የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በተለያዩ ጊዜያትና አካባቢዎች እየተከሰቱ ላሉ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ለሚያደርገው የዕለት ደራሽ ዕርዳታ አቅርቦት፣ ፈጣን የሆነ የግዥ ሥርዓት ባለመኖሩ ሕይወትን ለማዳን የሚያደርገው ጥረት እየተስተጓጎለበት እንደሆነ አስታወቀ፡፡ ችግሩን ለመቅረፍም የፈጣን የግዥ ሥርዓት ሕግ እንዲወጣ ጠየቀ፡፡
አስፈላጊ የሆኑ የዕለት ደራሽ ቁሳቁሶች በአስቸኳይ እንዲገዙ የሚፈቅድ ሕግና የአሠራር ሥርዓት ባለመኖሩ፣ ከመንግሥት ግዥና አስተዳደር ኤጀንሲ በየጊዜው ፈቃድ በመጠየቅ እየተሄደበት ያለው አሠራር አዋጭ ካለመሆኑም በላይ፣ ፈጣን የሰብዓዊ ዕርዳታ ለማድረስም አስቸጋሪና አሳሳቢ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
ኮሚሽነሩ አቶ ምትኩ ካሳ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰላምና የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ጋር በነበራቸው ውይይት፣ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ካለው ሰብዓዊ ቀውስና ፈጣን ዕርዳታ አስፈላጊነት አንፃር በፓርላማው በኩል ታይቶ ልዩ ፈቃድ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ አገሪቱ በተለይ እየተከሰተ ካለው ከባድና አስቸጋሪ ሁኔታ አኳያ፣ አስቸኳይ ወይም ድንገተኛ ችግር የሚፈታ አሠራርና የፋይናንስ ሥርዓት እንደሚያስፈልግም ተገልጿል፡፡
የአገሪቱ ሕግ የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታን በሚመልስ ደረጃ ባለመቃኘቱ፣ የነፍስ አድን ሥራ ለማከናወን ቀጥተኛ ትዕዛዝ የሚፈቅድ ሕግ ምክር ቤቱ እንዲያወጣ ተጠይቋል፡፡
እንዲህ ዓይነት አሠራር አፋጣኝ ምላሽ እንደሚፈልግ የገለጹት የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ሲሆኑ፣ በተለይም የሰው ሕይወት ለማዳን ከሕጉ ውጭ ግዥ ሲፈጸም የኦዲት ግኝት ሆኖ እየተመዘገበ ለሌላ ችግር እየዳረጋቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ ሚኒስትሯ፣ ‹‹ሕይወትን ማዳን ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ ባለመሆኑ የምንታሰር ከሆነ እንታሰር እንጂ፣ በዚህ ምክንያት ዜጋ እንዲጎዳብን አንፈልግምም፣ አንፈቅድምም፤›› ብለዋል፡፡
ያለው አሠራር መቀጠል ስለሌለበት፣ ፓርላማው ተነጋግሮ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ሰጪነት አሠራር፣ ራሱን የቻለ የሕግ ማዕቀፍ ስለሚፈልግ፣ ሕጉ በአስቸኳይ እንዲወጣ ወ/ሮ ሙፈሪያት ጠይቀዋል፡፡