Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ጉዞ

የጂኦስፓሻል ዕውቀት የሰው ልጆችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚያቀልና ለባህል ዕድገትና ልውውጥ ቁልፍ ሚና እንደነበረው ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ዘርፉ ለሰው ልጆች ዘመናዊ አኗኗር ከማምጣቱ በተጨማሪ፣ ከአንደኛው የኢንዲስትሪ አብዮት ጀምሮ ለዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በኢትዮጵያ የጂኦስፓሻል መረጃ ፍላጎት በሁለተኛው ኢንዱስትሪ አብዮት እያደገ መምጣቱን የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህን ፍላጎት ለማሟላት የኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ራሱን ችሎ ከተቋቋመ ሁለት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ኢንስቲትዩት ከመሆኑ በፊት በተለያዩ ተቋማት ውስጥ እንደ አንድ የሥራ ዘርፍ አገልግሎት ይሰጥ ነበር፡፡ ኢንስቲትዩት ከሆነ በኋላ የተለያዩ አገልግሎቶች እየሰጠ ይገኛል፡፡ ቱሉ በሻ (ዶ/ር) የኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ስለ ጂኦስፓሻል ጥቅም፣  ምንነትና ስለሚሰጠው ግልጋሎት ሔለን ተስፋዬ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ጂኦስፓሻል ምንድነው? በኢትዮጵያ መቼ ተጀመረ?

ዶ/ር ቱሉ፡- ጂኦ ማለት መሬት ነው፡፡ ስፓሻል ማለት የቦታ መረጃ ነው፡፡ በአጠቃላይ ከመሬት ላይ የሚገኝ የቦታ መረጃ ማለት ነው፡፡ ይህ መረጃ በፎቶና በተለያዩ ነገሮች ሊቀመጥ ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ የጂኦስፓሻል መረጃ ፍላጎት በሁለተኛ የኢንዱስትሪ አብዮት ነው እያደገ የመጣው፡፡ በወቅቱ የጂኦስፓሻል መረጃ በኢትዮጵያ የተለያዩ የተፋሰስ ጥናቶችን ለማካሄድ ለአፈር፣ ለውኃና ለሌሎች የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ እንዲሁም የኃይድሮ ፓወር ኢነርጂ ለማመንጨት ውሏል፡፡ የቀድሞ የኢትዮ-ጂቡቲ የምድር ባቡር መስመር ዝርጋታና ለሌሎች መሠረተ ልማቶች ፕላን ዝግጅትም የጂኦስፓሻል መረጃ ከፍተኛ ጥቅም ሰጥቷል፡፡ ኢትዮጵያም ከጂኦስፓሻል ዘርፍ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን የወሰነችው በሁለተኛው ኢንዱስትሪ አብዮት መጨረሻዎች በ1914 ዓ.ም. ነው፡፡ ይህም ይፋ የተደረገው የጂኦግራፊን የካርታ አነሳስ ኢንስቲትዩት በማቋቋም ነበር፡፡ ኢንስቲትዩቱ ሲቋቋም የሕዋ ሳይንስና የሳተላይት ቴክኖሎጂ ገና ያልተጀመረ በመሆኑ፣ ለኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት ለስፓሻል ፕላኒንግ ግብዓትነት የሚውሉ የተለያዩ የጂኦስፓሻል መረጃዎች የሚመረቱት በምድር የቅየሳ ዘዴዎችና የአየር ፎቶግራፍ መረጃዎች በማሰባሰብ ነበር፡፡ ኢንስቲትዩቱ ከ1949 ዓ.ም. እስከ 1953 ዓ.ም. ድረስ ከአሜሪካ የኮሜርስ ዲፓርትመንት የኮስቴያና የጂኦዴቲክ ሰርቬይ ጋር በመተባበር የጥቁር ዓባይ (Blue Nile) ኢንቨስትጌሽን ፕሮጀክት በሚል ለኢትዮጵያ የመጀመርያ የጂኦስፓሻል መረጃ የሚመረትበት የጂኦግራፊ የቦታ መገኛ ኮኦርዲኔት ኔትዎርክ ለማቋቋም ተችሏል፡፡ የዚህ ኔትወርክ መቋቋም የአየር ፎቶግራፍና የተለያዩ የጂኦስፓሻል መረጃዎችን ለማምረት ብሔራዊ አቅም የፈጠረ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ ኔትወርኩን በማስፋፋትና ከዳሰሳ ሳተላይት ቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር ብሔራዊ የጂኦስፓሻል መረጃ አቅርቦትን ለማሳደግ ተችሏል፡፡   

ሪፖርተር፡- ጂኦስፓሻል በዓለም አቀፍ ደረጃ ለኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዕድገት ከፍተኛ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ከመቼ ወዲህ ነው?

ዶ/ር ቱሉ፡- ጂኦስፓሻል በዓለም አቀፍ ደረጃ ለኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደረግ የነበረው በሦስተኛው ኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን ጀምሮ ነው፡፡ በተለይም በሕዋ ሳይንስ፣ በሳተላይት ቴክኖሎጂና በኮምፒዩተር ሳይንስ ዕድገት ጋር ተያይዘው በመጡ ፈጣን ቴክኖሎጂ ለውጦች ነው፡፡ በ1970 እና በ1980ዎቹ በመሬት ምልከታ፣ በአሰሳ ሳተላይት ቴክኖሎጂና ከኮምፒዩተር ሳይንስ ዕድገት ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ፍላጎት በተለያዩ የኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዘርፎች እያደገ በመምጣቱ፣ ኢንስቲትዩቱ የመረጃ ተደራሽነትን ለመፍጠር በተለያዩ ጊዜያት ተልዕኮና ኃላፊነቱን በአዋጅ እያሻሻለ መዋቅራዊ ለውጦችን አድርጓል፡፡ የመጀመርው ሐሳብ ላይ የኢትዮ ምድር ባቡንና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ለመዘርጋት የጂኦስፓሻል መረጃ ከፍተኛ ጠቀሜታ ሰጥቷል፡፡ ይህ ኢትዮጵያ ከብዙ ዓመታት በፊት የጂኦስፓሻል መረጃ ተጠቃሚ መሆኗን ማሳያ ሲሆን፣ ዘርፉ ለእነዚህ መሠረተ ልማቶች ያለው ጥቅም የጎላ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- በጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት በተለያዩ ጊዜያት የነበረው የመዋቅር ለውጥ ምን ይመስላል? መዋቅራዊ ለውጥ ማድረጉ ምን ጠቀሜታ አስገኝቷል?

ዶ/ር ቱሉ፡- ኢትዮጵያ በአንደኛውና በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ፈጣን የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ዕድገት ለውጥ ለማምጣት በቀድሞው የኢትዮጵያ ካርታ ሥራ ኤጀንሲ አቅም ብቻ የሚመለስ አልነበረም፡፡ በዚህም ምክንያት በ1999 ዓ.ም. በኢንፎርሜሽን መረጃ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) የቀድሞውን የኢትዮጵያ ካርታ ሥራ ኤጀንሲ አቅምን በሚያጠናክር አግባብ አዲስ የጂኦስፓሻል አቅም ተፈጥሯል፡፡ በኢመደኤ የነበረው የጂኦስፓሻል የሥራ ሒደት በኢትዮጵያ ካርታ ሥራ ኤጀንሲ ባልተገነቡ የጂኦስፓሻል ዘርፎች ማለትም የአየር ፎቶግራፍ ቅየሳ፣ የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ማኔጅመንትና መረጃ ማጋራት የሚያስችል የፖሊሲ፣ የቴክኖሎጂ፣ የዳታና የኢኮሲስተም ግንባታና የጂኦስፓሻል ትንተና ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር፡፡ ይህ እንደ አገር ጠንካራ ብሔራዊ የጂኦስፓሻል አቅም እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ ኢትዮጵያ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማስቀጠል የጂኦስፓሻል መረጃ አቅርቦት በተቀናጀ አግባብ መመራት በማስፈልጉ በፌዴራል አስፈጻሚ አካላት ተግባርና ኃላፊነት መወሰኛ ቁጥር 1097/11 አንቀጽ 32/3/ መሠረት ቀደም ሲል በአዋጅ ቁጥር 806/06 አንቀጽ 13 ለኢመደኤ የተሰጠው የጂኦስፓሻል ተግባርና ኃላፊነት አዲስ ለተቋቋመው ለጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ተላልፏል፡፡ በመሆኑም የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ለቀድሞ በሁለቱ ተቋማት የነበረው የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ አቅምን በማቀናጀት፣ በምርምርና መረጃ አቅርቦት ዘርፍ ተደራሽነትን በማሳደግ በጂኦስፓሻል የቴክኖሎጂና የኢንዱስትሪ ሽግግርን ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላትና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር እየሠራ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- የጂኦስፓሻል መረጃ ማሰባሰብ ጠቀሜታውን በዝርዝር ቢገልጹልን?

ዶ/ር ቱሉ፡- የጂኦስፓሻል መረጃ ጥቅም ዘርፍ ብዙ ናቸው፡፡ ለገጠር ልማት፣ ለመስኖና ተፋሰስ፣ ለኃይድሮ ፓወር ግድብ ግንባታ፣ ለብሔራዊ ደኅንነትና በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለሚገነቡ የቱሪስት መስህቦች ጭምር መረጃው ጥቅም ይሰጣል፡፡ ይህም የቦታዎችን ከፍታና ዝቅታ እንዲሁም ምን ያህል ቦታ እንደሆኑ ለመረጃ ፈላጊው የሚያቀርብ በመሆኑ ሥራዎቻቸውን ቀለል ያደርግላቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ስለአንድ ቦታ ያሉትን መሠረታዊ መረጃዎች በዝርዝር ለማሳወቅ የሚያግዝ ነው፡፡ በዚህም ከ2004 ዓ.ም. እስከ 2013 ዓ.ም. ድረስ በተደረገው የገጠርና የከተማ መሬት ምዝገባ፣ ለመሠረተ ልማት ፕላኒንግና ግንባታ፣ ለከተሞች የማስተር ፕላን ስትራክቸራል ፕላን ዝግጅት፣ ለገጠር ልማት፣ ለመስኖ ተፋሰስና ለኃይድሮ ፓወር ግድብ ግንባታና ለሌሎች ለዘርፈ ብዙ ግብዓትነት የሚውሉ የኢትዮጵያ 40 በመቶ የቆዳ ሽፋን የሚሸፍን የአየር ፎቶግራፍ መረጃ ማሳሰብ ተችሏል፡፡ በአማራ ክልል ሙሉ ለሙሉ፣ ትግራይ ክልል ከትንሽ ቦታዎች በስተቀር የአየር ፎቶግራፍ መረጃ ተሰብስቧል፡፡ ኦሮሚያ፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦና ሕዝቦች፣ አፋር፣ ሐረር፣ ሶማሌ ክልሎችና ሌሎችም ሙሉ ለሙሉ የአየር ፎቶግራፍ መረጃ ለማሰባሰብ በአሥር ዓመት መሪ ልማት ዕቅድ ውስጥ አስገብተናል፡፡  

ሪፖርተር፡- ኢንስቲትዩቱ የሚያገኛቸውን መረጃዎች ለየትኞቹ የመንግሥት ተቋማት ተደራሽ ያደርጋል?

ዶ/ር ቱሉ፡- አብዛኛው የመንግሥት ተቋማት የጂኦስፓሻል መረጃዎች ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ብሔራዊ ደኅንነት፣ ትራንስፖርት ሚኒስቴርና ብዙ የመንግሥት ተቋማት መረጃዎችን ከኢንስቲትዩቱ ይወስዳሉ፡፡ መረጃ መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን በየጊዜው የመረጃ ጥራትና ደኅንነትን ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ባለው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ እንቅስቃሴዎች የሚያገለግል ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ መሠረታዊ ቶፖግራፊክ ካርታዎች ያመርታል፡፡ ለመሠረታዊ ካርታ ሥራ የሚያገለግሉ ግብዓቶች ያሰባስባል፡፡ የካርታ ስታንዳርድና ስፔስፊኬሽን ተከትሎ ስራውን እያከናወነ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ከኢንስቲትዩቱ የአሥር ዓመታት ሥራ ዕቅድ ዋና ዋናዎቹን ቢዘረዝሩልን?

ዶ/ር ቱሉ፡- የአሥር ዓመቱ የመሪ ልማት ዕቅድ ብዙ ናቸው፡፡ ጠንካራ የጂኦስፓሻል መሠረተ ልማት መገንባት አንዱ ነው፡፡ ይህም ሲባል ጂኦዴቴክ አገልግሎት ማዘመን፣ የጂኦስፓሻል መረጃ ማዕከል መገንባት፣ የመረጃ ተደራሽነትን ማረጋገጥ፣ የሥራ ዕድል መፍጠር ናቸው፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያን የዲጂታል ዕድገት ለማረጋገጥ ለ73 ከፍተኛና መካከለኛ ከተሞች ዲጂታል የአድራሻ ሥርዓት መዘርጋት፣ የጂኦስፓሻል ሽፋንን በኢትዮጵያ የልማት ኮሪደሮችና በብሔራዊ ደረጃ ማሳደግና ወቅቱን የጠበቀ መረጃ ተደራሽ ማድረግ የመሪ ልማት ዕቅዱ ቁልፎች ናቸው፡፡ የአየር ላይ ፎቶግራፍ ሽፋን ከ40 በመቶ ወደ መቶ በመቶ ማሳደግ፣ የአየር ፎቶግራፍ መረጃ ክለሳን በ20 በመቶ ማሳደግ በዋናነት የጠቀሳሉ፡፡ የመሪ ልማት ዕቅዱን ለማሳካት ኢንስቲትዩቱ ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል፡፡

ሪፖርተር፡- የጂኦስፓሻል ዘርፍ ፈተናዎች ምንድናቸው?

ዶ/ር ቱሉ ፡- የቴክኖሎጂ አቅምን ለመፍጠርና የተፈጠሩ አቅሞችን በአግባቡ ለመጠቀም የውጭ ምንዛሪ አቅርቦ እጥረት፣ አስተማማኝ ቴክኖሎጂ ለመታጠቅ አመቺ የግዥ አሠራር አለመኖር፣ ከአገር ውጭ ባለው የጂኦስፓሻል ኢንዱስትሪ ገበታ ላይ መሳተፍ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ያለመኖርና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ችግሮች አሉበት፡፡ ነገር ግን እዚህ ችግሮች ኢንስቲትዩቱን በማነቃቃት እንዲሁም ለኅብረተሰቡ ስለ ጂኦስፓሻል ጥቅም በማስረዳትና በማሳወቅ ዘርፉ ወደ አንድ ዕርምጃ እንዲያድግ ለማድረግ ብዙ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡ በመንግሥት ከፍተኛ ትኩረት እንዲያገኝም ኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግዴታን መሠረት ያደረገ የጤና መድኅን ሥርዓት

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ማኅበረሰብ አቀፍና የማኅበራዊ ጤና መድኅን ሥርዓቶችን መሠረት አድርጎም ይሠራል፡፡ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት በኢመደበኛ...

የመሠረተ ልማት ተደራሽነት የሚፈልገው የግብርና ትራንስፎርሜሽን

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም አርሶ አደሩን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን የማሳደግ ዓላማ ይዞ የተመሠረተ ነው፡፡ ተቋሙ የግብርናውን ዘርፍ ሊያሳድጉ የሚችሉ ጥናቶችን...

‹‹በአሁኑ ሰዓት እየፈተነን ያለው እንደ ልብ ተንቀሳቅሰን መሥራት አለመቻላችን ነው›› አቶ ልዑል ሰገድ መኮንንን፣ አይሲዳ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር

አይሲዳ አገር በቀል የዕርዳታ ድርጅት በኤችአይቪ ሥርጭት ቁጥጥር ላይ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ከ1998 ዓ.ም. ወዲህ ራሱን እንደ አዲስ አዋቅሮ በተለይ ለሰው ሠራሽና ለተፈጥሮ አደጋዎች ምላሽ...