Sunday, June 23, 2024

ኢትዮጵያ በፍጥነት ፊቷን ወደ ልማት ታዙር!

ኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋቷ በፍጥነት ተመልሶ ፊቷን ወደ ልማትና ዕድገት ማዞር አለባት፡፡ ዓለም የሚያከብራት ከተመፅዋችነት ተላቃ ራሷን ስትል ብቻ ነው፡፡ ጦርነት ክቡር የሆነውን የሰው ሕይወት ከመቅጠፉና የአገር አንጡራ ሀብት ከማውደሙ ባሻገር፣ በአገር ገጽታ ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ዕይታ ራሱን የቻለ ጉዳት አለው፡፡ የአገር ሉዓላዊነትንና ህልውናን ለአደጋ በማጋለጥ ሊያስከትል የሚችለው ጥፋት በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ለዘመናት አብሮ የኖረን ሕዝብ እርስ በርሱ ለማቃረንና ሌላ ግጭት ለመቀስቀስ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊኖራት የሚገባውን ተፅዕኖ በመሸርሸር፣ ልታገኝ የሚገባትን ጥቅምና ክብር ጭምር ሊያሳጣት የሚችል ነው፡፡ ጥንታዊ የሰው ዘር መገኛ በሆነችው ኢትዮጵያ ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ተፈጽሞ የጅምላ መቃብሮች መገኘታቸው፣ ለድርጊቶቹ ፈጻሚዎችና ደጋፊዎቻቸው ምንም ባይመስላቸውም የኢትዮጵያዊያንን ልብ ይሰብራሉ፡፡ ጦርነትን አማራጭ ያደረጉና በመጨረሻም ሽንፈትን የተጎነጩ ለድርጊታቸው ውኃ የማይቋጥር ምክንያት ቢደረድሩም፣ በሰው ልጆች ላይ ያስከተሉት መከራና በአገር ኢኮኖሚ ላይ ያደረሱት ጥፋት እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያን ከዚህ ዓይነቱ ማጥ ውስጥ በፍጥነት በመውጣትና ፊቷን ወደ ልማት በመመለስ፣ ኢትዮጵያዊያን በእኩልነትና በነፃነት የሚኖሩባት ምድር ማድረግ የግድ ነው፡፡

ኢትዮጵያ መልማት የምትችለው በዕርዳታ ሳይሆን በዜጎቿ ድካምና ጥረት ነው፡፡ በምግብ ራስን ከመቻል አልፎ በዕድገት ለመገስገስ በጋራ ታጥቆ መነሳት የግድ ነው፡፡ ለአገር ልማትና ዕድገት የሚደረገው ጉዞ የሚጀመረውም የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብን ተሳትፎና ውክልና በማረጋገጥ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ለአገር ዕድገት እናስባለን የሚሉ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያንም ሆኑ ፖለቲከኞች፣ ኢትዮጵያን በፍፁም ወደ ግጭት የማያስገባ ሰላማዊ የፖለቲካ ሒደት በተግባር እንዲጀመር ግፊት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሰላማዊና የጉልበት መንገድን እየቀላቀሉ ለማወናበድ የሚሞክሩ ግለሰቦችም ሆነ ስብስቦች በቃችሁ ሊባሉ ይገባል፡፡ በአራቱም ማዕዘናት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን አሁንም ከአገራቸው ህልውና የሚቀድም ምንም ነገር እንደሌለ በግልጽ እያስታወቁ፣ ኢትዮጵያን መልሶ የተለመደው ችግር ውስጥ ለመክተት መሞከር ስለማያዋጣ ይታሰብበት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአሁን በኋላ የብልሹ አሠራሮችና ጊዜ ያለፈባቸው የፖለቲካዊ ዕሳቤዎች ሰለባ ሊሆን ስለማይገባው፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ ለጋራ ለብሔራዊ ጉዳዮች ስምምነት እንዲኖር ማገዝ ይኖርባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከአሻጥርና ከሴራ አስተሳሰብ ተላቃ ወደ ልማት ፊቷን ማዞር የሚኖርባት፣ እስካሁን የተመጣበት መንገድ ለአገር የፈየደው ምንም ነገር ስለሌለ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ልዩነቶቻቸውን ይዘው በአንድ ድምፅ ለጋራ ልማትና ዕድገት መቆም እንደሚችሉ ማሳየት አለባቸው፡፡ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት በሥልጣኔ ወደፊት መራመድ እንጂ እርስ በርስ መፋጀት አይደለም፡፡

ኢትዮጵያን ሰላም ከመንሳት በተጨማሪ መንግሥታዊ ተቋማትን ማዳከም፣ የአገር መከላከያንና የፀጥታ ዘርፉን የአፈና መሣሪያ ማድረግ፣ የፍትሕ ተቋማትን ማሽመድመድ፣ የፋይናንስ ተቋማትን በቁጥጥር ሥር አውሎ ዝርፊያ መፈጸም፣ የገቢዎችንና የጉምሩክ ተቋማትን መጠቃቀሚያ ማድረግ፣ በአጠቃላይ የአገር ኢኮኖሚን የሚያመሰቃቅሉ ድርጊቶችን ማከናወንና የመሳሰሉት የጉልበተኞችና የሥርዓተ አልበኞች የጥፋት ተግባራት ናቸው፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ የአምባገነኖች መፈንጫ ሲሆን አገር ትወድማለች እንጂ አታድግም፡፡ ፖለቲከኞችም ሆኑ ተከታዮቻቸው እንዲህ ዓይነት ነውረኛ ድርጊት በኢትዮጵያ እንዳይደገም ይጠንቀቁ፡፡ ጥያቄ ሲኖራቸው በሕጋዊ መንገድ ለሚመለከተው አካል ያሳውቁ፡፡ ይህ አካል አልሰማ ሲል የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት ለሆነው ለኢትዮጵያ ሕዝብ በማስረጃ አስደግፈው በማቅረብ ያጋልጡት፡፡ ኢትዮጵያ የሰላማዊ ፖለቲካ ፉክክር እንዲካሄድባት ለሚያግዙ መደላድሎች እስከ መጨረሻው ጥግ አስተዋፅኦ ያበርክቱ፡፡ የፖለቲካ ፉክክር ለማድረግ የሚያስችል አጀንዳ የሌላቸው ራሳቸውን ገለል ቢያደርጉ ይመረጣል፡፡ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ የፖለቲካ ምኅዳር ነው፡፡ ይህንን ምኅዳር ለመፍጠር ደግሞ የሁሉንም ሰላማዊ የፖለቲካ ተፎካካሪዎች ስምምነት ይፈልጋል፡፡ ለዚህ ስምምነት ተገዥ መሆን የማይፈልጉ ገለል ማለት አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አገሩ ወደ ልማትና ዕድገት መገስገስ እንዳለባት ይፈልጋልና፡፡

ማንም ሆነ ማን ኢትዮጵያን ከዓላማውና ከፍላጎቱ በታች አድርጎ ማተረማመስ እንደማይችል ብሔራዊ መግባባት ሊፈጠር ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብ ሕይወትና በአገሩ ህልውና ላይ መቆመር ማክተም አለበት፡፡ በአቋራጭ ለሚገኝ ሥልጣንና ለሚያስገኘው ጥቅማ ጥቅም ብቻ ሲባል፣ ኢትዮጵያ የሥርዓተ አልበኞች መፈንጫ መሆን የለባትም፡፡ ሥልጣን የሚያዘው በሕጋዊ፣ በሰላማዊና በፍትሐዊ ምርጫ ብቻ መሆን ይኖርበታል፡፡ ለዚህም መደላድሉ በሚገባ እንዲመቻች ለማድረግ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ትብብር አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህ ቁመና ላይ መገኘት ሳይቻል ፖለቲከኛ ነኝ ብሎ መኩራራት አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያ ከአስመራሪው ድህነት ውስጥ መውጣት አለባት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም ለዚህ ዓላማ በአንድነት እንዲሠለፍ የራስን ድርሻ ለመወጣት ጥረት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ የድህነት አረንቋ ውስጥ ተሁኖ እርስ በርስ እየተባሉ የባዕዳን ተመፅዋች መሆን፣ ሉዓላዊነትን አሳልፎ ለመስጠት ያገለግላል፡፡ አንድ አገር በዓለም አደባባይ አንገቷን ቀና አድርጋ በኩራት የምትራመደው፣ ራሷን ችላ ከተመፅዋችነት ስትላቀቅና ሉዓላዊነቷን ባለማስደፈር ነው፡፡ ኢትዮጵያ በኩራት በዓለም የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ኮሪደሮች መንቀሳቀስ የምትችለው፣ በጠንካራ መሠረት ላይ ለመሆን የሚያስችላት ልማትና ዕድገት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ይህንን አቅም ለማግኘት ግን ውስጣዊ ሰላምና ስምምነት የግድ ይሆናል፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አሁንም ድረስ መፍትሔ ያልተገኘለት ትልቁ በሽታ አለመተማመን ነው፡፡ ለመተማመን ግድ መቀራረብ ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ ዙሪያ መለስ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር የሚያስችሉ ብሔራዊ መድረኮች መፈጠር አለባቸው፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶቹም ሆኑ መሪዎቻቸው ለግልጽነት፣ ለተጠያቂነትና ለኃላፊነት መርህ መገዛት አለባቸው፡፡ ለሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር የሚያበቃ ግልጽና የተብራራ አጀንዳ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከሴራ፣ ከቂም በቀልና ከክፋት የራቀ ሥልጡን መስተጋብር ለመፍጠር የሚያስችል ዝግጁነት መፍጠር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለሥልጣንና ለጥቅም ከመዋደቃቸው በፊት ሕዝብ ፊት ሊያቆሙዋቸው የሚችሉ፣ የተሻሉ አማራጭ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ይዘው መቅረብ አለባቸው፡፡ በዕውቀት ላይ የተመሠረቱ ውይይቶችን፣ ክርክሮችንና ድርድሮችን ለማድረግ አቅማቸውን ማሳየት ግዴታቸው መሆን አለበት፡፡ ከአሁን በኋላ በሕዝብ ስም እየማሉ ቁማር መጫወት እንደማይቻል በተግባር ያረጋግጡ፡፡ ሥልጣንና ጥቅም ሊያስገኝ ይችላል ከሚሉት ለአገር ከማያስብ ኃይል ጋር ከመጎዳኘት ይልቅ፣ ሕዝብን የሚያሳምን አጀንዳ ይዘው መቅረብ ይለማመዱ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአሁን በኋላ አጭበርባሪዎችና ከመጠን በላይ ራስ ወዳድ በሆኑ ፖለቲከኞች እንዲቀልዱበት ዕድል እንደማይሰጥ ይታወቅ፡፡ ሰላሙንና ደኅንነቱን እያናጉ ከውጭ ጠላት ጋር ጭምር የሚያሴሩ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ቦታ እንደሌላቸው ይረዱ፡፡

ኢትዮጵያ ከገባችበት ጦርነት በፍጥነት ወጥታ ወደ ልማት ፊቷን መመለስ አለባት፡፡ በጦርነቱ ምክንያት የፈረሱትን መሠረተ ልማቶች መልሶ ለመገንባት ከፍተኛ ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ሥራ አግኝተው የልማቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ ፊትን ወደ ልማት መመለስ የግድ ነው፡፡ የሕዝቡን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ማቃለል የሚቻለው በሥራ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለዜጎቿ የምትመች አገር ለማድረግ የሚረዱ በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች አሉ፡፡ እነዚህ ፀጋዎች በአንድነት ለአገር በመቆም ከተሠራባቸው ከበቂ በላይ የሆነ ሀብት ያስገኛሉ፡፡ ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ንግድና ኢንቨስትመንት፣ ወዘተ ተዝቆ የማያልቅ በረከት አላቸው፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያን ወደ ሰላምና መረጋጋት በፍጥነት በመመለስ መሠራት ያለበት፡፡ ከዚህ በፊት ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ የጋለ ወኔ ወደ ልማት መዞር ከተቻለ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ አስገራሚ ውጤቶችን ማስመዝገብ ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያንም ሆነ ኢትዮጵያዊያንን መልሶ የጦርነት አዙሪት ውስጥ መክተት ወንጀል ነው፡፡ ችግሮችን በሰከነ መንገድ በመነጋገር ለመፍታት የሚያስችሉ በርካታ አማራጮች ባሉበት አገር ውስጥ፣ የጥቂቶችን ፍላጎት ለማሳካት ሲባል ንፁኃንን ጦርነት ውስጥ መማገድ ነውረኝነት ነው፡፡ ለአገር ዕድገት ልዩነትን ይዞ አብሮ መሥራት በሚቻልበት በዚህ የሠለጠነ ዘመን፣ አገርን መቅኖ ቢስ የሚያደርግ ግጭት የመቀስቀስ አባዜ በሕግ ያስጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያ ወደፊት የምትራመደው በልማት እንጂ ፋይዳ ቢስ በሆኑ የጥፋት ድርጊቶች አይደለም፡፡ አሮጌ አስተሳሰቦችን አስወግዶ ከዘመኑ ጋር እኩል መራመድ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያ በፍጥነት ፊቷን ወደ ልማትና ዕድገት ማዞር ያለባት!   

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሕግ የማጥቂያ መሣሪያ እንዳይሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

የሕግ መሠረታዊ ዓላማ ዜጎችን ከማናቸውም ዓይነት ጥቃቶች መጠበቅ፣ ለሕይወታቸውና ለንብረታቸው ከለላ መስጠትና በሥርዓት እንዲኖሩ ማድረግ ማስቻል ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል...

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...