Thursday, September 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  ‹‹ሕወሓት የተንሻፈፈ መንገድ ላይ እንደነበር በግልጽ ማሳየት ያስፈልጋል›› አበባው አያሌው (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ የታሪክ ምሁር

  ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰሜን ዕዝ ላይ የሕወሓት አመራር አስፈጸመ የተባለው ያልተጠበቀ ዕርምጃ አንደኛ ወሩን አገባዷል፡፡ ይህ ድርጊት አላስፈላጊ የተባለ ጦርነት ውስጥ አስገብቷል፡፡ መንግሥት የሕግ ማስከበር ዕርምጃ ውስጥ እንዲገባ ካደረገው ምክንያት አንዱ፣ ይኼው የጥቅምት 24 ቀን አስከፊ ድርጊት መሆኑ በስፋት ይነገራል፡፡ ይህ ድርጊት በኢትዮጵያ የጦርነት ታሪክም ሆነ በዓለም ደረጃ አለመፈጸሙን የታሪክ ምሁሩ አበባው አያሌው (ረዳት ፕሮፌሰር) ይገልጻሉ፡፡ ከኢትዮጵያ የጦርነት ታሪክ በመነሳት የሕወሓት ቡድን ፈጸመው በተባለው ድርጊት ላይ በመመርኮዝ፣ ታሪካዊ ጉዳዮችንና በቀጣይ ምን መሆን አለበት የሚሉ ጥያቄዎች በመያዝ ዳዊት ታዬ  አበባው አያሌውን (ረዳት ፕሮፌሰር) አነጋግሯል፡፡

  ሪፖርተር፡- ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያ ታሪክ የጦርነት ታሪክ ነው ይባላል፡፡ በእርግጥ የኢትዮጵያ ታሪክ ከጦርነት ጋር የተሳሰረ ነው? ለምንድነው እንዲህ የሚባለው?

  ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፡- የኢትዮጵያ ታሪክ የጦርነት ነው የሚለው በኢትዮጵያውያንም በውጭ አገር ሰዎችም በአብዛኛው ይነገራል፡፡ ግን ይህ ትክክል ነው? አይደለም? ብለን ብንመለከት በእርግጥ ትክክል አይደለም፡፡ ትክክል ካልሆነ ደግሞ ከምን መጣ የሚለው መታየት አለበት፡፡ ይኼ ከሁለት ነገሮች የሚመነጭ ነው፡፡ አንደኛ የታሪክን ምንነት አለመገንዘብና ከዚያ ግንዛቤ ጉድለት የመጣ ነው፡፡ ስለዚህ ታሪክ ምንድነው ብንል? ታሪክ የሰው ልጅ በተለያዩ ዘመናት በተለያዩ የሕይወት መስኮች ያከናወናቸው ድርጊቶች ናቸው፡፡ የሰው ልጅ ኑሮ ምን ዓይነት ገጽታ አለው ካልንም በአንድ በኩል ፖለቲካው አለ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ማኅበራዊ ሕይወቱ አለ፡፡ ሃይማኖቱም አለ፡፡ ኢኮኖሚውም አለ፡፡ ስለዚህ ሕይወት ዘርፈ ብዙ ነች፡፡ እንዲህ ከሆነ ኅብረተሰቡ ብዙ ነገሮችን ነው የሚያከናውነው፡፡ ስለዚህ ታሪክ እነዚህን ሁሉ አጠቃሎ የሚይዝ ነው ማለት ነው፡፡ በእኛ አገር ግን ታሪክ ሲባል ሰው በአብዛኛው የሚሄደው የፖለቲካ ታሪኩ ላይ ነው፡፡ የፖለቲካ ታሪክ ደግሞ በአብዛኛው የሚናገረው በመንግሥት ታሪክ ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ የነገሥታት ታሪክ ይነሳል፡፡

  ስለዚህ የአብዛኛው ህሊና ላይ ያለው የመንግሥት ታሪካችን ላይ ነው፡፡ እከሌ በዚህ ጊዜ ነገሠ፣ እከሌ እከሌን አሸንፎ እንዲህ ሆነ፣ እከሌ በዚህ ጊዜ እከሌ ከእከሌ ጋር ተዋግቶ አሸንፎ ነገሠ፣ በዚህ ጊዜ እነ እንቶኔ ወግተውን ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ግብፅ፣ በዚያኛው ጊዜ ደግሞ ጣሊያን ወሮን ነበር የሚለው ይጎላል፡፡ በጽሑፍም ደረጃ እንዲህ ያለው ይበረከታል፡፡ ዜና መዋዕሎች የሚያወሩን ስለንጉሡና ስለንጉሡ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ስለሚያደርጓቸው ዘመቻዎች ነው የሚነግሩን፡፡ ከዚያም ወደ ቅርብ ጊዜ ያሉ ሰነዶች የያዙዋቸው ነገሮች የመንግሥትንና የፖለቲካውን ታሪክ ነው፡፡ ይህ ስለሆነ በዚህ ውስጥ ጎልተው የሚታዩት በየዘመናቱ የተደረጉ ጦርነቶች ናቸው፡፡

  የዮዲት ጉዲት ጦርነት ተብሎ ይነሳል፡፡ ከዚያ በኋላ በመካከለኛው ዘመን የአዳል መንግሥት ጦርነት ይወሳል፡፡ አንዱ ደጃዝማች ከሌላው ጋር ያደረገው፣ ንጉሥ ከንጉሥ ጋር ያደረገው የፖለቲካ ሽኩቻ፣ ከውጭ ወራሪዎች ጋር ያደረግናቸው ጦርነቶች፣ እነዚህ እነዚህ ነገሮች ሲያመዝኑ ዝም ብሎ በተለምዶ የኢትዮጵያ ታሪክ የጦርነት ታሪክ ነው ይባላል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ታሪክ ብዙ ዘርፍ አለው፡፡ የፖለቲካ ታሪክ አንድ ነገር ነው፡፡ ከዚያ ውጪ የባህል፣ የኢኮኖሚ፣ የሥነ ጥበብና የማኅበራዊ ታሪኮች አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ የታሪክ ትልልቅ ክፍሎች ናቸው፡፡ በእኛ አገር የታሪክ አጥኚዎችም፣ ጸሐፊዎችም በአብዛኛው የሚያመለከቱት የፖለቲካ ታሪኩን ነው፡፡ የማኅበራዊ፣ የሥነ ጥበብ፣ የኢኮኖሚና የባህል ታሪካችንን ብዙም ትኩረት ሰጥተነው አናውቅም፡፡ ወደ ምዕራቡ ዓለም ስትሄድ ከዚህ የተለየ ታሪክ ሁሉ እየጻፉ ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት ታሪክ?

  ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፡- ቀደም ብዬ ከጠቀስኩልህ ታሪኮች አልፈው የቴክኖሎጂ ታሪክ አላቸው፡፡ ምክንያቱም በመሠረታዊነት ቀይሯቸዋል፡፡ የኢንዱስትሪ አብዮቱና ቴክኖሎጂው ስለተቀየራቸው፣ የታሪካቸው አንድ ዘርፍ አድርገው ወስደውታል፡፡ እኛ አገር ግን የምንደጋግመው የፖለቲካ ታሪኩን ነው፡፡ በጥናትም፣ በመነበብም በአብዛኛው የሰውን ህሊና የሚይዘው ይኼው ነው፡፡ ስለዚህ ከፖለቲካ ታሪክ ወጥተን ሌላውን ታሪክ በደንብ ተመራምረን መጻፍ አለመቻላችን፣ ለዚህም ትኩረት አለመስጠታችን የፈጠረው ነው፡፡ ለምሳሌ የራሴን ብነግርህ በሁለተኛ ዲግሪዬ ላይ ጥናትና ምርምሬን ያደረግሁት በኢትዮጵያ የሥነ ሥዕል ታሪክ ላይ ነው፡፡ የሥነ ሥዕል ታሪኩን ስታየው የተለየና ልዩ ውበት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ከዚያ ወጣ ብለን ብንመለከት ታሪካችን የጦርነት ታሪክ አይደለም፡፡ ከዚህ ያለፈ ታሪክ ነው፡፡ ጦርነት አውሮፓ ውስጥ ነበር፡፡ ለዘመናት በጦርነት ያልተገነባ አገር የለም፡፡ እስካሁን ድረስ እኮ ጦርነት አለ፡፡ በአገራቸው አይዋጉት እንጂ ጦርነት አለ፡፡     

  ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ታሪክ የጦርነት ነው ወይ የሚለውን ጥያቄ ያስቀደምኩበት አንዱ ምክንያት፣ በኢትዮጵያ የተደረጉ ጦርነቶች ምን ይመስሉ ነበር የሚለውን ጉዳይ ከግምት በማስገባት ብቻ ሳይሆን፣ አሁን በቅርቡ በትግራይ ክልላዊ መንግሥት ሕግን ለማስከበር የተወሰደው ዕርምጃ መነሻ በሰሜን ዕዝ ላይ የሕወሓት አመራር ከፈጸመው ድርጊት ጋር በማያያዝ፣ ኢትዮጵያ እንዲህ ባለ መንገድ ጦርነት ውስጥ የገባችበት ጊዜ አለ ወይ ለማለት ነው፡፡ የሕወሓት ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ ወሰደ በተባለው ያፈነገጠ ዕርምጃ ዘርን መሠረት ያደረገና የገዛ ወገን ላይ የማይታሰብ ጥቃት ፈጽሟል ተብሏል፡፡ ይህ ድርጊትም በእጅጉ እየተወገዘ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ ወደ ጦርነት ተገብቷል፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ የጦርነት ታሪክ ወይም ከአገር ሠራዊት ጋር ተያይዞ እንዲህ ያለው ነገር አጋጥሞ ያውቃል ወይ? እንዲያውም በዓለም ታሪክ የሌለም ነው እየተባለ ነው፡፡ ወቅታዊ የጦርነቱን መነሻን እንዴት ያዩታል?

  ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፡- ኢትዮጵያ በረዥም ታሪኳ ውስጥ ብዙ ግጭቶችን አስተናግዳለች፡፡ ብዙ ጦርነቶችንም አሳልፋለች፡፡ የከፋ የምንለውና መንግሥትም አደጋ ላይ የወደቀበትና የተናጋበት የዘመነ መሣፍንትን ጊዜም አሳልፋለች፡፡ ነገር ግን እንደገና እያንሰራራ ነው የመጣው፡፡ ዘውድ ያንሰራራል፣ መንግሥት ያንሰራራል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ አሁን ትግራይ ውስጥ በሰሜን ዕዝ ላይ የተደረገውን ዓይነት ዘግናኝ፣ እንዲሁም በአገር ደረጃ ዜጎች ይህንን ባስታወሱ ቁጥር አንገት የሚያስደፋ ነገር ገጥሟት አያውቅም፡፡ ለምሳሌ ዘመነ መሣፍንትን ብንወስድ በርካታ ግጭቶች የነበሩበት ነው፡፡ የበጌ ምድር ባላባት ወይም ገዥ ከሌላው ገዥ ጋር ይዋጋል፡፡ የዳሞት ገዥ ከጎጃም ገዥ ጋር በተለያዩ ምክንያቶች ይጋጫል፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገር ሲፈጠር ግን ዘር አይጠይቅም፡፡ የአንዱ አንጋችና ሎሌ ከየትም ብሔር የመጣ ነው፡፡ ከደጃች ውቤ አንጋች አብዛኛው ሰሜን ነው፡፡ ወገራ አካባቢ ያለ ነው፡፡ ትግሬ ነው፡፡ በየትም ጊዜ በተደረጉ ጦርነቶችና ግጭቶች ላይ በራስ ወገን ላይ መነሳት፣ እንዲሁም ዘርን መርጦ የተነሳ ወይም ተደረገ ነገር አልነበረም፡፡ ይኼ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በሌላው አገር ታሪክስ አለ ወይ ብለን ከጠየቅክም በጭራሽ የለም፡፡

  እንዲያውም በተለያዩ ጊዜያት ትልልቅ አረመኔ መንግሥታት ተቋቁመው ነበር፡፡ ለምሳሌ ፋሺስቶችን ብንወስድ በጀርመን የናዚ ፓርቲ ይዞት የተነሳው የተለየና ራስን ከፍ የሚደርግ፣ ከሌላው የተለየን ፍጡራን ነን በማለት እንሻላለን ብሎ ነው የተነሳው፡፡ ጃፓኖች እዚያ ደረጃ አይድረሱ እንጂ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አካባቢ የዚያ ዓይነት አዝማሚያ ነበራቸው፡፡ ግን በወገናቸው ላይ አልተነሱም፡፡ በወገኑ ላይ እንዲህ ቃታ የሳበ፣ ወገኑን በዘር እየለየ የጨረሰ የለም፡፡ ይህንን በታሪክ የሚስተካከለው የለም፡፡ በትንሹ ይኼ ነው ብልህ ሊመሳሰል የሚችልና ልጠቅሰው የምችለው ምሳሌ የለም፡፡ በታሪካችንም ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡ በክፉ ጊዜ እንኳን ሊፈጸም የማይታሰብ ነው፡፡ ይህ ግን አስበህ፣ ሆን ብለህ፣ ተዘጋጅተህ፣ መሣሪያ አንስተህ አዘናግተህ፣ በተኛበት መግደል፣ እንዲሁም አንተ አማራ ነህ፣ ኦሮሞ ነህ እያልክ ወስደህ ማረድና መግደል በኢትዮጵያ ታሪክ ያልነበረና አምሳያም የሌለው ነው፡፡   

  ሪፖርተር፡- አምሳያም ያልተገኘለት ነው የተባለው ድርጊት ምንም ዓይነት ምክንያት ቢሰጠው ገላጭ ባይሆንም፣ ኢትዮጵያ ለዚህ ዓይነቱ አስከፊ ታሪክ የበቃችበት ዋነኛ ምክንያት ግን፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓት በብሔር ተቃኝቶ መጦዙ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ይህም የብሔር ፖለቲካ ያመጣው ጦስ እንደሆነ የሚያመላክት መሆኑን ብዙዎችን ያነጋገረ ነው፡፡ የሕወሓት ቡድን ለዚህ የበቃበት አንዱና ዋነኛ ምክንያት ይኼው በብሔር ፖለቲካ ውጤት ነው ማለት ይቻላል የሚሉም አሉ፡፡ በዚህ ሐሳብ ላይ የእርስዎ አመለካከት ምንድነው? ከዚህ በኋላስ በኢትዮጵያ ብሔርን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ አደገኛነት እንዴት ይገለጻል?

  ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፡- ይኼ ከመጣ እኮ ቆየ፡፡ ለምሳሌ ትናንት ማይካድራና ሁመራ ላይ የተፈጠረው አስደንጋጭ ነው፡፡ በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ ይደረጋል ተብሎ ያልታሰበ ነገር ነው የሆነው፡፡ የአንድ ብሔር ሰዎች አፈንግጠው ሌላውን መምታት ማለት እንዴት ይታሰባል? ሌላውን እንደ ባይተዋር አድርጎ ማጥቃት በጣም የከፋ ነገር ነው፡፡ የማይካድራና የሰሜን ዕዝ ጥቃቶች እኮ አሁን ወደ ምን ደረጃ ላይ እንሄዳለን የሚለውን ማመላከቻዎች ናቸው እንጂ፣ ብዙ የማንቂያ ደውሎች ነበሩ፡፡ አንደኛ ይብዛም ይነስም ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ ብሔር ተኮር ጥቃቶች ነበሩ፡፡ በአንድ በኩል የተወሰኑ ጽንፈኛ የፖለቲካ ቡድኖች ናቸው እንጂ፣ ይኼ እኮ ሕዝብ ለሕዝብ አይደለም ይባላል፡፡ እርግጥም ሕዝብ ለሕዝብ አይደለም፡፡ ጽንፈኛ የፖለቲካ ቡድኖች ነበሩ፡፡ ሥልጣን ይዞ የነበረው ሕወሓት/ኢሕአዴግ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ይተነኩስ ነበር፡፡ ለመደላደልም ሆነ ሥልጣኑን ለማራዘም ብሎ ይህንን ያደርግ ነበር፡፡ ደቡብ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ጌዴዮ፣ ጉጂ፣ ወዘተ አካባቢዎች እንዲህ ያሉ ነገሮች ተፈጠሩ፡፡ በአርብቶ አደሩ ዘንድ በውኃም በግጦሽም መጋጨት ነበር፡፡ ይህ ግጭት ግን ውሎ አያድርም፡፡ ያንን የሚፈቱበት የራሳቸው መንገድ አላቸው፡፡ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ ግን የፖለቲካ ሽፋን እያገኘ ከፌዴራሊዝምና ከአከላለሉ ጋር ሌላ ጥያቄ እየሆነ መጠኑ እየሰፋና እየከፋ መጣ፡፡ በ2010 ዓ.ም. የለውጥ እንቅስቃሴ ተጀመረ ሲባል እንደ አዲስ እንደገና አገረሸ፡፡

  ኦሮሚያ ሱማሌ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ደቡብ መልካቸው ከፖለቲካ ቡድን እያለፈ ወደ ሕዝብ የመሄድ አዝማሚያ እየመጣ ነው፡፡ በዚህ ላይ ትልቅ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሁሉ ሲደረጉ በተለይ ከ2010 ዓ.ም. በኋላ ያሉት ከበቂ በላይ የማንቂያ ደወሎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ካላነቁን ምንድነው ማድረግ የምንችለው? ስለዚህ መዘዙ ከመጀመርያው ጀምሮ የብሔር ፖለቲካ ይዘን መነሳታችን ነው፡፡ መነሻው ከዩኒቨርሲቲ ሆኖ ጫካ ገባ፡፡ 17 ዓመታት ቆይቶ ሲመጣ የብሔር ጭቆና ጥያቄ ትክክለኛ ጥያቄ ነው? አይደለም? ብሎ አልተመለከተም፡፡ እሱኑ የሙጥኝ ብሎ ቀጠለ፡፡ በተለያዩ የመዋቅራዊ ነገሮች ብሔር ገባ፡፡ ብሔር ሃይማኖት ውስጥ ገባ፡፡ ብሔር ትምህርት ተቋማት ውስጥ ገባ፡፡ ብሔር የመንግሥት አወቃቀር ውስጥ ገባ፡፡ ብሔር ማኅበራዊና ግንኙነት ውስጥ ገባ፡፡ ብሔር ኢኮኖሚ ውስጥ ገባ፡፡ ሁሉም ነገሮች የብሔር ቅኝት እየያዙ መጡ፡፡ ይኼ ከሆነ ተሳስተናል ማለት ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- ታዲያ መፍትሔው ምንድነው?  

  ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፡- የሚሻለው ነገር የብሔር ፖለቲካ የሚባለውን ነገር ማስቆም መቻል አለብን፡፡

  ሪፖርተር፡- ከችግሩ ንፃር እንዴት ማስቆም ይቻላል?

  ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፡- ይቁም ሲባል የመጀመርያው ነገር፣ አገርን የሚያህል ነገር ይዘን ስለብሔር ማቀንቀን ደረጃ ማውጣት ተገቢ ነው፡፡ ብሔርን ስናነሳ የተረሳው ነገር አንድነትና ኢትዮጵያ የሚባለው ነገር ነው፡፡ ይህ ሆን ብሎ እንዲጠፋና መድረክም እንዳያገኝ ሲደረግ ነበር፡፡ ትልቁ ነገር ብሔሮች የተፈጠሩት ከ1983 ዓ.ም. በኋላ አይደለም፡፡ የተፈጠሩት ከዚያ በፊት ነው፡፡ ፈጣሪቸው ሕወሓትኢሕአዴግ አይደለም፡፡ የብሔር ማንነታቸውን ያገኙት ትውልዶች በዘመናት ባደረጉት ሥራ ነው፡፡ ባህላቸውና ቋንቋቸው የዳበረው፣ የብሔር መገለጫ የሆኑ እሴቶች ሁሉ የዳበረው ቀድሞም ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት ስንል ብሔርን የሚያጠቃ ነገር አይደለም፡፡ ብሔርን የሚሸፍን ነገር አይደለም፡፡ ብሔር ኖሮ ነው ኢትዮጵያ የኖረችው፡፡ ከ1983 ዓ.ም. በፊት ኦሮሞነት ነበር፡፡ ትግሬነት ነበር፡፡ ሲዳማነት፣ ጉምዝነት ነበር፡፡ ሱማሌነት ነበር፡፡ እንደውም ኢትዮጵያውነትም ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊነትን የብሔር ዋና ጠላት አድርጎ መቁጠር አያስፈልግም፡፡ ምክንያቱም ትልቁ ጃንጥላ ኢትየጵዊነት ነው፡፡ ለብሔሮችም ትልቁ ዋስትና ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ ይህ ስለሆነ መድረክና ትኩረት ኢትዮጵያዊነት ላይ ማጠንጠን ያስፈልጋል፡፡

  ሁለተኛ ፖለቲካውን ከብሔር አደረጃጀት እየፀዱ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ ከብሔር ያለፈ ፖለቲካ ሊኖር ይገባል፡፡ ለአንዱ ብሔር ብለህ የፖቲካ እንቅስቃሴ ስታደርግ ሌላው ላይ ጣትህን ቀስረህ ወይም ሌላውን ጠላት አድርገህ መሆን የለበትም፡፡ ይልቁንም የሌላውን መብት እያከበርክ መሆን አለበት፡፡ በኢትዮጵያ ያሉብን ብሔር ተሻጋሪ ችግሮች ናቸው መባል አለበት፡፡ ሰብዓዊ መብት መጣስ ብሔር ተሻጋሪ ነው፡፡ የፖለቲካ ጥያቄዎቻችን አሁን ካለንበት ዘመን አንፃር ስንመለከት፣ በብሔር ደረጃ የምንፈታቸው የትኞቹ ናቸው፡፡ ከብሔር ባለፈስ የሚገናኙ የትኞቹ ናቸው? ብሎ ተመልክቶ መፍትሔ ማበጀትና በብሔር ተቧድኖ መቆራቆስ እየቀነሰ መሄድ አለበት፡፡

  ሪፖርተር፡- የብሔር ፖለቲካው ኢኮኖሚው ውስጥም መግባቱ፣ እንዲህ መሆኑ ደግሞ ጉዳቱ እየታየ ነው ይባላል፡፡ ሌላው ቀርቶ ባንኮች ራሳቸው እንዲህ ያለው ነገር እየታየባቸው መሆኑ ይወሳል፡፡ ገንዘብ ብሔር የሌለው ቢሆንም፣ ቢዝነሶች ከብሔር አንፃር እየተቃኙ ነው እየተባለ ስለሆነ በዚህ ረገድ ያለውን አደጋ እንዴት መቀነስ ይቻላል?

  ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፡- ከፖለቲካ ቀጥሎ ትልቁ ነገር ኢኮኖሚ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ፖለቲካውንም የሚያሽከረክረው ኢኮኖሚ ነው፡፡ የሰው ልጅ የፖለቲካ መስተጋብሩ ከፖለቲካ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደምናየው በአንድ ጊዜ በብሔር ባይባልም፣ በአካባቢነት የሚታዩ ችግሮች መላ ሊበጅላቸው ይገባል፡፡ ግን አንዳንድ ጊዜ ኢኮኖሚው ላይ ከደኅንነት አኳያ የሚመጡ ነገሮች አሉ፡፡

  ሪፖርተር፡- ደኅንነት ሲባል?

  ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፡- ከ1983 ዓ.ም. በፊት በንግድም ሆነ በሌላ ሲተሳሰር በአብዛኛው ብሔር የኢኮኖሚ ጨዋታ ውስጥ አልነበረም፡፡ ከ1983 ዓ.ም. በኋላ ግን ፖለቲካው ኢኮኖሚውንም አባለገው፡፡ ባለሀብቱንም ጥያቄ ውስጥ ጣለው፡፡ ምክንያቱም የአንድ ብሔር ተወላጅ የሆኑ ሥልጣንም የያዙ እንደፈለጉ ኢኮኖሚው ውስጥ አድራጊ ፈጣሪ ሆኑ፡፡ ስለዚህ ከእነሱ ጋር በሽርክና መሥራት አይቻልም፡፡ በሽርክና ኢንቨስት ማድረግም አይቻልም፡፡ እንዲህ ያለው ነገር ሰው ሌላ ነገር እንዲያስብ አድርጎታል ሊባል ይችላል፡፡ ስለዚህ በመንግሥት ደረጃ ይህንን ነገር ማክሸፍ ያስፈልጋል፡፡ ማርከሻውም ከዚያ መምጣት አለበት፡፡ ይህ ሲሆን የኢኮኖሚ መስተጋብሩ ኢኮኖሚውንም ፖለቲካውንም ሊታደግ ይችላል፡፡ በእርግጥ የብሔር ፖለቲካው ወደ ኢኮኖሚው ገብቷል፡፡ ይህ ደግሞ በዚያው ከቀጠለ ዞሮ ዞሮ ለፖለቲካው ሳንካ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ባለሀብቱ ዘንድ መተማመን መፈጠር አለበት፡፡

  ሪፖርተር፡- መተማመኛ የሚሆነው ምንድነው? ምንስ ቢሠራ ሊለወጥ ይችላል?

  ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፡- ለምሳሌ በመንግሥት ፖሊሲዎች ሊሆን ይችላል፡፡ ሁለተኛ  የባለሥልጣናት እጆች በአብዛኛው ሲደረግ የነበረው እኮ ወረቀት መሳይ ይዘው ብድር፣ ኢንቨስትመንት ሲሉ ነበር፡፡ ጠዋት ለታክሲ ያልነበረው ሰው እኮ ባለው ግንኙነት ብቻ በአንድ ጀንበር ሚሊየነር የሚሆንበት ዘመን ነው፡፡  እንዲህ ባለ ሁኔታ አንዳንዶች ገንዘባቸውን ወደ አንድ ጥግ ይዘው ቢገቡ አይገርምም፡፡ ግን ይህ መጥፋት አለበት፡፡ ከዚህ ሌላ ማንነትም ከብሔር መላቀቅ አለበት፡፡ ሌላው እንዴት ነው የምንቀበለው ከተባለ ዕውቅናው ከሰውየው ኢትዮጵያዊነት መምጣት አለበት፡፡ ሰውን መታወቂያ ስትሰጠው ማንነቱን በብሔር የምትገልጽ ከሆነ ነገ ከነገ ወዲያ ግጭቶች ይመጣሉ፡፡ ያቺ ማንነት በብዙ ትመነዘራለች፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት አንድ የሚያደርገን ስለሆነ በዚህ እንታወቅ፡፡ ኢትዮጵያዊነቴን የማገኘው ከኦሮሞነቴ ወይም ከአማራነቴ ከሆነ ስህተት ነው፡፡ 

  ሪፖርተር፡- በቅርቡ ጠቅላለይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በፓርላማ ማብራሪያቸው ምክንያት፣ የሕወሓት ቡድን ይህ ያህል ደረጃ ተደራጅቶ ይሠራ ነበር ወይ የሚል ጥያቄ በማስነሳት ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ የእሳቸውን ገለጻ እንዴት አገኙት?

  ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፡- ለምሳሌ የሕወሓት ቁንጮ አመራር በአገሪቱ ተደርጎ የማይታወቅ ነገር ፈጽሟል፡፡ ብዙዎቻችን ደንግጠናል፡፡ ከዚያ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ሰሞኑን ካደረጉት ንግግር እንደሰማነው የክሳቸውን ደኅንነትና ህልውና እስከ መፈታተን የደረሰ ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ከምን የመጡ ናቸው? በእውነት እንጠብቀው ነበር ወይ ብንል መልሱ አዎ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ እንቅስቃሴን የመገደብና በህልውና ላይ የመምጣት ነገርን አላወቅነውም፡፡ ሲናገሩ ነው ያወቅነው፡፡ ከዚያ ውጪ ግን በማካይድራ የተፈጸመው፣ ሌላ ቦታ ላይ ዜጋን ሲቀሰቅሱት የነበረው ነገር፣ መከላከያ ላይ የፈጸሙት ነገር ከባህሪያቸው የሚመነጭ ነው፡፡ ምክንያቱም እኔ በሕወሓት/ኢሕአዴግም አሁንም በሕወሓት ተስፋ ከቆረጥኩ ቆይቻለሁ፡፡ እነዚህ ሰዎች ለራሳቸው ህልውና ካልሆነ በቀር ምንም አያደርጉም፡፡ አንድ ጊዜ እንዲያውም ዕብዶች ብዬ ጽፌ ነበር፡፡

  ሪፖርተር፡- በዚህን ያህል ደረጃ የገለጹት በምን መነሻነት ነው? መቼም አንድ ነገር ሳይዙ እንደህ አይሉም ብዬ ነው፡፡

  ሪዳት ፕሮፌሰር አበባው፡- በ2001/2002 ዓ.ም. አካባቢ አርሶ አደሮችን ይሸልሙ ነበር፡፡ ሚሊየነር አርሶ አደሮች ተብለው ይሸለሙ ነበር፡፡ በወቅቱ አዲስ ነገር የሚባል ጋዜጣ ላይ እንደ ነፃ ሐሳብ አንድ አጭር ጽሑፍ አቅርቤ ነበር፡፡ ‹‹አርሶ አደሩ ሚሊየነር ቴክኖሎጂው ሞፈርና ቀንበር›› የሚል ነው፡፡ እዚህ ጽሑፍ ላይ ከፖለቲካው ተነስቼ ሳይሆን ከግብርና ፖሊሲው በመነሳት የጻፍኩት ነው፡፡ አርሶ አደር ሚሊየነር ይሁን ምንም ችግር የለውም፡፡ አሥር ሃያም ሚሊየን ይኑረው ጥሩ ነው፡፡ አርሶ አደር ሚሊየነር ተፈጥሯል፡፡ ጥሩ ነበር፡፡ ጥሩ የገበያ ትስስር ተደርጎ ጥሩ ግብዓት ግብርናው ላይ ተጠቅሞ፣ ገበያ ላይ ጥሩ ዋጋ ያላቸውን ምርቶች አምርቶ፣ ወዘተ. እንበል፡፡ ከዚያ አይሱዙ የገዛ አርሶ አደር፣ ሆቴል የገነባ አርሶ አደር ተባለ፡፡ ለዚህ ሽልማት ያስፈልጋል ወይ ነው? የግብርና ፖሊሲው የሚለው አርሶ አደር በትንሽ ይዞታ ካፒታል ካገኘ በኋላ፣ ወይም ሚሊየነር ከሆነ በኋላ ቴክኖሎጂ ሽግግር ያመጣል የሚል ነው፡፡ የቴክኖሎጂ ሽግግር ደግሞ አይሱዙ መግዛትና ሆቴል መገንባት አይደለም፡፡ ይህንን ማንም የከተማው ከበርቴ ያደርገዋል፡፡

  ጥያቄው ለምን ትራክተር አልገዙም ነው? አንድ ሆቴል ከመገንባትና አይሱዙ ከመግዛት ትራክተር መግዛት በጣም ይቀላል፡፡ ስለዚህ ለምንድነው ትራክተር ያልገዛው የቴክኖሎጂ ሽግግር ለምን አላመጣም? ስንል ባለው ትንሽ ይዞታ ትራክተሩን እንደ ግብዓት አይጠቀምም፡፡ ለዚያች መሬት ብሎ እንዴት ትራክተር ይገዛል ነው፡፡ ግን መሬት ቢሸጥና ቢለወጥ ትራክተርም ይግዛ፡፡ አሥር ሚሊዮን ብር ኖሮት በአምስት ሚሊዮኑ ተጨማሪ መሬት ቢገዛ ትራክተርን እንደ አንድ ግብዓት መጠቀም ያዋጣል፡፡ ግን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መሬት የሚሸጠውና የሚለውጠው በኢሕአዴግ መቃብር ላይ ነው ስላሉ፣ ለእኔ የጽሑፌ መደምደሚያ ያደረግኩት ኢሕአዴግ ዕብድ ነው፣ ዕብድ ደግሞ ቶሎ አይሞትም፣ ቢሞትም ቀብሩ ይዘገያል የሚል ነበር፡፡ ስለዚህ ከመጀመርያው ጀምሮ አነሳሳቸው አንድ ነው፡፡ ምን ዓይነት ተመሳሳይ ጭንቅላትና እኩይ ተግባር እንዳላቸው ያሳያል፡፡ በወቅቱ ብዙ ጥያቄዎች ነበሩኝ፡፡

  ሪፖርተር፡- ጥያቄዎን ያስታውሱኛል?

  ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፡- አዎ፡፡ ኢትዮጵያን ይጠላሉ፣ ታሪኳን ይጠላሉ፣ የሕዝቧን መፋቀርና አንድነቷን ይጠላሉ፡፡ በዚያው ልክ ይህችን አገር ያስተዳድራሉ፡፡ እንዴት ነው ይህ ነገር ቅኝ ገዥ ነህ? የምታስተዳድረውንና የወጣህበትን ሕዝብ ከጠላህ አንተ ማን ነህ? የሚል ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ያደረጉት ነገርም የሚገርም አይደለም፡፡ ከዚያ የባሰም አድርገዋል፡፡ የተሠራ አገር ሰርስረው ሰርስረው ወደኋላ ወስደዋል፡፡ አንድነቱ የተጠናከረን አገር በርዘዋል፡፡ 

  ሪፖርተር፡- አሁን ሕግ በማስከበር ሒደት የተደረሰበት ውጤት አለ፡፡ ግን ከዚህ በኋላ የሕወሓት ቡድን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ምንድነው? የትግራይም ሕዝብ እዚህ ላይ መታሰብ ስላለበት፣ የተፈጠረው ችግር እንዳይደገም ወደፊት ምን ሊሆን ይገባል ይላሉ?

  ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፡- አንደኛ እዚህ ላይ ደርሰናል፡፡ በቃ እንግዲህ የሕወሓት የመጨረሻ ክፋቱን ዓይተናል፡፡ ከዚህ በላይ ምንም ሊያመጣ አይችልም፡፡ ወገንን ከመግደል፣ የጠበቀውን ሠራዊት ከመግደል በላይ ምንም ሊያደደርግ አይችልም፡፡ ይህንን አገር መክዳትና የመሳሰለውን ብንልም ድርጊቱን ልንገልጸው አንችልም፡፡ ታዲያ እንዴት ነው መሆን የሚቻለው ቢባል ሦስት ነገሮችን ግምት ውስጥ አስገብቶ እነዚህን ለመፈጸም መትጋት ያስፈልጋል?

  ሪፖርተር፡- እነዚህ ሦስት ነገሮች ምንድን ናቸው?

  ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፡- አንደኛው እንዲህ ዓይነቱን ፓርቲ ለ30 ዓመታት ዓይተነዋል፡፡ የሰው ማንነቱን በዘር ወስኖታል፡፡ በብሔር ወስኖታል፡፡ ያን አድርጎ አጋጭቷል፡፡ አገሪቱን ትልቅ አደጋ ላይ ጥሏል፡፡ ከዚህ አልፎ ደግሞ መደበኛ ያልሆነ አደረጃጀት ያለው ቡድን ፈጥሮ ሰው አስፈጅቷል፡፡ ሳሞራ የሚባለው ቡድን ሚሊሻም አይደለም፡፡ ልዩ ኃይል አይደለም፡፡ ፖሊስ አይደለም፡፡ በተለየ ሁኔታ በፖለቲካ የተፈጠረና ገዳይ የሆነ ቡድን ነው፡፡ እዚህ ደረጃ ተደረሰ በማለት ምን ዓይነት ፓርቲ ነው ስንል ከፋሺስትና ከናዚ የሚስተካከል ፓርቲ ነው፡፡ ፋሺስትን ብንወስድ መደበኛ ፖሊስ ወይም ሠራዊት ኖሮ ጥቁር ለባሽ  ገዳዮች አሉት፡፡፡ እኛ አገር የካቲት 12 ጭፍጨፋ ሲያካሂዱ የነበሩ እነሱ ናቸው፡፡ ናዚዎችም ጄስታፓ የሚባል ገዳይ ቡድን አላቸው፡፡ አይሁዶቹን የሚገድል የነበረው እሱ ነው፡፡ ሕወሓትም እዚህ ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ነው፡፡ እዚህ ደረጃ ከደረሰ ይህ ፓርቲ ለአገር ህልውና አሥጊ ነው፡፡ የዚህን ፓርቲ ሐሳቡንም ማራመድ፣ ምልክቱንም መጠቀም ሁሉም በሕግ መታገድ አለበት፡፡ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተሞክሮ ይህንን ነው የሚያሳው፡፡ ስለዚህ ሐሳቡም፣ ምልክቱም በሙሉ መከልከል አለበት፡፡ እንዲህ ያለ ሕግ ያስፈልጋል፡፡ ለሌላውም ትምህርት ይሆናል፡፡ ለመሰሎቹም እንዲህ መሆን አለበት፡፡ ሁለተኛ በትግራይ አዲስ የፖለቲካ ኃይሎች እንዲፈጠረና የተፈቱት ደግሞ እንዲቀሰቀሱ ሰፊ ሥራ መሠራት አለበት፡፡ የትግራይ ሕዝብ ተጨቁኗል፡፡ ጭቆናው ደግሞ እየተባባሰ የመጣው ከ1983 ዓ.ም. በኋላ ነው፡፡  

  ሪፖርተር፡- ከ1983 ዓ.ም. በኋላ ተባብሷል የምንልበት ዋነኛ ምክንያት ምንድነው?

  ረዳት ፕሮፌሰር አበባው፡- ሕወሓት ለሁለት ተከፈለ በተባለበት ወቅት ነው፡፡፡ ከዚያ በኋላ የፖለቲካው አፈና ከፍተኛ ሆኗል፡፡ ፓርቲም እኮ መፈጠር የጀመረው ከ1993 ዓ.ም. በኋላ ነው፡፡ ስለዚህ የትግራይን ሕዝብ የምመለከተው እዚህ በየከተማው በማያቸው ጥቂት ሀብታሞችና የደላቸው፣ ሁለተኛ ደግሞ ዕቡይና እኩይ ባህሪ ባላቸው ሰዎች አይደለም፡፡ እዚያ ስንት ምስኪን አለ፡፡ ውኃ ለማግኘት ቀናት የሚጓዙ አሉ፡፡ ብዙ ቦታዎች እንደዚያ ነው፡፡ አፅቢ ወንበርታ፣ አበረ ወፀጋና የመሳሰሉትን ብትወስድ ውኃ የለም፡፡ ስለዚህ የትግራይ ሕዝብ በጭቆና በአፈና ውስጥ የነበረ ነው፡፡ ስለዚህ በትግራይ የፖለቲካ ምኅዳሩ መስፋት አለበት፡፡ ምኅዳሩ ሲሰፋ ደግሞ የሐሳብ ልዩነትም ይመጣል፡፡ የሐሳብ ልዩነቶች የሚስተናገዱበት መድረክ ይፈጠራል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያለው ዕርምጃ ወደ ጥሩ መንገድ ይወስዳል፡፡ ሦስተኛው የትግራይ ሕዝብ ከክልሉ ውጪ ብዙ አለ፡፡ ከአማራ ቀጥሎ ከክልሉ ውጪም በመኖር ሁለተኛ ትግራይ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይህ ከጥንት ጀምሮ ነው፡፡ ከክልሉ ውጪ ሲኖር ብዙ መስተጋብር አለ፡፡ ይህ የአንድነት ማጠናከሪያ መሆን አለበት፡፡ የሕወሓትን ዓላማ ለማክሸፍ በከተሞች አካባቢ ያሉ የትግራይ ተወላጆች የራሳቸው ሚና ሊኖራቸው ይገባል፡፡ መሀል አገር ላይ ያለውን እውነታ ደግሞ ሕወሓት እንደሚያወራው ሳይሆን፣ ያዩትንና የሚኖሩበትን ሁኔታ የማንፀባረቅ አለባቸው፡፡ ሕወሓት የተንሻፈፈ መንገድ ላይ እንደነበር በግልጽ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ሦስት ነገሮች ወሳኝ ናቸው፡፡

  ተዛማጅ ፅሁፎች