ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች በሥነ ልቦናና በማኅበራዊ እንቅስቃሴ ብቁ ባለመሆናቸው የተነሳ ለጥቃትና ለችግር ሲጋለጡ ይስተዋላል፡፡
የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) የሕፃናት ጥበቃ ስፔሻሊስት ወ/ሮ ሠርክዓለም አባተ በሕፃናት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ወይም ሕፃናትን ለተለያዩ ጉዳት የሚዳርጉ አራት ዓይነት ጥቃቶች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ እነርሱም ፆታዊ፣ አካላዊ፣ ስሜትን የሚነኩና ማንነትን የሚያንቋሽሹ፣ እንዲሁም የመገለል ጥቃቶች ናቸው፡፡
ከእነዚህም መካከል እጅግ የከፉት ፆታዊና ስሜትን የሚነኩት እንደሆኑ፣ በተለይ ፆታዊ ጥቃት ሲባል በርካታ መገለጫዎች እንዳሉት ያብራራሉ፡፡ ከመገለጫዎቹም ውስጥ የመጀመርያ ደረጃ የሆነው ማባበል፣ መተናኮስ፣ ማስገደድ ወዘተ ሲሆን፣ የመጨረሻ ደረጃው ግን ፆታዊ ግንኙነት እንደሆነ ነው፡፡
ፆታዊ ጥቃት በርካታ ጠባሳዎችን አዕምሮ ውስጥ ያሳድራል፡፡ ይህን መሰሉ ጥቃት የተፈጸመባቸው ሕፃናት ደግሞ ወዲያውኑ የሥነ ልቦናና የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን አድገው አዋቂ በሚሆኑበት ጊዜ በሌሎች ሕፃናት ላይ ተመሳሳይ ጥቃት ሊፈጽሙ ይችላሉ፡፡
ስሜትን የሚነኩና ማንነትን የሚያንቋሽሹ ጥቃቶች በርካታ መገለጫዎች ያሏቸው ሲሆን፣ እንደ አጠቃላይ ባህሪን፣ ዘርንና ሃይማኖትን መሠረት አድርገው የሚሰነዘሩ ስድቦች ይገኙበታል፡፡ እነዚህን ስድቦች ለመግለጽ የሚወጣው የጩኸት ድምፅም የጥቃቱ አካል ነው፡፡
አካላዊ ጥቃት በአካል ላይ ምልክቶችን ትቶ የሚያልፍ ጥቃት ሲሆን፣ ይህ ዓይነቱም ጥቃት እጅን ወይም ቁሳቁስን ተጠቅሞ መማታት ነው፡፡ መመረዝም ከዚህ የጥቃት ዓይነት ይመደባል፡፡
ሕፃናት ከቤተሰቦቻቸው ወይም ከአሳዳጊዎቻቸው ፍቅርና እንክብካቤን አጥብቀው ይሻሉ፡፡ ጤና መሆንና የመማር መብትም አላቸው፡፡ የተጠቀሰውን መብት የተነፈጉና ፍቅርና እንክብካቤን ያላገኙ ሕፃናት ለተለያዩ ተጨማሪ ችግሮች ይጋለጣሉ፡፡ በዚህም የተለያዩ ባህሪዎች ያድርባቸውና በስተመጨረሻም ወደ ጎዳና ሕይወት ያመራሉ፡፡
ከዚህ አኳያ ሕፃናትን የሚመለከት ተግባር የሚያከናውኑ ተቋማት ሕፃናትን ከተጠቀሱት ጥቃቶች ለመታደግ እንዲቻል የቅድመ መከላከል ስልቶችን ወይም ሥርዓቶችን መከተል እንዳለባቸው ወ/ሮ ሠርካለም ያስገነዝባሉ፡፡ ከስልቶቹም መካከል አንዱና ዋነኛው የሕፃናት ደኅንነት ጥበቃ ፖሊሲ ከየመሥሪያ ቤቱ ሥራ ጋር አጣጥም ለመተግበር የሚያስችል አሠራር ሊኖራቸው ይገባል፡፡