Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮሮና ክትባት ለማጓጓዝ ከቻይናው አሊባባ ግሩፕ ጋር ተዋዋለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለኮሮና ወረርሽኝ የተመረተ ክትባት ወደ ተለያዩ አገሮች ለማጓጓዝ፣ ከቻይናው አሊባባ ግሩፕ ጋር የአንድ ዓመት ውል መፈጸሙ ተገለጸ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎና የሎጂስቲክስ አገልግሎት ከቻይናው ቢሊየነር ጃክ ማ ንብረት የአሊባባ ግሩፕ ለሎጂስቲክስ ክንፍ ከሆነው፣ ሲያኖ ስማርት ሎጂስቲክስ ኔትወርክ ከተባለው ኩባንያ ጋር የአንድ ዓመት ውል መፈጸሙን ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍፁም አባዲ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የቻይና መንግሥት በሸንዞን አውሮፕላን ማረፊያ የኮሮና ክትባትን ወደ ተቀረው የዓለም ክፍል ለማሠራጨት በሚያስችልና የሚያስፈልገውን የቅዝቃዜ መጠን የሚያሟላ የማከማቻ መጋዘን ያሰነዳ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድም ከሸንዞን አውሮፕላን ማረፊያ የቅዝቃዜ መጠኑ እንደተጠበቀ የሚያጓጉዙ አውሮፕላኖች ወደ አዲስ አበባና ወደ ተለያዩ የዓለም አገሮች እንደሚያጓጉዝ ታውቋል፡፡

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የአየር መንገዱ አውሮፕላኖች የኮሮና ክትባቱን ለማጓጓዝ ተዘጋጅተዋል፡፡

በአዲስ አበባ በሚገኘው ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያም በቀን 500 ቶን የኮሮና ክትባት ማስተናገድ የሚችሉ፣ እንዲሁም የተለያዩ የቅዝቃዜ መጠኖችን የሚያሟሉ ማከማቻዎች ተዘጋጅተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቻይናው ኩባንያ ጋር ካደረገው ስምምነት በተጨማሪ፣ የኮሮና ክትባት በማምረት ላይ ከሚገኙ ሌሎች ኩባንያዎች ጋርም እየተነጋገረ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በዚሁ መሠረትም አየር መንገዱ በካናዳ፣ በአሜሪካና በአውሮፓ ከሚገኙ የኮሮና ክትባት አምራቾች ጋር በመነጋገር ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡ ይህ የሚሳካለት ከሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮሮና ወረርሽኝ ክትባትን ለማጓጓዝ ምቹና ተመራጭ አየር መንገድ ሊያደርገው ይችላል ተብሏል፡፡

የኮሮና ወረርሽኝ በመላው ዓለም ከተከሰተ ወዲህ በርካታ አየር መንገዶች ከስረው እየተዘጉ ሥራ ማቆማቸው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቻይናው ቢሊዮነር ጃክ ማ ፋውንዴሽን ጋር በመሠረተው ትብብር፣ ፋውንዴሽኑ ኮሮናን ለመከላከል የሚያስችሉ የሕክምና ቁሶችን ለሁሉም የአፍሪካ አገሮች ያቀረበውን ዕርዳታ ከቻይና ወደ አዲስ አበባ፣ በኋላም ወደ 52 የአፍሪካ አገሮች በመጓጓዝ አየር መንገዱን ከኪሳራ ታድጓል፡፡

ይህን የገበያ ዕድል ያስተዋለው የአየር መንገዱ ማኔጅመንት ‹‹ፋርማ ዊንግ›› የተባለ የሕክምና ቁሶች የሎጂስቲክ አገልግሎት በመክፈት፣ የትራንስፖርት አገልግሎቱን በከፍተኛ ደረጃ በማስፋፋት ላይ ነው፡፡

የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ አየር መንገዱ ከ60 እስከ 70 በመቶ ገቢውን እያገኘ የሚገኘው ከጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት ሲሆን፣ ለዚህም ሲባል 14 ግዙፍ የመንገደኛ አውሮፕላኖችን ለጭነት ማጓጓዣ ምቹ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች