አግዳሚ ወንበር ላይ ጎናቸውን ያሳረፉ ብዙ ናቸው፡፡ ዕድሜያቸው ገፋ ያሉ ቢበዙም አንዳንድ ጎልማሳዎችም በሥፍራው አሉ፡፡ አግዳሚ ወንበሮቹ የተያዙባቸው የሕክምና ተራ ጠባቂዎች ደግሞ አማራጭ ያደረጉት ካርቶን መሬት ላይ ዘርግተው አረፍ ማለትን ነው፡፡
ሕመማቸውና ጭንቀታቸው ከፊታቸው የሚነበብባቸው ሕሙማን ከእነሱ የባሰበትና በድጋፍ የመጣ ሲያዩ ፊታቸው ላይ የሚነበበው ሐዘኔታ የተለየ ነው፡፡ ሲቃቸው እንኳን ለእነሱ በሥፍራው ተገኝቶ ለጎበኛቸው ሰውም ሕመም ነው፡፡ ችግሩ ምን እንደሆነ ለመስማት ወደ ሕመምተኞቹ ጠጋ ለማለትም ያስገድዳል፡፡
እነዚህ የካንሰር ሕሙማን በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝ ሆስፒታል የጨረር ሕክምና ለማግኘት ወረፋ የሚጠብቁ ናቸው፡፡ በሆስፒታሉ ሦስት ዓይነት የካንሰር ሕክምና ማለትም ቀዶ ሕክምና፣ ኬሞ ቴራፒና ሬዲዮ ቴራፒ (ጨረር ሕክምና) ይሰጣል፡፡
ቀዶ ሕክምናው ክልል ከተሞችን ጨምሮ በተለያዩ ሆስፒታሎች የሚሰጥ ሲሆን፣ የጨረር ሕክምና ግን በመንግሥት የሕክምና ተቋም ብቻ ይሰጣል፡፡ አንዳንድ ሆስፒታሎች ደግሞ ኬሞቴራፒ ሕክምና ይሰጣሉ፡፡ በጨረር ሕክምናው ላለፉት 20 ዓመታት በላይ ብቸኛ ሆኖ አገልግሎት እየሰጠ ያለው ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ብቻ ነው፡፡
በሆስፒታሉ ሕክምናውን የሚሰጡ ሁለት የጨረር ሕክምና መሣሪያዎች ቢኖሩም፣ አንዱ ተበላሽቶ አገልግሎት መስጠት አቁሟል፡፡ በመሆኑም ሕክምናውን ፈልገው የሚመጡ ታካሚዎች ወራት የሚፈጀውን ወረፋ መጠበቅ ግዴታቸው ነው፡፡
የጨረር ሕክምና ወረፋው አሰልቺና ወራትን የሚወስድ ነው፡፡ በዓመት ሕክምናውን ፈልገው የሚመጡ ተገልጋዮች ቁጥርም በእጅጉ እየጨመረ እንደሚገኝና የአዲስ ታካሚዎች ቁጥር በዓመት ከአሥር ሺሕና ከዚያ በላይ እንደሆነ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የካንሰር ሕክምና ማዕከል ዲፓርትመንት ኃላፊ ዓይናለም አብርሃም (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ዓይናለም እንደሚሉት፣ ከዛሬ 20 ዓመት በፊት በዓመት 80 እና ከዚያ በላይ የሚሆኑ የካንሰር ሕሙማንን ሆስፒታሉ ያስተናግድ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ በሳምንት ከ120 እስከ 150 አዲስ የካንሰር ታማሚዎች ሕክምና ለማግኘት ይመጣሉ፡፡ የሕክምናው ፈላጊዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያለ ቢመጣም፣ በዘርፉ ያለው የሠለጠነ የሰው ኃይልና የሕክምና ቁሳቁስ የማይመጣጠን ነው፡፡
በሆስፒታሉ በሚገኘው የካንሰር ሕክምና ማዕከል የጨረር ሕክምና ለማግኘት ወረፋ የሚጠብቁ ሕሙማንም በርካታ ናቸው፡፡ ሕክምና ለማግኘት ከመጡት መካከል የ67 ዓመቱ አቶ ግርማ ነገሠ ይገኙበታል፡፡
አቶ ግርማ ከሱሉልታ የጨረር ሕክምና ለማግኘት የመጡ ቢሆንም፣ አንዱ ማሽን በመበላሸቱ ተራቸው እስኪደርሳቸው በመጠበባቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ዓይናቸው ላይ ለወጣው ዕባጭ ቀዶ ሕክምና ከተደረገላቸው በኋላ የጨረር ሕክምና እንደሚያስፈልጋቸው ተነግሯቸው ወረፋ በመጠበቅ ላይም ይገኛሉ፡፡
የዓይናቸው እብጠት ከፍተኛ ሲሆን፣ ሕክምናቸውን በመጠባበቅ ብዛት ማየት እየከበዳቸው መምጣቱን ይግልጻሉ፡፡ አቶ ግርማ፣ ማሽኑ አንዴ ተበላሽቷል ሲባሉ፣ ሌላ ጊዜ ወረፋው እስኪደርስ ሲጠብቁ የዓይን ዕይታቸውን እንዳያጡ ሥጋት ገብቷቸዋል፡፡
በማዕከሉ አንዱ የጨረር ሕክምና መሣሪያ በመበላሸቱ አገልግሎቱን ሳያገኙ የተመለሱት የወ/ሮ ሽታዬ ጋሩምሳ ልጅ ሃጫሉ ጉታ እንደነገረኝ፣ እናቱን እንዲሁ ከማመላለስ እርሱ ማሽኑ መሥራቱንና አለመሥራቱን ለማረጋገጥ በየጊዜው ይመላለሳል፡፡
ወ/ሮ ሽታዬ፣ የማኅፀን ካንሰር ተብለው የጨረር ሕክምና ለማግኘት መመላለስ ከጀመሩ ወራቶች መቆጠራቸውን ልጃቸው ሃጫሉ ይናገራል፡፡ የ50 ዓመት ዕድሜ ያላቸው እኚህ እናት፣ የወረፋው መዘግየት አልበቃ ብሎ ማሽኑ መበላሸቱ ተስፋ እንዳስቆረጣቸው ልጃቸው ይናገራል፡፡
‹‹ፈጣሪዋን እየተማፀነች ነው›› ሲልም ያክላል፡፡ ልክ እንደ ወ/ሮ ሽታዬ ሌሎች የካንሰር ሕክምና ናፋቂዎች በማዕከሉ ተኝተው አሊያም ቤት ሆነው ሕክምናውን ይጠባበቃሉ፡፡
የካንሰር ሕክምና አካል የሆኑት ቀዶ ሕክምናውና ኬሞቴራፒው በግል የጤና ተቋማት ዋጋው አይቀመሴ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለዚያውም የጨረር ሕክምናው በመንግሥት እንጂ በግል ጤና ተቋም አይገኝም፡፡
ለዚህም መንግሥት የጨረር ሕክምና ፍላጎት በተወሰነ መልኩ ለማሟላት ጅማ፣ ሐሮሚያ፣ መቀሌ፣ ሐዋሳን ጨምሮ ስድስት ቦታዎች ላይ ለመሥራት ማቀዱን ከተናገረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ እስካሁን ግን የጨረር ሕክምናውን መስጠት የጀመረ የለም፡፡
ችግሩን በጥቂቱ ሊያቃልል ይችላል የተባለ አዲስ ማሽን በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተተክሎ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ሳምንት ሆኖታል፡፡
ከዚህ በፊት ከነበሩት ሁለቱ የጨረር ሕክምና መስጫ መሣሪያዎች አንዱ ብቻ የሚሠራ ሲሆን፣ ይህ ተሠርቶ ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ለታካሚዎች በተሻለ ፍጥነት አገልግሎት ለመስጠት እንደሚቻል ዶ/ር ዓይናለም ይናገራሉ፡፡
ዶ/ር ዓይናለም እንደገለጹት፣ በጨረር ሕክምና መሣሪያ ዙሪያ ካሉት ችግሮች መካከል ለመሣሪያው የመለዋወጫ እጥረት መኖሩና ማሽኑ ሲበላሽ የሚጠግን የሠለጠነ የሰው ኃይል አለመኖሩ ይጠቀሳሉ፡፡ የካንሰር ሕክምና ባለሙያዎችም ስምንት ብቻ ናቸው፡፡
አንድ ሰው የጨረር ሕክምና ለማግኘት 12 ወራት መጠበቅ ይጠበቅበታል ያሉት ዶ/ር ዓይናለም፣ ከ145 ሰዎች 19 በመቶው ያህሉ ሕክምና በመጠባበቅ ላይ እያሉ እንደሚሞቱ ተናግረዋል፡፡
ለዚህም በዋነኝነት በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተተከለው አዲሱ የጨረር ማሽን ትልቅ ዕፎይታ ቢሆንም፣ ካለው ፍላጎት አንፃር በቂ እንዳልሆነ ይገልጻሉ፡፡
የዓለም የጨረር መከላከያ ባለሥልጣን አንድ የጨረር ሕክምና መሣሪያ ለአንድ ሚሊዮን ሕዝብ እንደሚያስፈልግ ቢያስቀምጥም፣ ኢትዮጵያ ከ110 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እያላት ስድስት የጨረር ሕክምና መሣሪያ ብቻ እንዳለ ይናገራሉ፡፡ ከእነዚህ መሣሪያዎች ውስጥ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝ ሆስፒታል የሚገኘው ብቻ ነው፡፡
ሊነር አክስለሬተር የሚባለው የጨረር ሕክምና መሣሪያ ለሐሮማያና ለጅማ የተገዛ ሲሆን፣ ወደ ሥራ ለማስገባት ጊዜ እንደሚወስድ ተገልጿል፡፡
በጥቁር አንበሳ የተተከለው አዲሱ የጨረር ሕክምና ማሽን ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር)፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጣሰው ወልደ ሃና (ፕሮፌሰር) እንዲሁም የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬና ሌሎች የመንግሥት ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተመርቋል፡፡ ከክመምና በመንግሥት የሕክምና ተቋም የሚጠው ጠጥቂር አንበሳ አስፔሻላይዝድ ሀየማሽኑ ሙሉ ወጪ የተሸፈነውም በጤና ሚኒስቴር ነው፡፡
በኢትዮጵያ የጨረር ሕክምና አገልግሎት በ1980ዎቹ ዓ.ም. ሲጀመር የካንሰር ሕክምና ፈላጊዎች ቁጥር አነስተኛ ነበር፡፡ አሁን ላይ እጅግ ብዙ የካንሰር ሕሙማን ሕክምና ፈልገው መደ ሆስፒታሉ ይጎርፋሉ፡፡
የኢትዮጵያ የካንሰር ሕክምና ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ በእጅጉ እየጨመረ ቢመጣም፣ በሕክምና አሰጣጥም ሆነ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲሁም በሰው ኃይል ያለው ዕድገት ተመጣጣኝ አይደለም፡፡
በየጊዜው ሥርጭቱ እየጨመረ ከመጣው የካንሰር ሕመም አንፃር በኢትዮጵያ ያለው የካንሰር ሕክምና እዚህ ግባ እንደማይባል በምርቃቱ ተገልጿል፡፡
ጅማ፣ ሐሮማያ፣ መቀሌ፣ ሐዋሳ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ጨምሮ በስድስት ሆስፒታሎች የጨረር ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት በጤና ሚኒስቴር በኩል ግዥ መፈጸሙም ተገልጿል፡፡
ከእነዚህ ቦታዎች ውስጥ በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝ ሆስፒታል የመጀመርያው ሊኒር አክስለሬተር የጨረር ሕክምና መስጫ መሣሪያ ተገጥሟል፡፡ በጅማና በሐሮሚያ የሚተከለው ይህ መሣሪያ በቅርቡ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር እየተሠራ እንደሆነ ዶ/ር ሊያ ተናግረዋል፡፡
አዲሱ መሣሪያ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለረዥም ዓመታት የሠሩ የካንሰር ሕክምና ባለሙያዎችን ጥረት ያደነቁት ጤና ሚኒስትሯ፣ አሁንም ሌሎች ቦታዎች ላይ በዘርፉ በጥልቀት ለመሥራት ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በካንሰር ሕክምና ላይ የሚሠሩ ባለሙያዎችን በማበረታታትና በዘርፉ ዘላቂ ችግሮችን ለመፍታት ሚኒስቴሩ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ዓይናለም በበኩላቸው፣ የካንሰር በሽታ መንስዔው በውል የማይታወቅ ቢሆንም፣ የአኗኗር ዘይቤን ማስተካከል ይመከራል ብለዋል፡፡ የአመጋገብ ሥርዓትን ማስተካከል፣ አላስፈላጊ ውፍረት እንዳይከሰት እንቅስቃሴ በማድረግና የታሸጉ ምግቦችን ባለማዘውተር በካንሰር በሽታ የመያዝ ዕድልን መቀነስ ይቻላል፡፡ ለካንሰር በሽታ አጋላጭ ተብለው የተቀመጡ ዕድሜ፣ ፆታና ዘረመል እንደሆኑም አክለዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው፣ በዓለም እ.ኤ.አ. በ2012 አዲስ በካንሰር የተያዙ ሰዎች ቁጥር 14 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን፣ ይህ በ2030 ወደ 21 ሚሊዮን ያድጋል፡፡ በበሽታው የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርደግሞ እ.ኤ.አ. በ2015 ከነበረበት 8.8 ሚሊዮን በ2030 ወደ 12 ሚሊዮን ሊያሻቅብ ይችላል፡፡