Sunday, June 23, 2024

ልዩነትን የማያከብር አንድነት ፋይዳ ቢስ ነው!

በየትኛውም የሕይወት መስክ ልዩነት መኖሩ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ከግለሰቦች እስከ ማኅበረሰቦች በሚኖሩ መስተጋብሮች ልዩነት ይኖራል፡፡ ዋናው ቁምነገር ግን ለልዩነት የሚደረገው አያያዝ ነው፡፡ በፖለቲካው መስክ ደግሞ የተለያዩ ዓላማዎች ያሉዋቸው ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን ይዘው መነጋገር፣ መከራከርና መደራደር ይችላሉ፡፡ ሁሌም ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ አላቸውና፡፡ ልዩነትን በፀጋ ተቀብሎ ለማስተናገድ አለመፈለግ የአምባገነንነት ባህሪ ነው፡፡ ዓላማን በጉልበት ብቻ ለማስፈጸም ድርቅ ማለት ልዩነትን አለማክበር ብቻ ሳይሆን፣ ለሰላምና ለዕድገት የሚውለውን የሰው ኃይል፣ ጊዜና ሀብት ለጥፋት ማመቻቸት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ነውጠኝነትንና አተራማሽነትን ሲመርጡ የኖሩ ኃይሎች ትልቁ ችግራቸው፣ ልዩነት ማለት ጠላትነት ነው ከሚል ስሌት መነሳታቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን የዘመናት ችግር መሻገር አለባት፡፡ አንድ ጉልበተኛ ተሸኝቶ ሌላ ጉልበተኛ ሲተካ አገር ሰላሟ ተቃውሶ ትተራመሳለች፡፡ አሁንም እንዲህ ዓይነት ምልክቶች እየታዩ ስለሆነ፣ ለጋራ ብሔራዊ ጉዳዮች ቅድሚያ ቢሰጥ መልካም ነው፡፡ በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ልዩነትን ሳያከብሩ አንድነት አለን ማለት ታጥቦ ጭቃ መሆን ነው፡፡ 

በዲፕሎማሲው መስክ አገሮች ከሌሎች ጋር የሚኖራቸው ግንኙነትና መስተጋብር በዘለቄታዊ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በአገሮች የውስጥ ጉዳይ አለመግባት በዓለም የታወቀ መርህ ቢኖርም፣ ይህ መርህ የሚከበረው ኃይልና ሀብት ላላቸው ብቻ ነው፡፡ ከዚያም አለፍ ሲል በጥቅም ድር ትስስር ውስጥ ተሠልፈው የሚሰጣቸውን ተልዕኮ በአግባቡ የሚፈጽሙ፣ ተቆጪም ገላማጭም የላቸውም፡፡ ለአንድ ኃያል አገር ወይም ተፅዕኖ ፈጣሪ ቡድን ሸብረክ ሳይባል ሉዓላዊነቱን ለማስከበር የሚጣጣር አገር፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሚደረግበት መሰናክል እግር ተወርች እንዲያዝ ይደረጋል፡፡ ዓለም አቀፍ ሚዲያውም ባለ በሌለ ኃይሉ ይዘምትበታል፡፡ በዚህ ዓይነቱ ወሳኝ ጊዜ ውስጣዊ ጥንካሬና ትብብር ከሌለ፣ ሥርዓተ መንግሥቱን የሚንዱ ድርጊቶች ያለ ከልካይ ይፈጸማሉ፡፡ ኢትዮጵያ አሁንም ሆነ በታሪክ የተለያዩ ምዕራፎች እስኪታክታት ድረስ ይህንን መረራ ፅዋ ተጎንጭታለች፡፡ ኢትዮጵያዊያን ልዩነቶቻቸውን አቻችለው ለጋራ ብሔራዊ ዓላማ መሠለፍ ሲያቅታቸው፣ የውጭ ጣልቃ ገብነቶች እየበረከቱ ትርምስ መፈጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ ልዩነትን በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ማስተናገድ የሚያስችል ባህል ማጎልበት ይገባል፡፡ አንድነትና ጥንካሬ የሚያስፈልገው አንድ ዓይነት ለመሆን ሳይሆን፣ ልዩነትን ይዞ ለአገር የጋራ ጉዳይ መሠለፍ ለመቻል ነው፡፡ ልዩነትን የማያከብር አንድነት ላይ ማተኮር ውጤቱ ውድቀት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት በፖለቲካ ድርጅቶች፣ በሙያና በጥቅም ማኅበራት፣ በማኅበረሰቡና በግለሰቦች መካከል ልዩነቶች ሲፈጠሩ፣ ልዩነቶች ተፈጥሮአዊ መሆናቸውን ከመቀበል ይልቅ ለጠብ መጋበዝ የተለመደ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን የበርካታ ማንነቶች፣ እምነቶች፣ ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ ልማዶችና ሌሎችም ልዩነቶች ባለቤት ሆነው አንድ ላይ መኖር ብቻ ሳይሆን፣ ተጋብተውና ተዋልደው መልከ ብዙ ሆነው መኖራቸው የታወቀ ነው፡፡ ይህንን የመሰለ ብዝኃነት ባለበት አገር ውስጥ ልዩነትን ማክበርና ለጋራ ብሔራዊ ጉዳይ አብሮ መሠለፍ በጣም ቀላል ጉዳይ መሆን ሲገባው፣ ለሕዝብ ክብርና ለአገር ህልውና ደንታ በማጣት ዘመን የማይሽራቸው ጥፋቶች ተፈጽመዋል፡፡ ለሥልጣንና ለሚያስገኘው ጥቅም ሲባል ብቻ ግጭት በመቀስቀስ ንፁኃንን መጨፍጨፍ፣ ከቀዬአቸው ማፈናቀል፣ ንብረታቸውን ማውደምና መዝረፍ የመሳሰሉ አስከፊ ድርጊቶች በተደጋጋሚ ተግባራዊ ተደርገዋል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ መጠነ ሰፊ ጦርነት እንዲቀሰቀስ ምክንያት በመሆን፣ ሰብዓዊ ቀውስ እንዲፈጠር ተደርጓል፡፡ ለአገር ልማትና ዕድገት መዋል የሚችል ወርቃማ ጊዜ፣ የሰው ኃይልና ሀብት ባክኗል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ለሚፈልጉ ኃይሎች ጥሩ አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ የውድቀት ታሪክ በመማር ልዩነትን የሚያከብር አንድነት ላይ ይተኮር፡፡

ብዙዎቹ ኢትዮጵያዊያን አገራቸውን ከግላዊና ከቡድናዊ ፍላጎት በላይ ለማድረግ፣ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸው የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን ለአገር ፈፅሞ ደንታ የሌላቸው፣ ሕዝቡን ልዩነቶቹን ተገን አድርገው የሚከፋፍሉና ከጥቅማቸው በስተቀር ምንም የማይታያቸው አሉ፡፡ እነዚህ ጥቂት ቢሆኑም ሀብት ያካበቱ፣ ሚዲያዎችን የተቆጣጠሩ፣ ከማንም በላይ መረጃ ያላቸውና ድምፃቸውም ጎልቶ የሚሰማ ናቸው፡፡ ከመንግሥታዊ መዋቅሮች እስከ ማኅበረሰቡ፣ ከግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ እስከ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የፋይናንስ እንቅስቃሴ የሚሳተፉ፣ በተለያዩ ሕገወጥ ንግዶችና እንቅስቃሴዎች ውስጥ ያሉ፣ በተለያዩ አገሮች ቃፊሮቻቸውን አስቀምጠው በማኅበራዊ ትስስር ገጾችና በተፅዕኖ ፈጣሪዎች እየታገዙ ደባ የሚሠሩ ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነት በሁሉም መስክ የደረጁ አገር አፍራሾችን ለመቋቋም የሚቻለው፣ ልዩነትን ይዞ ለጋራ አገራዊ ጉዳይ ኅብረት በመፍጠር ነው፡፡ አገርን መውደድ ማለት መፈክር ማስተጋባት ብቻ ሳይሆን፣ የወቅቱን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ሊሰነዘሩ የሚችሉ ጥቃቶችን ለመመከት አንድነት መፍጠር መቻል ነው፡፡ ልዩነትን አክብሮ አንድነት ላይ የማያተኩር የተናጠል ሩጫ ያስጠቃል፡፡

በአሁኑ ጊዜ እዚህ ግባ የማይባሉ ወይም ጊዜውን የማይዋጁ ቅራኔዎችን ከየሥርቻው እየፈለጉ ለጠብ ከመጋበዝ፣ አገርን የሚያሳስቡ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የጋራ መፍትሔ ፍለጋ ላይ መሰማራት ግዴታ መሆን አለበት፡፡ ተቆጥረው የማያልቁ ችግሮች እንደ ተራራ ተቆልለው በቅደም ተከተል የሚፈቱበትን ዘዴ በጋራ መቀመር ሲገባ፣ ተጨማሪ ችግሮችን መፈልፈል የጤነኞች ተግባር አይደለም፡፡ የውጭ ጣልቃ ገብነት ሊያመቻቹ የሚችሉ ሰንኮፎችን ለመንቀል የሚያስችሉ ትዕግሥት፣ ብልኃትና ጥበብ ላይ ማተኮር የግድ ነው፡፡ ዘመኑ የሚፈልገው በዕውቀት ላይ የተመሠረተ የሐሳብ ልዕልና ነው፡፡ ከሌሎች መሻል የሚቻለው ዘመኑ የደረሰበት የዕድገት ደረጃ ላይ በመገኘት ነው፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ እየተኖረ የዘመነ መሣፍንት ድርጊት ውስጥ መገኘት ውጤቱ ምን እንደሚሆን ጊዜው ፍንትው አድርጎ እያሳየ ነው፡፡ በዓለም የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ውስጥ ተቀባይነት ማግኘት የሚቻለው፣ ውስጣዊ አንድነትና ጥንካሬ መገንባት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ልዩነትን በአግባቡ ማስተናገድ በማይችል ዕሳቤ ውስብስቡን የዓለም ተፅዕኖ መጋፈጥ አይቻልም፡፡ ልዩነትን አቻችሎ አንድ ላይ የመሥራት ብቃትና ጥንካሬ ሲኖር ግን፣ በአስቸጋሪ ሁኔታም ውስጥ ጥቅምንም ሆነ ሉዓላዊነትን ማስከበር አያዳግትም፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ መገንዘብ ያለባቸው መሠረታዊ በሚባሉ አገራዊ ጉዳዮች መስማማት ሽንፈት እንዳልሆነ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነትና ዘለቄታዊ ጥቅም ላይ የጋራ አቋም መያዝ የግድ ነው፡፡ በሕዝብ ደኅንነትና በአገር ህልውና ላይ ድርድር እንደማይደረግ መገንዘብ የሁሉም ፖለቲከኞች ኃላፊነት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ሁሉም ነገር ከሕግ በታች እንዲሆን መስማማት ሥልጣኔ ነው፡፡ ከሥልጣን በፊት አገር መከበር አለባት፡፡ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት ከሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በፊት ምንም ነገር ሊቀድም አይገባም፡፡ የማንም ሰው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መገሰስ የለባቸውም፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ለድርድር የማይቀርብ እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ እነዚህና መሰል መሠረታዊ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ለመግባባት መቸገር ልክ አይሆንም፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር ሕጋዊ መንገዶችን በአግባቡ መከተል ሲጀምር፣ ሕገወጥነትና ሥርዓተ አልበኝነት ይወገዳሉ፡፡ ልዩነቶችን በማጦዝ የማይታረቁ ቅራኔዎችን መፈልፈል አገር ለማተራመስና ሕዝብን ቀውስ ውስጥ ለመክተት ያገለግላል እንጂ፣ ለዕድገት አንዲት ጋት እንደማያራምድ የታወቀ ነው፡፡ ይልቁንም ጣልቃ ለመግባት ለሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች እጅ ጥምዘዛ ያመቻቻል፡፡ አንድነትን በማጠናከር ኢትዮጵያን ከጉልበት አምላኪዎች ማላቀቅ ይገባል፡፡ ልዩነትን የማያከብር አንድነት ግን ፋይዳ ቢስ መሆኑን መገንዘብ የግድ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሕግ የማጥቂያ መሣሪያ እንዳይሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

የሕግ መሠረታዊ ዓላማ ዜጎችን ከማናቸውም ዓይነት ጥቃቶች መጠበቅ፣ ለሕይወታቸውና ለንብረታቸው ከለላ መስጠትና በሥርዓት እንዲኖሩ ማድረግ ማስቻል ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል...

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...