Monday, April 15, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ አላቸው!

መልካም ዕድሎችን ማበላሸት በተለመደባት ኢትዮጵያ ዛሬም ከታሪክ ለመማር አለመፈለግ እየተስተዋለባት ነው፡፡ ለፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔዎች አሉ፡፡ በተጨማሪም ሕጋዊና ሞራላዊ መፍትሔዎችን ጭምር ማመንጨት በሚቻልባት አገር ውስጥ፣ ማዶ ለማዶ ሆኖ ዛቻ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ሰሞኑን በገዥው ብልፅግና ፓርቲ ሰዎች መካከል የሚስተዋለው ፍጥጫ፣ ረብ የለሽና ለአገር የሚደረገውን መስዋዕትነት የሚያራክስ ነው፡፡ በማንኛውም ጉዳይ ላይ ልዩነት መኖሩ የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ልዩነትን በሥርዓት ለማስተናገድ ተነሳሽነት ማጣት ግን አስፈላጊ አይደለም፡፡ ኃይልን አማራጭ ማድረግ ወይም ከውይይትና ከድርድር መሸሽ፣ ለዚህ ዘመን የማይመጥን ያረጀ አስተሳሰብ ውጤት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ሁሉም ነገር ለውይይትና ለድርድር መቅረብ አለበት እንጂ፣ እኔ ያልኩት ካልሆነ በማለት ጦር ለመነቅነቅ ማሰብም ሆነ መሞከር ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ እውነት ያለው እኔ ዘንድ ነው የሚል ማንኛውም ወገን ሕጋዊና ሰላማዊ መድረክን አይሸሽም፡፡ ሌላው ቀርቶ የፌዴራል ሥርዓቱን በተመለከተ የሚስተዋሉት ልዩነቶች ለሕዝብ ዳኝነት መቅረብ አለባቸው እንጂ፣ ባረጀና ባፈጀ አስተሳሰብ የአንድ ወገንን ፍላጎት ለመጫን መወራጨት ለማንም አይጠቅምም፡፡ ሐሳብን ወደ ገበያ ይዞ ወጥቶ በሰላማዊ መንገድ መፎካከር ነው የሚያዋጣው፡፡ ፖለቲካዊ ችግሮችን በኃይል ለመፍታት መሞከር ለውድቀት ይዳርጋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ በግልጽ እያስገነዘበ ያለው ኢትዮጵያን ለምንም ነገር መደራደሪያ ማድረግ እንደማይቻል ነው፡፡ ይህ አስተዋይ ሕዝብ የአገሩን ህልውና የሚጎዳ ማንኛውም ዓይነት ድርጊት እንደማይታገስ የታወቀ ነው፡፡ ጠባብ ቡድናዊ ፍላጎትን በማስቀደም በስሙ መነገድ እንደማይቻል በግልጽ አስታውቋል፡፡ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ሆኖ በማሴር ቀውስ መፍጠርም አይሞከርም ብሏል፡፡ ማንም ግለሰብ ሆነ ቡድን ፍላጎቱን ከኢትዮጵያ ህልውና በታች በማድረግ፣ ሕጋዊና ሰላማዊ ሆኖ መንቀሳቀስ ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች መሳተፍ የሚቻለው፣ ብሔራዊ ደኅንነቷና ጥቅሞቿ ሳይጎዱ ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአገሩ ህልውና ላይ የመጣን ማንኛውንም ጥቃትም ሆነ ሴራ ስለማይታገስ፣ ከአጥፊና ከአውዳሚ ድርጊቶች መታቀብ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ህልውና ሲነካ እጁን አጣጥፎ የሚቀመጥ እንደሌለ በቅርቡ በሚገባ ታይቷል፡፡ ኢትዮጵያን ከሥልጣን፣ ከጥቅማ ጥቅም፣ ውሉ ከማይታወቅ የታሪክ ትርክት፣ ከማንነትና ከሃይማኖታዊ አጥር፣ ከዓርማዎችና ከምልክቶች ልክፍት፣ መያዣና መጨበጫ ከሌላቸው ርዕዮተ ዓለማዊና ዕሳቤዎች በላይ ማክበር ይገባል፡፡ አንድነቷ እንደ ብረት የጠነከረ፣ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ያላት፣ በኢኮኖሚ የዳበረችና ለሁሉም ሕዝቧ የምትመች ዴሞክራሲያዊት አገር መገንባት የሚቻለው በዚህ ቁመና ላይ መገኘት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ አላቸውና፡፡

ኢትዮጵያ በሰላምና በዕድገት ወደፊት መራመድ የምትችለው፣ ከራሳቸው በላይ ለአገራቸው የሚቆረቆሩ ኢትዮጵያዊያን ሲበዙ ነው፡፡ እንደ ከዚህ ቀደሙ የብዙኃኑ ድምፅ ታፎኖ አየሩን ለመቆጣጠር መሞከር፣ ከአገር በፊት የራስንና የቡድንን ጥቅም ብቻ በማስቀደም ማሴር አያዋጣም፡፡ በአክራሪ ብሔርተኝነት ካባ ውስጥ ተደብቆ አገርን ማተራመስና በሕዝብ መቆመርም ተገቢ አይደለም፡፡ አገርንና ሕዝብን ማዕከል የማያደርግ ነውጠኝነት ተቀባይነት የለውም፡፡ በኢትዮጵያዊነት ጣሪያ ሥር በመገደብ ከመፎካከር ይልቅ፣ ጠባብ ቡድናዊ ፍላጎትን አልፋና ኦሜጋ ማድረግ የኪሳራ ፖለቲካ ውጤት ነው፡፡ በሰላማዊ መንገድ መነጋገርና መደራደር እየተቻለ አንዱ ሌላውን ለማስገበር መራኮት ኋላቀርነት ነው፡፡ የማኅበረሰቦችን የሥነ ምግባርና የሞራል እሴቶች በመናድ ሕገወጥነትን ማስፋፋት፣ የሕግ የበላይነትን በመዳፈር ንፁኃንን መግደል፣ መዝረፍና ማፈናቀል ሥርዓተ አልባነት ነው፡፡ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ተነቅለው መጣል ካለባቸው አስከፊ ድርጊቶች ውስጥ፣ ሕጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክርን ለጉልበትና ለሕገወጥነት የሚዳርጉ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ 

ከዚህ ቀደም ለውይይትና ለድርድር ዕድል ባለመሰጠቱ በዚህች አገር የበርካቶች ደም ፈሷል፡፡ ግድያ፣ እስራት፣ ማሰቃየት፣ ማሳደድና ፀጥ ለጥ አድርጎ መግዛት የተለመደው ለሕጋዊና ለሰላማዊ ፖለቲካ ዕድል በመነፈጉ ነው፡፡ ሕዝብ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት መሆኑ እየታወቀ ሆን ተብሎ በጉልበተኞች በርካታ ችግሮች ተፈጥረዋል፡፡ በሕዝብ ሙሉ ፈቃድ በኢትዮጵያ ምድር ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን በእኩልነት የሚያስተናግድ ሥርዓት መፍጠር እየተቻለ፣ ጥቂት አምባገነኖች የተገኘውን መልካም አጋጣሚ አበላሽተው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመከራና ለዕንግልት ተዳርጓል፡፡ የፖለቲካ ሥልጣንን ተገን በማድረግ አገር መዝረፍ፣ ዜጎችን ማሰቃየትና ተስፋ ቢስ ማድረግ ለከፍተኛ ተቃውሞ መቀስቀስ ምክንያት ሆኗል፡፡ ሥልጣን ይዘው እንዳሻቸው ሲፈነጩ የነበሩ ኃይሎች በሕዝብ ተቃውሞ በውርደት ሲባረሩ፣ የያዛቸው አባዜ በቀላሉ የሚለቅ አልነበረምና ጦርነት ቀስቅሰው የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ከአጥፊና ከአውዳሚ ፖለቲካ በመላቀቅ ለውይይትና ለድርድር ቅድሚያ ይስጡ፡፡ ጠመንጃ አምላኪነትም ሆነ በማንነት ስም በማጭበርበር አገር ለማተራመስ መሞከር መጨረሻው ውርደት መሆኑን ይማሩ፡፡ ለፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔዎችን ገሸሽ ማድረግ አያዋጣም፡፡

ኢትዮጵያ መፃኢ ዕድሏ የሰመረ እንዲሆን መጪው ምርጫ ትልቅ አንድምታ ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ከተሠለፉ ኃይሎች ብዙዎቹ ራሳቸውን መግራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለሰላማዊና ለሕጋዊ የፖለቲካ ፉክክር ራሳቸውን ያስገዙ፡፡ ብሔር ውስጥ እየተደበቁ ከፋፋይ አጀንዳ ማራመድ፣ ሌላውን ተፎካካሪ መጥላትና እንደ ጠላት ማየት፣ ደጋፊን በሥርዓት አልበኝነት ማሰማራት፣ ለውይይትና ለድርድር ጀርባ መስጠትና ለዘመናዊው ዓለም የፖለቲካ አመለካከት ባዕድ መሆን ዋነኛ ችግሮቻቸው ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ከእነዚህ ህፀፆች ራሳቸውን በማፅዳት ለፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ራሳቸውን ያበቁ ቁጥራቸው ትንሽ የሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አመራሮች ቢኖሩም፣ አብዛኞቹ በዚህ ደረጃ ላይ አለመገኘታቸው ችግሩን ያከፋዋል፡፡ አብዛኞቹ የፖለቲካ ኃይሎች እንደ ወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ ራሳቸውን ስለማያዘጋጁ፣ ከዘመናት ልማዳዊ ድርጊቶች ለመላቀቅ ይከብዳቸዋል፡፡ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ሳይገባቸው በአፈ ጮሌነት ከተሰማሩት ጀምሮ፣ ፈፅሞ ለሕጋዊነት ዋጋ የማይሰጡ ጀብደኞችም አሉ፡፡ በሰጥቶ መቀበል መርህ በጋራ ለመሥራት ከመሞከር ይልቅ፣ በረባ ባልረባው በመተናነቅ ግጭት ለመቀስቀስ የሚያደቡም ሞልተዋል፡፡ ሰላም ሲሰፍን ጭር እያለባቸው አቧራ ማስነሳት የሚፈልጉም አሉ፡፡ ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት ፖለቲካዊ መፍትሔዎች መኖራቸውን ቢያውቁም፣ ለሥልጣን ሲሉ አገር ለማተራመስ ስለሚፈልጉ ፈቃደኛ አይደሉም፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን ሰላም ያስፈልገዋል፡፡ ከግጭትና ከመራር ድህነት ውስጥ መውጣት አለበት፡፡ የተሻለ ኑሮ ማግኘት ይገባዋል፡፡ ንፁህና ምቹ የመኖሪያ ሥፍራ፣ አስተማማኝ የሆነ ሥራና ገቢ፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት መንግሥታዊ ሥርዓት፣ ለሚቀጥለው ትውልድ የሚያስረክባት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ አገር እንድትኖረው የግድ ነው፡፡ ይህንን በተግባር ለማሳየት ደግሞ ሕዝቡ ከልቡ የሚቀበለው ምርጫ እንዲከናወን ዝግጅቱ መጀመር ይኖርበታል፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችና የምርጫ ተዋንያን ይህንን አስተዋይ ሕዝብ ማክበር አለባቸው፡፡ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት መሆኑን በግብርም በነቢብም ማረጋገጥ ይገባቸዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምፅ የሚያሰባስቡት ከመራጮች ነው፡፡ ሕዝብ ዘንድ የሚቀርብ ማንኛውም ፓርቲ ሕጋዊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መሆን አለበት፡፡ ይህንን ዓይነት ጨዋነት ሳያሳዩ በጭፍን መጋለብ አያዋጣም፡፡ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራው ለሕግ የበላይነት ዕውቅና ሳይሰጥ ሕገወጥነትን ካስቀደመ፣ ከሕዝብ በኩል የሚኖረው የአፀፋ ምላሽ ውድቀትን ያፋጥናል፡፡ ሕገወጥነት ያተረፈው አምባገነንነትን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ አምባገነንነት ከሚገባው በላይ አንገፍግፎታል፣ ከሚታገሰው በላይ ሆኖበታል፡፡ ካሁን በኋላ የሚሻው በነፃና በፍትሐዊ ምርጫ አማካይነት የሚታነፅ የእኩልነት ሥርዓት ነው፡፡ ሕዝብ የሥልጣኑ ባለቤት ስለሆነ ለፍላጎቱ ተገዙ፡፡ ሕጋዊነትን አጠናክሩ፡፡ በሕጋዊነት ቅጽር ውስጥ ተፎካከሩ፡፡ ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዳላቸው ተረዱ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...

በአዲስ አበባ ከ700 ሺሕ በላይ የትራፊክ የደንብ ጥሰቶች መፈጸማቸው ተገለጸ

በአዲስ አበባ 716,624 የትራፊክ የደንብ ጥሰቶች መፈጸማቸውን፣ የአዲስ አበባ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...

የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዳይዳፈን ጥንቃቄ ይደረግ!

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር አሁንም ጤና አልባ ሆኖ የተለመደው ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ወዲህ ሊሻሻል ያልቻለው የፖለቲካ ምኅዳር ሰሞኑን አዲስ...