Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የመንገድ ዳር የንግድ እንቅስቃሴን የሚያስተዳድር ረቂቅ መዘጋጀቱ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከመንገድ ዳር ንግድ እንቅስቃሴዎች ጋር በተገናኘ፣ የትራፊክ አስተዳደር ፍሰትን ለማጣጣምና የአደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ያለመ፣ የደረጃ አስተዳደር ረቂቅ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

የመንገድ ላይ ንግድ ደረጃ አስተዳደር ረቂቅ ሕግ በዋናነት፣ የመንገድ ላይ ንግድና የአስተዳደሩ ሥርዓት ምን መምሰል እንዳለበት የሚያስረዳ ነው፡፡ ለመንገድ ላይ ንግድ ቦታዎችና ነጋዴዎቹ ሊተገብሩት ስለሚገባ አሠራር ያካተተ ነው፡፡

የደረጃዎች ኤጀንሲ መሠረታዊና አጠቃላይ ደረጃ ዝግጅት ቡድን መሪ አቶ ወርቁ አደፍርስ እንደተናገሩት፣ ለኤጀንሲው በቀረበው ጥያቄ መሠረት ለአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የተዘጋጀ ረቂቅ ሲሆን፣ የመንገድ ላይ ንግድ በትራፊክ ፍሰትና በእግረኞች ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ችግር እያጋጠመ በመሆኑ የተዘጋጀ ነው፡፡

የደረጃዎች አስተዳደር ረቂቅ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው የገለጹት አቶ ወርቁ፣ የመንገድ ላይ ነጋዴዎችን ሕጋዊ ማድረግ፣ የትራፊክ ፍሰት እንዲሻሻልና ለከተማ ውበት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ በዋናነት የመንገድ ላይ የንግድ እንቅስቃሴ ረቂቅ አስተዳደር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖት ቢሮ ጥያቄ መሠረት ይዘጋጅ እንጂ፣ የደረጃ አስተዳደር ረቂቁ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚያገለግል መሆኑ ተገልጿል፡፡

የመንገድ ላይ ንግድ እንቅስቃሴን የሚቃኝ ባለቤት መጥፋቱ ትልቁ ችግር መሆኑን የገለጹት አቶ ወርቁ፣ የደረጃ አስተዳደር ረቂቁ ነጋዴዎችን፣ የትራንስፖርት ዘርፉን፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች አካላት የሚተገብሩት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ የደረጃዎች ዝግጅት ባለሙያ አቶ እሱባለው ሸዋንዳኝ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የደረጃ አስተዳደር ረቂቁ በዋናነት የእግረኞች ደኅንነት ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ በዘርፉ የተሰማሩ ዜጎችን ሕጋዊ ከማድረግ አንፃር ከፍተኛ ጥቅም አለው ብለዋል፡፡ የደረጃ አስተዳደር ረቂቁ የመንገድ ንግድ ቦታ አመራረጥ በዋነኝነት የትራፊክ መጨናነቅ ባለበት፣ በመስቀለኛ እንዲሁም በመንገዶች ላይ የንግድ እንቅስቃሴ እንዳይኖር የሚገድብ ነው፡፡

የንግድ ሥርዓቱ ምን መምሰል እንዳለበትና በዘርፉ የሚመለከታቸው አካላት ማድረግ ስላለባቸው ተግባራት በደረጃ አስተዳደሩ ረቂቅ ተቃኝቷል፡፡ የመንገድ ላይ የነጋዴዎች ኮሚቴ በማዋቀር በክፍላተ ከተሞች እንቅስቃሴውን የሚቆጣጠሩ፣ ቦታዎችን በመምረጥ በዚህ ሥርዓት ነጋዴዎች ራሳቸው ኃላፊነት እንዲወስዱ የሚደረግበት አሠራር መኖሩ ተጠቁሟል፡፡

የመንገድ ላይ ንግድ እንቅስቃሴ አስተዳደር ውስጥ ለአንድ የመንገድ ላይ ነጋዴ ከሁለት ካሬ ሜትር በላይ መሰጠት እንደሌለበትና ነጋዴዎች ሕጋዊ መሆን እንዳለባቸው በረቂቅ ደረጃ አስተዳደሩ ተካቷል፡፡

የደረጃ አስተዳደር ረቂቅ ያሉበት ክፍተቶች ከባለድርሻ አካላት፣ እንዲሁም ኅብረተሰቡ አስተያየት ሰጥተውበት በድጋሚ የሚስተካከል እንዲሆን፣ እስከ አምስት ዓመት ድረስ የረቂቅ ደረጃ አስተዳደሩ በማሻሻል ሒደት ውስጥ እንደሚያልፍ፣ ሙሉ ለሙሉ ባለመጠናቀቁም ተግባራዊ ለማድረግ ጅማሮ ላይ እንደሆነ አቶ ወርቁ  ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች