በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመጀመርያ ጨዋታውን ከሜዳው ውጪ የተጫወተው ፋሲል ከነማ የመልሱን ጨዋታ እሑድ ኅዳር 27 ቀን 2013 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚጫወት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴረሽን (ካፍ) አስታወቀ፡፡ ፋሲል ከነማ ባለፈው ዓርብ ኅዳር 18 ቀን ከሜዳው ውጪ ባደረገው በመጀመርያ ጨዋታ በቱኒዚያው ዩኤስ ሞናስቴር 2 ለ0 ተሸንፎ መመለሱ አይዘነጋም፡፡
ካፍ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚደረግ ከማሳወቁ በፊት ጨዋታውን የሚመሩት ዳኞች፣ የጨዋታ ታዛቢ ዳኞችና የኮቪድ-19 ፕሮቶኮል ተወካዮች በተገኙበት ውይይት ተደርጎ ከስምምነት ከተደረሰ በኋላ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጠንካራ የሕዝብ ድጋፍና የፋይናስ አቅም እንዳላቸው ከሚነገርላቸው ክለቦች መካከል የሚጠቀሰው ፋሲል ከነማ፣ የ2012 ውድድር ዓመት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ በፕሪሚየር ሊጉ አናት ከነበሩት መቐለ 70 እንደርታና ቅዱስ ጊዮርጊስን በማስከተል ሊጉን መምራት የቻለበት አጋጣሚ ነበር፡፡
ሆኖም በኮቪድ-19 ምክንያት ውድድሩ ሲቋረጥ፣ የፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ ዙር ጨዋታ የተጀመረበት ወቅት ስለነበረ፣ አወዳዳሪው አካል የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር በሊጉ አሸናፊም ሆነ ተሸናፊ እንዲሁም ወጪም ሆነ ወራጅ ሳይኖር ውድድሩ ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
ሊግ ካምፓኒው በወቅቱ የውድድር ዓመቱን መርሐ ግብር ከመሰረዙ ጎን ለጎን፣ በ2013 ውድድር ዓመት ኢትዮጵያን ወክሎ በአኅጉራዊ መድረክ የሚሳተፍ ክለብ እንደሌለ ሲያሳውቅ፣ ከእግር ኳሱ ቤተሰብ በዋናነት ፕሪሚየር ሊጉ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ሊጉን የመምራት ዕድል ያገኙት የመቐለ 70 እንደርታና የፋሲል ከነማ ክለብ ደጋፊዎችና አመራሮች ኢትዮጵያ ያለ ተወካይ መቅረት እንደሌለባት በመግለጽ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያሰሙ ነበር፡፡
አክሲዮን ማኅበሩ ከብዙ ክርክርና ውይይት በኋላ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ተሞክሮ በመነሳት ጉዳዩን እንደገና በመመልከት፣ የ2012 ውድድር ዓመት መርሐ ግብር እንዲሰረዝና በ2013 የውድድር ዓመት በአፍሪካ መድረክ የሚወከሉ ክለቦችን በሚመለከት በ2011 የውድድር ዓመት የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ መቐለ 70 እንደርታና በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ፋሲል ከነማ፣ በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግና በአፍሪካ ክለቦች ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ እንዲሳተፉ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ለአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ከሊቢያው አል አህሊ ቤንጋዚ ጋር በገለልተኛ ሜዳ እንዲጫወት ፕሮግራም ተይዞለት የነበረው የመቐለ 70 እንደርታ እግር ኳስ ክለብ፣ በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ክልል መካከል በተፈጠረው ግጭት ባለፈው እሑድ ኅዳር 19 ቀን 2013 ማከናወን የነበረበትን ጨዋታ አላደረገም፡፡ ካፍ የመቐለ 70 እንደርታን ጉዳይ በሚመለከት ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስ ምንም ዓይነት ውሳኔ እንዳሳለፉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
ለኮንፌዴሬሽን ዋንጫ በቱኒዚያው ዩኤስ ሞናስቴር ከሜዳው ውጪ 2 ለ0 የተረታው ፋሲል ከነማ፣ በመልሶ ጨዋታ ውጤቱን ገልብጦ ወደ ተከታዩ ዙር ለማለፍ 3 ለ0 ማሸነፍ ግድ ይለዋል፡፡ ለዚህ ሲባል ክለቡ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ለመልሶ ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጠንካራ ዝግጅት እያደረገ ስለመሆኑ ክለቡ በድረ ገጹ አስታውቋል፡፡