በኢትዮጵያ የካንሰር ሕሙማን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢመጣም፣ የሕክምና አገልግሎቱ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ በተለይ ለካንሰር ሕክምና ከሚያስፈልጉት አንዱ የሆነው የጨረር ሕክምናን ለማግኘት እስከ ዓመት የሚዘልቅ ወረፋ መጠበቅ ግድ ይላል፡፡ በዚህ መሀል በርካቶች ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡ ጤና ሚኒስቴር ችግሩን ለመቅረፍ አዲስ አበባን ጨምሮ በስድስት ሥፍራዎች የጨረር ሕክምናን ለማስፋፋት እየሠራ ይገኛል፡፡ ካለፉት 20 ዓመታት ወዲህ ብቸኛ ሆኖ የጨረር ሕክምና እየሰጠ የሚገኘው ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በሁለት ማሽኖች እየሠራ የነበረ ቢሆንም፣ አንዱ በመበላሸቱ በአንድ ማሽን ብቻ እንዲሠራ ተገዷል፡፡ ችግሩን ለማቃለል አዲስ ሊነር አክስለሬተር (የጨረር መሣሪያ) አስገብቶ ሥራ አስጀምሯል፡፡ ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. የማሽኑ በይፋ ሥራ መጀመር የተገለጸ ሲሆን፣ በሥነ ሥርዓቱ ላይም የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር)፣ የቀድሞ ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ፣ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የካንሰር ሕክምና ማዕከል ኃላፊ አይናለም አብርሃም (ዶ/ር) እና የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል፡፡