ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ ነገ ሰኞ ህዳር 21ቀን 2013 ዓም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ እንደሚሰጡ ታወቀ።
ሪፖርተር ከምክር ቤቱ ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ምክር ቤቱ ህዳር 21 ቀን 2013 ዓም ልዩ ስብሰባ እንደሚያካሂድና በዚህም ስብሰባው ላይ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ተገኝተው በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከምክር ቤቱ አባላት ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ይሰጣሉ።
በዚህም በአገሪቱ በተለይም በትግራይ ክልል እየተካሄደ የሚገኘው “የህግ ማስከበር ዘመቻ” የደረሰበትን አፈጻጸም ፤ በተመሳሳይም በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተካሄዱና እየተካሄዱ የሚገኙ የህግ ማስከበር ሂደቶችን በተመለከተ ማብራሪያ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የፌራል መንግስት በትግራይ ክልል እንዲከናወን ያዘዘው “የህግ ማስከበር ዘመቻ” በተጀመረ በ25ኛ ቀኑ ማለትም ቅዳሜ ህዳር 19 ቀን 2013 ዓም ላይ የአገር መከላለከያ ሠራዊት መቐለን እንደተቆጣጠረ የሠራዊቱ ዋና አዛዥ ኤታማዦር ሹም ጄንራል ብርሃኑ ጁላ መግለጻቸው ይታወቃል።