የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ታኅሣሥ 5 ቀን 2013 ዓ.ም. በሚያደርገው ጠቅላላ ጉባዔ ፕሬዚዳንትና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ያደርጋል፡፡ ከደቡብ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር በዕጩነት ቀርበው የነበሩት አቶ ተፈራ ሞላ በገዛ ፈቃዳቸው ከዕጩነት ራሳቸውን በማግለላቸው ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ብቸኛዋ ተወዳዳሪ ሆነው ይቀርባሉ፡፡
ላለፉት አራት ዓመታት (ከ2009 እስከ 2012) በሥራ አስፈጻሚነት የቆዩት አባላት ዘመናቸው መጠናቀቁን ተከትሎ ለሚደረገው ምርጫ ከትግራይና ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በስተቀር ሌሎች ክልሎች ዕጩዎቻቸውን ለፌዴሬሽኑ አሳውቀዋል፡፡
ከቀረቡት ዕጩዎች መካከል ቀደም ሲል ከደቡብ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር በዕጩነት ቀርበው የነበሩት አቶ ተፈራ ሞላ ከፉክክሩ ራሳቸውን ማግለላቸው ይፋ አድርገዋል፡፡
‹‹ለዚህ ታላቅ ኃላፊነት ከእሳቸው ጋር ለመፎካከር ከኦሮሚያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዕጩ ሆነው የቀረቡት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ፣ በዘርፉ ለአገሪቱ ካበረከቱት አስተዋጽኦ እንዲሁም በዚሁ ኃላፊነት ላይ ሆነው በቆዩባቸው ዓመታት ውስጥ ያሳዩት መልካም ተሞክሮ ከግምት በማስገባትና የጀመሯቸው ሥራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ኃላፊነቱን መስጠት ተገቢ መሆኑን በማመን ነው፤›› በማለት አቶ ተፈራ ሞላ ኅዳር 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በጻፉት ደብዳቤ የለቀቁበትን ምክንያት አብራርተዋል፡፡ ዕጩው ከአራት ዓመት በፊት በተደረገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ወቅት ከሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ጋር ተፎካክረው መሸነፋቸው አይዘነጋም፡፡