Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹የክልል ልዩ ኃይል ኢሕገ መንግሥታዊ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል›› ወ/ሮ ሙፈርያት ካሚል የሰላም...

‹‹የክልል ልዩ ኃይል ኢሕገ መንግሥታዊ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል›› ወ/ሮ ሙፈርያት ካሚል የሰላም ሚኒስትር

ቀን:

ክልሎች እያደረጇቸው ያሉ የክልል ልዩ ኃይሎች ሕገ መንግሥቱ ከሚፈቅደው የፖሊስ አደረጃጀት ውጪ በመሆናቸው፣ ፓርላማው የአገርን ሰላም ለማስጠበቅ ሲባል የራሱ የሆነ አሠራር ሊያበጅለት እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል አሳሰቡ። 

የፖሊስ ሕጉ ክልሎች የራሳቸው ፖሊሶች ይኖራቸዋል ሲል መደበኛ ሥልጠና ያገኘ ፖሊስ እንጂ፣ ከፊል የመከላከያ  ኃይል ባህሪ ይኖራቸዋል ማለት አይደለም ያሉት ሚኒስትሯ፣ የመደበኛ ፖሊስ ሥልጠናው፣ ትጥቁና ሥምሪቱ በግልጽ ምን እንደሆነ ይታወቃል ብለዋል፡፡ በክልሎች እየተደረገ ያለው ያልተገባ እንቅስቃሴ ሊታሰብበት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ምንም እንኳ የተቀመጠው የአሠራር ሥርዓት መደበኛም ሆነ መደበኛ ያልሆነ ፖሊስ ሥልጠናውና ትጥቁ ምን መምሰል እንዳለበት የሚገልጽ ቢሆንም፣ ይህ ጉዳይ ግን ፖለቲካዊ በመሆኑ በየደረጃው ያሉ የፖለቲካ አመራሮች ቢያስቡበት ይበጃል ብለዋል፡፡ አስፈላጊ ከሆነም ፓርላማው ሕግ ሊያወጣለት እንደሚገባ ሚኒስትሯ አሳስበዋል።

‹‹እንደ አገር ለመቆም አቋማችን ግልጽ በመሆኑ ትልቅ ሥራና  ሰፊ ውይይት ያስፈልገዋል፤›› ያሉት ወ/ሮ ሙፈሪያት፣ በየቦታው ለሚታየው የፀጥታ ችግር ሁሉም አመራር ኃላፊነት መወጣት ይገባዋል ሲሉ ጠይቀዋል።

የክልል ልዩ ኃይል አጀማመር ከ2000 ዓ.ም. በኋላ ባሉት ዓመታት የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) ኃይልን ለመቆጣጠር ታስቦ የተመሠረተ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህን ተከትሎም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርከት ያሉ የክልል መንግሥታት፣ ይህን መሰል ኃይል በማሠልጠን ወደ ሥራ ማስገባታቸው ይታወቃል፡፡

በዚህም አብዛኞቹ ክልላዊ መንግሥታት በክልላቸው ከሠፈሩት የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት በተጨማሪ፣ የሚፈቅድ ሕግ በሌለበት የራሳቸው የሆኑና በሺዎች የሚቆጠሩ የልዩ ኃይል ወይም የልዩ ፖሊስ ባለቤት መሆናቸው አነጋጋሪ ነው፡፡

የክልል ልዩ ኃይሎች ተጠሪነታቸው ለክልል ፕሬዚዳንቶች ነው፡፡ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከመከላከያ ሠራዊትና ከክልል ፖሊስ ጋር ያላቸው ግንኙነት በሕግ ምን እንደሚመስልም ግልጽ አይደለም ነው የሚባለው፡፡

ሚኒስትሯ ከላይ የተጠቀሰውን ማሳሰቢያ ያስተላለፉት፣ ፓርላማው የሰላም ሚኒስቴርን የ2013 በጀት ዓመት የሦስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ኅዳር 23 ቀን 2013 ዓ.ም. በገመገመበት ወቅት ነበር።

የፓርላማ አባላት የሰላም ሚኒስቴር የአገርን ሰላም ለማስጠበቅ ዕቅድ ከማዘጋጀት ባለፈ፣ መሬት ላይ የሚታይና ተጨባጭ የሆነ ሥራ በማከናወን እየታየ ላለው የሰላም ዕጦት ችግር ፈቺ መሆን እንደሚገባው አሳስበዋል።

የሰላም ሚኒስቴር፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ የተቋቋመ ነው፡፡ የአገሪቱን ቁልፍ የፀጥታና የስለላ ዘርፎች በተለይም የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የፋይናንስ ደኅንነትና መረጃ ማዕከል፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮችና ሌሎች ተቋማትን በበላይነት ይመራል፡፡

በተለይም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በውስጡ የያዛቸው የደኅንነት ተቋማት እንደ አገር ሊከሰቱ የሚችሉ ግጭቶችን ቅድመ ማስጠንቀቂያ መስጠት የሚችሉበትን አቅም በመገንባት፣ የሚጠበቅባቸውን አቋም መያዝ አለባቸው ተብሏል።

‹‹የዜጎች ሞት ልብሳችን ሆኗል፣ ብዙ ሀብትና ንብረት ማውደም ሱስ ሆኗል፡፡ ለዚህም  ይነስም ይብዛም በኃላፊነት ላይ ያለን ሰዎች ተጠያቂዎች ነን፤›› ያሉት በምክር ቤቱ የሰላምና የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የሰላም ዘርፍ ንዑስ ሰብሳቢ ወ/ሮ ብርቱካን ሰብስቤ ናቸው።

ሰብሳቢዋ አክለውም እንደ ተቋም  በተዋረድ በሚሊዮኖች ለሚሆኑ ዜጎች  ሥልጠናዎች ተሰጡ መባላቸውን፣ ነገር ግን  ለፖሊስ ኃይሉም ሆነ ለኅብረተሰቡ የሚሰጠው ሥልጠና የሚሞቱ ዜጎችን ካልታደገ፣ የሚወድሙ ሀብትና ንብረቶችን ከላስቆመ የሚኒስቴሩ ሥራ ከንቱ ነው ብለዋል፡፡

የሰላም ሚኒስትሯ በበኩላቸው ዘንድሮ 30 ሚሊዮን ለሚደርሱ ዜጎች ብሔራዊ የሥልጡን የምክክር ውይይት ለማዘጋጀት፣ የሥልጠና ሰነድ ተዘጋጅቷል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከዚህ ጋር በተያያዘ በብሔራዊ መግባባት ላይ ያተኮሩና የጋራ ታሪክና ትርክት እንዲኖር የሚያስችሉ ጉዳዮችን በመለየት፣  ዜጎች በጋራ ጉዳዮች ላይ አንድ ዓይነት ወይም ተቀራራቢ ዕሳቤ እንዲይዙ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ገልጿል።

በዚህም በዋነኝነት ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከምሁራን ጋር ከአገራዊ ታሪክ ዕይታና ዕሳቤ አንፃር በመነጋገር መግባባት ለመፍጠር እየተሠራ እንደሆነ፣ በተለይም ከአገሪቱ ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ የታሪክ ምሁራንን በማሰባሰብ ለመግባባት የሚያስፈልጉ ጉዳዮች  ምን ምን እንደሆኑ ተለይተዋል ሲሉ ወ/ሮ ሙፈሪያት ገልጸዋል።

በሚኒሰቴር መሥሪያ ቤቱ ሥር ባሉ የደኅንነት ተቋማት ጠንካራ ሪፎረም እየተደረገ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሯ፣ ሥርዓት አገልጋይ የነበሩ የፀጥታና የደኅንነት ተቋማት ወደ ሕዝብ አገልጋይነት እንዲሸጋገሩ እየተሠራ መሆኑን አክለዋል፡፡ ድሮ እንደ ባላንጣ ሲተያዩ የነበሩ የደኅንናትና የፀጥታ ተቋማት አሁን በመነጋገርና በመወያየት በጋራ እየሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በተያያዘ ዜና በሰላም ሚኒስቴር በኩል እየተሠራ ያለው ብሔራዊ የዜጎች መታወቂያ የፕሮጀክት ሥራ ተጠናቆ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ በተያዘው ዓመት 30 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች መታወቂያ ለመስጠት እየተሠራ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...