Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መለገስና መቆጣጠር

ኢትዮጵያውያን አንድነትን በተለያዩ ሁኔታዎች ይገልጻሉ፡፡ ውስጣችን አንድነት አለ፡፡ መተሰባሰቡም ቢሆን የኖርንበት ነው፡፡ ኋላ ላይ ለአብሮነታችን እንቅፋት የሆኑ የበዙ ችግሮች ቢገጥሙንም እነዚህን ስንክ ሳሮች ተሻግረናቸዋል፡፡ አንድ የምንሆንበትን፣ አንዱ ለሌላው የሚያስብበትን አጋጣሚዎች አግኝተን በዚያ እየተጓዝን ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡ ይህ የሚያሳየን አብሮነታችን ውስጣችን ስላለ እውነትም ስለሆነም ነው፡፡ ወሳኝ ሰዓት ላይ ይህ ለአገር ዘብ መቆም የኖርንበት በደማችንም ያለ ነው፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያውያን አንድ ነን የምንለው፡፡ አትግቡብን ብለን የምንሞግተውም ለዚሁ ነው፡፡

እንዲህ ያለው የመተሳሰብ አንዱ ለአንዱ መቆም እንዲሸረሸር የተሠራው ሥራ ብዙ ቢሆንም በተለይ በአገር ሉዓላዊነት ላይ ባለመደራደር እንታወቃለን፡፡ ከዚህ ባሻገር የሁላችንንም ዕገዛ አገር በምትሻበት ወቅት ልዩነቶቻችን አጥፍተን በአንድ የመቆማችን ምክንያት ተለያይተን መኖር አለመቻላችንን ያሳያል፡፡

ዛሬ ላይ በብዙ አጋጣሚዎች አንዱ ለሌላው ለመድረስ የሚደረጉ በጎ ተግባራትን ብዙ ጊዜ እንሰማለን፡፡ ለበጎ ተግባር ተብለው የሚዘረጉ እጆች ብዙ እየሆኑ ነው፡፡ በግዳጅ ሳይሆን በፈቃደኝነት የሚተገበሩ ተግባራትንም እያየን ነው፡፡ መስጠት የሚያስደስት ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም መታደግ አገርንም ማበልፀግ ስለመሆኑም ተገንዝበን እንዲህ ባለው መንገድ ልምምዳችን ከፍ ብሏል፡፡ በቅርቡ የኮቪድ-19 ጉዳይ በምሳሌነት ይቀርባል፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ የመከላከያ ሠራዊቱን ለመደገፍ ያየነው ተነሳሽነት በብዙ ልዩነቶቻችን መሀል አንድ የምንሆንበትም ብዙ ነገሮች እንዳሉ አሳይቷል፡፡

ለወገን በሚጠቅሙና ለአገር ለሚበጁ ሐሴቶች በሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ ዜጎች ያሳዩት ርብርብ የበለጠ ስለአገር ማሰብ መቻላችንን ያሳያል፡፡

መስጠት ከመንፈስ እርካታ ባሻገር አገር ላይ የሚያሳርፈውን አዎንታዊ አሻራም መረዳታችንን ይነግረናል፡፡ ለራስ ብቻ መኖር እንደማይቻል ያሳየናል፡፡ ይህንንም እየተረዳን ነው ማለት ነው፡፡ በዚህ ረገድ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ተምሳሌትነት እዚህ ላይ አለማንሳት አይቻልም፡፡ በበጎ ፈቃድ መከወን የሚችሉ ብዙ ነገሮችን አሳይተዋል፡፡ ይህም ነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከበጎ ሥራ ጋር በተያያዘ ብዙ ነገሮችን ያየነው፡፡

በመስጠትና መልካም ነገር በማድረግ ብዙ ነገሮች ስለማሳየታቸው ማንም አይክድም፡፡ ሌሎችም እንዲከተሏቸው አድርጓል፡፡

ይህ እየተለመደና እየሰፋ ይመጣል፡፡ የበለጠ እንዲጎለብት ነገም ያለ ስስት እጅ ለመዘርጋት አገርንም ለመጥቀም ከታሰበ በተለያዩ ጉዳዮች ከሕዝብ የሚሰበሰቡ ድጋፎች በአግባቡ ሥራ ላይ ስለመዋላቸው ማረጋገጫዎች ሊኖሩ ይገባል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገርም ውስጥም ሆነ በውጭም ያሉ ዜጎች ለተለያዩ ፕሮጀክቶች መልሶ መቋቋና ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ገንዘብ ሲያወጡ በዓይነት ሥጦታ ሲያበረክቱ እናያለን፡፡

እንዲህ ባለው ሁኔታ የሚሰበሰብ ሀብት ከመንግሥት በጀት ጋር የሚቀላቀል አይደለም፡፡ ካሰላነው ደግሞ ሀብቱ እጅግ ብዙ እንደሆነ እንገምታለን፡፡ ለህዳሴ ግድብ የተዋጣው የገንዘብ መጠን ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡

እንደ ህዳሴው አይሁን እንጂ ለሌሎች ጉዳዮች ግለሰቦችና ተቋማት የሚያበረክቱት ገንዘብ ልገሳው በተፈለገበት ወቅት የተሰበሰበው ገንዘብ በአግባቡ ሥራ ላይ መዋል አለመዋሉን ማሳወቅ ተገቢ ነው፡፡

ከመንግሥት በጀት ውጭ ነው በሚል ችላ ሊባል የማይገባውም ነው፡፡ ስለዚህ ለተለያዩ ጉዳዮች የሚሰበሰበው ገንዘብና ሀብት በአግባቡ ኦዲት መደረግ ዓላማውን ማሳካት አለማሳካቱን ማሳወቅ ተገቢ ነው፡፡ ተመሳሳይ ጥሪ ሲደረግ የሚዋጣው ወይም የምንደግፈው ነገር ውጤት ስላለው አሁንም አደርጋለሁ የሚለው እንዲጨምር ያደርጋል፡፡

ለምሳሌ እንደ ሸገርና እንጦጦ ያሉ ፕሮጀክቶች ያሳዩት አፈጻጸም ሌሎች ፕሮጀክቶችን ወልዷል፡፡ ብዙዎች ለአዲሶቹ ፕሮጀክቶች ሲደግፉ በዓይናችን ያየነው ነገር ስለሆነ ለተመሳሳይ ፕሮጀክቶች ድጋፍ ሲያደርጉ አላቅማሙም፡፡

ስለዚህ በበጎነት የሚደረጉ ድጋፎች ለታሰበላቸው ዓላማ መዋል አለመዋላቸውን የሚያረጋግጥ ራሱን የቻለ ተቋም ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ይህ ካልሆነም ለበጎ ተብለው የሚለገሱ የገንዘብም ሆነ የዓይነት ድጋፎች በአግባቡ ተሰብስበው በአግባቡ ለተፈላጊው ዓላማ መዋላቸውን የሚያረጋግጥ በሒሳብ አዋቂ ጭምር የተመሰከረ ሪፖርት የማቅረብ ልምድ መዳበር ይኖርበታል፡፡ በግልጽ ከሕዝብ የተሰበሰበ ሀብት በመንግሥት የበጀት ቋጥ ውስጥ ገብቶ ሥራ ላይ ካልዋለ በቀር አይመረመርም ኦዲት አይደረግም መባል የለበትምና ለተለያዩ በጎ ተግባራት የሚሰበሰቡ ሀብቶች ጉዳይ በወግ በወጉ ሆነው ለሰጪው ይኸው እንዲህ ሆኗል ማለት ይገባል፡፡

ይህም እየተነሳ ያለውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎትና ልገሳ የበለጠ እንዲያድግ ከማድረጉም በላይ በምንም ሁኔታ ውስጥ መስረቅ የለመዱ እጆችን ለመከላከልም ይረዳል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት