ሰላም! ሰላም! እንዴት ከረማችሁ? አከራረማችንንማ በድል ደምቆ እንዳሸበረቀ እየታየ ነው እንደምትሉኝ ይገባኛል፡፡ የዓመታት ግራ መጋባታችንና በገዛ አገራችን መቀለጃ የሆንበት ምክንያት፣ በጠቅላዩ አንደበት ሲነገረን እንዴት እንደነዘረኝ አልነግራችሁም፡፡ ያው እንደምታውቁት የደላላ ጆሮ ንቁ ነው፡፡ ከየአቅጣጫው የሚባለውን በቅጡ ካላዳመጠ አንድም ከመረጃ መረብ ውጪ ይሆናል፣ ሌላም የእንጀራ ገመዱ ተበጠሰ ማለት ነው፡፡ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ጆሮዬ ብቻ ሳይሆን ሁለ ነገሬ ያዳምጣል፡፡ አዳምጣለሁ ብቻ ሳይሆን በምሁሩ ወዳጄ ዕገዛ የተባለውን ሁሉ በየፈርጁ ለመተንተን እሞክራለሁ፡፡ የተነተንኩትን ደግሞ ወደ ገንዘብ ለመለወጥ እነዚያ እንደ መቃ የሰለሉ እግሮቼን ለጉዞ አዘጋጃቸዋለሁ፡፡ እኔ ወደ ጥሪት ፍለጋ ስኳትን ሞባይሌ ሥራ አይፈታም፡፡ አንዱ ምን አለኝ መሰላችሁ? ‹‹በመልዕክት ማስተላለፊያዬ አሁንም አሁንም ወደተለያዩ ሰዎች የምፈልገውን እልካለሁ፣ የመጡልኝን እቀበላለሁ፡፡ ወጪ በመቆጠብ የተሻለ ገቢ ማግኘት ብቻ ሳይሆን፣ በስልክ እየለፈለፉ መረጃን አሳልፎ መስጠትም ጎጂ ልማድ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በ‹ቴክስት ሜሴጅ› ከወዳጆቼና ከደንበኞቼ ጋር መገናኘቴን ቀጥያለሁ፤›› ሲለኝ፣ ባለ‹ቴክስት ሜሴጅ› ጦረኞች ምን እንደ ደረሰባቸው አያውቅም እንዴ ይኼ ሞኝ ዝም ብሎ የሚንደቀደቀው? ምን ዓይነቱ ወንፊት ነው!
አንዱ ደግሞ፣ ‹‹አንበርብር ቀን ሊወጣልህ ነው አሉ…›› ሲለኝ ምን ለማለት ፈልጎ ይሆን በማለት፣ ‹‹እስኪ አንተው ንገረኛ እንዴት ቀን እንደሚወጣልኝ…›› ብዬ መንገድ ከፈትኩለት፡፡ ትዕግሥትና ብልኃት ሲኖር እኮ ዘዴውም ይከሰትልናል፡፡ ተናደን ስንቸኩል ግን ፈንጂ እየረገጥን እንበላለን፡፡ እኔም ወጥመዴን ዘርግቼ ላስለፈልፈው ነው ይህንን ነገረኛ፡፡ ‹‹ያው ከወሳኝ ምንጮቼ ባገኘሁት አስተማማኝ መረጃ መሠረት…›› እያለ እንደ ዘመኑ ያልበሰሉ ተንታኞች ነገሩን ሲያደራ፣ ምንም እንዳልተፈጠረ ዓይኑን እያየሁ እጠባበቀው ጀመር፡፡ አስተያየቴ አላማረውም መሰል፣ ‹‹ምነው?›› አለኝ፡፡ እኔም ሳቅ እያልኩ፣ ‹‹የጀመርከውን ጨርስልኝ እንጂ…›› ብዬ ፈርጠም ስል፣ ‹‹እዚህ አገር እኮ ከአስተማማኝ ምንጭ መረጃ ሲገኝ ማጣጣል ልማድ ነው…›› ብሎኝ እየተነጫነጨ ጥሎኝ ሄደ፡፡ ወይ ጉድ ነገሩን ያመጣው እሱ፣ መልሶ የሚበሳጨው እሱ፡፡ የብስጭቱ ምክንያት የገባኝ ቆይቶ ነው፡፡ እሱ ከየትም የለቃቀመውን ተራ የመንደር ወሬ ከአስተማማኝ ምንጭ ብሎ ሊነግረኝ ሲግደረደር፣ እኔ ደግሞ ሰፍ ብዬ ዓይኖቼን እያንከራተትኩ እንድሰማው ነበር ለካ የፈለገው፡፡ ስንቶች በስንቶች እንቶ ፈንቶ ወሬ አዕምሮአቸው የሚጦዘው እኮ ትዕግሥትና ስክነት ስለሚጎድላቸው ነው፡፡ በጦር ሜዳ ተሸንፎ እግሩን ነቅሎ የሚሸሽ እንደ አሸናፊ በየፌስቡኩ ሲዘላብድ፣ እውነት መስሏቸው የሚቆዝሙ የዋህ ወዳጆቼን ሳስብ ውስጤ ይስቃል፡፡ ለመደሰት ትንሽ የሚበቃቸው በአልባሌ ወሬም ሲፍረከረኩ ግርም ባይለኝም ያሳዝኑኛል፡፡ ለስንቱ እንዘን!
ደላላ በተፈጥሮው የቆቅ ባህሪ እንዳለው እኔ ራሴ ህያው ምስክር ነኝ፡፡ ጠቅላዩ እንዳሉት የትውስታ ችግር ብዙዎቻችንን የሚያጠቃን ቢሆንም፣ ደላላ ግን የዛሬ አሥር ዓመት የተሰጠውን የስልክ ቁጥር በቃሉ እንደማይረሳ ስነግራችሁ በእርግጠኝነት ነው፡፡ የጠቅላዩን ትዕግሥትና ወደር የለሽ ችሎታ የማስታውሰውን ያህል፣ እዚህች መከረኛ አገር ውስጥ የደረሱ በርካታ ውጥንቅጦችን አልረሳቸውም፡፡ ልክ እንደ ፖሊስ የዕለት ሁኔታ መዝገብ ሁሉንም ፈተናዎቻችንን አዕምሮዬ መዝግቧቸዋል፡፡ ዝነኛው የክራር ንጉሥ ካሳ ተሰማ ነፍሱን ይማረውና፣ ‹‹አላውቅም ነበር ትናንትና ሲያልፍ ለካስ ዛሬ ኖሯል የሚያስለፈልፍ›› እንዳለው፣ ችግሮቻችን ሁሉ ተሸፋፍነው ኖረው ልክ እንደ መንገድ ዳር ቱቦ ድንገት ሲፈነዱ የተፈጠረብንን አስቡ፡፡ ነገር ግን እኔና ቢጤዎቼ የስንቶቹን ጥጋብና ዕብሪት በዚህች በተቀደሰች ምድር ላይ እንዳየን ብነግራችሁ፣ ሌላ ራስ ምታት መጨመር ስለሆነ ትንሽ እንሰንብት፡፡ ጠቅላዩ ግን ከነገሩን በላይ ለታሪክ ድርሳናት የሚሆኑ ብዙ ዘግናኝ ነገሮችን በሆዳቸው ያመቁ ይመስለኛል፡፡ ስንቱ ታምቆ ይቻል ይሆን!
የቀኑን ውሎዬን አገባድጄ አመሻሽ ላይ ቤት ሲደርስ ማንጠገቦሽ በሚገባ አጫጭሳና አሟሙቃ ነበር የጠበቀችኝ፡፡ የቡናው እንፋሎት የቤቱን አየር እያወደው ባልና ሚስት ገና ጫጉላቸውን እንዳልጨረሱ ተጋቢዎች የመሆን ያህል እስኪሰማን ድረስ በሐሴት ተሞልተናል፡፡ በስንት ልፋትና ውጣ ውረድ የተገኘ ኮሚሽን ማንጠግቦሽ እጅ ሲገባ፣ የእኔ ብኩንነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያበቃለት ይመስል ነበር፡፡ ድሮ ከድለላ ይገኝ የነበረው ኮሚሽን ከላዩ ላይ ለመጠጥ ግብዣና ለአዝማሪ ይቀሽብለት እንዳልነበር፣ ዛሬ ግን በእርግጥም ታሪክ ሆኗል፡፡ ልክ እንደ ጀብደኞች የእኔም አመል አናቱን የተመታ ይመስል፣ ቤቴ በጊዜ መግባት ከጀመርኩ ሰነባበትኩ፡፡ በባሏ የአስተሳሰብና የባህርይ ለውጥ የተደመመችው ማንጠግቦሽ፣ ‹‹የአገራችን አንዳንድ መፈክሮች ቢቀየሩ?›› አለችኝ፡፡ እኔም ግራ ገብቶኝ፣ ‹‹የትኞቹ መፈክሮች?›› በማለት ስጠይቃት ማንጠግቦሽ በባሏ ግራ መጋባት እየተደመመች፣ ‹‹ድህነትን ታሪክ ነው ተረት እናደርጋለን የሚሉት…›› ስትል ተግባብተን አንድ ላይ መሳቅ ጀመርን፡፡ ‹‹እነሱ ተዝቆ የማያልቅ ሀብት ከአገር እየዘረፉ ጠግበው፣ እኛን የድህነት አዘቅት ውስጥ ከተውን ሲያሾፉብን የነበረው ሳይበቃቸው፣ ነፃ አወጣናችሁ ብለው በዕብሪት ሲጀነኑብን እንዳልነበር ይኸው አንድዬ በሰው ተመስሎ ልክ አስገባልን…›› ስትለኝ አንገቴን በአዎንታ ከመወዝወዝ በቀር ቃላት አልነበሩኝም፡፡ ጥጋበኛን ለማብረድ ለእሱ ምን ይሳነዋል!
ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹አገር በመፈክር አይለወጥም…›› በማለት ዘወትር የሚነግረኝ አይረሳኝም፡፡ ‹‹በየመንገዱና በየጥጋጥጉ መፈክር ሰቅሎ እንቅልፍ የሚለጥጥ አገር አያልፍለትም…›› ሲልም በአንክሮ እሰማው ነበር፡፡ ይህ መልዕክት ለእኔ አዲስ ባይሆንም፣ ጠቅላያችንም በሚገባ አስረግጠው ነግረውናል፡፡ ተመፅዋች ሆነን ሉዓላዊ አገር መሆን እንደማንችል፣ ራሳችንን ስንችል ግን እንደምንከበር ደጋግመው ነግረውናል፡፡ የትውስታ ችግር ከሌለብን በስተቀር፡፡ እርግጥ ነው እኔ ደላላው አንበርብር ይህንን ከደምና ከአጥንት ጋር የተዋሀደ ንግግር መረሳት የለበትም እላለሁ፡፡ ዕቅድ የሚሳካው ዕቅዱን ሊደግፉ የሚችሉ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች በስልትና በጥበብ ሲታገዙ ብቻ ነው፡፡ የመፈክር ጋጋታ ሲበዛ አንድ ችግር እንደለ ግልጽ ነው፡፡ ‹‹መፈክር የሚያበዙ ለመሥራት ያልወሰኑ፣ ወይም ከንድፈ ሐሳብ ተላቀው ወደ ተግባር ለመግባት የማይችሉ ናቸው…›› ሲልም የነገረኝ ይኼ የዘወትር መምህሬ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ የባሻዬ ልጅ አስተምህሮ እኔን የማለዳ ወፍ አድርጎኛል፡፡ የተገኘውን ቀራርሞ ወደ መጠጥ ቤት የሚደረገው ጉዞ እንዲያበቃና ኑሮ በፕሮግራም መመራት እንዳለበት የሚጎተጉተውም እሱ ነው፡፡ ስለዚህ ከእኔና ከማንጠግቦሽ ቤት ድህነት በተግባር ታሪክ የሚሆንበት ጫፍ ላይ ተደርሷል፡፡ ስለዚህ ከሚገኙት መልካም አጋጣሚዎች የሀብትን መንገድ በሥራ ማመቻቸት የደላላው አምንበርብር ምንተስኖት የማይቀለበስ ዕቅድ ሆኗል፡፡ በመላው ኢትዮጵያም የጠቅላዩ ማሳሰቢያ ወደ ተግባር ተተርጉሞ የሀብት ተራራ ላይ እንድንቆም ፈጣሪ ይርዳን፡፡ አሜን በሉ!
አዛውንቱ ባሻዬ በምርኩዛቸው እየተረዱ ደረሱ፡፡ የማንጠግቦሽ ቡና አፍንጫቸውን የቀሰቀሰው በመሆኑ እንጂ፣ ሲመሻሽ የትም መሄድ አይፈልጉም ነበር፡፡ ‹‹ቡናሽ እንደ አቶሚክ ቦምብ ነቀነቀኝና ሳልወድ በግድ እየተጎተትሁ መጣሁ…›› አሏት፡፡ ማንጠግቦሽ ምንም እንኳን የባሻዬን በዚህ ሰዓት መምጣት ባትፈልገውም፣ የቡናዋ መሞገስ ደስ ስላሰኛት በፈገግታ ነው የተቀበለቻቸው፡፡ ባሻዬ እንደገቡ፣ ‹‹ልጅ አንበርብር ሥራ እንዴት ነው እባክህ? ይህንን ባውንድ ታፍሰዋለህ አሉ?›› በማለት ፀጥታውን ገፈፉት፡፡ ‹‹እግዚአብሔር የተመሠገነ ይሁን፣ ከላይና ከታች እየተሯሯጡ የሚያገኙት የሀቅ ገንዘብ ያስደስታል፡፡ ምንም ሳይለፉ እንደ መና በምትሀት የሚወርደው የገንዘብ ዶፍ ምንጩ አልገባን አለን እንጂ፣ የእኔ ምን አላት ብለው ነው?›› በማለት ምላሽ ስሰጣቸው ባሻዬ መሬቱን በከዘራቸው እየቆረቆሩ፣ ‹‹ልክ ነህ፡፡ አንዳንዴ እኮ አፍላ ኮበሌና ግማሽ እንጀራ የምትበላ የማትመስል ኮረዳ የሚሊዮን ብር አውቶሞቢል ነው የሚያሽከረክሩት ሲባል ቅዥት ይመስለኛል…›› ብለው፣ ‹‹እስኪ ዙሪያህን ተመልከት፡፡ ከሚሠራው ይልቅ እኮ የማይሠራው ነው የሀብት ቁልል ላይ ተደላድሎ የተቀመጠ የሚመስለው፡፡ ለማንኛውም አሁን ዋናው ሰንኮፍ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሲነቀል አገሬ የሚሠራባት እንጂ፣ እየዘረፈ የሚፈነጭባት መስክ አትሆንም…›› ሲሉ በሐሳብ ጭልጥ ብዬ ነበር፡፡ የስንቱ ክፋት አዕምሮዬ ውስጥ ድር አድርቶ ኖሮ አፌን መረረኝ፡፡ ወይ ምሬት!
ከተማውን ሙሉ ከሚያስሱ ደላላ ጓደኞቼ ጋር የሚያነጋግረኝ ይኼ ባሻዬ ያነሱት ነገር ነው፡፡ አንድ ጊዜ አንድ የታወቀ በዝርፊያ የከበረ የዘመኑ ሰው አንዱን ደላላ፣ በወር ውስጥ ለአራተኛ ጊዜ የሚከራይ ሙሉ ቪላ ፈልግልኝ ያለውን ፈጽሞ አልረሳውም፡፡ አንዲት እንቡጥ ልጅነቷ ዓይኖቿና መላ አካላቷ ላይ የሚያሳብቁባትን አስረግዞ ለማስቀመጥ መፈለጉን ሲነግረው፣ ሰውዬው ያለውን ገንዘብ በሙሉ በየቦታው እያስወለደ የሚያስቀምጣቸው ሴቶችና ሕፃናት ላይ ኢንቨስት የሚያደርገው ያስመስል ነበር፡፡ እነዚህ እንቡጥ የትናንት ልጃገረዶች በወለዱ ማግሥት ያማረ ቪላ ውስጥ እየተንፈላሰሱ፣ የሚሊዮን ብር አውቶሞቢል ጎዳናው ላይ እንደሚያሽከረክሩ ቢነገር ማን ያምናል ስልም ራሴን እጠይቅ ነበር፡፡ በየምሽት ጭፈራ ቤትና በውስኪና ቮድካ መቸርቸሪያ ጓዳዎች ውስጥ ይታደሙ የነበሩ ባለጊዜ ወጣት ሚሊየነሮችና የእነሱ የዕድሜ ተቃራኒ የሆኑ አናረጅም ባይ ወይዛዝርት ድሪያም፣ ይደንቃል ስልም በተመስጦ ጭልጥ ማለቴ አይዘነጋም፡፡ ምስኪኑ ተሯርጦ ያገኛትን አምላኩን ባርክልኝ ብሎ ሲተኛ፣ እነ አየር ባየር ‹‹ሌቱም አይነጋልኝ›› እያሉ በየባንኮኒውና በየዝጉብኝ ይሸፍታሉ፡፡ በአንድ አገር ውስጥ ሁለት የማይመሳሰሉ ፍጡራን መኖራቸው የፅድቅና የኩነኔ ማሳያዎች እንዲሆኑ ነው ወይ? በማለትም ለመመራመር ሞክሬያለሁ፡፡ ያም ሆነ ይህ ዑደቱ እየቀጠለ የሚሄድ ቢመስልም መቆሙ ግን የግድ ነበር፡፡ ጓዛቸውን ሸክፈው ከአራት ኪሎ ሲባረሩ በዓይኔ አይቻለሁና፡፡ ስንቱን አሳየን ፈጣሪ!
ማንጠግቦሽ እንዲህ ዓይነቱ ውጣ ውረድ የበዛበት ውጥንቅጥ ሲነገራት ራሷን ያማታል፡፡ የፈጣሪ ትዕዛዝ ተጥሶ የሰው ልጅ ሕግጋቱን በተቃራኒ አቅጣጫ እየጠመዘዘ የሚነጉድ ስለሚመስላት፣ ‹‹ለኃጥያን የመጣ ለፃድቃን ይተርፋል…›› እያለች አምላኳን ትለማመናለች፡፡ ‹‹አገራችንንና ሕዝባችንን ሰላም ሰጥቶ፣ ፍቅር ሰጥቶ፣ በጤናና በብልፅግና ያኖር ዘንድ አምላካችንን እንማፀን…›› ስትልም ትደመጣለች፡፡ እኔም በበኩሌ ክፋትና ኃጢያት ባሉበት እርኩሰት እንጂ ፅድቅ ስለማይኖር ወደ ፈጣሪ አቤት ማለት ያስፈልጋል እላለሁ፡፡ ባሻዬም፣ ‹‹የዓለም ፍፃሜ ስለመድረሱ የተነገሩት ምልክቶች እየታዩ ስለሆነ ንስሐ መግባት ያስፈልጋል…›› ይላሉ፡፡ ምሁሩ ልጃቸው ደግሞ ተጨማሪ ነገር አለ ይላል፡፡ ‹‹ለህሊናም ሆነ ለፈጣሪ ሲባል የሰው ልጅ መተዛዘንና መከባበር አለበት፡፡ በሐሰት ውንጀላ፣ በሽንገላ፣ በምቀኝነትና በሰይጣናዊ መንፈስ በመነሳሳት የሰውን ልጅ በማጥቃትና በመሳሰሉት አገርንና ሕዝብን ደም ሲያስለቅሱ የነበሩ በግፋቸው ልክ ዋጋቸውን ያገኛሉ…›› ሲል የሁላችንም ጆሮዎች ቆሙ፡፡ ‹‹ከአጭበርባሪዎች የተለዩት እነዚህ ደግሞ ምንድናቸው?›› ሲሉ ባሻዬ፣ ‹‹እነ እከሌ ባልልም አባዬ አንተም ታውቃቸዋለህ፣ አገርም ያውቃቸዋል፡፡ ነገር ግን በእርኩሰት የተሞሉና ሰይጣንን የሚያስንቁ እኩዮችን ዓለምም እያወቃቸው ነው እኮ፡፡ የራሳቸውና የቢጤዎቻቸው ፍላጎት እስከተሟላ ድረስ ብቻ፣ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን ደንታ የሌላቸው መሆናቸው ግልጽ ከሆነ ሰነበተ እኮ፡፡ የአገርንና የሕዝብን ጥቅም የሚመዝኑት ከራሳቸው ፍላጎት ጋር በማነፃፀር ብቻ መሆኑን ሕዝባችን አውቆ አንቅሮ ተፋቸው እኮ፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ባሉበት አገር ውስጥ እንዴት ዕድገት ይኖራል ተብሎ ይታሰባል?›› በማለት ጥያቄ አቀረበ፡፡ ማንጠግቦሽ ለመልሱ ማንም አልቀደማትም፡፡ ‹‹ልክ ነህ! ‹ከራስ በላይ ነፋስ› የሚሉ ሰይጣኖች ባሉበት አገር ውስጥ መፍትሔው ተባብሮ ክንድን ማሳየት ብቻ ነው፡፡ ትህትናና ቅንነት ጠቃሚ ቢሆኑም፣ ክንድን ማሳየት ደግሞ የግድ ነው…›› ስትል ሁላችንም በመስማማት ልክ ነው አልን፡፡ ወደድንም ጠላንም ጠንካራ መሆን አለብን፡፡ እንደ ጠቅላያችንና ሠራዊታችን ክንደ ብርቱ መሆን አለብን፡፡ መልካም ሰንበት!