Tuesday, May 28, 2024

ሰብዓዊ ድጋፍ 40 በመቶ እንዲጨምር ያደረገው ኮቪድ-19

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኮቪድ-19 በቻይና ለመጀመርያ ጊዜ ከተከሰተ አንድ ዓመት ሊሞላው የሳምንት ዕድሜ ቀርቶታል፡፡ ከቻይና ውሃን ከተማ ተነስቶ ዓለምን ያጥለቀለቀው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የዓለምን ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ማኅበራዊ ኑሮ ፈትኗል፡፡ ኢኮኖሚው ተጎድቷል፣ ማኅበራዊ ሕይወት ተፋልሷል፣ በፖለቲካው ላይም ጫና ተፈጥሯል፡፡

እስካሁን የግልና አካባቢ ንፅህናን ከመጠበቅ ውጪ መድኃኒት ያልተገኘለት ወረርሽኝ ከ60 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን አጥቅቷል፡፡ ከ1.4 ሚሊዮን በላይ ሰዎችንም ገድሏል፡፡ ከ40 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ ከበሽታው አገግመዋል፡፡ ይሁን እንጂ ወረርሽኙ እ.ኤ.አ. በ2021 ሥጋት ሆኖ ይቀጥላል ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) አስታውቋል፡፡

ኮቪድ-19 እየተከላከሉ መኖር አማራጭ በሆነበት በአሁኑ ሰዓት፣ በዓለም በርካታ ትምህርት ቤቶች በበይነ መረብና በገጽ ለገጽ ተከፍተዋል፡፡ ኢንዱስትሪዎችና ንግዶችም እንዲሁ፡፡ ሆኖም ሰዎች ቤት ውስጥ በመቀመጣቸው ረገብ ብሎና በአንዳንድ አገሮችም በቁጥጥር ሥር ውሎ የነበረው ኮቪድ-19 ማገርሸት ጀምሯል፡፡ ይህም የቀደሙ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች ሳይፈቱ መሆኑ ችግሩን አሳሳቢ አድርጎታል፡፡

በተለይ ቀድሞውንም በሰብዓዊ ቀውስና በጦርነት ውስጥ የነበሩ ሕዝቦች የችግሩ ከፍተኛ ገፈት ቀማሽ ናቸው፡፡

ተመድ ባወጣው ሪፖርት፣ እ.ኤ.አ. በ2021 የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት ይጨምራል፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ጦርነትና የእርስ በርስ ግጭት በተጨማሪ፣ ኮቪድ-19 ለዓለም ሌላ ጫና ይዞ በመምጣቱ ነው፡፡

ተመድ እንደሚለው፣ እ.ኤ.አ. በ2021 ከ33 ሰዎች አንድ የውኃ፣ የምግብና የግል ንፅህና መጠበቂያ ዕርዳታ የሚፈልግ ይሆናል፡፡ ወረርሽኙ የሰብዓዊ ድጋፍ ዕርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር እንዲያሻቅብ ሲያደርግ፣ በአንድ ዓመት ውስጥም ብዙዎች ወደ ድህነት አረንቋ እንዲዘፈቁ ምክንያት ሆኗል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2021 ወደ 235 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የሰብዓዊ ድጋፍና ጥበቃ የሚፈልጉ ይሆናሉ፡፡ ይህ በዓለም ከ33 ሰዎች አንድ ማለት ሲሆን፣ ከአምናው ሲነፃፀር የ40 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

ተመድ እ.ኤ.አ. የ2021 ግሎባል ሒውማኒተሪያን ኦቨርቪውን አስመልክቶ በድረ ገጹ ባሠፈረው ሪፖርት፣ አምና ከ45 ሰዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚፈልገው አንድ የነበረ ሲሆን፣ ይህ አሁን ጨምሯል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ኮቪድ-19 ነው፡፡ ይህ ቁጥር ባለፉት አሠርት ከተመዘገቡት ትልቁ እንደሆነም ሪፖርቱ አሳይቷል፡፡

ተመድ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በ56 አገሮች በጣም በችግር ውስጥ የሚገኙ 160 ሚሊዮን ሰዎችን የሚረዳ ሲሆን፣ ለዚህም 35 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው አስታውቋል፡፡

እንደ ሪፖርቱ ከሆነ፣ በዓለም ሰብዓዊ ዕርዳታ ከሚያስፈልጋቸው 235 ሚሊዮን ሰዎች መካከል አብዛኞቹ የሚገኙት በሶሪያ፣ በየመን፣ በአፍጋኒስታን፣ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና በኢትዮጵያ ነው፡፡

‹‹ቀውሱ ከሚያበቃበት ጊዜ አልደረስንም፤›› የሚሉት የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ፣ ወረርሽኙ ባስከተለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ምክንያት ለሰብዓዊ ዕርዳታው የሚያስፈልገውን ገንዘብ ማግኘትም አዳጋች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹የሰዎች ሕይወት በቢላ ስለት ላይ እንደመቀመጥ ከባድ ሆኗል፣ ምግብ ተወዷል፣ ገቢ ቀንሷል፣ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፣ የክትባት ፕሮግራሙ ገና ነው፤›› ሲሉም የችግሩን አሳሳቢነት ጠቁመዋል፡፡

እ.ኤ.ኤ. ከ1990ዎቹ በኋላ ድህነት በከባድ ሁኔታ የሚጨምረው እ.ኤ.አ. በ2021 ነው፡፡ የሰዎች የመኖር ጣሪያ ዕድሜም ይቀንሳል፡፡ በዓመት በኤድስ፣ በቲቢና፣ በወባ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም በእጥፍ ይጨምራል፣ የሚራቡ ሰዎች ቁጥርም ወደ እጥፍ ይጠጋል የሚል ሥጋትም ተፈጥሯል፡፡

ቀድሞውንም ከፍተኛ ረሃብ የተከሰተባት የመን በችግሩ በጣም ትጎዳለች፡፡ በተለይ የባህረ ሰላጤው አገሮች ቀድሞ ያደርጉ የነበሩትን ድጋፍ ማቋረጣቸው ችግሩን አሳሳቢ አድርጎታል፡፡ የዕርዳታው መቋረጥ በየመን የዕርዳታ ፕሮግራሞች እንዳይፈጸሙ አድርጓል፡፡ ክሊኒኮችም ተዘግተዋል፡፡

በሶሪያ ባለው ግጭት የተጎዱ፣ የተሰደዱና በጎረቤት አገሮች የተቀመጡ ዜጎች ከዕርዳታ ፈላጊዎቹ ይመደባሉ፡፡

ሰዎች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመጠቃታቸው ሳይሆን፣ ወረርሽኙ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ባሳደረው አሉታዊ ተፅዕኖ ምክንያት ለችግርና ለሰብዓዊ ዕርዳታ መጋለጣቸውን ያስታወሰው ሪፖርቱ፣ ይህም በደሃ አገሮች ውስጥ በድኅነት የሚኖሩትን ይበልጥ እንደጎዳ ተነግሯል፡፡

ኮቪድ-19 ዓለም እ.ኤ.አ. ከ1930 ወዲህ ያላስተናገደችውን ዓይነት የኢኮኖሚ ቀውስ አስከትሏል፡፡ ድህነት ካለፉት 22 ዓመታት ወዲህ የተንሰራፋው ዘንድሮ ነው፡፡ ሥራ አጥነት ጨምሯል፡፡ በተለይ በኢመደበኛ ዘርፍ የተሰማሩ ከ15 እስከ 19 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶችና ወጣቶች ክፉኛ ተመትተዋል፡፡ የትምህርት ቤቶች መዘጋት በዓለም 91 በመቶ ያህል ተማሪዎችን ጎድቷል፡፡

የፖለቲካ አለመግባባት ሕፃናትንና ሰላማዊ ሰዎችን ጎድቷል፡፡ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሴቶችና ልጃገረዶች ለፆታዊ ጥቃት ተጋልጠዋል፡፡ በጤናና በዕርዳታ ድጋፍ ሰጪዎች ላይ የሚሰነዘር ጥቃትም አይሏል፡፡ ላለፉት ተከታታይ ዘጠኝ ዓመታት በቦምብ ጥቃት የደረሰባቸው ሰላማዊ ሰዎች በብዛት የሚኖሩባቸው ሥፍራዎች ናቸው፡፡

 ያለፈው አሥር ዓመት ሰዎች በግጭትና ጥቃት ምክንያት በብዛት እዚያው በአገራቸው የተፈናቀሉበት ነው፡፡ አሁን ላይ አዳዲስ የተፈናቀሉትን ጨምሮ 51 ሚሊዮን ሰዎች ከቄዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡ የስደተኞች ቁጥር ደግሞ በእጥፍ ጨምሮ 20 ሚሊዮን ደርሷል፡፡

ረሃብ የጨመረ ሲሆን፣ በ22 አገሮች የሚገኙ 77 ሚሊዮን ሕዝቦች ለረሃብ ተጋልጠዋል፡፡ እ.ኤ.አ. 2020 ሲጠናቀቅ 270 ሚሊዮን ያህል ሰዎች የምግብ ዋስትና ያጣሉ፡፡

ያለፈው አሥር ዓመት የሙቀት መጠን የጨመረበት ነው፡፡ ከባድ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎች የተስተዋሉበት ይህ ጊዜ፣ የሰዎችን ለችግር ተጋላጭነት ጨምሮታል፡፡ በ2021 የመጀመርያ ሩብ ዓመትም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የባህር ሙቀት እንዲጨምር፣ የዝናብ ወቅት እንዲዘበራረቅና ሃሪኬን እንዲከሰት ያደርጋል፡፡

የበሽታ ወረርሽኞች ጨምረዋል፡፡ የኮቪድ-19 መከሰት ደግሞ ከአምስት ዓመት በታች የሚገኙ አምስት ሚሊዮን ሕፃናት ላይ የኮሌራ ሥጋት ደቅኗል፡፡ ወረርሽኙ በኤችአይቪ/ኤድስ ቲቢና ወባ ላይ ላለፉት 20 ዓመታት የተሠራውን ሥራ መና ያስቀራል፣ ዓመታዊ የሞት ቁጥሩም በእጥፍ ሊጨምር ይችላል የሚል ሥጋት እንዳለ የተመድ ሪፖርት ያሳያል፡፡  

ሰብዓዊ ድጋፍ 40

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -