Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዋሽ ባንክ በትርፉና በሀብቱ ቀዳሚ የግል ባንክ መሆኑ ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለባንኩ አመራሮች የ75 ሚሊዮን ብር ሽልማት ሰጠ

ቀዳሚ ከሆኑት ኢትዮጵያ የግል ባንኮች አንዱ የሆነው አዋሽ ባንክ፣ በ2012 የሒሳብ ዓመት ያልተጣራ የትርፍ መጠኑን ከ4.2 ቢሊዮን ብር በላይ በማድረስ የሒሳብ ዓመቱን ማጠናቀቁን ገልጿል፡፡ ከታክስና ሌሎች ተቀናሾች ተደርገው 2.6 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱንም አመልክቷል፡፡ ይህም ከቀዳሚው ዓመት የሰባት በመቶ ብልጫ ያሳየ መሆኑን ቅዳሜ ኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ባካሄዴው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ይፋ አድርጓል፡፡

በ2012 የሒሳብ ዓመት ያስመዘገበው ትርፍ መጠን በ25 ዓመት በባንክ ኢንዱስትሪ ታሪክ እስካሁን ያልተመዘገበ ከፍተኛ ትርፍ መሆኑም ተገልጿል፡፡ ከትርፍ ባሻገር በሒሳብ ዓመቱ የባንኩን አፈጻጸም የሚያሳዩ አኃዛዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ የባንኩ 2012 የሒሳብ ዓመት ያስመዘገበው ትርፍ የተገኘው በተለያዩ አፈጻጸሞቹ ባስገኘለት አመርቂ ውጤት መሆኑን የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ዲባባ አብደታ (አምባሳደር፣ ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ ከዓመታዊ መረጃው መገንዘብ እንደተቻለውም፣ አዋሽ ባንክ በ2012 የሒሳብ ዓመት ማጠናቀቂያ ላይ በተቀማጭ ገንዘብ ረገድ የ19 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ 74.3 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በብድር አሰጣጥ ረገድም በሒሳብ ዓመቱ የብድር መጠኑን በ21 በመቶ በማሳደግ፣ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የተሰጠውን ብድር መጠን 57.4 ቢሊዮን አድርሷል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የባንኩ የተበላሸ ብድር ምጣኔ 1.7 በመቶ መሆኑም ባንኩ በብድር አመላለስ ላይ ያሳየው አፈጻጸም ውጤታማ እንደሆነ የሚያሳይ ነው ተብሏል፡፡

ባንኩ ከግል ባንኮች ቀዳሚ መሆኑን ከሚያመላክቱት ማሳያዎች አንዱ የባንኩ አጠቃላይ የሀብት መጠን ሲሆን፣ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ የባንኩ አጠቃላይ የሀብት መጠን 28 በመቶ ወይም 14.6 ቢሊዮን ብር ዕድገት በማሳየት 89.3 ቢሊዮን ብር መድረሱ ነው፡፡ የባንኩ ካፒታልም በ2011 መጨረሻ ላይ ከነበረበት 4.39 ቢሊዮን ብር፣ በ2012 መጨረሻ ላይ የ1.46 ቢሊዮን ብር ወይም የ33.4 በመቶ ዕድገት በማሳየት 5.85 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህም በግል ባንኮች ውስጥ ከፍተኛ የሚባል የተከፈለ ካፒታል መጠን ነው፡፡

ባንኩ የተከፈለ ካፒታሉን ወደ 12 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት፣ ባንኩ የ2012 የሒሳብ ዓመት ጠቅላላ ገቢ ከ10.2 ቢሊዮን ብር በላይ በማሳደግ የመጀመርያው የግል ባንክ መሆን ችሏል፡፡ ካለፈው ዓመት በ27 በመቶ ወይም በ2.2 ቢሊዮን ብር ብልጫ ከማሳየቱም በላይ፣ በሒሳብ ዓመቱ አገኛለሁ ብሎ ካቀደው ጠቅላላ ገቢ ደግሞ የ662.5 ሚሊዮን ብር ብልጫ አሳይቷል፡፡

ዓመታዊ ወጪው ደግሞ በ32 በመቶው የጨመረ ሲሆን፣ የ2012 ዓመታዊ ወጪ 6.2 ቢሊዮን ብር መድረሱም ተመልክቷል፡፡ ከጠቅላላ ወጪ ትልቁ ድርሻ የያዘው ለተቀማጭ ወለድ የተከፈለና የሠራተኞች ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ነው፡፡ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል 12 ቢሊዮን ብር እንደሚደርስም አስታውቋል፡፡  

በተጠናቀቀው ሒሳብ ዓመት በርካታ ተግዳሮቶች የነበሩበት ቢሆንም፣ ባንኩ ባስቀመጠው ስትራቴጂ መሠረት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ቀውሶችን ተቆጣጥሮ አመርቂ ውጤት ሊያስመዘግብ መቻሉን የአዋሽ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ዲባባ (ዶ/ር፣ አምባሳደር) ለጠቅላላ ጉባዔው ገልጸዋል፡፡

‹‹የተጠናቀቀው በጀት ዓመት በዓለማችን ከተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተነሳ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ በአጠቃላይና ለባንኪንግ ኢንዱስትሪው ደግሞ በተለየ ሁኔታ ፈታኝ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄደው የዋጋ ንረት፣ በኢንዱስትሪው ተግዳሮት ሆኖ እንደቆየ የቦርድ ሊቀመንበሩ አስታውሰው፣ ከዚህም ሌላ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የነበሩ የፖለቲካ አለመረጋጋቶችና የፀጥታ ሥጋቶች፣ እንዲሁም በባንኮች መካከል ያለው ከፍተኛ ፉክክር እያደገ የመጣበት ዓመት የነበረ ብለዋል፡፡ ሆኖም ባንኩ ያስመዘገበው አኩሪ ውጤት ከቀደሙት ዓመታት እጅጉን የላቀ እንደነበር አመልክተዋል፡፡  

የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በርካታ ተግዳሮቶች የነበሩ ቢሆንም፣ እነዚህን ተግዳሮቶች በመቋቋምና የተሻለ አፈጻጸም እንዲገኝ በተደረገው ጥረት፣ ባንኩ ለአምስተኛ ጊዜ መሪነቱን አረጋግጦ እንዲቀጥል አስችሎታል፡፡

የባንኩ ባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በኢንዱስትሪው ብዙም ያልተለመደ የተባለ፣ ግን መበረታታት የሚኖርበት ዕውቅና አሰጣጥ መፈጸሙንም የቦርድ ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡ ይህም ባንኩን ለተከታታይ ዓመታት በከፍተኛ አትራፊነት ደረጃ ላይ እንዲበቃና ጠንካራ መሠረት እንዲኖረው በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የባንኩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች 75 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው ሽልማት እንዲሰጥ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

የባንኩን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጨምሮ ለምክትሎቻቸው ቦርዱ የሰጠውን ዕውቅና በተመለከተ የቦርድ ሊቀመንበር ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ ባንኩ አሁን ላለበት ደረጃ ያበቁ በመሆናቸው ዕውቅናው እንደተሰጣቸው አመልክተዋል፡፡ ‹‹በእነዚህ ሁሉ ዓመታት አስደማሚ ውጤት ላስመዘገቡት ለባንኩ ሠራተኞች ምሥጋና የሚገባቸው ከመሆኑም በላይ፣ በከፍተኛ ባለአክሲዮኖች በቀረበው በጎ ሐሳብ መሠረት ባለፉት አሥር ዓመታት ባንካችንን በፕሬዚዳንትነት ላገለገሉት የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚና ለከፍተኛ የማኔጅመንት አባላት በተለየ ሁኔታ የዕውቅናና ሽልማት እንዲሰጣቸው በተወሰነ መሠረት ተፈጻሚ ሆኗል፤›› ብለዋል፡፡

በዚሁ መሠረት የባንኩን አመራር ኃላፊነት ከተረከቡ ጊዜ ጀምሮ ባንኩን በተከታታይ አሥር ዓመታት ትርፋማና ውጤታማ ላደረጉ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ባንኩን ከነበረበት የሁለተኛ ደረጃ ወደ መሪ የግል ባንክ በማሳደግ ኃላፊነታቸውን በብቃትና በታማኝነት ለተወጡት ለዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ፀሐይ ባንኩን የሚመጥን ቤት ተገዝቶ እንዲሰጣቸው መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ ለዋና ሥራ አስፈጻሚው ባንኩ የገዛላቸው አንድ የመኖሪያ ቤት በቦሌ አካባቢ የሚገኝ ሲሆን፣ ቤቱ የተገዛበት ዋጋም 45 ሚሊዮን ብር እንደሆነም ተገልጿል፡፡

ለዋና ሥራ አስፈጻሚው ከተበረከተው የዕውቅና ስጦታ ባሻገር ለሰባት ምክትል ፕሬዚዳንቶች ደግሞ በድምሩ 30 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ተገዝቶ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ‹‹የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ከስድስት ቢሊዮን ብር ወደ 12 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ ሲወሰን፣ ከተጨማሪው አዲስ ስድስት ቢሊዮን ብር ውስጥ ከአምስት በመቶ በላይ 300 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ለሠራተኞች እንዲሸጡ መደረጉ ይታወሳል፡፡ ለሠራተኞች እንዲሸጡ ከተመደቡት 300 ሚሊዮን አክሲዮኖች ውስጥ የ30 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች ለሰባት ከፍተኛ የማኔጅመንት አባላት በባንኩ ወጪ አክሲዮኖች ተገዝተውላቸዋል፡፡ አክሲዮኖቹ ግዥ የተፈጸመላቸው ከፍተኛ የማኔጅመንት አባላት ውስጥ ለአምስት ምክትል ፕሬዚንቶች ለእያንዳንዳቸው የአምስት ሚሊዮን ብር አክሲዮን ተገዝቶላቸዋል፡፡ ለሁለት ምክትል ፕሬዚዳንቶች ደግሞ የአራት ሚሊዮን ብርና የአንድ ሚሊዮን ብር አክሲዮኖች በባንኩ ወጪ ተገዝተው የዕውቅና ሽልማት ከምሥጋና ጋር እንዲሰጣቸው መደረጉንም ቦርድ ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡

የዕውቅና ሽልማት አሰጣጡም የተወሰኑ ከፍተኛ የባንኩ ባለአክሲዮኖች፣ አዋሽ ባንክና አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ የቦርድ ዳይሬክተሮችና የማኔጅመንት አባላት በተገኙበት ኅዳር 10 ቀን 2010 ዓ.ም. የተበረከተ መሆኑም ታውቋል፡፡ የቦርድ ሰብሳቢው ይህ የማበረታቻ ሽልማት የባንኩ አመራሮች ከዚህ በፊት ላስመዘገቡት ከፍተኛ ውጤትና ባንኩን ከግል ባንኮች ከነበረበት የሁለተኛ ደረጃ ወደ አንደኝነት ደረጃ በማሳደጋቸው የተደረገ ዕውቅና ብቻ አለመሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ለወደፊትም ባንካችን ለሚያስመዘግባቸው ውጤቶች ወሳኝና እንደ እርሾ ሆኖ ለበለጠ ሥራ መነሳሻ እንደሚያገለግል የቦርዱ እምነት ብቻ ሳይሆን የተከበሩ የአዋሽ ባንክ ባለአክሲዮኖችም ፅኑ እምነት ጭምር እንደሆነ ቦርዱ ያምናል፤›› ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የባንክ ኢንዱስትሪው ውድድር ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ወቅትና ወደ 15 የሚጠጉ አዳዲስ ባንኮች ኢንዱስትሪውን ለመቀላቀል በዝግጅት ላይ በሚገኙበት ስለሆነ፣ ባንኩ ማኔጅመንት ከዚህ በፊትም ሠርቶ ያሳየና አዋሽን ወደ ተሻለ ደረጃ ያሳደገ ማኔጅመንት ስለሆነ፣ በቀጣይነትም በተለመደው ታማኝነት እንደሚያገለግሉ በማሰብ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ዕውቅና ከፍተኛ ሀብት የሚያስተዳሩ የሥራ ኃላፊዎች ላስገኙት ውጤት በዚህ ደረጃ ዕውቅና መስጠቱ ሥራቸውን በኃላፊነት እንዲወጡ በማድረጉ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ እንደሚታመን ተጠቅሷል፡፡ በተለይ የባንኩ ፕሬዚዳንት በዚህ ደረጃ ዕውቅና እንዲሰጣቸው ካደረጋቸው በርካታ ምክንያቶች ውስጥ፣ ባንኩን ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ያደረሱበት ደረጃ ታይቶ ጭምር መሆኑን የባንኩ የቦርድ ሊቀመንበር አመልክተዋል፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታት ባንኩ ከየት ወዴት ደረሰ የሚለው አኃዛዊ መረጃዎችን ጭምር ያቀረቡት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ በዕለቱ በሪፖርታቸው ውስጥ ካካተቱት መካከል አንዱ ከግል ባንኮች ሁለተኛ ደረጃ ላይ የነበረውን አዋሽ ባንክ ወደ አንደኛ ደረጃ ማምጣታቸው ነው፡፡

የቦርድ ሊቀመንበሩ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ አሁን ባንኩ የደረሰበት የ74 ቢሊዮን ብር የተቀማጭ ገንዘብ መጠን፣ ባንኩ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ከግል ባንኮች የነበረውን የመሪነት የገበያ ድርሻ በእጅጉ እንዲያሰፋ ያደረገው ሲሆን፣ ይህም ዕውቅና የተሰጣቸው ዋና ሥራ አስፈጻሚው ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ባደረጉት አመራር የተገኘ ውጤት መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

ባንኩ ከተቀማጭ ገንዘብ ረገድ ባለፉት አሥር ዓመታት በየዓመቱ በአማካይ ሰባት ቢሊዮን ብር ዕድገት ሲያስመዝገብ የነበረ መሆኑን የጠቀሱት ዲባባ (ዶ/ር)፣ በንፅፅር ያስቀመጡትም በ2002 የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ 6.1 ቢሊዮን ብር እንደነበርና አሁን 74 ቢሊዮን ብር መድረሱ በአሥር ዓመታት ውስጥ የታየውን ለውጥ የሚያሳይ ነው፡፡  

በትርፍ ረገድም የአሥር ዓመት ክንውኑን ወደ ኋላ መለስ በማለት በሪፖርታቸው ያካተቱት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ እ.ኤ.አ. በ2010 ላይ የባንኩ ትርፍ 351 ሚሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ 4.2 ቢሊዮን ብር መድረሱ ባለፉት አሥር ዓመታት ባንኩ በምን ያህል ደረጃ እያደገ እንደመጣ ያመላክታል ተብሏል፡፡

በተመሳሳይ ከአሥር ዓመታት በፊት የባንኩ ሀብት ከዘጠኝ ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ አሁን 89.3 ቢሊዮን ብር መድረሱን በመጥቀስም፣ በአሥር ዓመታት ውስጥ የሀብት መጠኑን በ80.3 ቢሊዮን ብር ማደጉም ተመልክቷል፡፡ አዋሽ ባንክ በ2012 የሰጠው የብድር መጠን ካለፈው ዓመት አንፃር የ9.6 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው ነው፡፡

የባንኩን የአሥር ዓመት ጉዞና ውጤታማነቱን ለማሳየት ሌላው እንደ ምሳሌ የተነሳው፣ የባንኩ ቅርንጫፎች ቁጥር ነው፡፡ በአሥር ዓመት ውስጥ የባንኩ የቅርንጫፎች ብዛት 461 በመጨመር 465 መድረሱን ገልጸዋል፡፡ ይህም በአማካይ ባለፉት አሥር ዓመታት በየዓመቱ 40 ቅርንጫፎች መከፈታቸውን ያሳያል፡፡ የባንኩ የተከፈለ ካፒታልም የዛሬ አሥር ዓመት 550 ሚሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ 2012 ላይ ግን 5.58 ቢሊዮን ብር ለመድረሱ አሁን ዕውቅና የተሰጣቸው የሥራ ኃላፊዎች ባደረጉ አስተዋጽኦ ጭምር መሆኑም ተመልክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች