Friday, December 8, 2023

በትግራይ ክልል በሕግ ማስከበር ዘመቻ ታየ የተባለው መድልኦና መገለል ተቃርኖ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

‹‹በሥራ ምክንያት በተደጋጋሚ ወደ አሜሪካ እመላለሳለሁ። በዚህ ምክንያት ባለፈው ሳምንት ወደ አሜሪካ መጓዝ ስለነበረብኝ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሼ ለጉዞ የሚያስፈልጉኝን ሒደቶች ብፈጽምም፣ የኢሚግሬሽን መስኮትን ግን ማለፍ አልቻልኩም። ከአገር መውጣት አትችልም ተባልኩ፡፡ ምክንያቱን የሚነግረኝ አልነበረም፤›› ሲል ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀ አንድ በአዲስ አበባ የሚኖር የትግራይ ተወላጅ የገጠመውን ለሪፖርተር ገልጿል።

ይህ በአርባዎቹ ዕድሜ መጀመርያ ላይ የሚገኘው ስሙ እንዳይጠቀስ የገለጸ መንገደኛ ቋሚ ነዋሪነቱ በአዲስ በአበባ እንደሆነ፣ የቤተሰብ ኃላፊ መሆኑን፣ በተጨማሪም ቤተሰቦቹ አሁንም በአዲስ አበባ ነዋሪ እንደሆኑ ለሚያስተናግዱት ሠራተኞች ቢያስረዳም እንዳልጠቀመው ተናግሯል። 

‹‹ፓስፖርቴንና መታወቂያዬን ብለው ከተመለከቱ በኋላ ተጨማሪ የራሳቸውን ወረቀት እያስተያዩ ደቂቃዎች ከፈጁ በኋላ ከአገር መውጣት አትችልም አሉኝ። ምክንያቱን ስጠይቅ ከላይ የመጣ መመርያ ነው አሉኝ፤›› በማለት የገጠመውን አስረድቷል። 

የገጠመውን ችግር እንዴት መፍታት እንደሚችል ቢጠይቅም፣ ትብብር አለማግኘቱንና በደፈናው ‹‹የሚመለከተውን አካል ጠይቅ›› የሚል ምላሽ እንደተሰጠው ይናገራል። 

በዚሁ አጋጣሚ በአውሮፕላን ማረፊያው ተርሚናል ውስጥ ያገኘው አንድ የሚያውቀው መንገደኛ እንደነበርም ይኸው መንገደኛ ይገልጻል። ከረዥም ጊዜ በኋላ በአጋጣሚ ያገኘው የቀድሞ ወዳጁ ወደ ካናዳ ተጓዥ እንደነበር የገለጸው ይኸው ባለታሪክ፣ ይኸው ወዳጁም ተመሳሳይ ዕጣ እንደገጠመው አክሏል። 

ይህ የቀድሞ ወዳጅ የትግራይ ተወላጁ ቢሆንም፣ ዜግነቱን ቀይሮ ካናዳዊ ስለመሆኑ እዚያው ውስጥ ሲጨዋወቱ በነበረበት ወቅት እንዳወቀ ገልጿል። 

‹‹ነገር ግን እሱም እንደ እኔ መውጣት አትችልም እንደተባለና በሁኔታው ተገርመን መፍትሔው ግራ እንደገባን ከተርሚናሉ ወጣን፤›› ሲል አስረድቷል። 

የትግራይ ተወላጆች ከአገር ውጭ እንዳይወጡ ተብሏል የሚል ተባራሪ ወሬ ቢሰማም እውነት ይሆናል ብሎ እንዳልተቀበለው፣ ምናልባት ከሚፈለጉ የሕወሓት አመራሮች ጋር ግንኙነት ያላቸው እንዳይወጡ ተከልክለው ያስተዋሉ፣ ነገሩን አስፍተው ያሰራጩት ወሬ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ብቻ እንደነበረውም ጥርጣሬውን አጋርቷል። 

‹ዜግነቱን የቀየረው ወዳጄ መውጣት አትችልም ሲባል ግን ነገሩ በጅምላ የተወሰነ ክልከላ እንደሆነ ገባኝ። የካናዳው ትግርኛ ተናጋሪ ወዳጄ ወደ አገሩ መመለስ ካልቻለ እኔ ምን አፍ አለኝ?›› በማለት የገጠመውን ሁኔታ ዘርዝሯል። 

ይህ ታሪክ የእነዚህ መንገደኞች ብቻ አይደለም፡፡ በርካታ የትግራይ ተወላጆች በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ዘመቻ መወሰድ ከጀመረበት ዕለት አንስቶ በተለያዩ ምክንያቶች በሕጋዊ መንገድ ከአገር ለመውጣት አለመቻላቸው በገሃድ የሚታወቅ ሀቅ ሆኗል። 

ነገሩ ከዚህም አልፎ ከትግራይ ክልል ውጪ በሚገኙ የተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች፣ በተለይም በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ከሚሠሩባቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላልተወሰነ ጊዜ በቤታቸው እንዲቆዩ ተደርገዋል። 

መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሂውማን ራይትስ ዋች ከሳምንት በፊት ተዓማኒ ማስረጃዎች አግኝቻለው ብሎ ባወጣው መግለጫ፣ ይህንኑ በትግራይ ተወላጆች ላይ የሚፈጸም መድልኦ አመልክቷል።

በአንድ ሲቪል የሆነ የመንግሥት ተቋም የሚሠራ ግለሰብን በማነጋገር፣ ያለበቂ ምክንያት ወደ ሥራ ገበታው እንዳይመጣ መደረጉን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ ይገልጻል። 

‹‹እኔ ብቻ ሳልሆን ሌሎች አብረውኝ የሚሠሩ የትግራይ ተወላጆች ላልተወሰነ ጊዜ ወደ ሥራ እንዳንመጣ በአለቆቻችን ተነገረን። ለምን እንደሆነና ለምን ያህል ጊዜ ቤታችን እንደምንቀመጥ ብንጠይቅም፣ ምክንያቱን እንደማያውቁና ከላይ የመጣ ትዕዛዝ እንደሆነ አለቆቻችን ነገሩን እንጂ ምክንያቱን ማወቅ አልቻልንም፤›› ማለታቸውን ተቋሙ ይገልጻል። 

ከሥራ ገበታቸው መታገድ ብቻ ሳይሆን የመንቀሰቀስ መብታቸውንም ተነፍገዋል የሚለው ይኸው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ቡድን፣ በሰዎች ላይ መድልኦ ማግለል መፈጸም፣ እንዲሁም አመክንዮ በሌለው መንገድ በሰዎች የግል መብት ላይ ጣልቃ መግባት በዓለም አቀፍ ሕግ የተከለከለ እንደሆነ በመግለጫው አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ኃላፊዎች ይህንን ጥሰት ማስተካከል እንዳለባቸው የሚገልጸው መግለጫው፣ የተፈጸሙት ጥሰቶች በሕዝቦች መካከል መጠራጠርን እንደሚያፋፍሙና የትግራይ ተወላጆች ከሌላው ማኅበረሰብ እንዲነጠሉ ሊያደርግ እንደሚችልም በመግለጫው አስረድቷል። 

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ይህንኑ በትግራይ ተወላጆች ላይ የሚፈጸም መድልኦና መገለል ኮንኗል።

በትግራይ ተወላጆች ላይ ብሔርን መሠረት ያደረገ መድልኦዎና መገለል እየደረሰ መሆኑን ከሚቀርቡለት በርካታ ቅሬታዎች መገንዘቡን የሚገልጸው ኮሚሽኑ፣ ይህም በከፍተኛ ደረጃ እንዳሳሰበው አመልክቷል። 

ድርጊቱ በተወሰኑ ሰዎች ላይ በተለይም ከሥራ አስገዳጅ የእረፍት ጊዜ በማስወሰድና ለሥራ፣ ለሕክምናና ለትምህርት  የሚደረጉ ጉዞዎችን  በመከልከል የሚገለጽ መሆኑን እንደተረዳም ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

እንደዚህ ዓይነት ብሔርን መሠረት ያደረገ መድልኦና መገለል እንዲፈጸም የሚፈቅድ የመንግሥት ፖሊሲም ሆነ የሕግ ማዕቀፍ በአገሪቱ እንደሌለ የሚገልጸው ኮሚሽኑ፣ የተወሰኑ ተጠርጣሪዎችን ለመከታተል የተነደፈ የፀጥታ ጥበቃ ዕርምጃ  በተግባር ተለጥጦ አላስፈላጊ  ማኅበረሰባዊ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ አስታውቋል።

በዚህ ረገድ ኮሚሽኑ ሲያደርግ በነበረው ክትትል መሠረት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች ጋር ውይይት በማድረግ፣ ችግሩ በአፋጣኝ እንደሚቀረፍ እንደተገለጸለትና ይህንንም ምላሽ  በበጎ እንደተቀበለው አስታውቋል።

‹‹ስለሆነም ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት በሙሉና በተለይም የኤርፖርት  ደኅንነት ሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ያለበቂ ሕጋዊ ምክንያት ማናቸውንም ተጓዦችን ከጉዞ እንዳይከለክሉ በጥብቅ አሳስባለሁ፣ ሁኔታውንም በቅርበት እከታተላለሁ፤›› ብሏል። 

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኮሚሽኑ ከፍተኛ አማካሪ አቶ ምሥጋናው ሙሉጌታ እየተፈጸመ ያለውን መድልኦና መገለል፣ ኮሚሽኑ የመብት ጥሰት ከተፈጸመባቸው ግለሰቦችና ከመገናኛ ብዙኃን መረዳቱን ገልጸዋል። 

በርከት ያሉ የጥሰቱ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች በአካል ወደ ኮሚሽኑ በመምጣት የደረሰባቸውን በደል እንደገለጹ፣ ተመሳሳይ ቅሬታዎችም በስልክ ለኮሚሽኑ እንደቀረቡ ገልጸዋል። 

የመብት ጥሰቱ ብሔርን መሠረት ያደረገ በመሆኑ የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል የሚሉት አቶ ምሥጋናው፣ የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብም ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች ጋር መነጋገሩን ገልጸዋል። 

ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በነበረው ውይይትም ኃላፊዎቹ የተፈጸመው የመብት ጥሰት ተገቢ እንዳልሆነ፣ ለደኅንነት ጥበቃ ተብሎ በተወሰኑ ግለሰቦች ላይ የተጣለውን ገደብ የመንግሥት መዋቅሮች ለጥጠው በመተግበራቸው የተፈጠረ መሆኑን በማስረዳት፣ እንዲስተካከል እንደሚደረግ ቃል መግባታቸውን አስረድተዋል። 

ኮሚሽኑ በዚህ ጉዳይ ላይ ክትትል ማድረጉን እንደቀጠለ የገለጹት አቶ ምሥጋናው፣ አሁንም ችግሩ የገጠማቸው ሰዎች የኮሚሽኑን ነፃ የስልክ መስመር በመጠቀም እንዲያሳውቁ ጠይቀዋል። 

ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ባለሙያ፣ በትግራይ ተወላጆች ላይ የደረሰው መድልኦ ከጥሰትነቱ ባለፈ የመንግሥትን የመረጃ መሰብሰብ አቅም ውስንነት የሚያሳይ እንደሆነ ይገልጻሉ። 

በአጠቃላይ የትግራይ ተወላጆች ሰለባ የሆኑበት ምክንያት፣ እያጣሩ ነፃ ማውጣትና መንግሥት ለዚህ ጉዳይ በፍጥነት መልስ ሰጥቶ ማስተካከል እንዳለበት የሚያሳስቡት እኚሁ ባለሙያ፣ ይህ በፍጥነት መፍትሔ ካላገኘ በትግራይ ክልል የሚደረገውን የማረጋጋት ሥራ አስቸጋሪ ሊያደርገው ይችላል ሲሉ ሥጋታቸውን ይገልጻሉ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰኞ ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. በትግራይ ክልል ስለተካሄደው ‹‹የሕግ ማስከበር ዘመቻ” በሰጡት ማብራሪያ፣ የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል ያለውን የሕወሓት አመራር በሕግ ተጠያቂ እንዲሆን ከማድረግ ውጪ ሌላ ዓላማ የለውም ብለዋል። 

በዚህ ዘመቻ የትግራይ ሕዝብ ጭምር ተባባሪ እንደነበር ሲገልጹም፣ ‹‹በሁመራ በኩል እንዴት መከላከያን ትመታላችሁ ብሎ አብሮ የታገለና የቆሰለ የትግራይ ሕዝብ አለ። ሽሬ ስንደርስ መከላከያን የአካባቢው ነዋሪ እጁን ዘርግቶ ብቻ ሳይሆን የተቀበለን እናንተን እንድንመታ ያስታጠቁን ነው፡፡ እኛ ግን እናንተ ላይ ጥይት አንተኩስም ብሎ ሁለት መቶ ብሬን አምጥቶ አስረክቧል፤›› ብለዋል።

አክለውም፣ ‹‹አክሱም ስንደርስ ቁስለኞችን ደብቆ አቆይቶ አስረክቦናል። መቀሌ ላይ ከማኅበረሰቡ ጋር በነበረን ስብሰባ ዘገያችሁ ቢሆንም እንኳን መጣችሁ ደስ ብሎናል። ከመጣችሁ ደግሞ ቶሎ ብላችሁ መብራት ስልክ መልሱልን፡፡ ሕግና ሥርዓት የሌለው ከተማ እንዳይሆን አስተዳደር አቋቁሙልን ነው ያሉን፤›› ብለዋል። 

በሕግ እንዲጠየቅ ከሚፈለገው የሕወሓት አመራር ጋር ትስስር የሌላቸው፣ በትግራይም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ከሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው መደገፍና መጠበቅ እንደሚገባ ገልጸዋል። 

‹‹ይህንን ካላደረግን ቦታው ተቀያየረ እንጂ ከፅንፈኛው ሕወሓት አመራር አልተለየንም፤›› ሲሉም አክለዋል። ከላይ የተገለጸውን መድልኦና መገለል በተመለከተም ማብራራያ የሰጡ ሲሆን፣ የትግራይ ተወላጆች ከሥራ ውጪ ሆነው እንዲቆዩ መደረጉንም ሳይሸሽጉ ምክንያት ያሉትን አቅርበዋል። 

‹‹በትግራይ ክልል ብሔርን መሠረት አድርጎ በተፈጸመ ጭፍጨፋ በሌላ አካባቢ ያሉት የትግራይ ተወላጆች ላይ የቂም በቀል ጥቃት ተሰንዝሮ አደጋ እንዳይደርስባቸው ታስቦ የተደረገ መሆኑን፣ እነሱም ሆነ የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ መገንዘብ አለበት፤›› ሲሉ አንደኛው ምክንያት ይህ መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላኛውን ምክንያት ሲጠቅሱም፣ ‹‹የሕወሓት አመራር ዓላማን ለማስፈጸም የተገዙ ብዙ የትግራይ ተወላጅ ከክልሉ ውጪ መኖራቸው ደግሞ ምንም ጥርጥር የሌለው ነገር ነው። ቤቱ ቦምብና ፈንጂ የያዘ ብዙ አለ እዚህ። እስኪፈነዳ ድረስ መጠበቅ የለብንም፣ ከማይካድራው መማር አለብን፡፡ በሁለቱ ምክንያት እየተወሰደ ያለ ዕርምጃ ነው። ይህ እየተጣራ ሁሉም ቦታውን መያዝ ይኖርበታል፤›› ብለዋል። 

ከዚህ ውጪ ከትግራይ ሕዝብ ጋር ፀብ እንደሌለና በሕግ ማስከበር ዘመቻውም የተባበረ ሕዝብ እንደሆነ ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -