Friday, December 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ለሩብ በጀት ዓመት ያቀዱትን ሊተገብሩ አልቻሉም

ተዛማጅ ፅሁፎች

ይከስራል የተባለው የኮንስትራክሽን ዘርፍ አተረፈ

በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ሥር ከሚተዳደሩና በንግድና አገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ አምስት የልማት ድርጅቶች በ2013 የመጀመርያ ሩብ ዓመት 2.04 ቢሊዮን ብር ከየአገልግሎት ሽያጭ እንደሚያገኙ ታቅዶ 1.3 ቢሊዮን ብር ማግኘታቸው ተገለጸ፡፡ ከኮንስትራክሽን ዘርፍ ይከስራል የተባለው የኮንስትራክሽን ድርጅት አተረፈ፡፡

በአገልግሎት ዘርፍ የተካተቱት የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሸን፣ የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት፣ አዲስ አበባ ሒልተን፣ ፍል ውኃ አገልግሎት ድርጅትና የጊዮን ሆቴሎች ድርጅት ሲሆኑ፣ የ2013 የመጀመርያ ሩብ ዓመት የ1.3 ቢሊዮን ብር የሽያጭ አፈጻጸማቸው ከዕቅዳቸው አንፃር 55 በመቶ ብቻ ማሳካታቸውን የሚያመለክት ነው፡፡ ይህም በሩብ ዓመቱ ያገኙት ገቢ ከዕቅዳቸው ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ያነሰ መሆኑን ነው፡፡ ባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ግን ሒልተን ሆቴልን ሳይጨምር አራቱ የንግድ የአገልግሎት ዘርፍ ድርጅቶች አግኝተውት የነበረው ገቢ 1.73 ቢሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡ ዘንድሮ በአንድ ድርጅት የጨመረው ዘርፉ ያገኘው የትርፍ መጠን ግን 1.3 ቢሊዮን ብር መሆኑ የትርፍ ምጣኔው ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ ከ430 ሚሊዮን ብር በላይ ያነሰ መሆኑን ያመለክታል፡፡ የእነዚህ አምስት ድርጅቶች ገቢ ከዕቅድ አንፃር ሲታይ በ55 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱ በሩብ ዓመቱ ሊገኝ ይችላል የተባለውንም የትርፍ መጠን እንዲቀንስ አድርጎታል፡፡ በመረጃው መሠረት አምስቱ የንግድና የአገልግሎት ዘርፍ ድርጅቶች በ2013 የመጀመርያ ሩብ ዓመት ከታክስ በፊት ያገኛሉ ተብሎ የታቀደው 90 ሚሊዮን ብር ቢሆንም አፈጻማቸው ግን 64 ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡

ይህም የትርፍ አፈጻጸም ከዕቅዳቸው አንፃር ሲታይ 71 በመቶ እንደሆነም ታውቋል፡፡ የ2013 የመጀመርያ ሩብ ዓመት የትርፍ አፈጻጸማቸው ከቀዳሚ ዓመት የትርፍ ግኝት ጋር ሲነፃፀር ከ13.6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያንስ ነው፡፡

የ2012 የመጀመርያው ሩብ ዓመት ዘንድሮ ያካተተውን ሒልተን ሆቴል ሳይጨምር ቀሪዎቹ አራቱ ድርጅቶች ከታክስ በፊት 47.21 ሚሊዮን ለማትረፍ አቅደው 77.6 ሚሊዮን ብር ማትረፋቸው ተገልጾ የነበረ መሆኑ አይዘነጋም፡፡

በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩት አምስቱ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የዘንድሮው ጥቅል የአገልግሎት ገቢያቸውና የትርፍ ምጣኔያቸውን ሊቀንሱ የቻሉባቸው የተለያዩ ምክንያቶች የሚጠቀሱ ሲሆን፣ በተለይ ዘርፉ ከአገልግሎት ጋር የተሳሰረ መሆኑና የአገልግሎት ዘርፉ ደግሞ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የታየው የሥራ መቀዛቀዝ ያስከተለው ተፅዕኖ ስለመሆኑ ይጠቀሳል፡፡

የእነዚህ ድርጅቶች ዕቅድም ከዚሁ ኮቪድ-19 ሊያስከትል ከሚችለው ተፅዕኖ ጋር በተያያዘ ሊኖር የሚችለውን ክፍተት ከግምት በማስገባት ከቀዳሚው ዓመት ባነሰ መልኩ የገቢያቸውንም ሆነ የትርፍ ምጣኔያቸውን ቀንሰው እንዲያቅዱ አድርጓቸዋል፡፡

እነዚህ ድርጅቶች የተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ በውጭ ምንዛሪ ገቢ የሚያስገኙ አገልግሎቶች ያሉዋቸው በመሆኑ፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝታቸው ቀንሶ ታይቷል፡፡ አምስቱ ድርጅቶች በ2013 የሒሳብ ዓመት ከጠቅላላ ገቢያቸው ውስጥ በውጭ ምንዛሪ ሽያጭ ያገኙበት ገቢ አራት ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት ኤጀንሲው እንዳስታወቀው በፋይናንስ ዘርፍ ሥር የሚገኙት ሦስቱ የመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት በጥቅል ያስመዘገቡት ገቢ በ2012 የመጀመርያ ሩብ ዓመት ያገኙት ገቢ ጋር ሲነፃፀር ወደ ግማሽ የተጠጋ ቅናሽ ታይቶባቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የኢትዮጵያ፣ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በጥምር ያገኙት የገቢ መጠን ከቀደመው ዓመት መጠነኛ ቅናሽ የታየበት ሲሆን፣ በተለይ በትርፍ ረገድ ግን ካለፈው ዓመት ከታክስ በፊት 6.5 ቢሊዮን ብር የነበረው ትርፍ በ2013 ወደ 3.8 ዝቅ ማለቱን መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኤጀንሲው በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩት ሁለቱ የመንግሥት ድርጅቶች በ2013 የመጀመርያ ሩብ ዓመት አትራፊ መሆን መቻላቸው ተገልጿል፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን 573.57 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት አቅዶ 601.3 ሚሊዮን ብር ገቢ በማግኘት ከዕቅዱ በላይ ገቢ ማግኘት ችሏል፡፡

እንደ ኤጀንሲው መረጃ ኮርፖሬሸኑ በመጀመርያው ሩብ ዓመት 32.1 ሚሊዮን ብር ይከስራል ተብሎ የታቀደ ቢሆንም ተቋሙ ባካሄደው ለውጥ የታሰበው ኪሳራ ቀርቶ የ96.5 ሚሊዮን ብር ትርፍ ሊያስመዘግብ መቻሉ ተገልጿል፡፡

ሌላው በኮንስትራክሽን ዘርፍ ውስጥ የተካተተው የኢትዮጵያ ኮንስትራከሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ሥራዎች ኮርፖሬሸን ደግሞ በሩብ ዓመቱ አገኘዋለሁ ያለውን ያህል ገቢ ባያገኝም ከታክስ በፊት ያገኘው ትርፍ ከዕቅዱ መጠነኛ ጭማሪ ማሳየቱ ተገልጿል፡፡

በኤጀንሲው መረጃ መሠረት የኢትዮጵያ ኮንስትራከሽን ዲዛይንና ሱፐር ቪዥን ኮርፖሬሸን በሩብ ዓመቱ 255.6 ሚሊዮን ብር ገቢ አቅዶ 178.6 ሚሊዮን ብር ገቢ አግኝቷል፡፡ ገቢው በ70 በመቶ የቀነሰ ቢሆንም ከታክስ በፊት 49.5 ሚሊዮን ብር ማግኘት ችሏል፡፡ ይህም ከዕቅዱ የሁለት በመቶ ጭማሪ ያሳየ ነው፡፡ ዕቅዱ 48.63 ሚሊዮን ብር ለማግኘት እንደነበርም ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች