቃቸው ጥቂት የክፋት ኃይሎች ውጭ ያለው የትግራይ ሕዝብ መቐለ እስኪገባ ድረስ ለመከላከያ ሠራዊቱ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ሁሉ በማድረጉ የሠራዊቱን ድልና የቡድኑን ሽንፈት አፋጥኖታል፤ብለዋል።

ቡድኑ በየትኛውም መመዘኛ ለትግራይ ሕዝብ አይመጥነውምያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣

ለድጋፉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የሕወሓት ቡድን በሸሸበት ከተማና አካባቢ ሁሉ የጤና ተቋማትን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ድልድዮችን፣ መንገዶችን፣ መሥሪያ ቤቶችን አውድሞ ሄዷል፤ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ያፈረሳቸውን መሠረተ ልማቶች በፍጥነት በመገንባት  ሕዝቡ ወደ ሰላማዊ ኑሮው እንዲመለስ ለማድረግ የተቻለው ሁሉ እንደሚደረግ ቃል ገብተዋል።

በተያያዘ ዜና የመከላከያ ሠራዊት ኅብረት ሥልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተና ጄኔራል ሀሰን ኢብራሂም ዓርብ ኅዳር 18 ቀን 2018 ዓ.ም ምሽት በሰጡት መግለጫ፣ የመከላከያ ሰራዊት ሀውዜን፣ አልነጃሺ፣ አዲቀየህ፣ ማይመሳኖንና ውቅሮን ከሕወሓት ታጣቂ ኃይል ሙሉ በሙሉ ነፃ ማድረጉን አረጋግጠዋል።

የሕግ ማስከበር ዘመቻው በውጤታማነት መከናወኑን ያስታወቁት ጄኔራል መኮንኑ በዓድዋ ግንባር የተንቀሳቀሰው ሠራዊት ሀውዜንን፣ አብርሃ ወአፅብሃንና ውቅሮን የተቆጣጠረ መሆኑን፣ አጉላን ደግሞ በግማሽ ቀን መያዙን ገልጸዋል። በሁለተኛው ግንባር ማለትም በአዲግራት በኩል ሠራዊቱ ሰንቀጣንና አል ነጃሺን በመቆጣጠር ውቅሮን መያዙን በመግለጫው አስረድተዋል።

በሦስተኛው የራያ ግንባር የሚገኘው ሠራዊት አዲቀይህን ከያዘ በኋላ ሔዋነን በመቆጣጠር የትግራይ ልዩ ኃይልን ሁሉንም ምሽጎች ደርምሶ ወደፊት መገስገሱን አስታውቀዋል። በአጉላን በኩል መንገድ ለመዝጋት ቢሞክርም እንዳልተሳካለትና ወደኋላ ማፈግፈጉን ጠቁመው፣ አሁን ግን መቀሌ ከተማ ብቻ መቅረቱንና በጥቂት ቀናት ወስጥ ዘመቻው እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል፡፡

የሦስተኛው ምዕራፍ ዘመቻ ዓላማ የሕወሓት አመራሮችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ለሕግ ማቅረብ መሆኑን ያስታወሱት ሌተና ጄኔራል ሀሰን፣ ሠራዊቱ ነፃ ባወጣባቸው ሥፍራዎች ሁሉ የትግራይ ሕዝብ በሠራዊቱ ላይ አልተኮሰም ብለዋል፡፡ ይህም የሕወሓት አመራሮችና ሕዝቡ አንድ አለመሆናቸውን ማረጋገጫ ነው ሲሉ አክለው፣ ሕዝቡ እንዲያውም ለሠራዊቱ ወገንተኝነት አሳይቷል ሲሉ ሁኔታውን አስረድተዋል፡፡

የሕወሓት አመራሮችና ቡድናቸው በፕሮፓጋንዳ ጭምር እያፈገፈጉ መሄዳቸው ሽንፈታቸውን እያረጋገጠ እንደሆነም ጄኔራል ሀሰን ጠቁመዋል።

የደቡብ ግንባር የበላይ አዛዥ ሌተና ጄኔራል ባጫ ደበሌ ከሥፍራው በሰጡት ሌላ መግለጫ፣ ከባድ ምት ያረፈበት የትግራይ ልዩ ወደ አዲጉደም እንደሸሸ አስረድተዋል፡፡ ሠራዊቱ አካባቢውን በተቆጣጠረበት ወቅት ልዩ ኃይሉ ይጠቀምባቸው የነበሩ ስድስት ታንኮች፣ ሁለት ዙ23 የአየር መቃወሚያዎችና በርካታ መሣሪያዎች መደምሰሳቸውን አስታውቀዋል፡፡ ሠራዊቱ አስቸጋሪ መልክዓ ምድር በብቃት በማለፍ ከፊቱ የቆመውን ኃይል መደምሰሱን አስረድተዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥታቸው በሕወሓት አመራር ከሁለት ዓመት በላይ ሲከናወኑ የቆዩትን ፀብ አጫሪነትና አገር የማፍረስ እንቅስቃሴዎች በከፍተኛ ሆደ ሰፊነትና ትዕግሥት ማሳለፉን፣ ለበርካታ ጊዜያትም ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መድከሙን፣ ነገር ግን ይህም አልበቃ ብሎ በሰሜን ዕዝ የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈጸመው ጥቃት በአገሪቱ ሕግ መሠረት ከፍተኛ የአገር ክህደት ወንጀል በመሆኑ ሕገ መንግሥታዊውን ሥርዓት ለማስከበር ኃላፊነቱ እንደሆነ አስታወቁ፡፡

በተጨማሪም ዓርብ ኅዳር 18 ቀን 2018 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበርና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ልዩ ልዑክ ተቀብለው ሲያነጋግሩ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት፡፡ የላይቤሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኢሊየን ጆንሰን ሲሪሊፍ፣ የሞዛምቢክ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጆአኪም ቺሳኖ፣ እንዲህም የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ካግሌማ ሞቴላንተ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በትግራይ ክልል እየተካሄደ ባለው ዘመቻ ላይ ለመነጋገር አዲስ አበባ የመጡት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ‹‹ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ›› በሚለው መርህ መሠረት ልዩ ልዑኩን በመላካቸውና አንጋፋዎቹ የልዑካን አባላትም ሥጋት ገብቷቸው እዚህ ድረስ በመምጣታቸው አመሥግነው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በሕገ መንግሥቱ የተሰጠውን ሕግ የማስከበር ኃላፊነት እየተወጣ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ይህንን ኃላፊነት አለመወጣት ግን ኢትዮጵያን ትልቅ ዋጋ ያስከፍላታል ሲሉ ማስታወቃቸውን፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ካወጣው መግለጫ መረዳት ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...