ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚደረገው ድርድር የአስገዳጅነት ውጤት ያለው ሊሆን ይገባል ማለቷ ተሰማ፡፡
የሱዳኑ የውኃ ሀብትና የመስኖ ሚኒስትር ያሲር አባስ (ፕሮፌሰር) ከቀናት በፊት የህዳሴ ግድቡን ድርድር አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት፣ ሱዳን በአፍሪካ ኅብረት ለሚመራው የሦስቱ አገሮች ማለትም ለኢትዮጵያ፣ ለግብፅና ለሱዳን ድርድር እንደምትገዛ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ድርድር የሚደረሰው ስምምነት አስገዳጅ ካልሆነ፣ ሱዳን ከኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ልታገኛቸው የምትችላቸው ሰፋፊ ጥቅሞች በተሟላ ሁኔታ ሊሳኩ አይችሉም ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሦስቱ አገሮች መካከል የሚደረገው ድርድር ወደ ስምምነት መድረስ ያልተቻለባቸው ምክንያቶች የተወሰኑ የቴክኒክና ሕግ ነክ ጉዳዮች እንደሆኑ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ስምምነት በሚደረስበት የድርድር ውጤት አስገዳጅ ሊሆን ይገባል የሚለው የሕግ ክርክርና የህዳሴ ግድቡ የውኃ ሙሌት ሒደት ላይ ልዩነት በፈጠሩ አገሮች ልዩነታቸውን የሚፈቱበት መንገድ ምን ሊሆን ይገባል፡፡ እንዲሁም በድርድሩ የሚደረሰው ስምምነት ከሌሎች በዓባይ ውኃ ላይ ከተደረጉ የቀድሞ ስምምነቶች ጋር ያለው ትስስርን የተመለከቱ እንደሆኑ አክለዋል፡፡
በህዳሴ ግድቡ ላይ ያሉ ቀሪ የልዩነት ነጥቦችን ለመፍታት በሦስቱም አገሮች በኩል ፖለቲካዊ ፍላጎትና ቁርጠኝነት ሊኖር እንደሚገባ፣ ይህ ቁርጠኝነት ከመጣ የሁሉንም ወገኖች ፍላጎት የሚያሟላ ስምምነት ላይ ሊደረስ ይችላል የሚል እምነት በሱዳን በኩል መኖሩን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ በኩል ድርድርን መሠረት ያደረገ ስምምነት እንዲደረስ፣ ልዩነቶችም ድርድርና ውይይትን መሠረት ባደረገ መንገድ እንዲፈቱ አቋም መያዙን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ከህዳሴ ግድቡ በላይ በሚገኘው የዓባይ ውኃ ተፋሰስ ላይ ኢትዮጵያ የምታካሂዳቸውን የወደፊት የልማት ፕሮጀክቶች የመቆጣጠር ፍላጎት፣ በተለይ በግብፅ በኩል በመንፀባረቁ ኢትዮጵያ ይህንን የተመለከተ ድርድር እንደማታደርግ አስታውቃለች፡፡