ጉዞ ከመገናኛ ወደ መርካቶ ሊጀመር ነው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ… ኢትዮጵያ… እናት አገር…›› ይላል ያ የምንወደውና በሰቀቀን የተለየነው የሙዚቃ ንጉሥ ጥላሁን ገሠሠ። ከአቅሟ በላይ የተገጠመላት ስፒከር ሚኒባስ ታክሲያችንን ሊያንሳፍፋት ደርሶ ይነዝራታል። ኮሮና ተረስቶ በሙሉ ወንበር በመጫናችን፣ አንዳችን ሌላኛችንን በዓይነ ቁራኛ እየጠበቅን የኪስ ዘበኛ ሆነናል። የዘንድሮ ኑሮ ከሰውነት ተራ ማጉደሉ አልበቃ ብሎት፣ ሌባ ኪሳችንን ሲያራቁተው በዓውደ ምን ይውጠን ይሆን? ይህችም ኑሮ ሆና ተመሥገን እያልን መኖራችን ሳያንስ፣ የነገ ተስፋችንን ለማምከን ታጥቀው የተነሱ ራስ ወዳዶች ደግሞ ጦር ሰብቀውብን መነሳታቸው ሲታሰብ ሕመሙ ይበረታል፡፡ ታክሲያችን ስትሞላ ወያላው አወያይ መስሎ ፊቱን ወደ እኛ አዙሮ ተቀመጠ። ‹‹…ኢትዮጵያ የእኔ መመኪያ…›› በትልቁ ስፒከር ወደ ጆሯችን እየተንቆረቆረ ነው፡፡ የእናት አገር ጉዳይ ሲነሳ ሁለመናችን ጆሮ ሆኖ በተመስጦ ሙዚቃውን እያዳመጥን ነው፡፡ የአገር ጉዳይ ነዋ!
‹‹ሾፌር ሙዚቃውን ትንሽ ቀነስ አድርገው እስኪ?›› አለ ከወያላው አጠገብ የተቀመጠ ለሾፌሩ የራቀ ተሳፋሪ ጮክ ብሎ። ሾፌሩ እንዳልሰማ በዝምታ አለፈው። ተሳፋሪው በስጨት ብሎ፣ ‹‹ለምን አትቀንሰውም? አይሰማህም እንዴ? አቦ ቀንሰው…›› አለ። ይህን ጊዜ ከግራ ከቀኝ የንዴት ተኩስ ሲከፈት፣ ሾፌሩ ግን በእርጋታ፣ ‹‹ወንድሜ ችግር ካለብህ ላቁምልህና ውረድ፣ ካልሆነ ግን የብዙኃኑን የአገር ፍቅር ስሜት አትፈታተን…›› ሲል ሰማነው። ይህን ጊዜ ሰውየው ደንገጥ ብሎ ዝም አለ፡፡ ከቀልቡ አልነበረም መሰል፡፡ መሀል ወንበር የተቀመጠው በጋዜጣ የተለበደ አዲስ መጽሐፍ ይዞ አንዱ እየሳቀና እ.ህ.ህ. እያለ ያነባል፡፡ ሌላው ቀና ብሎ ሲያየው፣ ‹‹ሐሳብን በሐሳብ የሚሞገትበት አሪፍ ዘመን ላይ በመድረሳችን ለፈጣሪ ምሥጋና ይድረሰው…›› አለ፡፡ ያኛው ‹‹ለምኑ?›› ሲለው መጽሐፉን ወደፊቱ ቀረብ እያደረገ፣ ‹‹ይኼውልህ አንድ ታላቅ የቀድሞ ባለሥልጣን የጻፉት መጽሐፍ ነው. . .›› ብሎት እንደገና ወደ ጆሮው ቀረብ ብሎ፣ ‹‹ባለሥልጣናቱ መጻፍ ሲጀምሩ ለዴሞክራሲ መልካም ነው፣ እንኳንም መጻፍ ጀመሩ፡፡ ካሁን በኋላ እንግዲህ በብዕር እየተተጋተግን እንሟገታለን፡፡ ድንገት ካላደፈረሱብን በስተቀር…›› አለው፡፡ ያኛው ደግሞ፣ ‹‹በሐሳብ መሞገት ሲያቅታቸው ሰይፍ ይዘው የተነሱ ምን ይደረጉ…›› ብሎ ጥያቄ ቢጤ ጣል ሲያደርግበት፣ ‹‹በሰይፍ የሚያመልኩ በሰይፍ ይወድቃሉ ነው የሚባለው…›› ሲለው ሳቅ በሳቅ ሆንን፡፡ ምን ይደረግ ታዲያ!
በዚህ መሀል ‹‹አወያይ…›› አለ አንድ ወጣት መሳይ ተሳፋሪ ወያላውን እያስተዋለ። ፊታችንን ስስ ፈገግታ እያለበሰው የታክሲ ገጠመኞቻችንን ማስታወስ ልንጀምር ስንል ቀጠለ። ‹‹የዛሬው የውይይት አጀንዳችን ምንድነው? ግልጽ አድርግልን እንጂ። ፈዘህ እንደ አንዳንድ የተኮፈሱ ባለሥልጣናት የምታየን ምን እንድንልህ ትፈልጋለህ?›› እያለ ጠየቀው። ትንፋሹ አንድ ሁለት መለኪያ ቀማምሶ እንደ ተሳፈረ ነገረን። ወያላው እየተቅለሰለሰ ዘወር ብሎ፣ ‹‹የዛሬው ርዕሳችን ጦርነት ድሮና ዘንድሮ ነው…›› ሲል ሁሉም አጨበጨቡለት። ‹‹ፀድቋል?›› ብሎ ጠየቀ፡፡ አዎንታችንን በፈገግታ ነገር ነው። የጨዋታችን አጀማመሩ እየኮረኮረን በሳቅ ተጥለቅልቀን። መሳቅ ያቃታቸው በበዙበት ጊዜ የሚስቁ ምንኛ የተባረኩ ያስብላል። ‹‹ለፀብ ከመቋመጥ ለሰላም ብናስብ በአሁኑ ጊዜ በምድራችን ላይ ከአርባ በላይ ጦርነቶች ባልኖሩ ነበር፤›› ሲል አንዱ መሀል መቀመጫ ያለው መጽሐፍ አንባቢ ከት ብሎ ሳቀ፡፡ ቀና ብለን ስናየው የግንባሩ ሥር ተገታትሯል፡፡ ወደው አይስቁ!
‹‹ማሳሰቢያ!›› አለን ጎልማሳው ወያላ፡፡ ‹‹ማንም ሰው ገንቢ የሆነ ትውስታና ንፅፅር እንዲያቀርብ ይጠበቅበታል. . .›› ሲል አሳሰበ። ውይይቱን ያስጀመረው ወጣት፣ ‹‹የዛሬን አያድርገውና ጦርነት በሰበር ዜና ላይቭ ሳይቀርብ ውጤቱ የሚሰማው ድርጊቱ ካለፈ ከወር በኋላ ነበር…›› ሲል፣ ‹‹አሁንስ?›› አለው ወያላው አቋርጦ፣ ‹‹አሁንማ ካፌ ውስጥ ተቀምጠው የጦር ሜዳ ውሎውን ከእነ መልክዓ ምድሩና አሠላለፉ ትን እስኪለን የሚተነትኑልን ጮካዎች ቢዝነስ እየሠሩብን ነው…›› እያለ ሲስቅ ፈገግ ተባለለት። ‹‹ምን ይህ ብቻ ሰበር ዜና ጠብቁ ብለው ሌሊቱን ሙሉ አስፈጥጠው የሚያድሩ ሚዲያ ተብዬዎችም አሉልህ እኮ፡፡ የሰበር ዜና ማስታወቂያ ከመብዛቱ የተነሳ እኛው ተሰባብረን እንዳንቀር ፈርቻለሁ…›› እያለ ተሳፋሪዎችን ሲያስደምም መሀል ወንበር የተሰየመው ባለመጽሐፍ ቀልቡ አልነበረም፡፡ ከመጽሐፉ ጋር ወጉን ቀጥሏል፡፡ ድንገት ‹‹ኧረ በለው…›› ሲል ዞር ብዬ አየሁት፡፡ ‹‹ይገርምሃል ይኼ ነገር እውነት ነው?›› ብሎ አንድ ዓረፍተ ነገር አስነበበኝ፡፡ ትከሻዬን እየሰበቅኩ ‹‹እንጃ!›› ማለት እንጂ ምን ልበለው? ከሰውየው ጋር አልጻፍኩት!
ወዲያው ያው ወጣት ተቀብሎ እንዲህ አለ፡፡ ‹‹ምነው ግን በእኛ ዘመን ክፋት እንዲህ ጣራ ነካ… ወገን የገዛ ወገኑን ለምን ገደለ? ውስጣችን ምን ዓይነት ካንሰር ቢበቅል ነው ሰይጣንን የሚያስንቁ ፍጡራን መሀላችን የተገኙት…›› ብሎ የአቋም መግለጫ የሚመስል ንግግሩን አሰማን። ሦስተኛ ወንበር ላይ የተቀመጡ ዕድሜ የጠገቡ አዛውንት ‹‹ልክ ብለሃል ልጄ። ይህንን ክፋትና ጭካኔ የሸፈነው እኮ ሥልጣንና በዘረፋ የተገኘ ሀብት ነው፡፡ ነቅንቀን ነቅንቀን ገለል ስናደርጋቸው አረመኔነታቸው ገሃድ ወጣ፡፡ አሁን ግን የእኛን ሕይወት የሚያጨልሙ በሕግ የሚዳኙበት ጊዜ መድረሱ መልካም ነገር ነው። ጊዜ የሰጠው ባለጌ ተከበር ሲባል እንቢ ካለ በልምጭ፣ ካልሆነ ደግሞ በክትክታ ዱላ ታስተነፍሰዋለህ፡፡ አይደለም እንዴ?›› ሲሉ ሁሉም በአዎንታ አንገታቸውን ነቀነቁ። መጽሐፍ አንባቢው፣ ‹‹እህህህ…›› እያለ እንደገና ‹‹ጉድ… ጉድ…›› ሲል ያበደ መሰለን፡፡ መጽሐፍ የሚያነብ ሳይሆን መርዶ የሰማ ይመስላል፡፡ ማን ያውቃል!
መጀመርያ ወንበር ላይ የተቀመጠች አንዲት ወጣት ባለመጽሐፉን ዞር ብላ አየችው፡፡ ሰውየው ጭንቅላቱን መጽሐፉ ላይ ደፍቷል፡፡ ‹‹ምን ሆኖ ነው?›› ስትል ሰውየው ድንገት ቀና ብሎ፣ ‹‹ይኼንን አንብበሻል?›› አላት፡፡ ተንጠራርታ ርዕሱን አየችው፡፡ ሳቅ ብላ ‹‹ጀምሬዋለሁ…›› አለችው፡፡ ‹‹እንዴት አገኘሽው?›› የሚል ጥያቄ አቀረበላት፡፡ ማስቲካዋን ጣጣጣጣ አድርጋ፣ ‹‹ልክ እንዳንተ ነበር የሆንኩት…›› አለችው፡፡ ‹‹እኔ ምን ሆኛለሁ?›› ብሎ ትኩር ብሎ አያት፡፡ ፊቷን መለስ አድርጋ፣ ‹‹ይኼ ሰውዬ ጤነኛ ነው?›› ብላ ወረደች፡፡ ሰውዬው ግራ ገብቶት ቀና ብሎ አየኝ፡፡ እኔም አየሁት፡፡ ወፈፍ አድርጎት ይሆን? የለም ግራ ገብቶት ነው፡፡ የጨነቀ ለታ አሉ!
ድሮና ዘንድሮ የሚለው አጀንዳችን ተረስቶ በድንገተኛ ማዕበል እየተገፋን መጓዛችንን ሳናቆም እንነጉዳለን። ታክሲያችን እንደ እርጅናዋ ሳትሆን እየከነፈች ወደ ታላቁ የገበያ ሥፍራ መርካቶ እየገሰገሰች ነው። ወያላው ወራጆችን እየሸኘ አዳዲስ ተሳፋሪዎች አስገብቷል። ሥራው ላይ ኮስታራ ይመስላል። ለሥራ የታጠቀ መንፈስ ባለቤት መሆኑ ብቻ ሞገስ ሰጥቶታል። ታታሪ ሠራተኛ ይከበር ዘንድ ይገባዋል እኮ ጎበዝ። ለዘመናት መኝታና ወሬ በበዛበት አገር ሠራተኛ አይከበርም ነበር፡፡ ከቶውንም ይናቅ እንደነበር ታሪካችን ይነግረናል፡፡ ይህ በደል ሆኖ ታይቶን ለማናውቅ ግድ ባይሰጠንም፣ ሰውን የሚያስከብረው ሥራው ነው ሲባል አልሰማችሁም? ብንሰማም እንረሳዋለን!
መንገዱ ላይ ሰው እርስ በእርሱ እየተጋፋ ዱላ ቀረሽ በሚመስል ሁኔታ ይተራመሳል። ድንገት ወያላው፣ ‹‹እንግዲህ ማን ጀግና ማን ፈሪ እንደሆነ እየለየ ነው…›› ሲል ስቀን ልንለየው የወሰንን እንመስል ነበር፡፡ ሰውየው ደግሞ መጽሐፉን እያጠፈ፣ ‹‹ደረስን አይደል?›› ብሎ ጠየቀኝ፡፡ ‹‹አዎን›› አልኩት፡፡ በትዝብት ስሜት እያየኝ፣ ‹‹እስካሁን ሳናግርህ ለምንድነው መልስ የነፈግከኝ?›› አለኝ፡፡ እየተገረምኩ፣ ‹‹ዝም ማለት መብቴ መሰለኝ…›› በማለት ቆጣ ብዬ አየሁት፡፡ ‹‹ማለቴ ስለመጽሐፉ ሳዋይህ ዝም አልከኝ እኮ?›› አለኝ የማኩረፍ በሚመስል ቅያሜ፡፡ ‹‹ስላላነበብኩት ነገር ምን ልበልህ ታዲያ?›› አልኩት፡፡ ‹‹ባይሆን ለአንዳንዶቹ አስተያየቶቼ ምላሽ ይኖርሃል ብዬ ሳስብ አንተ ግን ዘጋኸኝ…›› በማለት ቅያሜውን ነገረኝ፡፡ ወሬያችንን ሲሰማ የነበረው ወያላ ድንገት ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹ወንድሜ ምን ነካህ? ስለማያውቀው ጉዳይ ምን ይንገርህ? ነው ወይስ እንደ ሰዎቹ በሕዝብና በዴሞክራሲ ስም እየቀለደ ጦርነት ቅስቀሳ ውስጥ ይክተትህ… በሐሰተኛ ትርክት ሕዝቡን እንደሚያባሉት ሰይጣኖች አንተንም ከራስህ ጋር ያጣላህ…›› ሲለው መርካቶ ደረስን፡፡ ይኼኔ ነበር አዛውንቱ ወያላው ታክሲው ላይ የለጠፈውን ጥቅስ ያሳዩን፡፡ ‹‹ራስህን አትካብ ተንቀሳቃሽ አፈር ነህና›› ይላል ጥቅሱ፡፡ ወይ ጉድ ራሳቸውን ሲክቡ የነበሩት የት እንደ ደረሱ፣ መዘዙም የማይወጡበት አዘቅት ውስጥ ይከታል ነው መልዕክቱ፡፡ መልካም ጉዞ!