Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹ጀግኖች ባይኖሩ ኖሮ በዚህ ሁኔታ ላይ አንገኝም ነበር›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

‹‹ጀግኖች ባይኖሩ ኖሮ በዚህ ሁኔታ ላይ አንገኝም ነበር›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)

ቀን:

ቅዳሜ ኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. የትግራይ ክልል ርዕሰ ከተማ መቀሌ በአገር መከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ሥር መዋሉን ያበሰሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ሰኞ ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ማለዳ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ ለመስጠት ሲደርሱ የጠበቃቸው የጋለ አቀባበል ነበር፡፡ የምክር ቤቱ አባላት፣ ጥሪ የተደረገላቸው ዲፕሎማቶች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮችና ሌሎች እንግዶች በታደሙበት ሥነ ሥርዓት ላይ በርካታ ጥያቄዎች ከምክር ቤቱ አባላት ቀርበውላቸዋል፡፡ በተለይ በሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ የተፈጸመው ጥቃትና የማይካድራ ጭፍጨፋ ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ የሰሜን ዕዝ ታቅዶበት በሰው ኃይልም ሆነ በትጥቅ ከተቀሩት ዕዞች በላይ እንዲበልጥ መደረጉን፣ በሠራዊቱ አደረጃጀት በአመራርም ሆነ በሠራዊት ጥንቅር የትግራይ ክልል የበላይነት እንዲይዝ ሲሠራ መኖሩንና የመሳሰሉትን ድርጊቶች አስረድተዋል፡፡ በሕወሓት አመራር አማካይነት ሰሜን ዕዝ እንዲጠቃ ተደርጎ ትጥቅ ከተዘረፈ በኋላ ጦርነቱ ተቀስቅሶ፣ ጥቃቱን በማክሸፍ የተሠራውን ጀብዱ ተንትነዋል፡፡ ‹‹ጀግኖች ባይኖሩ ኖሮ በዚህ ሁኔታ ላይ አንገኝም ነበር፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በየዓውደ ግንባሩ አመራር የሰጡትን ጄኔራል መኮንኖች ስማቸውን እየጠሩ በጀግንነታቸው አወድሰዋቸዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ያተኮረው የፓርላማ ውሎ ማብራሪያ

በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለውን ‹‹የሕግ ማስከበር ዘመቻ›› እና ከዚሁ ጋር የተያያዙ ሌሎች ወቅታዊ አገራዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ እንዲያቀርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥሪ የተደረገላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ሰኞ ኅዳር 21 ቀን 2013 .ም. ወደ ምክር ቤቱ አዳራሽ ሲዘልቁ የምክር ቤቱ አባላት ከመቀመጫቸው ተነስተው ከፍተኛ አቀባበል አድርገውላቸዋል። 

የምክር ቤቱ አባላት ከመቀመጫቸው ተነስተው በጭብጨባ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የተቀበሉበት ምክንያት፣ በትግራይ ክልል እየተካሄደ የሚገኘው የሕግ ማስከበር ዘመቻ የመጨረሻ ምዕራፍ ቅዳሜ ኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. የመቀሌ ከተማን በመቆጣጠር በአጭር ጊዜ ውስጥ መጠናቀቁ ይፋ በመደረጉ ነው። 

የምክር ቤቱ አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሷቸው ጥያቄዎች በአመዛኙ መንግሥት የትግራይ ክልልን በሚያስተዳድረው አመራር ላይ የሕግ ማስከበር ዘመቻ ለመውሰድ ከመገደዱ አስቀድሞ ለምን ለረዥም ጊዜ መታገስ እንደፈለገ፣ የክልሉ ገዥ ፓርቲ የሕወሓት አመራር በሥፍራው የሚገኘውን የመከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ከመውጋቱ አስቀድሞ መረጃ አልነበረውም ወይ የሰሜን ዕዝ ሠራዊትን የወጋው፣ በማይካድራ ዘርን መሠረት ያደረገ ጥቃት በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ እንዲፈጸምና አንድ ሺሕ ነዋሪዎችን ያስጨፈጨፈው ሕወሓትና አመራሩ አሸባሪ ተብለው እንዲፈረጁ መንግሥት ለምን አያደርግም? የሚሉ ጥያቄዎች ነበሩ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የቀረቡላቸውን ጥያቄዎች በቀጥታ ከመመለስ ይልቅ፣ የተፈጠረው ችግር ከዬት እንደጀመረና የት እንደደረሰ ለማሳየት ወደ ኋላ ተመልሰው በአገሪቱ የነበሩ የፖለቲካ ሁኔታዎችን በመዘርዘር አመዛኞቹን ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ አድርገዋል። 

የትግራይ ክልልን ይመራ ከነበረው ሕወሓትበተለይም ከበላይ አመራሩ ጋር የተፈጠረው የፖለቲካ ልዩነት ብቻ ሳይሆን፣ ‹‹እኛ ከሌለን አገር ይፈርሳል የሚል መርዝ የሆነ አሰተሳሰብ›› መሠረታዊ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ አስተሳሰብ በተግባር የተገለጠባቸውን ሁነቶች እየጠቀሱ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩየሕወሓት አመራር የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊትን ለመውጋት የደፈረበትን ምክንያትና ይህንን በማድረግ ለማሳካት ያሰበው ፖለቲካዊ ግብ ምን እንደሆነ ለማሳያትም ሞክረዋል። 

ለዚህም ይረዳቸው ዘንድ መቀመጫውን በትግራይ ክልል ያደረገው ሰሜን ዕዝ፣ በኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ያለውን ድርሻና ወታደራዊ አቅም ለማስገንዘብ ሞክረዋል። 

‹‹በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ የመከላከያ ሠራዊቱ ዕዞች ተደምረው በትግራይ ክልል የሚገኘውን የሰሜን ዕዝ የሰው ኃይል አያክሉም። ሰሜን ዕዝ ማለት ይኼ ነው በአጭር ቋንቋ፤›› ሲሉ በሰሜን ዕዝ የሚገኘው የሠራዊት ብዛት፣ ከአጠቃላይ የአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ከግማሽ በላይ መሆኑን አስረድተዋል። 

በሰው ኃይል ብዛት ብቻ ሳይሆን በታጠቀው የጦር መሣሪያም ሆነ በስንቅ የሰሜን ዕዝ እንደሚበልጥ ተናግረዋል።

‹‹የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት የመሣሪያ ዲፖ ያለው ትግራይ ክልል ነውአንድም ጥይት የለም እዚህ። ኢትዮጵያ ያላት ሮኬትና ሚሳይል በሙሉ ያለው ትግራይ ክልል ነው። ሚሳይል ተኳሽ በሙሉ የአንድ አካባቢ (የትግራይ) ሰዎች ናቸው፤›› ብለዋል። 

ትግራይ በሚገኘው የሰሜን ዕዝ የተከማቸውን ሮኬት ለማውጣት ብዙ ሙከራ ቢደረግም ማውጣት እንዳልተቻለምክንያት ሲጠየቅም የኤርትራ መንግሥት ይወጋናል የሚል ምክንያት መቅረቡን ገልጸዋል። 

‹‹ትጥቁን ለማውጣት ስንንቀሳቀስ ሕፃናትንና ሴቶችን መንገድ ላይ ያስተኛሉምክንያቱም እነሱ እየተዘጋጁ ስለነበረ። እኛ ጨፍልቀን ብንወጣ እንኳን ሌላው ሕዝብ ቀርቶ እናንተም አትቀበሉንም። እንዴትስ መከላከያ ሕፃን ጨፍልቆና ገሎ ይወጣል?›› ብለዋል። 

ትጥቁ እንዳይወጣ የሚሰጡት ምክንያት የኤርትራ መንግሥት ትግራይን ይወጋል የሚል ቢሆንም፣ እውነቱ ግን ትጥቁ እንዳይወጣ እንጂ ኤርትራ ወደ ውጊያ እንደማትገባ ያውቁታል ብለዋል። 

ሚሳይሎቹን ማስነሻ ቁልፍ በማዕከላዊ ዕዝ እንዲሰጡ ሲጠየቁ ቁልፉ በክልሉ አመራር እጅ ሳይሆን በሰሜን ዕዝ ሠራዊት እጅ እንደሆነ አሳይተው እንደመለሱት፣ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት እየተኮሱት እንደሚገኙ ተናግረዋል። 

‹‹ሌላ ቦታ ኢትዮጵያን የሚወጋ ግጭት ስለገጠመን ስለግጭቱ ሪፖርት አቅርበን፣ የተወሰነ ጦርና ትጥቅ ግጭት ወደ ገጠመን አካባቢ ተንቀሳቅሶ ኢትዮጵያን እንዲከላከል ስንጠይቅ በፍፁም አሉ። ከሁሉ ግን ተስፋ ቆርጠን እንድንዘጋጅ ያደረገን ይህ ነው፡፡ በዚህ ደረጃ አገራቸውን ይከዳሉ ብለን አንገምትም ነበር፤›› ብለዋል። 

የአገሪቱ መድፍ፣ ሚሳይል፣ ታንክ ሙሉ በሙሉ ያለው በትግራይ ክልል መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ትልልቆቹ የነዳጅ ዴፖዎችም ያሉት በትግራይ ክልል እንደሆነ፣ ይህም የመከላከያ ሠራዊቱ እንቅስቃሴ እንዲገደብና በዚህ ኃይል ፈቃድና ቁጥጥር ሥር እንዲወድቅ ታቅዶ የተሠራበት መሆኑን አመልክተዋል። 

‹‹በነገራችን ላይ የመከላከያ ስንቁም ትጥቁም ለዓመታት እዚያ ብቻ እንዲከማች የተደረገበት ምክንያት አሁን የመጣው ለውጥ ቢመጣም፣ ባይመጣም፣ የአገሪቱ የመከላከል አቅም እዚያ ብቻ እንዲሆን ታስቦ ነው። ምንም ጥርጣሬም ሚስጥርም የለውም ይኼ፤›› ሲሉም፣ ከፖለቲካ ልዩነት ውጪ ያለውን የኃይል ሚዛንና አሠላለፍ አብራርተዋል። 

የሕወሓት አመራሮች የሰሜን ዕዝን በመውጋት ትጥቁን ከመዝረፋቸው አስቀድሞ የሰሜን ዕዝ አዛዥ የነበሩትን ጄኔራል ድሪባን ምሳ ጋብዘው እንዳበሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩጄኔራሉ ከምሳ በኋላ ራሳቸውን እንደሳቱና እስካሁን ድረስም በጦር ኃይሎች ሆስፒታል በሕክምና ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በጄኔራሉ ምትክ የሰሜን ዕዝን እንዲመሩ ተሹመው ወደ ክልሉ የተላኩትን አመራር ወደ ክልሉ እንዳይገቡ ማድረጋቸውንእንዲሁም የሰሜን ዕዝ ምክትል አዛዥን እንዳፈኑም አስረድተዋል። 

ይህንን አድርገው ሲያበቁ ጥቅምት 24 ቀን 2013 .ም. ምሽት በሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ ውጊያ ከፍተው የትግራይ ተወላጅ ያልሆኑ በርካታ የዕዙ አባላትን መግደላቸውንና ማገታቸውን፣ ይህንን ጥቃት ካደረሱ በኋላም የነበራቸው ዕቅድ ወደ አማራ ክልል መግባት እንደነበር ገልጸዋል። 

በሌላ አካባቢ የሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት ወደ ትግራይ ክልል እስኪደርስ ድረስ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ የመከላከል ሥራ መሥራቱን፣ ከዚያ በኋላም የመከላከያ ሠራዊቱ ጀግንነት በተሞላበት መንገድ የተቃጣውን ጥቃት በመቀልበስ በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ የሕወሓት ኃይልን ከእነ አመራሩ በማስወገድ መቀሌን እንደተቆጣጠረ ገልጸዋል።

የሰሜን ዕዝ ስንቅ፣ ትጥቅና አደረጃጀት፣ እንዲሁም በዕዙ ላይ የደረሰው ጥቃት እንዴት እንደተፈጸመ በማብራራት ሒደት ውስጥም የመከላከያ ሠራዊቱ የተገነባበት አጠቃላይ ሥዕል ምን ይመስል እንደነበር፣ እሳቸው ከመጡ በኋላ ያደረጉትን ሪፎርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለው አብራርተዋል።

የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት የተገነባው መቶ በመቶ ከሕገ መንግሥቱ በሚፃረር መንገድ እንደሆነሠራዊቱ ተልዕኮው ለሕገ መንግሥቱ ሳይሆን ለአብዮታዊ ዴሞክራሲና የዚህ የፖለቲካ ርዕዮት ባለቤት ለሆነው ፓርቲ ዘብ መቆም ብቻ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ሠራዊቱ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ከሌለ ኢትዮጵያ እንደሌለች አድርጎ እንዲገነዘብ ተደርጎ ከመሠራቱ ባለፈበአንድ ወገን የበላይነት ቁጥጥር ውስጥ እንዲወድቅ ተደርጎ መዋቀሩንም ገልጸዋል።

ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት የነበረው የመከላከያ ሠራዊት አደረጃጀት ለቀጣይ ዓመታት ማስተካከል በሚከብድ ሁኔታ ከዋናው መሥሪያ ቤት አንስቶ፣ በዕዞቹና በተለያዩ ብርጌዶቹ ውስጥ የተመደበው አመራርና የሰው ኃይል በትግራይ ተወላጆች የተሞላ እንደነበር አስረድተዋል።

ለአብነት ባቀረቡት አኃዛዊ ማስረጃም በመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ ከሚገኙ የጄኔራል ማዕረግ የያዙ አጠቃላይ አመራሮች ውስጥ 60 በመቶ የትግራይ ተወላጆች መሆናቸውን፣ የሌተና ጀኔራል ማዕረግ ካላቸው አጠቃላይ አመራሮች ውስጥ 40 በመቶ ከዚሁ አካቢቢ መሆናቸውን፣ በሜጀር ጀኔራል ደግሞ 45 በመቶ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የብርጋዴር ጄኔራል ማዕረግ ካለቸው አጠቃላይ አመራሮች ውስጥ 40 በመቶ ከትግራይ መሆናቸውን፣ የኮሎኔል ማዕረግ ደግሞ 58 በመቶ እንደሆኑ፣ በሌተና ኮሎኔል ማዕረግ ደግሞ 66 በመቶ፣ የሻለቃ ማዕረግ ካላቸው የሠራዊቱ አባላት ውስጥም 53 በመቶ በዚሁ አካባቢ ሰዎች የተያዘ እንደነበር ይፋ አድርገዋል።

ከላይ ያቀረቡት በወታደራዊ ማዕረግ ያለውን ስብጥር የሚመለከት ሲሆንሠራዊቱን የመምራት ሥልጣንን በተመለከተም ተከታዩን አኃዛዊ መረጃ አቅርበዋል።

በመከላከያ ተቋሙ አመራር የሚሰጡ ኃይሎችን በተመለከተ 80 በመቶ የሚሆነው ወታደራዊ ሥልጣን በትግራይ ተወላጆች መያዙን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩየሠራዊቱ ዕዞች አዛዥና ምክትል አዛዥ ሆነው የተመደቡት መቶ በመቶ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የሠራዊቱ አባላት እንደነበሩ ተናግረዋል።

በተመሳሳይም የክፍለ ጦሮችና የሜካናይዝድ ጦር አዛዦች መቶ በመቶ በዚሁ አካባቢ ተዘላጆች ተይዞ እንደነበርበእግረኛ ክፍለ ጦር 80 በመቶ፣ በሜካናይዝድ ብርጌድ 85 በመቶ፣ በእግረኛ ብርጌድ 80 በመቶ በትግራይ ተወላጆች ቁጥጥር ሥር እንደነበር፣ የመከላከያ ሥልጠና ተቋማትም 85 በመቶ በትግራይ ተወላጆች መያዛቸውን ገልጸዋል።

አቅም ያለው አመራር ከአንድ አካባቢ ከትግራይ ብቻ እንዲወጣ ተደርጎ ሠራዊቱ መደራጀቱ ለማንም እንደማይጠቅም የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩእሳቸው ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ማሻሻያ ለማድረግ መሞከሩን ጠቁመዋል።

እነዚህን ነባራዊ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት በትንሹም ቢሆን ለመቀየርና ኢትዮጵያን የሚመስል መከላከያ ለማዋቀር ጅምር ሥራዎች መከናወናቸውን ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩበተደረገው ማሻሻያም በአማካይ 55 በመቶ በትግራይ ተወላጆች ተይዞ የነበረውን ከሻለቃ እስከ ጄኔራል ያለውን ወታደራዊ የሥልጣን እርከን ወደ 26 በመቶ ዝቅ እንዲል መደረጉን ገልጸዋል።

አሁንም ቢሆን የትግራይ ተወላጆች ብዛት ከፍ ያለ ቢሆንም፣ የትግራይ ክልል በመከላከያ ረገድ በቂ ድርሻ እንዲኖረው ፅኑ ፍላጎት በመንግሥት ዘንድ በመኖሩ የሌሎችን ድርሻ በማከል መወሰኑን ገልጸዋል።

በሁሉም የአገሪቱ ዕዞች የነበረው የመቶ በመቶ ስብጥርም በአማካይ ወደ 25 በመቶ ዝቅ እንዲል መደረጉን ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል የተከናወነው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በዚህ የተዛባ የመከላከያ አደረጃጀት ውስጥ ቢሆንም፣ ሠራዊቱ ላይ የደረሰው ግፍ የፈጠረው ቁጣ አኩሪ ሥራ በአጭር ጊዜ በጥንቃቄ እንዲከናወን ማስቻሉን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየጦር ግንባሩ በመሠለፍ አኩሪ ሥራ ያከናወኑ የጦር መኰንኖችና ጄኔራሎችንም አወድሰዋል። በጦሩ ተልዕኮና ጀግንነት መደነቃቸውን በመግለጽም፣ ‹‹ጀግኖች ባይኖሩ ኖሮ አሁን ያለንበት ሁኔታ ላይ አንገኝም ነበር፤›› ብለዋል። ለዚህ ደግሞ የትግራይ ሕዝብ ድጋፍ የላቀ እንደነበር ገልጸዋል።

‹‹የጽንፈኛው ኃይል አባላት ያፈኗቸውን ሰዎችና ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ከመቀሌ ሸሽተው አገረ ሰላም አካባቢ ይገኛሉ፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ቀጣዩ ሥራ ወንጀለኞችን ለቅሞ ለሕግ ማቅረብ እንደሆነ አስታውቀዋል።

የሕወሓት አመራሮች ከመቀሌ ሸሽተው ቢሄዱም ቀንና ሌሊት በዕይታ ሥር መሆናቸውን አስታውቀው ሴቶች፣ ሕፃናትና አግተው የያዙዋቸውን ሰዎች ላለመጉዳት ሲባል ጥንቃቄ እየተደረገ እየታደኑ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

‹‹የጦር ወንጀለኞች፣ አገር ከሃዲዎችና የዘር ማጥፋት ፈጻሚዎችን ለሕግ የማቅረብ ሥራ ይከናወናል፣ የታሰሩትን ነፃ ለማውጣት፣ የተሰረቀውን ለማስመለስም ይሠራል፤›› ብለዋል

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...