Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየተዘነጋው ኤችአይቪ ኤድስ ዳግም ዋጋ ያስከፍል ይሆን?

የተዘነጋው ኤችአይቪ ኤድስ ዳግም ዋጋ ያስከፍል ይሆን?

ቀን:

በርካታ ሕፃናትን ያለወላጅ አስቀርቷል፡፡ ሕፃናቱ ወደው ባላመጡት በሽታ ተሰቃይተዋል፡፡ ለኅልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል፡፡ ከዛሬ 15 ዓመታት በፊት በሺዎች የሚቆጠሩ እንደ ቅጠል ረግፈዋል፡፡ ምን መዓት መጣ ተብሎ በየአድባራቱና ገዳማቱ እግዚኦታ ተደርጓል፡፡ በየመስጂዱ አላህን ያልተለማመነና ያልተማፀነ ነበር ለማለት አያስደፍርም፡፡

ስለ ቫይረሱ ግንዛቤ ለመስጠት ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ተሠርቷል፡፡ ከጥበብ ዓለም ጎራ ብንል እንኳን ሙዚቀኞች ስለቫይረሱ አስከፊነትና ማግለልም እንደማይበጅ ዘምረዋል፡፡ ከእነዚህ ሙዚቃዎች ውስጥ ጎሳዬ ተስፋዬ፣ ፀደኒያ ገብረማርቆስ፣ አብዱ ኪያር፣ ሚካኤል በላይነህ፣ ኃይልዬን ጨምሮ ‹‹ማለባበስ ይቅር›› ብለው ያዜሙት ይገኝበታል፡፡ ሌሎችም ቫይረሱን ለመዋጋት የጋራ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ በሥራዎቻቸው መክረዋል፡፡

ከእነዚህ ሙዚቃዎች መካከል አንጋፋዎቹ የተሳተፉበት ‹‹መላ መላ›› የተሰኘው ዜማ ይገኝበታል፡፡

                    ‹‹ድንበሩንስ አልፎ ዘልቋል መንደራችን

ቁጭ ብለን አየነው ሲገባ ቤታችን

በልባችን ዙሪያ ምሽጉን መሽጎ

እንዴት ይጨርሰን በኛው ተሸሽጎ…

ሁሉን ነገር በእኛ አንሁን ቸልተኛ

ሕይወት ይሁን ሥጋት እየሳቡ መሥራት

መላ መላ መላ ወገን አትበል ችላ

እስቲ መላ በሉ የአገር ልጆች ሁሉ፡፡››

አንጋፋዎቹ ሙዚቀኞች ዓለማየሁ እሸቴ፣ ምኒልክ ወስናቸው (ነፍስ ኄር)፣ አረጋኸኝ ወራሽ፣ ታምራት ሞላ፣ ኢዮብ መኰንን (ነፍስ ኄር) ፣ ፀደኒያ ገብረማርቆስ፣ ዘሪቱ ከበደ፣ ኒኒ ስለኤች አይቪ ኤድስ ሥርጭትና አስከፊነት በጋራ ያዜሙት ነው፡፡

በወቅቱ ብዙዎች ስለበሽታው አስከፊነት አንጎራጉረዋል፡፡ በኪነጥበባቱም ሆነ በመገናኛ ብዙኃን ስለቫይረሱ አስከፊነት ያልሠራ አለ ለማለት ያዳግታል፡፡

በእነዚህና በመሳሰሉት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭትን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው አይዘነጋም፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ በኤችአይቪ ላይ ይሠሩ የነበሩ ተቋማት መቀዛቀዛቸውን የፌዴራል የኤች አይቪኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት ገልጿል፡፡

ከዚህ ቀደም በእያንዳንዱ መርሐ ግብር የቫይረሱን አስከፊነት የሚያስገነዝብ በመኖሩ ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱ በተጨባጭ የታየ ሲሆን፣ አሁን ላይ በመቀዛቀዙ የሥርጭት መጠኑ ከፍ እያለ መምጣቱ ተነግሯል፡፡

በዋናነት የማስተባበር ሥራውን የሚያከናውነው ጽሕፈት ቤቱ ቢሆንም፣ አጋዥ አካላት ድጋፎቻቸውን እንደ ቀድሞው ባለመቀጠላቸው ሥርጭቱ መጠኑ ከፍ ሊል እንደቻለ ይነገራል፡፡

በኢትዮጵያ የቫይረሱ ሥርጭት ከፍ ማለት በዋናነት በሴቶች ላይ እንደሚበዛ አኃዞች ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም የተለያዩ ሥራዎች መሠራት እንዳለበት ጽሕፈት ቤቱ ይገልጻል፡፡

የሴቶች ተሳትፎ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በፖለቲካ አነስተኛ መሆኑ ለኤችአይቪ ኤድስ ይበልጥ ተግላጭ እንዳደረጋቸውና ስለቫይረሱ ያላቸው ግንዛቤ አናሳ መሆኑም ሌላው ችግር እንደሆነ አክሏል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2016 የወጣው የኢትዮጵያ የሥነ ጤና ዳሰሳ  ሪፖርት፣ በቫይረሱ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች የግንዛቤና የመሠረታዊ ዕውቀት ችግር እንዳለባቸው ያሳያል፡፡

19 በመቶ ሴቶች ስለኤችአይቪ ኤድስ ግንዛቤና ዕውቀት ያላቸው ሲሆን፣ የወንዶች ደግሞ 39 በመቶ ነው፡፡ የወንዶቹ ከሴቶች አኳያ የተሻለ ይባል እንጂ ገና መሠራት እንዳለበት የጽሕፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል በትረ ተናግረዋል፡፡

ኅዳር 22 ቀን 2013 ዓ.ም. የዓለም ኤድስ ቀን በኢትዮጵያ ‹‹ኤችአይቪን ለመግታት ዓለም አቀፋዊ ትብብርና የጋራ ኃላፊነት›› በሚል መሪ ቃል ተከብሯል፡፡

የኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭትን ለመግታት ከከፍተኛ አመራሮች ጀምሮ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሙያ ማኅበራት፣ የኪነጥበብ ማኅበራት፣ ኤችአይቪ ኤድስ በደማቸው የሚገኝ ዜጎች ማኅበራት ጥምረት ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ተጠቁሟል፡፡

ባለድርሻ አካላት በዋነኛነት የመረጃ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ኅብረተሰቡ ስለቫይረሱ ያለውን አስተሳሰብ ከፍ ለማድረግና የባህሪ ለውጥ እንዲመጣ ለማስቻል የሚዲያዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑ በዕለቱ ተገልጿል፡፡

ኤችአይቪ ኤድስን ለመግታት የአንድ ተቋም ኃላፊነት ብቻ አለመሆኑን የጠቆሙት አቶ ዳንኤል፣ በተለይም ወጣቱና የነገ አገር ተረካቢ የሆነው ትውልድ በአንፃራዊ በቫይረሱ መያዛቸው እየተስተዋለ ይገኛል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቫይረሱ የሥርጭት ምጣኔ 0.9 በመቶ ሲሆን፣ በዚህም ሥሌት 669,236 የሚሆኑ ዜጎች ቫይረሱ በደማቸው ይገኛል፡፡ በተለያዩ የማኅበረሰቡ ክፍሎችና በከተማና በገጠር የሥርጭት መጠኑ ይለያያል፡፡ አዳዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ዜጎች ቁጥር እየቀነሰ እንዳልሆነም ተጠቁሟል፡፡

ቫይረሱ ካለባቸው ሰዎች 669,263 ውስጥ 413,547 (61.8 በመቶ) ሴቶች ናቸው፡፡ ይህ እንደ አገር ሴቶችን በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማኅበራዊ እንቅስቃሴ ማሳደግ እንደሚጠበቅ ጠቋሚ መሆኑ ተነግሯል፡፡

በዓለም እ.ኤ.አ. 1981 ጀምሮ ከ32.7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት 38 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው ይገኛል፡፡ በየዓመቱ 1.7 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ደግሞ አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ መሆናቸውን  የዩኤንኤድስ የ2019 መረጃ ያሳያል፡፡

የዓለም ኤድስ ቀን ቫይረሱ በደማቸው ለሚገኙና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፋቸውን ለማሳየትና በኤድስ ሕይወታቸውን ያጡትን ወገኖች ለማስታወስ በየዓመቱ ኀዳር 22 ቀን እንደሚከበር ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...