Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያ አሁንም አዲስ ሥራ ለመጀመር አዳጋች ከሆኑ አገሮች ተርታ እንዳለች ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ አዳዲስ ቢዝነሶችን ለመጀመር አሁንም ፈታኝ ከሆኑ የዓለም አገሮች ተርታ መሆኗ በተደረገ የዳሳሳ ጥናት መታወቁ ተገለጸ፡፡ ይኼ የተገለጸው የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈውና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አማካይነት በተዘጋጀው፣ ‹‹የኢትዮጵያ የኢንቨስትመነት አማራጮችና የተሻሻለው የኢንቨስትመንት ሕግ›› በሚል በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ በቀረበ አንድ የዳሳሳ ጥናት መረጃ ነው፡፡

ገለጻውን ያቀረቡት ወ/ሪት ፋንቱ ፋሪስ በዓለም ባንክ የግሉ ዘርፍ ባለሙያ ሲሆኑ፣ አገሪቱ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ አስቀምጣቸው የነበሩ ከልካይ መመርያዎችና ውስብሰብ አስተዳደራዊ ሒደቶች፣ ኢትዮጵያ እንደ ኬንያና ሩዋንዳ ካሉ ጎረቤት አገሮች ጋር ስትነፃፀር፣ በከፍተኛ መጠን ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መሆኗን ገልጸዋል፡፡

የተጀመሩ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችም በአግባቡና በተጠና መንገድ አለመከናወናቸው፣ በኢትዮጵያ የላላ መደበኛ የሥራ እንቅስቃሴ እንዲኖርና መደበኛ ያልሆነው ዘርፍ እንዲጎላ ሲያደርገው ቆይቷል ሲሉ ወ/ሪት ፋንቱ ገልጸዋል፡፡

ባለሙያዋ ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ ወደ 80 የሚጠጉ የሪፎርም አጀንዳዎች መቅረጿን፣ በተለይም ምጣኔ ሀብታዊ ሒደቱን የሚከታተሉ 12 ኮሚቴዎች ተቋቁመው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብሳቢነት ተጨባጭ የሆነ ሥራ መከናወን መጀመሩ፣ አገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ያሻግራታል ብለዋል፡፡ በተለይም አሳሪ የሆኑ የኢንቨስትመንት ሕጎችን ማሻሻሏ፣ ብሔራዊ የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነትንና በርካታ የሆነ የሥራ ዕድሎችን ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እንድታገኝ ይረዳታል ሲሉ ወ/ሪት ፋንቱ አክለው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ወ/ሪት ሌሊሴ ነሜ በበኩላቸው፣ አንዳንድ የመንግሥት አካላት ለኢንቨስትመንት ያላቸው ተገቢ ያልሆነ ዕይታ፣ በመንግሥት አስፈጻሚ አካላት መካከል ያለው የማስፈጸም ችግር፣ የአገልግሎት አሰጣጥ አለመዘመን፣ በመሬት አቅርቦት ወጥነት የሌለው አሠራርና የግብዓት እጥረት ችግሮች በአገሪቱ ኢንቨስትመንት በታሰበው ልክ እንዳይስፋፋ ማነቆ ሆኗል ብለዋል፡፡ አዳዲስ አዋጆች መውጣታቸው መልካም ለውጥ ቢሆንም፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና በክልል የኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ቢሮዎች መካከል መናበብ እስከሌለ ድረስ ችግሩን መቅረፍ አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ ላይ ሐሳባቸውን የሰነዘሩት በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአግሮ ፕሮሰሲንግና ፋርማሲዩቲካል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ገብረየሱስ፣ ‹‹ኢንቨስትመንት የአንድ ተቋም ሥራ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ ከገጽታ ግንባታ አንፃር ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ትልቅ ሥራ ሠርቷል ያሉት አቶ ተካ፣ ‹‹ሆኖም አዳዲስ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ከማስተዋወቅ ባሻገር፣ እጃችን ላይ ያሉ ኢንቨስተሮችንና ኢንቨስትመንቶችን በምቹ ሁኔታ እንዲሠሩ ማድረግ ወሳኝ ሥራ ሊሆን ይገባል፤›› ብለዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት አማራጮች አሉን ብቻ ሳይሆን፣ አማራጮቹ በትክክል ሳይጓደሉ መቅረብ መቻላቸውን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል፡፡

በተጨማሪም ኢንቨስትመንቶች ፈቃዳቸው በመሀል ከተማ ይሰጥ እንጂ፣ ወደ መሬት ወርደው የሚሠሩት ክልሎች ላይ እንደ መሆኑ መጠን የዕውቀትና የአሠራር ሥልጠና ሊሰጣቸው ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ገልጸዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ ኢንቨስተሮችና ተወካዮቾቻቸውም የተለያዩ አስተያየቶችን የሰነዘሩ ሲሆን፣ በተለይም መንግሥት በግሉ ሴክተር ላይ አመኔታ ሊያሳድር ይገባል ብለዋል፡፡ ከዚያው ጎን ለጎንም ለኢንቨስትመንት ፈቃድ ለማግኘት መከልከልን እንጂ መፍቀድን የማያበረታታው አገልግሎት አሰጣጥ ሊስተካከል ይገባዋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡  

በኤልያስ ተገኝ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች